Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየኢኮኖሚ ጥገኝነትም የሚፈተነው የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ

የኢኮኖሚ ጥገኝነትም የሚፈተነው የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ

ቀን:

ኢትዮጵያ ውስጥ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ በሚፈለገውን ያህል አይደለም፡፡ ይህም የሆነው በተለያዩ ጫናዎች ሳቢያ ሲሆን፣ ከጫናዎቹም መካከል አብዛኛዎቹ ሴቶች በኢኮኖሚ የወንዶች ጥገኛ ሆነው መቅረታቸው ነው፡፡

በኢትዮጵያ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እየተሻሻለ ቢመጣም፣ በፖለቲካ ውሳኔ ሰጪነትና ኃላፊነት ላይ ያላቸው ሚና እምብዛም አይደለም፡፡ በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ያላቸው የመምራት ዕድልም እንዲሁ፡፡

የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎና አመራርነት ማሳደግ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ግማሽ ያህሉን የሚይዙ ሴቶችን መወከል ነው ቢባልም፣ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ሚኒስቴሮች ድረስ በመሪነትና በውሳኔ ሰጪነት ብዙም ተሳትፎ የላቸውም፡፡

- Advertisement -

ይህ በእነዚህ ተቋማት ብቻ ሳይሆን ባሉባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥም ተመሳሳይ ነው፡፡ በመላ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ፓርቲዎች ውስጥም በሴት የሚመራ  የለም፡፡

ሴቶች በፖለቲካ መሳተፍ አለባቸው፡፡ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮቻቸው ሊቀረፍላቸውና በአጠቃላይ የሥርዓተ ፆታ እኩልነት ሊረጋገጥ ይገባል በሚል የሚሠራው የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት (ኢሴማቅ)፣ ችግሩንና መፍትሔውን ያመላክታል፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎችም ግብዓት ይሆናል ያለውን አመላካች  ጥናት ዓምና በሚያዝያ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

ሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ፓርቲያቸውን ወክለው በተመራጭነት እንዲወዳደሩ፣ የተመረጡ ሴቶች በተወከሉበት ምክር ቤትና በፖለቲካ ፓርቲያቸው የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያደርጉትን ጥረትና በቀጣይም ይህንን ለማጎልበት ይረዳ ዘንድ በሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎና የሚያጋጥሙ ውስንነቶች ዙሪያ የተጠናው ጥናት እንዳመለከተው፣ በተለይ ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እያደገ ነው፡፡

ከ20 ዓመታት ወዲህ ያለው ሲታይም፣ ከ45 በመቶ እስከ 48 በመቶ መራጮች ሴቶች ናቸው፡፡ በተመራጭ ደግሞ የዛሬ 20 ዓመት 2.4 በመቶ የነበረው አሁን ላይ 38.7 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ይህ በክልሎች 40 በመቶ ድረስ አድጓል፡፡

ሆኖም ሴቶች ፖለቲካ ውስጥ እንዳይሳተፉ ሦስት መሰናክሎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው አባታዊ የሆነ ሥርዓት ሲሆን፣ ሁለተኛው የፖለቲካ ባህሉ ጨቋኝ መሆኑ ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ በፖለቲካ ፓርቲዎች እክል መሆናቸውን ጥናቱ ያሳያል፡፡

አባታዊ የሆነ ሥርዓትና የፖለቲካ ባህሉ ጨቋኝ መሆን በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚገለጽ ሲሆን፣ በራሱ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የሚስተዋል እክልም አለ፡፡ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን ወደ ፓርቲው ለማስገባትም ሆነ ከመጡ በኋላ የበላይ ለማድረግና ወደ ውሳኔ ሰጪነት ደረጃ ለማምጣት ብዙም ሲሠሩ አለመታየታቸውም  ሌላው ችግር ነው፡፡ ሴቶች በኅብረተሰቡ ደረጃ ያላቸው የ50 በመቶ ውክልናም  በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የለም፡፡

ሴቶች በኢኮኖሚ አቅማቸው አለመጎልበታቸውም የፖለቲካ ተሳትፏቸውን ፈትኖታል፡፡

የቤት ውስጥ ሥራን የማከናወን፣ የማስተዳደርና ልጆችን የመንከባከብ ኃላፊነት ከጫንቃዋ ላይ አለመውረድ ወይም ለእሷ ብቻ አሳልፎ የመስጠት ሁኔታ በፖለቲካ ተሳትፎዋ ላይ ከተጋረጡት ጫናዎች መካከልም ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ ብሔራዊ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፣ የሴቶች መምርያ ዋና ተጠሪና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሴቶች ክንፍ ሰብሳቢ ወ/ሮ ቅድስት ግርማ እንደገለጹትም፣ አንዲት ሴት በፖለቲካው ለመሳተፍ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ለመሆን መጀመርያ የሐሳብ ነፃነት ሊኖራት ይገባል፡፡

