Tuesday, July 23, 2024

አገር የምትረጋጋው በልማትና በፀጥታ ጉዳዮች መግባባት ሲቻል ነው!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አዲስ አበባን ጨምሮ ከተለያዩ ክልሎች ተወካዮች ጋር ተከታታይ ውይይቶች ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወክለው በውይይቶቹ የተገኙ ግለሰቦች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በርካታ ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ ከጥያቄዎቹ መካከል የልማትና የፀጥታ ጉዳዮች ሰፊ ትኩረት ያገኙ ነበሩ፡፡ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ፣ የውኃ፣ የጤና፣ የትምህርትና መሰል መሠረተ ልማቶች ከኑሮ ውድነትና ተዛማጅ ጉዳዮች ጋር ተነስተው ነበር፡፡ በፀጥታ ጉዳይም በየአካባቢው በሚካሄዱ ግጭቶች ምክንያት እየደረሱ ያሉ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳቶች በስፋት ተዳሰዋል፡፡ ብዙዎቹ የተነሱት ጥያቄዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ በገዥው ፓርቲና በሚመሩት መንግሥት የሚታወቁ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ምላሽ ሲሰጡ ጥያቄዎቹን ተራ በተራ በማንሳት በማነፃፀሪያዎች እያስደገፉ ነበር፡፡ ሕዝብና መንግሥት በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ሊያግባባቸው የሚችል አማካይ እንዲኖር አንዳንድ መሠረታዊ ጉዳዮች መነሳት አለባቸው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ ‹‹በወንዝ ዳር ፕሮጀክት›› እና ‹‹በመንገድ ኮሪደር ልማት›› መርሐ ግብሮች፣ ይዞታዎችን የማፍረስና አጥሮችን ወደ ውስጥ የማስገባት ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ ነው፡፡ ‹‹ስማርት ሲቲ›› በተሰኘው ከተማን የመለወጥ ግዙፍ እንቅስቃሴ፣ የከተማዋን ገጽታ የሚለውጡ ተግባራት ሲከናወኑ በከተማ አስተዳደሩና በነዋሪዎች መካከል መግባባት መኖር አለበት፡፡ አገሩ ወይም ከተማው በልማትና በዕድገት ስትለወጥለት የሚጠላ ዜጋ ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ልማቱም ሆነ ዕድገቱ የጋራ ሲሆን፣ ከአንድ አካባቢ ተነስተው ወደ ሌላ የሚሠፍሩ ዜጎች፣ በተቻለ መጠን ከነበሩበት ያላነሰ ተስማሚ የመኖሪያና የመሥሪያ ቦታ ማግኘታቸው መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ እንደተነገረው ነዋሪዎች የተሻለ መኖሪያና መሥሪያ አግኝተው ከሆነ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን የተባለውና እየተደረገ ያለው የማይመጣጠን ከሆነ ማስተካከያ ማድረግ የግድ መሆን አለበት፡፡

አዲስ አበባ ከተማን ለመለወጥ የሚደረገው ጥረት ሰው ተኮር መሆን ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ቀደም በአካባቢ ልማት ፕሮግራም ስም ከቀዬአቸው ተነስተው የትም የተጣሉ ዜጎች የደረሰባቸው መከራ አይዘነጋም፡፡ አንድ ዜጋ ከኖረበት አካባቢ በልማት ስም ሲነሳ፣ ከዚህ በፊት ለአካባቢው ተፈላጊነት መጨመር ያደረገው አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡ ከበርካታ ዓመታት በፊት ዜጎች መኖሪያቸውን ሲቀልሱ ምንም ዓይነት ትኩረት ያልነበራቸው አካባቢዎች፣ በአሁኑ ጊዜ የመንግሥትም ሆነ የባለሀብቶች ቀልብ ሲያርፍባቸው የገበያ ዋጋውን ተመጣጣኝ ባይሆን እንኳ ዳጎስ ያለ ካሳና መሰል ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እዚህ ላይ ዜጎች ለአገራቸው ልማት የሚከፍሉት ዋጋ መኖሩ እንዳለ ሆኖ፣ በተቻለ መጠን የማያስከፋቸው አሠራር ተግባራዊ መደረግ ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥት ከሕዝብ ጋር በግልጽ ተነጋግሮ መተማመን አለበት፡፡

