Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየአፍ መፍቻ ቋንቋ ቀን ሲታሰብ

የአፍ መፍቻ ቋንቋ ቀን ሲታሰብ

ቀን:

ሰዎች በተለያዩ ቋንቋዎች የመማር ዕድል ቢያገኙ ይበልጥ ከማኅበረሰባቸው እንዲግባቡና የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር ያስችላል፡፡ ሆኖም ይህንን ዕድል ያገኙ የዓለም ሕዝቦች ከ40 በመቶ እንደማይበልጡ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ይገልጻል፡፡

በዓለም ሰባት ሺሕ ቋንቋዎች የሚነገሩ ቢሆንም፣ ከእነዚህ 50 በመቶ ያህሉ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡ ቋንቋዎቹን ለማዳን ጥረት ካልተደረገ በዚሁ ምዕተ ዓመት 90 በመቶ ያህሉ እንደሚሞቱም ድርጅቱ አሳስቧል፡፡

ቋንቋዎች፣ ባህልና ዕውቀትም ከአፍ መፍቻ ቋንቋ ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸውና ተያይዘው እንዳይጠፉ በባንግላዴሽ በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመጠቀም መብት አብዮት ምክንያት፣ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት እንዲያገኝ ሆኗል፡፡

- Advertisement -

እ.ኤ.አ. በ1950ዎቹ በባንግላዴሽ የተጀመረው በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመጠቀምና የተለያዩ ባህሎችን ጠብቆ የማቆየት አብዮት ከብዙ መስዋዕትነት በኋላ ሲሳካ፣ አገሪቱ  በዓለም በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመጠቀም መብት እንዲከበርና በየዓመቱ እንዲታወስ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ)፣ እ.ኤ.አ. በ1999 ባቀረበችው ሐሳብ መሠረት፣ ድርጀቱ ከ2000 ጀምሮ በየዓመቱ (ፌብሩዋሪ 21) ዓለም አቀፍ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ቀን ሆኖ እንዲከበር ወስኗል፡፡

የዘንድሮው ጭብጥ ‹‹በብዝኃ ቋንቋ መማር ትምህርትን ከትውልድ ትውልድ ለማሸጋገር ምሰሶ ነው›› (Multilingual Education is a Pillar of intergenerational Learning) በሚል በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ሁነቶች የታሰበ ሲሆን፣ በኢትዮጵያም በባንግላዴሽ ኤምባሲ አስተባባሪነት፣ በዩኔስኮ፣ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና (ዩኤንኢሲኤ) ትብብር በዩኤንኢሲኤ  የተከናወነው በየካቲት 2016 ዓ.ም. አጋማሽ ነበር፡፡

የኢሲኤ ዋና ጸሐፊን ወክለው ንግግር ያደረጉት ምክትል ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ፔድሮ እንዳሉት፣ ስለአፍ መፍቻ ቋንቋ ሲወራ እንደቀላል ይታያል ወይም ስሜታዊና ስሜት ቀስቃሽ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ሆኖም ከምልክትና ከተምሳሌትነት ወይም ከመግባቢያነቱም ባለፈ የባህል ነፀብራቅ ነው፡፡ የግለሰብና የማኅበረሰብ መገለጫ ነው፡፡ የተከፋፈለ ማኅበረሰብን የሚያግባባና የሚያሳትፍም ነው፡፡

‹‹20ኛው ክፍለ ዘመን የዕውቀት ነው፣ ድንበር የማይገድበው የዕውቀት ዘመን ነው፡፡ ማንም ቋንቋ ያለው ዕውቀት አለው፡፡ የአፍ መፍቻ ቋንቋም የዕውቀት መግቢያ ነው›› ሲሉም በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር እውቀትን ጠብቆ ለማቆየት ያለውን አበርክቶ ገልጸዋል፡፡

ቋንቋ ከማንነት፣ ከተግባቦት፣ ከትምህርት፣ ከምልክትና ከተለያዩ አንፃሮች ወሳኝ ቢሆንም፣ በሉዓላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ምክንያት የአፍ መፍቻ ቋንቋ እየተመናመነ የመሄድ ሥጋት ተጋርጦበታል፡፡ ቋንቋ ሲሞት ደግሞ የሰው ልጆች ባህላዊ ሀብት አብሮ ይሞታል ብለዋል፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች የመጥፋት አደጋ ቢያንዣብብባቸውም፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቋንቋዎች ብቻ በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ገብተው ማኅበረሰቡ ይጠቀምባቸዋል፡፡ የዲጂታል ዓለሙም የሚጠቀመው ከመቶ ያነሱ ቋንቋዎች መሆኑ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች እንዲመናመኑ ምክንያት ሆኗል፡፡

እንደ ሚስተር ፔድሮ፣ በየሁለት ሳምንታቱ አንድ ቋንቋ ይጠፋል፡፡ ቋንቋው የሚጠፋው ብቻውን ሳይሆን የተናጋሪውን ባህልና አገር በቀሉን ዕውቀት ጭምር ይዞ  ነው፡፡

ለቋንቋዎች እየጠፉ መሄድ በርካታና የተለያዩ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን፣ ከመስፋፋት፣ ከታጣቂ ቡድኖች፣ ከሰው ልጆች አሠፋፈር፣ ኢኮኖሚና ባህል ይጠቀሳሉ፡፡ ቅኝ ግዛት ለአፍ መፍቻ ቋንቋዎች መጥፋት የራሱን ተፅዕኖ ሲያሳድር፣ አሁን ዓለም የደረሰችበት ሉዓላዊነት (ግሎባላይዜሽን) 90 በመቶ የዓለም ሕዝብ 20 በመቶ የዓለም ቋንቋን እንዲናገር አድርጓል። በርካታ ቋንቋዎች  በአፍ ብቻ የሚነገሩ መሆኑም እየተመናመነ ለመሄዱ እንደምክንያት ይነሳል፡፡

ይህንን ለመቀልበስ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ከታች ከልጅነት ጀምሮ ማስተማር አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ለማመልከትም ዘንድሮ የተከበረው የአፍ መፍቻ ቋንቋ ቀን ከትምህርት ጋር ተያይዞ ነው፡፡

እንደ ዩኔስኮ፣ በተለያዩ ቋንቋዎች መማር ተሳታፊነትን ከማጠናከር ባለፈ ተፅዕኖ ፈጣሪ ያልሆኑና አገር በቀል ቋንቋዎች ተጠብቀው እንዲቆዩ ያስችላል፡፡ ትምህርትን በፍትሐዊነት ለማዳረስና በሕይወት ዘመን ሁሉ ትምህርትና ክህሎት እየቀሰሙ ለመሄድም ወሳኝ ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በአፍ መፍቻ ቋንቋን መሰረት አድርጎ የተለያዩ ቋንቋዎችን የመማር ዕድል እያደገ/ለውጥ እያመጣ እንደሆነ ዩኔስኮ ቢገልጽም፣  በአብዛኛዎቹ የዓለም አገሮች ተማሪዎች ትምህርት የሚከታተሉት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አይደለም፡፡ ከአፍ መፍቻ ቋንቋም አልፎ በብዝኃ ቋንቋ መማር፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታው የጎላ ቢሆንም፣ 40 በመቶ የዓለም ሕዝብ በሚናገረው፣ በሚችለውና በሚገባው ቋንቋ የመማር ዕድል የለውም፡፡

በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት የአፍ መፍቻ ቋንቋ እጠቃቀምን አስመልክቶ ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣የመጀመሪያ ቋንቋ እንደትምህርት ዓይነትና እንደማስተማሪያ ቋንቋነት ከቅድመ አንደኛ ትምህርት ጀምሮ በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ይሰጣል፡፡

ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የመጀመሪያ ቋንቋቸውን የመጠቀም፣ የመጠበቅ፣ የማልማት እንዲሁም ለቋንቋው የሚስማማ ሥርዓተ ጽሕፈት የመምረጥ ወይም የመቅረጽ መብት እንዳላቸው በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ 2012 ዓ.ም ተደንግጓል።

በዚሁ መሠረት በቅድመ አንደኛ ትምህርት 63 የመጀመሪያ ቋንቋዎች በማስተማሪያነት እያገለገሉ ይገኛሉ። በቅድመ አንደኛ ትምህርት ስድስት የመማር አውዶች ያሉ ሲሆን፣ አንዱ የመማር አውድ ቋንቋና ተግባቦት ነው። የመማር አውዶቹ በተናጠል እንደትምህርት ዓይነት የሚሰጡ ሳይሆኑ በተቀናጀ አቀራረብ እንዲማሯቸው የሚደረጉ ናቸው፡፡ 

በተጨማሪ ሃምሳ ሰባት የሚሆኑ የመጀመሪያ ቋንቋ ዓይነቶች ከአንደኛ ደረጃ እስከ  ሁለተኛ ደረጃ ድረስ እንደትምህርት ዓይነት እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሠላሳ የሚሆኑት የመጀመሪያ ቋንቋዎች  በሁለተኛ ደረጃ እንደትምህርት ዓይነት እየተሰጡ ነው፡፡

በመጀመሪያ ቋንቋ መማር ለተማሪዎች ሥነ ትምህርታዊና ሥነልቦናዊ ጥቅሞችን ስለሚያስገኝላቸው ለትምህርት ጥራትም አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው እሙን ነው፡፡

ተማሪዎች በመጀመሪያ ቋንቋ መማራቸው የትምህርት ይዘቶችን በበለጠ ፍጥነት ለመረዳት ቀላል ያደርግላቸዋል።  የተወሳሰቡ ፅንሰ-ሀሳቦችን በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት ያስችላቸዋል። ያልተለመዱ ቃላትን ወይም ሀረጎችን ከመተርጎም ጋር የተያያዘውን የግንዛቤ ጫና ይቀንስላቸዋል።

ይህም ተማሪዎች በጉዳዩ ላይ የበለጠ እንዲያተኩሩ ዕድል ይሰጣቸዋል። በመሆኑም በመጀመሪያ ቋንቋቸው መማራቸው የተሻለ የትምህርት ስኬት እንዲያስመዘግቡ ያግዛቸዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር ጥናቶችን ጠቅሶ እንደሚለው፣ በመጀመሪያ ቋንቋቸው የሚማሩ ተማሪዎች በሁለተኛ ወይም በውጭ ቋንቋ ከሚማሩት ጋር ሲነፃፀሩ የተሻለ የትምህርት ውጤት እንዳላቸው አላቸው። በትምህርት ቤት የመቆየት እና ከፍተኛ የብቃት ደረጃ የማግኘት ዕድላቸውም ሰፊ ነው።

የቋንቋ ገደብ ስለማይኖርባቸው ተማሪዎች በንቃት መሳተፍ ይችላሉ። በውጭ ወይም በሁለተኛ ቋንቋ ሊፈጥሩ የሚችሉትን ጭንቀትና ውጥረትን ያስወግዳሉ፤ ምቾት በማግኘት ለመማር ይነሳሳሉ። ተማሪዎች ከመምህራንና ከእኩዮቻቸው ጋር በቀላሉ ሀሳቦችን በመለዋወጥ በራስ መተማመንን ያዳብራሉ።

በመጀመሪያ ቋንቋ መማር ለትምህርት ጥራት አስተዋጽዖ እንዲኖረው በቋንቋው የሠለጠኑ መምህራን፣ በጥራት የተዘጋጁ በቂ የመማሪያ ማስተማሪያ መጻሕፍት፣ ተጨማሪ አጋዥ የንባብ መጻሕፍትና ሌሎችም አስፈላጊ ሁኔታዎች መሟላት ይገባቸዋል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር፣ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ትምህርት ቢሮዎች የመምህራን ትምህርትና ሥልጠና መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት የመጀመሪያ ቋንቋን መምህራንን እንዲሠለጥኑ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

የመማሪያ ማስተማሪያ መጻሕፍትን በማዘጋጀት፣ በማሳተምና በማሠራጨት ተማሪዎች በመጀመሪያ ቋንቋቸው እንዲማሩ እየተደረገ ነው፡፡ ለአብነት ያህል ትምህርት ሚኒስቴር ለ2ኛ ደረጃ የሚያገለግሉ ሃያ ሁለት የመጀመሪያ ቋንቋዎች የመማሪያ ማስተማሪያ መጻሕፍትን በማዘጋጀት፣ በማሳተምና በማሠራጨት ተማሪዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ሚኒስቴሩ ይገልጻል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