Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሚያስፈልገው በጀት 30 በመቶ ብቻ እየተገኘ እንደሆነ ተገለጸ

የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሚያስፈልገው በጀት 30 በመቶ ብቻ እየተገኘ እንደሆነ ተገለጸ

ቀን:

  • በየቀኑ 60 ሰዎች በቲቢ ሳቢያ ሕይወታቸውን እያጡ ነው ተብሏል

በኢትዮጵያ የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚውሉ መድኃኒቶች፣ ግብዓቶችና አስፈላጊ የሕክምና መሣሪያዎችን ለማሟላት ከሚያስፈልገው አጠቃላይ ገንዘብ 70 በመቶ ወይም ከ86.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘት እንዳልተቻለ ተገለጸ። 

ይህ የተነገረው የአሜሪካ ኤምባሲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ከአሜሪካው ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓትን ለማዘመን እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎችን በተመለከተ ለጋዜጠኞች በተደረገ ገለጻ ነው። 

በዝግጅቱ ላይ የዩኤስአይዲ በኢትዮጵያ የሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ) ተላላፊ በሽታዎች የሥራ ክፍል ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት የውልሰው ካሳዬ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፣ ኢትዮጵያ በአሁን ወቅት በዓለም የጤና ድርጅት 30 ከፍተኛ የቲቢና የኤችአይቪ ሥርጭት በከፍተኛ ደረጃ ከተስፋፋባቸው አገሮች አንዷ ናት ብለዋል፡፡

ከፍተኛ አማካሪው አክለውም ቲቢን ለመከላከልና መቆጣጠር ከሚያስፈልገው ፈንድ 30 በመቶው ብቻ ነው እየተገኘ ያለው ብለዋል። 

ሪፖርተር የተመለከተው ከዩኤስኤአይዲ ኢትዮጵያ የሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ) ተላላፊ በሽታዎች የሥራ ክፍል ሰነድ የበጀት እጥረቱ ላለፉት ዓመታት እየተባባሰ መምጣቱን ያሳያል። 

በዚህም መሠረት እ.ኤ.አ. በ2018 የሚያስፈልገው በጀት 92,637,236 ሚሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ አቅም ወደ 9.7 ሚሊዮን ዶላር፣ ዩኤስአይዲን ጨምሮ በውጭ  ደጋፊዎች ወደ 38.87 ሚሊዮን ዶላር ቢገኝም በአጠቃላይ ከሚያስፈልገው 52 በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ ብቻ ነበር ማግኘት መቻሉ ታውቋል፡፡

በተከታታይ ዓመታት የሚያስፈልገው የበጀት መጠን እያደገ 125 ሚሊዮን ዶላር ላይ ቢደርስም፣ በተቃራኒው በአገር ውስጥ አቅም የሚሸፈነው እ.ኤ.አ. በ2019 እና 2020 በጥቂቱ ከፍ ብሎ 10.33 ሚሊዮን ዶላር ደርሶ የነበረ ቢሆንም፣ ተከታትለው በመጡት ዓመታት እየወረደ ሄዶ እ.ኤ.አ. በ2022 ወደ 7.1 ሚሊዮን ዶላር በጀት ዝቅ ብሏል ተብሏል፡፡ 

የበጀት እጥረቱ እ.ኤ.አ. በ2022 67 በመቶ ደርሶ እንደነበር ሪፖርተር ከሰነድ ማረጋገጥ ሲችል፣ የተራድኦ ድርጅቱ ከፍተኛ አማካሪ የውልሰው (ዶ/ር) አሁን ወደ 70 በመቶ ከፍ ማለቱንና ሁሉም ለቲቢ ሕክምና የሚውሉ መድኃኒት፣ ግብዓትና የሕክምና አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎች በደጋፊዎች ዕርዳታ ወደ አገሪቱ እንዲገባ እንደሚደረግ አብራርተዋል። 

የተራድኦ ድርጅቱ ቲቢን ለተመለከቱ ሥራዎች ከሚያበረክተው በዓመት ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ባሻገር ነው የበጀት እጥረቱ ቀጥሏል የተባለው።

የቤተሰብ አባላቸው በበሽታው ከሚጠቃባቸው ቤተሰቦች 50 በመቶ በሚሆኑት ላይ እጅግ አስከፊ የሚባል ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድርባቸውም ገልጸዋል። 

የውልሰው (ዶ/ር)፣ ‹‹አስከፊ ተፅዕኖ ስንል በበሽታው የተጠቃ የቤተሰባቸው አባልን ለመንከባከብ የሚያወጡት ወጪ፣ ለተቀረው ቤተሰብ ለመኖር በሚያስፈልገው የኢኮኖሚ አቅም ላይ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል። ከፍተኛ አማካሪው በበሽታው ዙሪያ ባሉ ሥራዎች ላይ የግሉ ዘርፍ እንቅስቃሴ ደካማ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በአገሪቱ በየዓመቱ 156,000 ሰዎች በሳምባ በሽታ እንደሚጠቁ፣ ከእነዚህ ውስጥ 2,000 ያህሉ በበሽታው ለተጠቁ ሰዎች ሕክምና የሚሰጡ ሁለት ዓይነት መድኃኒቶችን የተለማመደና መቋቋም የሚችል (Multi-Drug Resistant TB/ MDR-TB) በተባለው የበሽታው ዝርያ ዓይነት የሚጠቁ ናቸው የተባለ ሲሆን፣ 21,000 ዜጎች ደግሞ ሕይወታቸውን እንደሚያሳጣቸው ተነግሯል። 

የውልሰው (ዶ/ር)፣ ‹‹ይህ የሞት ደረጃ ማለት ቲቢ በቀን 60 ሰዎችን ሕይወት እያሳጣ ነው ማለት ነው። በየቀኑ የአንድ አውቶብስ ሰው ገደል ውስጥ ገፍተን እንደ መክተት ነው፤›› ሲሉ ገልጸውታል። 

ያለው የገንዘብ እጥረት በአጠቃላይ በአገሪቱ ቀላል የቲቢ በሽታ ከሚያጋጥማቸው 27 በመቶውን ማግኘትና ማከም እንዳይቻል ማድረጉን፣ እንዲሁም ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሁለት መድኃኒቶችን መቋቋም የሚችል የቲቢ ዓይነት (MDR-TB) የሚያዙ ሰዎችንም ማግኘትና ማግኘት የማያስችል ሁኔታ መፍጠሩም ተነግሯል።

እንደ የውልሰው (ዶ/ር) ማብራሪያ የአዳዲስ የምርመራ ቴክኖሎጂዎችና ፀረ ቲቢ መድኃኒቶች ግኝት የመድኃኒቶቹን የመርዛማነት መጠን፣ ይሰጥ የነበረውን መድኃኒት ብዛትና ይወስድ የነበረውን ጊዜ አሳጥሯል፡፡

ለ690 የመንግሥት የጤና ተቋማት በተሠራጨ ጂንኤክስፐርት (Genexpert) በተባለ አዲስ የምርመራ መንገድ፣ ከዚህ ቀደም ለ17 ዓመታት ገደማ እስከ ሦስት ወር ይፈጅ የነበረውን የምርመራ ሒደት ከ70 ደቂቃ እስከ ሁለት ሰዓት ባለ ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ እየተቻለ መሆኑን ተናግረዋል። 

በበሽታው ከተጠቃ ሰው ጋር አብረው ለሚኖሩ ሰዎች የሚሰጡ እስከ አንድ ወር ድረስ ከሚቆዩ መድኃኒቶች አቅርቦት ጀምሮ፣ በኢትዮጵያ ለቀላል የቲቢ በሽታ የሚወሰድ መድኃኒት ጊዜን ከስድስት ወር ወደ አራት ወራት፣ ሁለት ዓይነት የመድኃኒት ዓይነቶችን መቋቋም ለሚችለው የቲቢ ዓይነት ታካሚዎች የሚሰጥ መድኃኒት መወሰድ ያለበት ጊዜን ከሁለት ዓመት ወደ ዘጠኝ ወር ዝቅ መደረጉን፣ እንዲሁም ከፍተኛ መድኃኒቶችን የመቋቋም አቅም ላለው የቲቢ ዓይነት (XDR-TV) ደግሞ ከዘጠኝ እስከ 11 ወራት ባልበለጠ ጊዜ የሕክምና መድኃኒት መስጫ ጊዜውን ማሳጠር እንደተቻለ ተነግሯል። 

የውልሰው (ዶ/ር)፣ ‹‹ከሦስት ዓመት በፊት የቲቢ ባክቴሪያን ለማጥፋት የሚሰጠው መድኃኒት መርዛማነት ሲኖረው፣ ታካሚዎች በቀን እስከ 30 የመድኃኒት ፍሬዎች እስከ ዘጠኝ ወራት ለሚደርስ ጊዜ ይወስዱ ነበር፤›› ብለዋል። 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...