ይህ ዓይነቱ ነፃነት የሚገኘው ደግሞ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት በመላቀቅ ነው፡፡  በኢኮኖሚ ጥገኛ የሆነች ሴት፣ የፖለቲካ ተሳትፎዋ የመነመነ እንደሚሆን ገልጸው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሴቶች በባሎቻቸው ወይም በወንድሞቻቸው ኢኮኖሚ ጥገኛ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

‹የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ስኬት ለላቀ የፖለቲካ ተሳትፎ›› በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን አስመልክቶ በተካሄደው የልምድ ልውውጥ ወ/ሮ ቅድስት እንዳብራሩት፣ ፖለቲካ ሁልጊዜ ከኢኮኖሚ ጋር አብሮ የሚሄድ ነው፡፡

በዚህም የተነሳ ሴቷ የኢኮኖሚ ነፃነት ሳትቀዳጅ ወይም ከየትኛውም አካል ጥገኝነት ሳትላቀቅ ፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ብትሳተፍ ሐሳቧ ተቀባይነትን እንደሚያጣና በቤተሰቦቿም ዘንድ ‹አርፈሽ ተቀመጭ› እንደምትባል ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሴራና መንገዳገድ የበዛበት መሆኑን፣ በዚህ ላይ ራሷን ካልቻለች ወይም የኢኮኖሚ አቅም ካጣች ብዙ ዋጋ ሊያስከፍላት እንደሚችል፣ የምትንቀሳቀሰውም በሌሎች ፈቃደኝነት መሆኑን ልትገነዘበው እንደሚገባ ወ/ሮ ቅድስት ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡

እንደ ወ/ሮ ቅድስት አባባል፣ እሳቸው በፖለቲካ ፓርቲ ታቅፈው ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን ለማበርት የሚያስችላቸውን እንቅስቃሴ በጀመሩበት ወቅት ከባለቤታቸው ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ደርሶባቸው ነበር፡፡

የአራት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ቅድስት፣ የጀመሩትን የፖለቲካ ተሳትፎ በምንም መልኩ እንደማያቋርጡ ለባለቤታቸው በተደጋጋሚ ጊዜ እንደነገሯቸውና በመጨረሻም መግባባት ላይ እንደደረሱ፣ የጀመሩትንም እንቅስቃሴ አጠናክረው እንደቀጠሉ ልምዳቸውን ጠቅሰው ተናግረዋል፡፡

ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በሁሉም ሴቶች እንደሚደርስ፣ የሴቶችን የፖለቲከ ተሳትፎ ወደኋላ የሚጎትተው የባሎች እንቢተኝነትና ፈቃደኛ ሆነው አለመገኘት መሆኑን የእሳቸው ተሞክሮ እንደሚያሳይ አስረድተዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ተረጋግቶ ችግሩን በውይይት መፍታት እንደሚቻል ከወ/ሮ ቅርስት ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

‹‹የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ የብዙ ድምር ውጤት ሆኖ እናገኘዋለን፤›› ያሉት ደግሞ የፆታና የሰብዓዊ መብቶች ኤክስፐርት ወ/ሮ ጨረር አክሊሉ ናቸው፡፡ እንደ ኤክስፐርቷ፣ በፓርላማ ውስጥ የሴቶች ቁጥር አድጎ ሊታይ የቻለበት ምክንያት በፓርቲ ደረጃ በፆታ ላይ የተመሠረተ ሥርዓት በመዘርጋቱ ነው፡፡

ኢኮኖሚ ወሳኝ እንደሆነና በተለይ ሴቶችን ከጥገኝነት እንደሚያወጣ፣ ሆኖም ሴቶችን በኢኮኖሚ ለማበልፀግም ሆነ በሴቶች ፖለቲካ ተሳትፎና አመራር ሰጪነት ብዙም እንዳልተሠራ አክለዋል፡፡  

‹‹የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ፤›› ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ ኃይለ ማርያም፣ ኅብረቱ ከተመሠረተ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ባለፉት አራት ዓመታት በርካታ ሥራዎች እንዳከናወነ ተናግረዋል፡፡

ካከናወናቸውም ሥራዎች መካከል በ2011 ዓ.ም. የተካሄደውን የሲዳማ ሕዝብ፣ ስድስተኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብና የወላይታ ደግሞ ሕዝበ ውሳኔዎችን ታዝቦ ሪፖርት ማድረጉ እንደሚገኝበት አስታውቀዋል፡፡

ከዚህም ሌላ የመራጮች ትምህርት ዘመቻ በማካሄድም ለአባላቱ የፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ገንዘብ የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸትና የመራጮች ትምህርት እንዲካሄድ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስረድተዋል፡፡

በስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫም የሲዳማ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ፣ የወላይታ ዳግም ሕዝብ ውሳኔዎችን የትዝብት ሪፖርቶችን በማውጣት ለሚመለከታቸው አካላት እንዲደርሳቸው ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

የካቲት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በዋሽንግተን ሆቴል የተካሄደውን ይህንኑ የልምድ ልውውጥ መድረክ በመተባበር ያዘጋጁት የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶችና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማኅበራት እንዲሁም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና ትምራን ናቸው፡፡.  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...