Monday, May 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

‹‹ለምጣዱ ሲባል…››

በቤተልሔም መኰንን

እንደምናውቀው ምንም ነገር ከመፈጠሩ በፊት የሚፈጠረው በሐሳብ ነው፡፡ መጀመሪያ ሐሳብ ወደ ሰዎች አዕምሮ ሳይመጣ በአካል የሚመጣ ምንም ነገር የለም፡፡ ለዚህም ነው ንድፍና ዲዛይን የሚደረገው፡፡ መጀመሪያ በሐሳብ ውስጥ ያለውን ወረቀት ላይ ይሰፍራል፡፡ ከዚያም በዚያ መሠረት ይሠራል፣ ለዚህ ነው ሐሳብ የነገሮች ሁሉ መነሻ የሚሆነው፡፡ በምድራችን ላይ የምናያቸው በጎም ይሁን መጥፎ ነገሮች የሐሳቦች ውጤቶች ናቸው፡፡ ብራይት ብራዘርስ የሚባሉ ሁለት ወንድማማቾች የሰው ልጅ እንዴት መብረር እንደሚችል ስላሰቡና በሐሳባቸው ጸንተው ወደ ተግባር መቀየር በመቻላቸው ዛሬ ዓለም ወደ አንድ መንደርነት ለመቀየር ተችሏል፡፡ በአሁን ሰዓት ጠዋት ኢትዮጵያ ቁርስህን በልተህ ማታ አውሮፓ እራትህን መብላት የምትችልበት ሁኔታ የተፈጠረው በአሳቢዎች ብርቱ ጥረትና ትጋት ነው፡፡

የሁለት ወንድማማቾች ሐሳብ፣ ሁለቱ ብቻ ያደረጉት ጥረት ዓለምን በዚህ ደረጃ መቀየር ከቻለ፣ የአጠቃላይ የዓለም ሕዝብ ሐሳቦች ምድርን ምን ሊያደርጋት ይችል እንደነበር መረዳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን አብዛኛዎቻችን በሌሎች አሳቢዎች ትከሻ ላይ ሐሳባችንን ጥለን ጣጣዋ ያለቀላት ዓለም እየጠበቅን፣ ይልቁንም በጎ አስተዋጽኦ ከማበርከት ይልቅ ሳናውቀው በአሉታዊ አስተሳሰቦች ውስጥ ተውጠን ዓለምን ሲዖል ከሚያደርጓት አሳቢዎች ጎራ ተሠልፈን እንገኛለን፡፡ ምክንያቱም ምድር ላይ እስካለን ድረስና እስትንፋሳችን እስከተሰጠን ድረስ በጎም ይሁን መጥፎ ሐሳቦች በአዕምሮአችን መመላለሳቸው የማይቀር ስለሆን በጎ ያሰብን እየመሰለን፣ ለምን እገሌ እንዲህ አደረገ፣ ለምን ያኛው እንዲህ ሆነ፣ ቅጣት ይገባዋል፣ ትክክል አይደለም፣ ይወገድ፣ ይገደል፣ የመሳሰሉት ከደሙ ንጹህ ነኝ ዓይነት አስተሳሰቦችን እያሰብንና በራሳችን ፍርድ እየሰጠን የበለጠ አሉታዊ ሐሳቦችን እያበረታታን በጥፋት ላይ ጥፋት እየደረብን እንገኛለን፡፡

ሆኖም ግን ዓለም ላይ ያለን ሰዎች የራሳችንን የማሰብ አቅም ተጠቅመን እኔ ምን ላስብ፣ እኔ በበኩሌ ምን ላድርግ፣ የእኔ ድርሻ ምንድነው፣ ጣቴን ከመቀሰሬ በፊት እኔ ምን እያደረግኩ ነው ብንልና ምን ማድረግ እችላለሁ ብንል፣ ጠብታ ውኃ አለት ትሸረሽራለች እንደሚባለው፣ ቢያንስ እኛ ራሳችንን ከምንከሳቸው ሰዎች ጎራ አውጥተን ከአሳቢዎች ተርታ ብናሰልፍ ለዓለም ባንደርስ፣ ለአገራችን፣ ለአገራችን ባንደርስ ለአካባቢያችን፣ ለአካባቢያችን ባንደርስ ለቤተሰባችን መድረስ እንችላለን፡፡

የሐሳብን ኃይል ብዙዎቻችን ሳንረዳው የምንቀር አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ወደራሳችን ስናመጣው የራሳችን ሐሳብ ሌሎች ላይ በድርጊት እስካልተከሰተ ድረስ፣ ውጤት ያለው አይመስለንም፡፡ በቃላት አውጥተን ብንናገረውም እንኳን በወቅቱ በድርጊቱ እስካልፈጸምነው ድረስ ምንም ያደረግን አይመስለንም፡፡ ግን ብታምኑም ባታምኑም በሐሳብ ደረጃ አስበን በቃላት የምንናገረው ነገር ሲደጋገም ድርጊት ሆኖ መከሰቱ አይቀርም፤ ነገሩ ቀናም ይሁን አሉታዊ ነገር በሕይወታችን ላይ መሆኑ አይቀርም፤ ምክንያቱም አዕምሮአችን ለእኛ የሚሆነውን ነገር የሚሠራው ሐሳባችንን ተከትሎ ነው፡፡ በቃ አዕምሮአችን የሚገባው የእኛ ሐሳብ ብቻ ነው፣ ቀኑን ሙሉ በውስጣችን የምናውጠነጥነውና በቃላትም እያወጣን የምንናገረው ነገር ለአዕምሮችን መምሪያው ነው፡፡ ስለዚህ ሁሌም በዚያ ዙሪያ ለእኛ ሲሠራ ይውላል ማለት ነው፣ ለዚህ ነው ብዙ ጊዜ ለሌሎች የምንመኘው አሉታዊም ይሁን በጎ ነገር ለእኛ ለራሳችን የሚሆነው፡፡ የሐሳቡ ባለቤት እኛ እስከሆንን ድረስ ለማንም ብናስብ፣ በማንም ላይ ብናስብ አዕምሯችን ለራሳችን አዘጋጅቶ ያቀርብልናል፡፡ በዚህ ነገር በአንድ ወቅት ያጋጠመኝ ነገር ሁሌም አልረሳውም፡፡ ከባለቤቴ ጋር መኪናው ውስጥ ሬዲዮ እየሰማን ወደ ሥራ እየሄድን፣ በሬድዮው ስለአፍንጫ ሕመም ያወራል፡፡ እኔም ገርሞኝ አፍንጫ ደሞ ይታመማል እንዴ እያልኩ እያሰብኩና እየተመራመርኩ ነበር የምሄደው፡፡ ከዚህ በፊት የአፍንጫ ሕመም ሲባል አላውቅምና ስለነገሩ በጣም ተመስጬ ነበር የምሰማውና የማውጠነጥነው፡፡ ከዚያ ለካ ለአዕምሮዬ በሐሳቤ ትዕዛዝ እየሰጠሁት ነበር፡፡ በማግሥቱ የአፍንጫ ሕመም እንዴት እንደሆነ በተግባር አሳየኝ፣ እንዴት እንዳረገኝ መቼም አልረሳውም፡፡ ከዚያ ወዲህም ከዚያ በፊትም አፍንጫዬን እንደዚያ ታምሜ አላውቅም፡፡ አምላክ አሁንም አይመልስብኝ፡፡

በመጽሐፍ ላይ የሁለት ጓደኛማቾች ታሪክ አለ፡፡ አንደኛው ፉክክሩ ከራሱ ጋር ስለሆነ ሁሌም በራሱ ዓለም ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ ሲጸልይም ለራሱ እንዲሆንለት የሚፈልገውን ነገር ይጸልያል እናም ይሳካለታል፡፡ ሌላኛው ግን ፉክክሩ ከጓደኛው ጋር ነውና ሁሌም ጓደኛው የሆነ ነገር ሲያገኝ ይበሳጫልና በልጦ መገኘት ይፈልጋል፡፡ እናም ሲጸልይ ከጓኛው የሚበልጥበትን ነገር እያሰበ ነበርና ግን ሁሌም የጸለየው ይደርስለታል፡፡ ችግሩ ግን ለጓደኛው ሁሌም እሱ ከተሰጠው የበለጠ እንደተሰጠው ያያልና በጣም ይበሳጫል፡፡ እሱ አንድ ሲጠይቅና ሲሰጠው ለጓደኛው ሁለት ሆኖ ያየዋል፡፡ በመጨረሻም በቃ እኔ በጸለይኩት ለእሱ እጥፍ ሆኖ እየተሰጠው ስለሆነ ልበልጠው አልቻልኩም ብሎ ያስብና በቃ እኔ አንድ ዓይኔ ይጥፋ ብዬ ብጸልይ የእሱ ሁለት ዓይን ይጠፋል፡፡ በዚያም እኔም በአንድ ዓይን እበልጠዋለሁ በማለት ያስብና ለአምላኩ አንድ ዓይኑ እንዲጠፋ ጸለየ እናም እንደጠየቀው አንድ ዓይኑ ጠፋ፡፡ ነገር ግን የጓደኛው ግን ሁለቱም ዓይኖች እንደነበሩት ጤነኞች ሆነው ቀጠሉ፡፡

ከሁለቱ ጓደኞች ታሪክ እንደምንረዳው አንደኛው ጸሎቱም ትኩረቱም ራሱ ላይ ብቻ ነውና ሁልጊዜም መልካም መልካሙን ይመኛል፣ የሚያድግበትን የሚሻሻልበትንና ከራሱ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍበትን መንገድ ብቻ ነው የሚያስበው፡፡ ስለዚህ ላለው ይጨመርለታል እንደተባለው በከፍታው ላይ ከፍታ ይጨመርለታል፡፡ ያኛው ግን ከራሱ ጋር ከተሰጠው ከተጨመረለት፣ ጸሎቱ በመሰማቱ ከማመስገንና ከመደሰት ይልቅ ዓይኑም ሐሳቡም የጓደኛው ላይ ስለሆነ እሱ ጋ ያለውን መልካም ነገር ማየት አይችልም፡፡ ሐሳቡ ሁሌም እሱ ከጓደኛው እንደሚያንስ ስለሆነ በተግባርም ያገኘው ነገር ከጓደኛው ማነስ ነው፡፡

ስለዚህ በውስጣችን ሁሌ የምናመላልሰውን ሐሳብ ማስተዋል አለብን፡፡ እኛ ጠላት አለን ብለን ሁለም ስለጠላታችን የምናስብ ከሆነ በገዛ ፈቃዳችን አዕምሮአችንን የጠላታችን ግብረአበር አድርገን በደንብ አድርጎ እንዲጎዳን እያሠራነው መሆኑን መረዳት አለብን፡፡ ጠላት አዎ ሊኖረን ይችላል፣ ዲያቢሎስ እስካለ ሁሌም በሰዎች አዕምሮ እየተጠቀመ ለመጉዳት ሊሠራ ይችላል፡፡ ግን የሚገርመው እሱ የራሳችንን አዕምሮ ተጠቅሞ ራሳችንን እየጎዳን እንዳለ ስንቶቻችን እናውቃለን፡፡ ወደድንም ጠላንም መረዳት ያለብን፣ መርጠን ፈቅደን መልካሙን ሐሳብ አስበን፣ አዕምሮዎችንን በበጎ አስተሳሰቦች ዘወትር እስካልቃኘነው ድረስ በምንሰማውም ይሁን፣ በምናየው የራሳችንን ጠላት አስረን እየቀለብን ውድቀታችን ላይ በርትተን እየሠራን መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ ምክንያቱም ሐሳብም አይቆምም፣ አዕምሮም 24 ሰዓት ሥራውን አያቆምም፡፡ ስለዚህ የሚያየውንም የሚሰማውንም በተባራሪ የሚመጣውንም መረጃ ያውጠነጥናል፣ ለዚህ ነው ሁሌም የምናይና የምንሰማውን አዘውትረን የምንከታተለውን ነገር መምረጥ ያለብን፡፡ እንደ አንደኛው ሐሳቡንና ትኩረቱን ራሱ ላይ እንዳደረገው ጓደኛ ሁላችንም ብንሆን ጠላት የቱንም ያህል ሊጎዳን ቢያሴር፣ ሰይፍ ቢመዝ ራሱ ይሰየፍበታል እንጂ እኛን ጫፋችን ላይ አይደርስም፡፡ ምክንያቱም እየዘራን ያለነው የሐሳብ ዘር መልካም ስለሆነ የዘራችሁትን ታጭዳላችሁ እንደተባለው መልካም ማጨዳችን የማይቀር ነው፡፡ እኛ ጋ ያለው አምላክ ደግሞ ከጠላታችን ጉልበት እጅግ የላቀ ነው፡፡

ስለዚህ ወገኖቼ በዙሪያችን እንዲለወጥ የምንፈልገው ነገር ካለ እኛ ሐሳባችንን እንለውጥ፡፡ ትኩረታችንን እኛና የእኛ ጉዳይ ላይ እናርግ፡፡ በነገራችን ላይ የራሳችንን ጉዳይ በደንብ ከጨረስን እኮ ለሚቀጥለው ወደ ሌሎችም ጉዳይ ገብተን ለውጥ የማምጣት አቅም ማግኘት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ የኑሮው መወደድ የሚያሳስበን ከሆነ ሁለት አማራጭ አለን፡፡ እየተራብንና ነጋዴና ገበሬ፣ መንግሥትንም እየረገምን በሐሳባችን ምሬትን እያውጠነጠን ራሳችን ላይ የባሰ መከራ ማምጣት፣ ወይ ደግሞ እኔ ይኼን ኑሮ ለማሸነፍ ምን ላድርግ ማለት ትኩረታችንን ሙሉ ምን ማድረግ እንደምንችል ማሰብ ላይ ስናደርግ ተዓምረኛው አዕምሯችን መፍትሔ ይዞ ብቅ ይላል፡፡ ምክንያቱም እንደዚያ ሆኖ ነው የተሠራው፡፡ እኛ ከልባችን ሆነን በተደጋጋሚ የምናስባቸውን ሐሳቦች ወደ ተግባር መቀየር ነው ሥራው፣ ከዚያም የራሳችንን አልፈን የሌሎችን ችግር መቅረፍ እንችላለን፡፡ በተጨማሪ ችግር የሆነውን የኑሮ ውድነት በአገሪቷ ላይ ችግር እንዳይሆን መሥራት እንችላለን ማለት ነው፡፡

ስለአገራችንም ሁኔታ እያንዳንዳችን ቁጭ ብለን የምናስበው ነገር ውጤት መሆኑን መረዳት አለብን፡፡ አብዛኞቻችን አሁን ላይ የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና የምትፈርስበትን ቀን እየጠበቅን ነው የምንመስለው፡፡ በሐሳባችን ውስጥ እያመላለስን ያለነው ያለችበትን ውድቀትና ጨለማ ነው፡፡ አስቡት ሐሳብ የዚህን ያህል ኃይል ካለው፣ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አገራችን 20 ሚሊዮኑ እንኳን ስለመፍረሷ ዘወትር የሚያስብና የሚያወራ ከሆነ፣ አስባችሁታል ምን ያህል አንድ ጥይት ሳንተኩስ የገዛ አገራችንን እያፈረስን እንደሆነ፡፡ ግን እስቲ አሁንም የሰይጣን ጆሮ ይደፈን ግን ቆም ብለን አገራችን ብትፈርስስ ብለን እናስብ በኢትዮጵያ አገራችን በየክልላችን በየብሔሮቻችን የምናሳልፋቸው በዓሎቻችን ቡሄ እየዞርን ጎረቤቶቻችን ጋ ስንጨፍር፣ አዲስ ዓመት አበባዮሽ ስንጨፍር፣ ሥዕል ስናዞር፣ መስቀል ስንደምር፣ ገና፣ ጥምቀትን በአደባባይ ታቦት ስናስወጣ፣ ፋሲካ፣ ጾሞቻችን ስናስቀድስ፣ የቅዳሴ ሥርዓታችን፣ ፀበል ስንሄድ፣ ሙስሊሙም ዒድን፣ አረፋን ሲያከብር ያለው ገጽታ የት ይደርሳል? አገራችን ላይ ያለው ባህል፣ ወግና ሥርዓት አስተዳደጋችን የልጅነት ጨዋታዎቻችን፣ በየባህላችን የሽምግልና ሥርዓታችን፣ የሠርግና የመልስ ሥርዓታችን፣ የሐዘን ሰዓት አብሮነታችን ለቅሶ ሲገጥመን ቀብር፣ ሠልስት ሐዘናችንን የምንጽናናበት ሕዝባችን አገራችን ዕድራችን ዕቁባችን እያንዳንዱ ማኅበራዊ እሴቶቻችን ይህቺን የምታምረዋን ክፉዋን መስማት የማንፈልገው፣ ነኳት ሲሉን አራስ ነብር የምንሆንላትን አገራችንን አንድ ቀን ብናጣትስ አስበነው እናውቃለን፡፡ ስለአገራችን ምን እያሰብን ነው? ወደድንም ጠላንም አገራችንን ለማፍረስ ሁላችንም ታትረን እየሠራን ነው፡፡ 

በአንድ ወቅት አንድ አገር ላይ አንድ ወረርሽኝ ተነሳ ልክ እንደ ኮረና፡፡ በየቀኑ ይኼን ያህል ሰው ተያዘ፣ ይኼን ያህል ሰው ሞተ እየተባለ በየሚዲያው ቀን በቀን ይዘገባል፡፡ ነገር ግን ወረርሽኙ የበለጠ እየተስፋፋና እየተዛመተ ቁጥሩ ከዕለት ዕለት የበለጠ እየጨመረ መቆጣጠር የማይቻልበት ደረጃ ደረሰ፡፡ በኋላ የአገሪቷ መሪ የሚዲያ ባለሙያዎችን በአጠቃላይ ሰብሰቦ ከዚህ በኋላ ስለዚህ ወረርሽኝ ምንም ዓይነት ዘገባ እንዳያወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጠ፡፡ እናም ስለወረርሽኙ መዘገብ ሲቆም በሚገርም ሁኔታ ወረርሽኙን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ መቆጣጠር ተቻለ፡፡  ስለዚህም አገራችን ላይ እየተፈጠረ ላለው ቀውስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሁላችንም አስተዋጽኦ እያበረከትን መሆኑን መረዳት አለብን፡፡ ስለዚህም ይቺን ስስታችን የሆነች አገራችንን ሳናጣት ቆም ብለን ማስተዋል ያለብን ጊዜ አሁን ነው፡፡ በአቅማችን ምንም ልናደርግላት ባንችል እንኳን ሐሳባችንን ማስተካከልና በጎዋን በማሰብ ብቻ ከጥፋትና ከመፍረስ ልንታደጋት እንችላለን፡፡

አዎ የምናየው የምንሰማው ነገር ላያስደስተን ይችላል፡፡ ወይ ደግሞ ምሬት ውስጥ ሊያስገባን ይችላል፡፡ ነገር ግን በቃ እኛ አለን፣ አንዴ አፍሪካ ላይ ተፈጥረናልና እንደዚህ ዓይነት ወቅት ላይ ተገኝተናል፡፡ ስለዚህ ከዚህ ሁኔታ የምንወጣበትን ራሳችንና አገራችንን የምናድንበትን ሁኔታ ማሰብ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ፈጣሪ አለ እሱን መማፀንን ነው ያለን አማራጭ፡፡ ይኼን አደረግን ማለት የበኩላችንን ለአገራችን አደረግን ማለት ነው፡፡

ደግሞ ሁሉም ያልፋል፣ መረዳት ያለብን የኅዳር ሚካኤል መታጠን የጀመረበትን ወቅት በታሪክ ብናይ፣ አሁን ካለንበት ጊዜ በከፋ ደረጃ በአዲስ አበባ ውስጥ እንኳን ከ30,000 በላይ ሰዎች በወረርሽኙ ምክንያት ማለቃቸውን፣ መቀበሪያ ሁሉ ጠፍቶ እንደነበር በታሪክ ይወሳል፡፡ ከዚያም በላይ አገራችን በጣሊያን ተወራ ብዙ ሕዝብ እንዳለቀ በታሪክ የምናውቀው ነው፡፡ አሁን በቅርብ ዓመታት እንኳን ኮረና ስንቶችን እንዳሳጣንና ምን ዓይነት አስጨናቂ ጊዜ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ እነዚያ ሁሉ ጊዜያት አልፈው አገራችን ቀጥላለች፡፡ ስለዚህ አሁን የሚያስጨንቁንም ጊዜያት ያልፋሉ፡፡

በአንፃሩም ደግሞ የእኛ ዓይነት ችግር የገጠማቸው አገሮች ችግሩን ያላለፉና ፈርሰው የቀሩ፣ መንግሥት አልባ የሆኑና እንደ ሊቢያ የወንበዴዎችና የአሸባሪዎች መናኸሪያ የሆኑ አገሮች፣ እንደነ ሶርያ ሕዝቦቻቸው በዓለም ላይ የተበተኑ እንዳሉም መዘገንጋት የለብንም፡፡ ሶሪያና የመን ድሮ ከእኛ አገር እንኳን የቤት ሠራተኝነት ለመቀጠር ዜጎቻችን ይሄዱባቸው የነበሩ ሀብታም አገሮች ነበሩ፡፡ ዛሬ ወደ እኛ ጋ መጥተው ሲለምኑ እያየን ነው፡፡ ከእነዚህ አገሮች መማር፣ የምንወዳትን አገራችንን እንዳናጣትና ነገ የእኛም ዕጣ እንዳይሆን የምንወስነው እኛው ነን፡፡ አባቶቻችን ስንት የተዋደቁላት፣ ደምና አጥንት የተከፈለላት አገር፣ በእኛ ዘመን በእኛ ትውልድ እንዳናፈርሳት የምናስበውንና የምንናገረውን ነገር መጠንቀቅ አለብን፡፡ ስለዚህ ሁሌም ስለአገራችን ቀናና በጎውን እናስብ፡፡ ትኩረታችንን እኛ ማድረግ የምችለው በጎ አስተዋጽኦ ላይ እናድርግ፡፡ ከዚያ የሚቀረውን ለፈጣሪ ስንሰጥ ሁሉም ነገር መልካም ይሆናል፡፡ ፈጣሪ የሚገባውን እሱ ያደርጋል፣ መፍረዱን መክሰሱን ለእሱ እንስጠው፣ ፍርድና ፍትሕ የሚያመጣው እሱ ነው፡፡ አንዳንዴ እኛ ራሳችን ስንማረር ስንፈርድ እኛ ከፈጣሪ በላይ ትክክል ነን ብለን እያሰብን መሆኑን አስተውለን እናውቃለን? በእሱ ሥራ እየገባን እኮ ነው የገዛ ሕይወታችንን ያመረርነው፡፡ ስለዚህ አሁንም ስለአገራችን ብለን ተረጋግተን ሐሳባችን ላይ ብቻ እንሥራ፣ የእኛ ድርሻ እሱ ብቻ ነው፡፡ ሐሳባችን ማንን ያስደስታል ብለን እናስብ እግዚአብሔርን ወይስ ሰይጣንን!!

በሌላ በኩል ደግሞ ከፊታችን ስለሚጠብቀን ጨለማ ሳይሆን ብርሃን እናስብ፡፡ እንዲያውም ሊነጋ ሲል ይጨልማል አይደል የሚባለው፡፡ አሁን በጣም የጨለመ የሚመስለው ሊነጋ ሲልስ ቢሆንስ? መከራችንን እንደ ዕድል ከተጠቀምንበት ለታላቅነታችን መጀመሪያ ሊሆን ይሆናል እንዲህ እየተፈተን ያለነው፡፡ ብዙ ታላላቅ አገሮች ታላላቅ የሆኑት ችግሮቻቸውን ጥርስ ስለነከሱባቸውና ታግለው ስለጣሏቸው ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉንም ነገር ሰከን ብለን እንድናገናዝብና ወደ ቀልባችን ተመልሰን መፍትሔዎች ላይ እንድናተኩር ሊሆን ይገባል፡፡ ራሳችንን በበጎ ሐሳቦች፣ በተስፋና በእምነት እንሙላውና የበኩላችንን እንጣር፡፡

አሁን እኛ ባለንበት ዘመን የሠለጠኑ የምንላቸው አገሮች ያላቸውን ሀብቶች በሙሉ ጨርሰዋልና እንደ እኛ አገር ዓይነት ገና ያልተነካ ሀብት የያዙ አገሮች ላይ ዓይናቸውን ጥለው እየጎመዡ መሆናቸው ይነገራል፡፡ ለዚህም ነው እኛ ጋ ኮሽ ባለ ቁጥር ጫጫታው የሚበዛው፡፡ እስካሁንም አንፈርስ ስላልናቸው ነው በሆሆይታ ሊገነጣጥሉን የሚያሰፈስፉት፡፡ ስለዚህ ትኩረታችንን በረከታችን ላይ እናድርገው፣ ሊቀራመቱን ያሰፈሰፉትን ሲያምራችሁ ይቅር ልንላቸው ይገባል፡፡ የትም ወጥተን ሳንናገር፣ ጠጠር ሳናነሳ ሐሳባችንን በማስተካከል፣ የአገራችንን በጎ በማሰብና ጠላቶቻችንም አንሰማም በማለት አገራችንን ልናድናት በረከቷንም ልንቋደስ እንችላለን፡፡ ስለዚህ ‹‹ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ›› እንደሚባለው ለአገራችን ስንል ገበናችንን ሸፍነን ክፉ ቀን እስኪያልፍ ጠላትን አናስደስት፣ ስለአገራችን ቀና እናስብ፣ ቀና እናውራ ቀና እንመኝ፣ ለልጆቻችን ይችን የምታምር አገራችንን እናቆይላቸው እላለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles