Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠሩ የአውሮፓ ኢንቨስተሮች የመሬትና የቢሮክራሲ ማነቆዎች እንዳስቸገራቸው ገለጹ

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠሩ የአውሮፓ ኢንቨስተሮች የመሬትና የቢሮክራሲ ማነቆዎች እንዳስቸገራቸው ገለጹ

ቀን:

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠሩ የአውሮፓ ኢንቨስተሮች ከመሬትና ከቢሮክራሲ ጋር የተያያዙ ማነቆዎች ሊያሠሯቸው እንዳልቻሉ አስታወቁ፡፡  

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙና ወደፊት መጥተው መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ዕቅድ ያላቸው አውሮፓውያን ባለሀብቶች መሬት ለማግኘት ከፍተኛ ቢሮክራሲ እንደሚገጥማቸው፣ ውሳኔ ለማግኘት ረዥም ጊዜ እንደሚወስድባቸው፣ ከላይኛው እስከ ታችኛው የመንግሥት መዋቅር በቂ የሆነ የኢንቨስትመንት መረጃ እንደማያገኙና ይህም ለኢንቨስትመንት ሥራቸው አዳጋች እንደሆነባቸው የአውሮፓ ቻምበር ባዘጋጀው ውይይት ላይ ተናግረዋል፡፡

ማክሰኞ መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. የአውሮፓ ቻምበር ከአውሮፓ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ልማትና በመሬት አቅርቦት ላይ ያተኮረ የፖሊሲ ሰነድ ይፋ ሲያደርግ፣ ‹‹የመሬት ተደራሽነት፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጪ ላሉ ባለሀብቶች የመሬት አሰጣጥ ሒደትን ማመቻቸት›› በሚል ርዕስ፣ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጪ በልማት ሥራ የተሰማሩ ባለሀብቶች ለልማት መሬት ከማግኘት ጋር ተያይዞ ስለሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ውይይት ተካሂዷል፡፡

በአውሮፓ ቻምበር ይፋ የተደረገው ሰነድ እንደሚያስረዳው፣ ባለሀብቶች መሬት ለማግኘት ለረዥም ጊዜ ሲጠብቁ መቆየት፣ የታችኛው የክልልና የወረዳ መዋቅር መሬት ሳያዘጋጅ ባለሀብቶችን አስገብቶ ማጉላላት፣ ከፍተኛ የመሬት ካሳ ፍላጎት መጨመር፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የክልልና የወረዳ አመራሮች በተደጋጋሚ ከፍተኛ ገንዘብ መጠየቅ፣ ቅድመ ዝግጅት የሌለው የኢንቨስትመንት ፍላጎት፣ የማስተግበሪያ ደንብና መመርያ ፈጽሞ የሌላቸው የመሬት አጠቃቀም ሕጎች መኖራቸው ተጠቅሷል፡፡

የክልል መንግሥታት መዋቅር ስለማይረጋ በየጊዜው መለዋወጡ፣ የተቋማት መለያየት ወይም ወደ መዋሀድ፣ ኃላፊዎች ባሉበት አለመርጋት፣ የመሠረተ ልማት እጥረት፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ቅንጅት አለመኖር፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ፈጻሚዎች አቅመ ቢስ መሆን፣ ከኢንቨስትመንት ሥራቸው ጋር የማይገናኙ የተጭበረበሩ ተጨማሪ ገንዘብ ጥያቄዎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውና በተለይም በወረዳ የመሬት አስተዳደር አካላት የሚቀርቡ ጥያቄዎች ናቸው፡፡

የአውሮፓ ቻምበር የፀጥታ ችግር፣ የግብዓት ውስንነት፣ ወጥነት የሌለው የመሬት አሰጣጥና አሠራር፣ መሬትን ላልተፈለገ ዓላማ ማዋልና አጥሮ እንዲቀመጥ የማድረግ ማነቆዎችን በዝርዝር አቅርቧል፡፡

የፖሊሲ ሰነዱ በኢትዮጵያ መንግሥት ሊታሰብባቸው የሚገቡ የውሳኔ ሐሳቦችን ያካተተ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ግልጽነት፣ ፍትሐዊነትና ቀልጣፋ የመሬት አስተዳደር በማስፈን ኢንቨስትመንትንና ኢኮኖሚ ልማትን የሚያበረታታ ወጥነት ያለው ፖሊሲ እንዲመጣ ጠይቋል፡፡

በተመሳሳይ በፌዴራልና በክልል መንግሥት ውል ያለው ቅንጅታዊ አሠራር እንዲጠናከር፣ የመሬት አሰጣጥና የካሳ ክፍያ ጉዳይ ግልጽነት ያለው ሥርዓት እንደሚያስፈልገው አሳስቧል፡፡

የካሳ ክፍያን ሥሌት በተመለከተ መመርያዎች ማውጣትና የመሬት ግምትን እንደ ግብርና ሚኒስቴር ካሉ አካላት ጋር ማስተባበር፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን የአገልግሎት ውጤታማነት ማሻሻል፣ በሁሉም የአስተዳደር እርከኖች የመሬት ምደባ መመርያዎችን ማዘጋጀት፣ ከተፈናቀሉ ግለሰቦች ጋር የምክክር ስብሰባዎች ማካሄድ የሚሉ ሐሳቦችም በአውሮፓ ቻምበር ተነስተዋል፡፡

ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከፍተኛ ኃላፊዎች እንደሚገኙ ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም በመድረኩ አልተገኙም፡፡ አንድ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሥራ ኃላፊ ለተነሱት ችግሮች ማብራሪያ ሲሰጡ በመሬት ዙሪያ የሚነሱ ችግሮች የሚካዱ አይደለም ብለዋል፡፡ ኮሚሽኑ መሬትን በተመለከተ ችግሮች ሲገኙ ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርግ የገለጹት የሥራ ኃላፊው፣ ‹‹ተወዳዳሪ አገር ለመፍጠር የሚቀርቡት የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች በተለይም እንደ መሬት ዓይነት ጉዳዮች ተወዳዳሪ አልሆኑም ከተባለ መለስ ብለን ማየት ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም በሥራ ላይ ባሉ ባለሀብቶች የሚነሱ ጥያቄዎች ካልተፈቱ አዲስ መሳብ አይደለም ያሉትንም ማቆየት እንደማይቻል፣ ኢንቨስተር ስለችግር እየተናገረ መቀጠል ስለሌለበት ኮሚሽኑ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...