Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አየር መንገዱ በቦሌ ኤርፖርት በመንገደኞች እየተሰሙ ያሉ ቅሬታዎችን አጣራለሁ አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰሞኑን በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከመንገደኞች አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ እየተሰሙ ያሉ ቅሬታዎችን በማጣራት፣ መፍትሔ ለመስጠት እንደሚሠራ አስታወቀ፡፡

አየር መንገዱ ማክሰኞ መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ መሠረት፣ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከመንገደኞች አገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተነሱትን ቅሬታዎች መርምሮ መፍትሔ ለመስጠት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር  በመሆን ተገቢው የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወሰድ እየሠራ ነው፡፡

አየር መንገዱ በቦሌ ኤርፖርት በመንገደኞች እየተሰሙ ያሉ ቅሬታዎችን አጣራለሁ አለ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ
አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው

በተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ቅሬታዎች እየተነሱ መሆኑን የገለጸው አየር መንገዱ፣ ከደንበኞች ለቀረቡ ቅሬታዎችና አስተያየቶች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሒደቱን ሲከታተል መቆየቱን ገልጿል፡፡

በተያያዘ መረጃ በአየር መንገዱ ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን በተመለከተ ‹‹ብሔራዊ የአየር ትራንስፖርት ፋሲሊቲ ኮሚቴ›› በሰጠው መግለጫ እንደተገለጸው፣ በሻንጣ አገልግሎት ላይ የተፈጠረውን ቅሬታ ለማሻሻል ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው ብሏል፡፡ አሠራሩን በኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ለማስደገፍ እየተሠራ ነው ሲሉ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገልጸዋል፡፡

በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በሻንጣ ፍተሻ ወቅት በፀጥታና ፍተሻ አካላት የሚፈጸሙ አግባብ ያልሆኑ ድርጊቶች መኖራቸውን፣ በርካታ ግለሰቦች በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ቅሬታ ሲያቀርቡ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታት ያስችላል የተባለው ቴክኖሎጂ እያንዳንዱ ሻንጣ ከውጭ አገር መጥቶ መንገደኞቹ አስኪረከቡና ከኢትዮጵያ የሚወጡ መንገደኞችን ሻንጣዎች ከተረከበ ጀምሮ አውሮፕላን ላይ እስኪጫን ድረስ ያለውን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ፣ መጉላላቶችን ለመቀነስ እየተሠራ መሆኑን አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ሥራ መሠረት በጥቂት ወራት ውስጥ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አቶ መስፍን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በትራንስፖርት ሚኒስትሩ የሚመራ ‹‹ብሔራዊ የአየር ትራንስፖርት ፋሲሊቴሽን ኮሚቴ›› በማቋቋም፣ የአገሪቱን የአገልግሎት አሰጣጥ ፕሮግራም በማዘጋጀት ወደ ተግባር መገባቱን በመግለጫው ወቅት ተገልጿል፡፡ 

የአየር ትራንስፖርት አካላትን ሪፎርም በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል ውጤት ማምጣት እንደታቻለ፣ ኮሚቴው በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በቅርቡ የተነሱት አንዳንድ ቅሬታዎች ሆን ተብሎ የተቋሙን ገጽታ ለማበላሸት ቢሆንም፣ ኤርፖርት ውስጥ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በካሜራ ዕይታ ውስጥ በመሆኑና የቀረቡ ከካሜራ ዕይታ ውጪ የሆነ አሠራር ባለመኖሩ አንዳንድ ዕርምጃዎች መወሰዳቸውን የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ክፍተት በታየ ቁጥር የሚወሰደው ዕርምጃ ጥብቅ መሆኑን በመገንዘብ ችግሮችን ለመፍታት ከተወሰዱት ዕርምጃዎች መካከል፣ ከሥራ የተባረሩና በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሠራተኞች መኖራቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ዘለዓለም መንግሥቴ በበኩላቸው፣ የአየር መንገዱ ሰላምና ደኅንነት በቴክኖሎጂ በመታገዝ በጥብቅ ዲሲፕሊን እየተጠበቀ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በኤርፖርት ዙሪያ የወንጀል ተግባራት ላይ በሚሳተፉ ግለሰቦች ላይ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ በመሆኑ፣ ተገቢው  ማጣራት ተደርጎ  ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።

የአየር ትራፊክ ማኔጅመንትን በተመለከተ በአየር መንገዱ በየሁለት ደቂቃ ልዩነት አውሮፕላኖች ማረፍ የሚችሉበት አሠራር መፈጠሩን፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስድስት ወር ሥራ አፈጻጸም በተመለከተ በተያዘው በጀት ዓመት መንገደኞችን በማጓጓዝ ረገድ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ29 በመቶ፣ በገቢ የ14 በመቶ፣ እንዲሁም በትርፋማነት 22 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን አቶ መስፍን ገልጸዋል፡፡

አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት በ145 አውሮፕላኖች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን፣ በቅርቡ ለ120 የአዳዲስ አውሮፕላኖች ግዥ ትዕዛዝ መስጠቱን፣ እ.ኤ.አ. 2035 አሁን ካሉት ጋር ተደምሮ 271 አውሮፕላኖች የማድረስ ዕቅድ እንደተያዘ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም የቦሌ ኤርፖርት እያደገ የመጣውን የመንገደኞች ብዛት ለማስተናገድ በመጥበቡ ምክንያት የተርሚናል ሁለት ዓለም አቀፍ ደንበኞች የማስተናገጃ ሕንፃ ማስፋፊያ በመከናወን ላይ እንደሆነ፣ በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል፡፡

ሁለተኛው የአውሮፕላን መንደርደሪያ በማርጀቱ ምክንያት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በማውጣት ዕድሳት እየተደረገ መሆኑንንም አክለዋል፡፡ መንደርደሪያው በማርጀቱ ምክንያት የአውሮፕላኖችን እንቅስቃሴ በመገደብ መጓተት እየፈጠረ በመሆኑ ጥገና ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች