Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አጉል ብልጠት!

ሰላም! ሰላም! እየጀመርን የምናቋርጠው፣ እየቀጠልን የምንበጥሰው ከመብዛቱ የተነሳ እንኳን ሰላምታው ምሳና እራቱ ቢረሳን ምን ይፈረድብናል? ለማንኛውም ሰላም ለሁላችሁ ይሁን እላለሁ፡፡ ሰላም በሌለበት ጠብ ይበረታል፡፡ ጠብ በበረታበት ደግሞ ትርፉ ጥፋት ብቻ ነው፡፡ ከጥፋት ይሰውራችሁ፡፡ እንዲሁም ከአጥፍቶ ጠፊዎች፡፡ በነገራችን ላይ የአጥፍቶ ጠፊ ጉዳይ ሲነሳ ቦምብ እያፈነዱ ለዕልቂት ከሚዳርጉት በተለየ ፆታ፣ ዘር፣ እምነትና የቆዳ ቀለም ሳይለዩ በተሳለ ጎራዴ አንገት የሚቀሉ መቀፍቀፋቸው የዓለም ፍፃሜ ምልክት ይሆን ወይ እያልኩ እጨነቃለሁ፡፡ ግድ የማይሰጠው ደግሞ፣ ‹‹አንበርብር ልፋ ብሎህ ነው እንጂ ማን ለማን ደንታ ሲኖረው አይተሃል?›› ብሎ በነገር ጠቅ ያደርገኛል፡፡ በነገር ጠቅ ጠቅ የተጀመረው ወግ ከእናቱ አንቀልባ ላይ አልወርድ እንዳለ ሕፃን የሆነው ፖለቲካችን ላይ ይከመርና ሥራ ያስፈታኛል፡፡ እግሬ እስኪነቃ ስዞር የማየውንና የምሰማውን ልንገራችሁ ብዬ ብነሳ፣ ግማሻችሁ ወደ ሆስፒታል ግማሻችሁ ወደ ፀበል ሪፈር ስለምትደረጉ ይቅርባችሁ፡፡ ይቅር ማለትን የመሰለ ነገር እያለ እኮ ነው በማይረባው ጭምር እየተናጀስን ጤና የምናጣው፡፡ ጤና ያጣ ጊዜ!

ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ሰሞኑን ምን እንደሰማ አላውቅም፣ ‹‹እህህ…›› ይላል፡፡ ‹‹ምን ሆነሃል?›› ብዬ ስጠይቀው፣ ‹‹ተወኝ እባክህ…›› እያለ ይንጎራደዳል፡፡ የእሱ እንዲህ መሆን ውስጤን ሲጐረብጠው ውሎ ምሽት ላይ ቤት ስገባ ውዷ ማንጠግቦሽ በኩርፊያ ፊቷ ተራራ አክሏል፡፡ ‹‹ምንድነው ነገሩ?›› ስላት፣ እሷም እንደ ባሻዬ ልጅ ‹‹እህህ…›› ከማለት ውጪ መልስ ነፈገችኝ፡፡ ‹‹ኧረ ምንድነው ነገሩ?›› ብላት ብሠራት የኩርፊያዋን ሚስጥር ለመናገር ፈቃደኛ ያልሆነችው ማንጠግቦሽ እንዲሁ ስትገላበጥ አደረች፡፡ እንዳይነጋ የለም ባንኜ ስነሳ አጠገቤ የለችም፡፡ አንዴ ጓዳ፣ ከዚያም ማዕድ ቤት፣ በኋላም ጓሮውን ብዞር እሷን ማግኘት አልተቻለኝም፡፡ ቢቸግረኝ ሞባይል ስልኳ ላይ ደወልኩ ዝግ ነው፡፡ የባሰ አታምጣ በአንዴ አመዴ ቡን አለ፡፡ ከንፈሬ ደረቀ፡፡ ዓይኖቼ ፈጠው ቀሩ፡፡ ምንድነው ነገሩ? እንጃ!

እግሬን እየጐተትኩ ወደ አዛውንቱ ባሻዬ ቤት አመራሁ፡፡ ማልደው ቤተ ክርስቲያን መሄዳቸው ተነገረኝ፡፡ ተመልሼ መጥቼ ባለሦስት እግር መቀመጫ አውጥቼ የጠዋቷን ፀሐይ እየሞቅኩ በሐሳብ ነጎድኩ፡፡ በዚህ መሀል ስልኬ ጮኸ፡፡ ተፈናጥሬ ተነስቼ ማን እንደደወለ የስልኬ ጠባብ ስክሪን ላይ ሳጮልቅ ማንጠግቦሽ ናት፡፡ እየተንገበገብኩ ‹‹ሃሎ…ሃሎ…›› ስል፣ ‹‹አንበርብር ምን ሆነሃል? ለምንድነው እንደ ሶሎግ ውሻ የምታለከልከው…›› አለችኝ፡፡ ወይ ጉድ? ትናንት ኩርፊያ ዛሬ ዘለፋ፡፡ ‹‹የት ሆነሽ ነው?›› ስላት፣ ‹‹የአንተን ጉድ ላጣራ ነበር አልተሳካልኝም እባክህ…›› ብላ ዘጋችው፡፡ የእኔ ጉድ ምን ይሆን? ምኑስ ነው ያልተሳካው? ለማንኛውም እሷ እንኳን ደህና ሆነች ብዬ ወደ ድለላዬ አዘገምኩ፡፡ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት እያንዳንዱ ቀን ያስፈልገዋል፡፡ አለበለዚያ የዘንድሮ ኑሮ እንደ ዶዘር በላዩ ላይ ይሄድበታል፡፡ የዘንድሮ ኑሮ ደግሞ ምሕረት አልባ ሆኗል፡፡ ወገኖቼ አለን እንዳንል አዕምሮአችን ጭው ብሎ ጠፍቷል፣ የለንም እንዳንል አካላችን ይወራጫል፡፡ ያበደ ኑሮ እያሳበደን ቁጭ ካልንበት ላንነሳ ስለምንችል ብንንቀሳቀስ ይሻላል፡፡ አለፍ አለፍ እያልን!

የሆዴን በሆዴ ብዬ አንድ የማሻሽጠው ቪላ ስለነበር ወደ እዚያው አመራሁ፡፡ ገዥው ቅብርር ያለ በሃያዎቹ አጋማሽ ላይ የሚገኝ ወጣት ሲሆን፣ ጆሮው ላይ የሰካው ‹ብሉቱዝ› በጣም ‹ቢዚ› ያደረገው በመሆኑ አልፎ አልፎ ነው የሚያናግረኝ፡፡ በሙዚቃ ይሁን በቀልድ ወይም በሌላ ነገር እያዋራኝ ሲስቅ፣ በቅርቡ ከአማኑኤል ‹‹ግራጁዌት›› ያደረገ እየመሰለኝ መሳቀቄ አልቀረም፡፡ ብቻ እንደ ምንም ብዬ የዛሬውን ቢዝነሴን ዳር ላድርስ እንጂ፣ ከእንዲህ ዓይነቱ ዋዘኛ ጋር ደንበኝነት ማበጀት አልታየኝም፡፡ የምታብረቀርቀው ዘናጭ ቪ8 መኪናው ውስጥ ገብተን ወደ ሲኤምሲ አቅጣጫ ጉዞአችንን ስንጀምር፣ ‹‹ይገርምሃል በደላላ ቤት መግዛት አልፈልግም ነበር፡፡ ነገር ግን ምን ታደርገዋለህ አንተ እጅ ላይ ጣለኝ…›› ብሎ አስገምጋሚ ሳቁን ሲለቀው ቀኑን ረገምኩት፡፡ አንዳንዱ ቀን ደግሞ ከእንዲህ ዓይነቱ ጋርም ያገናኛል፡፡ ቀልቡ ወይ ከእኔ ወይ ከራሱ ሳይሆን የሚፈለገው ቪላ ጋ ደርሰን ቆምን፡፡ ከቲክቶክ በቃረመው ቀልድ ወጋኝ እኮ!

ባለቤቱ ከዓመት በፊት ገንብተው የጨረሱትን ቪላ ከ80 ሚሊዮን ብር በታች አንዲት ሰባራ ሳንቲም ሳይቀንሱ እንደሚሸጡት ኮምጨጭ ብለው ሲናገሩ፣ አጅሬ ጎረምሳው ተዟዙሮ አይቶ ገቢ እንደሚያደርገው ሲያውጅ እኔ አላመንኩም፡፡ የማገኘው ዳጎስ ያለ ኮሚሽን ከሚያስገኝልኝ ይልቅ እኔን ያስደነቀኝ፣ ይኼ ወጠጤ ጎረምሳ በዚህ ዕድሜው ለአንድ ቪላ መግዣ 80 ሚሊዮን ብር ከየት አመጣ የሚለው ነው፡፡ አንድ ቪላ በዚህን ያህል ብር እንደ ቀልድ ከሸመተ ለሌላ ሌላው ያካበተው ስንት ይሆን ብዬ በሐሳብ ጭልጥ አልኩ፡፡ ከነጎድኩበት የቀን ቅዠት የመለሰኝ የገዥና የሻጭ በከፍተኛ ሳቅ የታጀበ መተቃቀፍና ‹‹ቺርስ›› ዓይነት መጨባበጥ ነበር፡፡ እኔም የድርሻዬን በሞባይል አካውንቴ ተቀብዬ ሰዎቹን በቆሙበት ጥዬአቸው ስሄድ፣ ውስጤ በደስታ ምትክ በሐዘን ተቆራምዶ ስለነበር የምረግጠውን እንኳ በቅጡ ማየት ተሳነኝ፡፡ ‹እጅን በአፍ የሚያስጭን› የሚሉት ይህንን ይጨምር አይጨምር ባይታወቅም፣ እኔ ግን ሳላስበው ቤቴ የደረስኩት እጄን አፌ ላይ መርጌ ነበር፡፡ ዘንድሮ ገና ስንት ጉድ ይታያል!

እኔ አንበርብር ምንተስኖት ለድለላ ላይ ታች ስማስን የባከኑት ዓመታት ያንን ቦርቆ ያልጠገበ ጎረምሳ ያደርሳሉ፡፡ ኑሮዬ በበርካታ ቀዳዳዎች የተከበበ በመሆኑ አንዱን ስደፍን ሌላው ሲያፈተልክ፣ ፀጉሬ ከመሸበት አልፎ ተመልጧል፡፡ ይህች ገዳዳ ባርኔጣዬ ባትከልለኝ ኖሮ የዘንድሮ ንፋስ የቀረውን ፀጉር ይዞት ሄዶ ባልጩት መምሰሌ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የሆነስ ሆነና የእኛ ነው የምንለው ሀብት ወይም ጥሬ ገንዘብ ምንጩ ካልታወቀ እንዴት መተማመን ይቻላል? በየሥፍራው የሚገነቡት ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች፣ የሚከፈቱት ታላላቅ ሆቴሎች፣ እንደ እንጉዳይ የሚፈሉት ሱፐር ማርኬቶች፣ ውድ የአልባሳትና የመጫሚያ መደብሮች፣ እኔ ነኝ ያሉ ሬስቶራንቶች፣ ዋጋቸው የማይቀመስ ሽቶ ቤቶችና የመሳሰሉት የንግድ መናኸሪያዎች በባለቤትነት የሚይዙዋቸው እነ ማን ናቸው? ትናንት የት የነበሩ ናቸው? ምን ሠርተው ምን አፈሩ? ከትቢያ ተነስተው በምን ያህል ፍጥነት ላይ ተሰቀሉ? የሚሉት ጥያቄዎች ‹ሆድ ይፍጀው› ያስብሉኛል፡፡ ለአንዱ የእኔ ቢጤ ደላላ ጥያቄዎቼን ብደረድርለት፣ ‹‹ሰውዬው ‹ጎመን በጤና› ሲባል አልሰማህም መሰል…›› ብሎኝ፣ ‹‹…እኛ ደላሎች ‹ማወቁንስ እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን› የሚባለውን አባባል ስለምናውቅ ዝም ነው ጭጭ ነው…›› ብሎኝ በቆምኩበት ጥሎኝ ሄደ፡፡ ንካው ልበል ወይስ ልተው!

ሆዴን ባር ባር ሲለኝ ያ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው ትዝ የሚለኝ፡፡ ደወልኩለትና ወደ ግሮሰሪያችን ብቅ እንዲል ነገርኩት፡፡ ግሮሰሪያችን በደንበኞች ከዳር እስከ ዳር ጢም ብላለች፡፡ ጥግ ላይ ሆኜ የቀረበልኝን ያላበው ቢራ በአንድ ትንፋሽ ሳንቆረቁር የባሻዬ ልጅ ደረሰ፡፡ ‹‹እህህ… ከምትል ከቢራ ጋር ወግ ብትይዝ ሳይሻልህ አይቀርም…›› እያልኩ ወጌን ጀመርኩ፡፡ ‹‹እህህ ነው እንጂ ሰው በአያሌው ታሞ፣ ካማረሩትማ ይጨምራል ደግሞ…›› እያለ በዝግታ አንጎራጎረ፡፡ ‹‹የአንተ እህህ እና የማንጠግቦሽ ኩርፊያ አልገባኝ ስላለ ወርቁን ትተህ ሰሙን ብትፈታልኝ ብዬ ነው የፈለግኩህ…›› ማለት ስጀምር ሳቁን ለቀቀው፡፡ እየደጋገመ ሲስቅ ቆይቶ፣ ‹‹አይ አንበርብር እኔ ነኝ ጉድ የሠራሁህ…›› አለኝ፡፡ በአልገባኝም አየሁት፡፡ ‹‹ማንጠግቦሽን ትናንት እስኪ ማታ ቤት ሲገባ ኩርፍ በይበትና የሚሆነውን ንገሪኝ ብላት፣ ኩርፊያዋን የእውነት አድርጋው እንቅልፍ እንደነሳችህ ነገረችኝ፡፡ ሚስቶች ሲያኮርፉ ባሎች እንዴት ነው የሚሆኑት የሚል ጥናት እየሠራሁ ስለነበር፣ ማንጠግቦሽ ኩርፊያው ለሃያ አራት ሰዓት የሚቆይ መስሏት አንተንም ራሷንም ስትበጠብጥ አደረች…›› እያለ ሲነግረኝ፣ ‹‹ጉድህን አውቃለሁ ብዬ ሳይሳካልኝ ቀረ…›› ያለኝ ድምጿ ጆሮዬ ላይ አስተጋባ፡፡ ኧረ ጐበዝ፣ የተማረውና ያልተማረው ድንበሯ ያልተለየበት አገር ውስጥ እየኖርን እንዴት አገር ያድጋል? እንዴትስ አንዱ ሌላውን ያስተምራል? እኔ ከዕውቀቱ ያልገፋሁ ደላላ ወገናችሁ አሁንስ በጣም ፈራሁ፡፡ ውሎ ሲያድር ነገራችን ሁሉ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን እያልኩ ሥጋት ገባኝ፡፡ በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ጦስ የሰው ልጅ ሥራ ሊፈታ ነው ተብሎ ዓለምን ሥጋት ወሮት እኛ እዚህ እርስ በርስ ሥጋት የምንፈጣጠርበት ምክንያት አልገባ አለኝ፡፡ የገባችሁ አስረዱኝ እባካችሁ!

እስኪ እንሰነባበት፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነገር ግራ ቢያጋባኝም የግሮሰሪው ደንበኞች ወግ ግን ጆሮዬን እየሳበው፣ እያከታተልኩ የጠጣሁት ቢራ ሰውነቴን ዘና እያደረገው እንደነበር እውነቱን ባልናገር ጥሩ አይደለም፡፡ አንዱ ከወዲያ ማዶ ሆኖ ለሌላኛው፣ ‹‹ማንን ነው ለመምረጥ የተዘጋጀኸው?›› በማለት በሞቅታ የታጀበ ጥያቄ ድንገት ሲያቀርብለት ግሮሰሪዋ ከመቅጽበት በፀጥታ ተዋጠች፡፡ የምን ምርጫ ነው የሚያወሩት እነዚህ ሰዎች፡፡ ያው ሰው መልሶ፣ ‹‹ፖለቲካ ሲወራ የምን ፀጥታ ነው? የምን በፍርኃት መራድ ነው?›› ሲል አንዳንዶች ሹልክ እያሉ ወጡ፡፡ ‹‹ፖለቲካና ኮረንቲን በሩቁ ነው እያላችሁ እስከ መቼ ትኖራላችሁ?›› እያለ ያው ሰው ነገሩን ሲቀጥል አንዱ ከደጅ ገባ፡፡ ገና ደርሶ የሚጠጣውን ከማዘዙ፣ ‹‹ወንድም ኳሱን በአየር ከምትጠልዝ መሬት ብታስይዘው አይሻልም?›› ከማለቱ፣ ‹‹እባክህ ተወኝ ኳስ በመሬት ብቻ አይደምቅም፡፡ ከዚህ ይልቅ በአገራችን ጉዳይ በያገባኛል ስሜት መነጋገር ይበጃል…›› ሲለው ፀጥታው ጨመረ፡፡ አንዱ በለሆሳስ፣ ‹‹ይኼ ተናግሮ አናጋሪ…›› ሲል ሌላው፣ ‹‹የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም ብሎ ነው እባክህ…›› ይባባላሉ፡፡ አደባባይ ላይ ደፈር ተብሎ የሚናገር ሲኖርም የእኛ ሰው ‹ጠርጥር ገንፎ ውስጥ አለ ስንጥር› የሚለውን ዕድሜ ጠገብ አባባል እየተቀባበለ፣ እንደ ልቡ ተናጋሪውን ማማት ሲጀምር የገዛ ልቡ ውስጥ ያለውን ፍርኃት የሚያሸንፍለት ያገኘ ይመስል ይቦርቃል፡፡ ፍርኃት እንዲህ የሚያስቦርቅ ከሆነ ቢቀርስ ያሰኛል፡፡ ፈሪ ሁሉ!

ምሁሩን የባሻዬን ልጅ፣ ‹‹ይኼ ሁሉ ቱማታ ምን ይሆን?›› በማለት ጥያቄ ሳቀርብለት፣ ‹‹በፀጥታ ውስጥ የሚሰማ ጥልቅ ጩኸት ነው…›› ሲለኝ የባሰውን አደናገረኝ፡፡ ያ ነገረኛ ሰው፣ ‹‹በቃ ከእከሌና ከእከሌ ማለት ካቃተህ ከቆሎና ከአሻሮ ማንን ትመርጣለህ?›› ሲል ግሮሰሪዋ በአንድ እግሯ ቆመች፣ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ሳቅ አጥለቀለቃት፡፡ ባንኮኒው ላይ የቆመው፣ ‹‹ካልጠፋ አማራጭ ከቆሎና ከአሻሮ እንዴት ምረጡ ትላለህ?›› ብሎ ሲጠይቀው፣ ‹‹ብትፈልግ ከቢራና ከአረቄ፣ ከንፍሮና ከገንፎ፣ ከጃኬትና ከካፖርት፣ ከባቡርና ከመኪና፣ ወዘተ መምረጥም መብትህ ነው…›› ብሎ ሲሰናበተን አማራጭ ፍለጋ የምንሄድበት ርቀት እየታየኝ በሐሳብ ነጎድኩ፡፡ ወደ ራሴ መለስ ብዬ ምርጫዬን ሳሰላስል ራሴን አጣብቂኝ ውስጥ ከተትኩት፡፡ እግር ወይስ ዓይን ብዬ ምሁሩን የባሻዬ ልጅ ምረጥ ስለው፣ ‹‹ከምንና ከምን?›› ብሎ በዓይኑ ጠቀሰኝ፡፡ ‹ሁሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት› አሉ? አንዳንዴ እኮ ብልጥ መሆንም ደግ ነው፡፡ ብልጠቱ ግን አጉል እንዳይሆን መጠንቀቅም ያስፈልጋል፡፡ አጉል ብልጠት ከግንድም ሆነ ከግንብ ጋር እያላተመ ስንቱን ሲደፋው ታዝበናል፡፡ ‹‹ትዝብት በማይዳሰስ ቅርስነት እዚህ አገር ለምን እንደማይመዘገብ ግራ ይገባኛል…›› የሚለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ እሱ ደግሞ የማያመጣው ጉድ የለም እኮ፡፡ እኔ ግን ከቅርስነቱ ይልቅ ውስጣችን መሽጎ ለኃፍረት ሲዳርገን ደስ ይለኛል፡፡ አጉል ብልጠት በዛ እኮ፡፡ መልካም ሰንበት!         

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት