Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልዓቢይ ጾም እና ረመዳን

ዓቢይ ጾም እና ረመዳን

ቀን:

ሁለቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች ክርስትና እና እስልምና የተቀደሱና የተባረኩ ወሮች የሚሏቸውን የጾም ወሮቻቸውን በተመሳሳይ ጊዜ በፀሓይ ከነገ መጋቢት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. (የጨረቃ መጋቢት 1 ቀን 2024/ ዓመተ 2024 የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የፀሓይና የጨረቃ ጥምር ቀመር ሲሆን ካውሮጳው ጋር አይገናኝም) እና በጨረቃ ከረመዳን 1 ቀን 1445 ዓመተ ሒጅራ ጀምሮ ይይዛሉ፡፡ የክርስቲያኖቹ (ኦርቶዶክስና ካቶሊክ) ጾም በጨረቃ ጭምር የሚታወቀው ‹‹ዓቢይ ጾም›› (ትልቁ ጾም) ሲባል፣ በጨረቃ ብቻ የሚቆጥረው የሙስሊሞቹ ጾም ‹‹ረመዳን›› ይባላል፡፡ የወሩ መጠሪያም ከጾሙ ስም የተገኘ ነው፡፡

ዓቢይ ጾም

ከትንሣኤ (ፋሲካ) በፊት ጾምን መጾም ለክርስትና አማኞች በጣም አስፈላጊ ከሆኑት መካከል ዋናው ነው፡፡ ታላቁ ጾም- ዓቢይ ጾም ለመንፈሳዊ ንጽህና የተሰጠ ጥልቅ መንፈሳዊ ጊዜ እንደሆነ ይታሰባል፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ፣ በኮፕቲክ አብያተ ክርስቲያን በአጠቃላይ 55 ቀናት ይጾማል፡፡ ይህም የዝግጅት ሳምንትን ሰባት ቀን (ከመጋቢት 2-8)፣ እግዚእ ኢየሱስ የጾመውን 40 ቀን (ከመጋቢት 9- ሚያዝያ 18) እና ሰሙነ ሕማማትን (ከሚያዝያ 19-26) ያካተተ ነው፡፡ የጾሙ ቀናት በፀሓይና በጨረቃ ጥምር ቀመር በሚገኘው በፋሲካ (ትንሣኤ) ላይ የተመሠረቱ በመሆናቸው በየዓመቱ ይለወጣሉ፡፡ ትንሣኤውም በዕለተ እሑድ ሚያዝያ 27 ቀን ይውላል፡፡

- Advertisement -

እስከ ዛሬ ድረስ የሚኖረውን የሚንቀሳቀሱትን ፋሲካን የመሰሉ አጽዋማትና በዓላት የሚገኙበትን መንገድ የመሠረተው አሥራ ሁለተኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ዲሜጥሮስ ነው።  ስለ ዓቢይ ጾም በቅዱስ ዲድስቅልያ እንደተመዘገበው ምዕመናን ‹‹መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመባቸው አርባ ቀናት ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ ይጾሙ ዘንድ ከሥጋና ሥጋዊ ከሆነው ከማንኛውም ነገር መከልከል አለባቸው፤›› ይላል።  እንዲሁም ‹‹ከቅዱሳን አርባ ቀናት አስቀድሞ ያለው ሳምንት (የመዘጋጃ ሳምንት) ሥርዓት ሊከበርባቸው ከሚገባቸው ጾመ ቤተክርስቲያን አንዱ ተብሎ የሚመደብ ነው፤›› ብሏል።  ሰሙነ ሕማማትን  (ከቅዱሳን አርባ ቀናት ቀጥሎ ባለው ሳምንት) በተመለከተም ዲድስቅልያ ‹‹ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ በዳቦ፣ በጨውና በውኃ ብቻ መጾም አለበት፤›› ይላል።

 ታላቁን ዓርብ (ዓርብ ስቅለት) እና ብሩህ ቅዳሜን (ቀዳም ሥዑር) በተመለከተም፣ ‹‹እሑድ ዶሮ እስኪጮህ ድረስ በፍጹም መከልከል አለባቸው።  ነገር ግን አንድ ሰው ሁለቱንም ቀናት አንድ ላይ መጾም ካልቻለ ቅዳሜን ብቻ መጾም ተቀባይነት አለው፤›› በማለት ተጠቅሷል።

ረመዳን

በሙስሊሞች የሚተገበረው የረመዳን ወር ጾም ከንጋት እስከ ማታ ድረስ የሚዘልቅ ነው፡፡ ይህ የተቀደሰው የረመዳን ወር በአዲስ ጨረቃ ዕይታ መሠረት ሰኞ፣ መጋቢት 2 ወይም ማክሰኞ መጋቢት 3 ይጀምራል።

በሙስሊሞች ትውፊት መሠረት የረመዳን ወር የቅዱስ ቁርዓን የመጀመሪያዎቹ ጥቅሶች ለነቢዩ መሐመድ ከ 1,400 ዓመታት በፊት የወረዱበት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ጾሙ በቀን ሰዓት ከመብላት፣ ከመጠጣት፣ ከማጨስና ከጾታዊ ግንኙነት መታቀብን ያካትታል።

ዒድ አልፈጥር የሚውለው ሸዋል 1 ቀን ሚያዝያ 1 ቀን ወይም 2 ላይ ይሆናል፡፡

ረመዳን በየዓመቱ በተለያዩ ቀናት ለምን ይጀምራል?

አልጀዚራ እንደዘገበው፣ ረመዳን የሚጀምረው በየዓመቱ ከ10 እስከ 12 ቀናት ቀደም ብሎ ነው። ምክንያቱም ኢስላማዊው የዘመን አቆጣጠር በጨረቃ የሒጅራ አቆጣጠር ስለተመሠረተ ነው፡፡ ወሮቹ 29 እና ​​30 ቀናት የሚረዝሙ ናቸው።

የጨረቃ ዓመት ከፀሓይ ዓመት በ11 ቀናት አጭር ስለሆነ ረመዳን እ.ኤ.አ. በ2030 በአንድ ዓመት ሁለት ጊዜ ይከበራል – መጀመሪያ ከጥር (ጃንዋሪ) 5 ጀምሮ ከዚያም በታኅሣሥ (ዲሴምበር) 26 ይጀምራል። የሚቀጥለው ረመዳን ከመጋቢት (ማርች) 12 በኋላ የሚጀምርበት ጊዜ ከ33 ዓመታት በኋላ ይሆናል – እ.ኤ.አ. በ2057።

ለሁለቱም ሃይማኖቶች ሠናይ የጾም ወራት!

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...