በፀጥታው ረገድ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚስተዋሉ አደገኛ የወንጀል ድርጊቶችን ፈር ለማስያዝ፣ መንግሥትም ሆነ የፀጥታ ክፍሎቹ ከሕዝብ ጋር ተቀራርበው መሥራት አለባቸው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ከኪስ አውላቂነት እስከ ከባድ ዘረፋ ድረስ የተሰማሩ በርካታ ግለሰቦችና ቡድኖች አሉ፡፡ እነዚህ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች የተቀናጀ ክትትል ቢደረግባቸው፣ የዘረፋው መጠን በዚህ ያህል ተስፋፍቶ ከአቅም በላይ አይሆንም፡፡ የፖሊስ ሥራ ወንጀል እንዳይፈጸም በጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ኃላፊነትን መወጣት ሲሆን፣ አልፎ አልፎ የወንጀል ድርጊት ሲያጋጥም በፍጥነት በቁጥጥር ሥር ማዋል ነው፡፡ ይህ ተግባር ስኬታማ የሚሆነው ፖሊስ ከሕዝብ ጋር ጠንካራ ቁርኝት ፈጥሮ መሥራት ሲችል ነው፡፡ ለይስሙላ ያህል የሕዝብ ትብብር መጠየቅ ሳይሆን በተግባር የሚፈተን ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የወንጀል መስፋፋት ይቀጥላል፡፡

በከተማው ውስጥ በትራንስፖርት ዘርፍ በተሰማሩ ግለሰቦችና ቡድኖች በነዋሪዎች ላይ የሚፈጸመው ዝርፊያ ከልካይ ያጣ ነው የሚመስለው፡፡ ‹‹ሿሿ›› ከሚባለው የሚኒ ባስ ታክሲዎች ውንብድና ጀምሮ እስከ ሜትር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ድረስ የሚስተዋለው ዝርፊያ፣ ከንብረት ቅሚያ አንስቶ እስከ ሕይወት ድረስ ዋጋ እየተከፈለበት ነው፡፡ በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ የተደራጀ የፖሊስ ኃይል ከሕዝቡ ጋር ተናቦ መሥራት ከቻለ፣ ይህንን አደገኛ ወንጀል ለማስቆም የጥቂት ሳምንታት ሥራ ብቻ ነው የሚበቃው፡፡ እርግጥ ነው ወንጀሉ ዱካው እንዳይገኝ ትብብር የሚያደርጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉ ሁሉ፣ በፖሊስ ውስጥም ተባባሪዎች መኖራቸው ጥረቱን ለማደናቀፍ ያስችላል፡፡ ነገር ግን ሕዝብና ፖሊስ ተግባብተው ከተባበሩ ችግሩ በአጭሩ ይቀጫል፡፡ የከተማው አስተዳደርም ሆነ የፌዴራል መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ጠንካራና ቁርጠኛ አቋም ሊኖራቸው ይገባል፡፡

አገር ሰላም የምታገኘው ሕዝብና መንግሥትን ሆድና ጀርባ የሚያደርጓቸው እንከኖች ሲወገዱ ነው፡፡ እንከኖቹ ደግሞ ሕዝብና መንግሥት ውስጥ የመሸጉ በመሆናቸው ለግልጽነት፣ ለተጠያቂነትና ለኃላፊነት መርህ መገዛት ያስፈልጋል፡፡ ሕዝብ የመንግሥት ቀጣሪ እንደ መሆኑ መጠን ለልማቱና ለሰላሙ መንግሥትን ማገዝና መቆጣጠር ይኖርበታል፡፡ መንግሥትም የቀጠረውን ሕዝብ በፍፁም ጨዋነትና ኃላፊነት ስሜት ማገልገል ይጠበቅበታል፡፡ ሕግ አውጭው ፓርላማ፣ አስፈጻሚው መንግሥትና ሕግ ተርጓሚው አካልም በሚዛናዊ ቁጥጥር አንዱ ከሌላው ጋር የሚናበቡበትን አሠራር በሕጉ መሠረት ማከናወን አለባቸው፡፡ በተለይ መንግሥት ልማቱን ለማቀላጠፍ፣ ሕግ ለማስከበርና ሌሎች ኃላፊነቶቹን ለመወጣት ከሕዝብ ጋር አብሮ መሥራት አለበት፡፡ የአገር ጉዳይ በድጋፍና በተቃውሞ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ የሚቀነበብ ሳይሆን፣ ሰፋ ያለ ዕይታ ያለው ጉዳይ መሆኑ ይታመን፡፡ አገር የምትረጋጋው በልማትና በፀጥታ ጉዳዮች መግባባት ሲቻል ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ ትርፍ ቢያገኝም የውጭ ምንዛሪ ገቢው ቅናሽ ማሳየቱ ተጠቆመ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የውጭ ምንዛሪ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...