Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአደገኛ ቦዘኔ መቆጣጠሪያ አዋጅ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ቀረበበት

የአደገኛ ቦዘኔ መቆጣጠሪያ አዋጅ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ቀረበበት

ቀን:

መንግሥት አደገኛ ቦዘኔነት ‹‹እየጨመረና እየተስፋፋ›› በመሄድ ላይ ነው በማለት ከ20 ዓመታት በፊት ባወጣው የአደገኛ ቦዘኔ መቆጣጠሪያ አዋጅ ውስጥ፣ የዋስትና መብትን የሚነፍገው ድንጋጌ ሕገ መንግሥቱን የሚሰጥ ነው ተብሎ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ቀረበበት፡፡

አደገኛ ቦዘኔነትን ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ 384/96 አንቀጽ ስድስት ንዑስ አንቀጽ ሦስት በአደገኛ ቦዘኔነት ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው በዋስትና አይለቀቅም ተብሎ ተደንግጓል፡፡ ይህ ድንጋጌ ሕገ መንግሥቱን ይቃረናል የሚል አቤቱታ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የቀረበ ሲሆን፣ ጉባዔው ከሰሞኑ ከሕግ ባለሙያዎች ጋር ውይይት አካሂዶበታል፡፡

የአዋጁ አንቀጽ ሕገ ወንግሥቱን ይቃረናል በሚል የሕገ መንግሥት ትርጉም ይሰጥልን በሚል ያቀረበው ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የድሬዳዋ ምድብ ችሎት ነው፡፡

በውይይቱ የተሳተፉ የሕግ ባለሙዎች የተጠቀሰው አዋጅ የዋስትና መብትን መከልከሉ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ 6 ላይ የተያዙ ሰዎች በዋስትና የመፈታት መብት አላቸው የሚለውንና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 ሥር የተዘረዘሩትን መብቶች ይቃረናል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ባለሙያዎቹ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 መሠረት ዜጎች በፖለቲካ በማኅበራዊ አመጣጣቸው፣ በሀብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግባቸው ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው የሚለውን ድንጋጌ በማንሳት ተከራክረዋል፡፡

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ አቶ ሙሴ መዝገቡ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ አንድን መብት ለመገደብ ቅቡልነት ያለው ዓላማ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ በአዋጁ መግቢያ ላይ የቀረበው ዓላማ የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ የሚለው ቅቡልነት ቢኖረውም ከዕርምጃ ጋር በተገናኘ ግን የወንጀል ዓይነትና ክብደትን መሠረት አድርጎ ዋስትናን መከልከል እንደ ቅቡልነት የሚታይ አይደለም ብለዋል፡፡

የሕጋዊነት መርህ በሚል ያነሱት ሌላኛው ጉዳይ አንድ ሕግ ግልጽና ተደራሽ መሆን እንዳለበት ቢደነገግም፣ በዚህ አዋጅ አንቀጽ ስድስት ንዑስ አንቀጽ 3 ላይ በአደገኛ ቦዘኔነት በሚገባ የተጠረጠረ በሚል የቀረበው አሻሚ የሆነ ጉዳይ ስለመሆኑ ያብራራሉ፡፡

ከሕግ ባለሙያ ለሰብዓዊ መብቶች ድርጅት የመጡ ተወካይ በበኩላቸው ዋስትናን የሚከለክለው ሕግ ፍትሐዊነቱ፣ ምክንያታዊነቱና ተገቢነቱን ትክክለኛነቱ ተፈትሾ በተገቢው መለኪያ ተገምግሞ፣ በተለይም በሕገ መንግሥቱ ከተቀመጡት ድንጎጌዎች አንፃር ታይቶ በሕጉ እንዲሳኩ ከሚፈለጉ ትልሞች አንፃር ሊፈተሽ ይገባል ብለዋል፡፡ በማብራሪያቸው በዋስ የመፈታት መብት በአገሪቱ ሕገ መንግሥትም ይሁን ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው ተገቢነት ባላቸው ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ሕጎች አንፃር በመርህ ደረጃ የተቀመጠ ነው ብለዋል፡፡ አክለውም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት ማንኛውም የፌዴራልም ይሁን የክልል አካል ሕገ መንግሥቱን የማክበርና የማስከበር ግዴታ እንዳለበት መደንገጉን ገልጸዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን የዋስትና መርህና የተያዙ ሰዎች መብት ሕግ አውጪው አካል በቀላሉ ሕግ አውጥቶ የሚነፍገውና የሚከለክለው የሚችለው አይደለም ብለዋል፡፡ ለፍርድ ቤቶች ሥልጣን የማይሰጥ ከሆነ ሕግ አውጪው ሕጎችን በቀላሉ እያወጣ መብቶች እንዲጥሱ የሚያደርግ መሆኑን፣ ሕግ አውጪው በሕገ መንግሥቱ የተሰጡ መብቶችን ሊነፍግ አይገባም የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ይህ ሁኔታ ከቀጠለና በአደገኛ ቦዘኔነት የሚጠረጠሩ ሰዎች ዋስትና የሚከለከሉ ከሆነ፣ በተመሳሳይ አሠራር ነገም በስርቆትና በመሰል ጉዳዮች ላይ የዋስትና መብት እንዲነፈግ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ከኦሮሚያ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመጡ ተሳታፊ በተመሳሳይ ሕገ መንግሥቱ የግል ሕይወት የመከበርና የመጠበቅ መብት፣ እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 ንዑስ አንድ ላይ ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የበላይ ሕግ ስለመሆኑ የተደነገገውን የሚጥስና አዋጁ ዜጎችን ለይቶ የመብት ክልከላ የሚያደርግ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡

የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር ተወካዮች በበኩላቸው ሕገ መንግሥቱ የዋስትና መብት ሊከለክል እንደሚችል፣ ነገር ግን በዘፈቀደ እንዳይሆን ደግሞ የአዋጁ ዓላማ የተቀመጠ በመሆኑ የዋስትና መብትን የሚጥስ ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

አደገኛ ቦዘኔን ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ላይ የቀረበው የዋስትና መብትን የሚከለክለው ድንጋጌ የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብት ይጥሳል የሚል እምነት እንደሌላቸው፣ አዋጁ ሕገ መንግሥታዊ ነው በሚል መልስ የሰጡት ደግሞ የፍትሕ ሚኒስቴር የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ተወካይ አቶ ሙሉቀን ካሳው ናቸው፡፡

በቀጣይ አጣሪ ጉባዔው የቀረቡትን ሐሳቦችና አስተያየቶች ተመልክቶ የሕገ መንግሥት ትርጉም የሚያስፈልገው ከሆነ ውሳኔውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚልከው ሲሆን፣ የትርጉም ችግር የለበትም ተብሎ ከተወሰነ ደግሞ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ድሬዳዋ ምድብ ችሎት መልስ እንደሚሰጥበት ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...