Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያና ማልታ ማሪታይምን ጨምሮ በበርካታ ዘርፎች የሚያሠራቸውን የመጀመሪያ የቢዝነስ ፎረም አካሄዱ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያና የማልታ ባለሀብቶች በማሪታይም፣ በጤና፣ በአቪዬሼን፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በፋርማሲዩቲካልና መሰል ዘርፎች በጋራ እንዲሠሩ የሚያስችል፣ በርካታ የማልታ ባለሀብቶች የተገኙበት የመጀመሪያ የቢዝነስ ፎረም ተካሄደ፡፡

በሁለቱ አገሮች መካከል በተካሄደው የመጀመሪያው የቢዝነስ ፎረም ላይ እንደተገለጸው፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመምረጥ የማልታ ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን የማስፋፋት ፍላጎት እንዳላቸው ነው፡፡

ማክሰኞ መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል የተካሄደው የቢዝነስ ፎረም ላይ ከተዘረዘሩት የቢዝነስ አማራጮች መካከል ጤና፣ አቪዬሼን፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ፋርማሲዩቲካል፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ እንዲሁም ማልታ የደሴት አገር በመሆኗ በርካታ ልምድ ያገኘችበት የማሪታይም አገልግሎት ይገኙበታል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወ/ሮ ሃና አርዓያ ሥላሴ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በማልታ ካደረጉት ጎብኝት በኋላ ሁለቱ አገሮች በቅርብ ጊዜ የተፈራረሙትን ስምምነቶች አስታውሰው፣ በስምምነቶቹ ላይ የተነሱትን ጉዳዮች አስፍተው የመቀጠል ዓላማ መኖሩን ገልጸዋል፡፡

ከስምምነቶቹ አንደኛው ሥልጠናዎችን የሚመለከት መሆኑን ያስታወሱት ኮሚሽነሯ፣ ‹‹ማልታ በተለይ የደሴት አገር በመሆኗ ማሪታይም በጣም ሰፊና ለብዙ ዘመናት የቆየ ልምድ አላት፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ከዚህ በመነሳት ሥልጠናዎችን ተጠቅሞ ‹‹የኢትዮጵያን የማሪታይም ሥራ የማስፋፋት ዕድል ይሰጣል፤›› ሲሉ ስለስምምነቱ ገልጸዋል ፡፡   

 የስምምነቱ አካል የነበረው ማልታ ጠንካራ በሆነችበት የአቪዬሽን ዘርፍም የኢትዮጵያ ባለሙያዎችን ማሠልጠንና መሰል ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹ማልታ በአፍሪካና በአውሮፓ መካከል የምትገኝ ትንሽ አገር በመሆኗ፣ ለኢትዮጵያ ቢዝነሶች ዕድል ትፈጥራለች፤›› ሲሉ የገለጹት ኮሚሽነሯ፣ ‹‹ከማልታ ጋር የቢዝነስ ግንኙነት ሲኖረን ለቀሪው የአውሮፓ ክፍል ዕድል የሚሰጥት ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ምሥጋኑ አረጋ (አምባሳደር) በኢትዮጵያ  የማልታ አምባሳደር ኖናልድ ሚካልፍ፣ የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መላኩ አዘዘ (ኢንጂነር) እና የማልታ ንግድ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አላቶን ቡቲጄግ በተገኙበት ነው ፎረሙ የተካሄደው፡፡

ማልታ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ከከፈተች ሁለት ዓመት ከግማሽ ሲሆናት፣ የኢትዮጵያ የመንግሥት ተወካዮች እንደገለጹት ሁለቱ አገሮች ባለፉት ሦስት ዓመታት የጠበቀ ዲፕሎማሲ ግንኙነት እየገነቡ ነው፡፡

ማልታ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ በአፍሪካና በአውሮፓ መካከል በሜዲትራኒን ባህር ውስጥ የምትገኝ ደሴት ስትሆን፣ ከግማሽ ሚሊዮን ትንሸ ከፍ ያለ የሕዝብ ቁጥር ሲኖራት፣ የአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርትም (GDP) ከ18 ቢሊዮን ዶላር የማይበልጥ ነው፡፡

በአብዛኛው የማልታ ኢንቨስተሮች በአፍሪካ መዋዕለ ንዋያቸውን የሚያፈሱት በሰሜን አፍሪካ አገሮች ግብፅ፣ ሊቢያ፣ ቲኒዝያና ሞሮኮ ነው፡፡ የአገሪቱ ንግድ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አን ቶን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የማልታ ባለሀብቶች በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች መዋዕለ ንዋቸውን የማፍሰስ ፍላጎት ሲኖራቸው ኢትዮጵያ አንደኛዋ ትልቋ መዳረሻ ልትሆን ትችላለች፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች