Friday, May 24, 2024

አወዛጋቢው ትጥቅ ማስፈታትና መልሶ የማቋቋም ጉዳይ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛዋ ማይክ ሐመርን ወደ አዲስ አበባ ልካለች፡፡ ከሐሙስ የካቲት 28 ቀን 2016 ዓ.ም. እስከ መጪው ረቡዕ መጋቢት 4 ቀን 2016 ዓ.ም. በሚካሄደው የፕሪቶሪያ ስምምነት አተገባበር መገምገሚያ ስብሰባ ላይ፣ ስምምነቱን ፈራሚዎች ብቻ ሳይሆኑ አደራዳሪዎቹም ይታደሙበታል፡፡ በዚህ ስብሰባ በሕወሓትና በፌዴራል መንግሥት መካከል የተፈረመው የፕራቶሪያ ስምምነት የትግበራ ሒደት ምን እንደሚመስል አንድ በአንድ እንደሚገመገም ተነግሯል፡፡

አወዛጋቢው ትጥቅ ማስፈታትና መልሶ የማቋቋም ጉዳይ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

በዚህ ግምገማ ደግሞ የስምምነቱ አንድ አንቀጽ የያዘው የታጠቁ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታትና መልሶ የማቋቋም ጉዳይ ይገመገማል ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡ የታጠቁ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታትና መልሶ የማቋቋም ሥራ ለረጅም ጊዜ መንግሥትና ሕወሓትን ሲያወዛግብ የቆየና ብዙ መጓተት የገጠመው መሆኑ ተደጋግሞ ይወሳል፡፡ መንግሥት የሕወሓት ኃይሎችን ሆን ብሎ ትጥቅ ሳያስፈታ እንደቆየ ሲወቀስ ቆይቷል፡፡ በተቃራኒው ብዙ ሰበቦችን እየደረደረ ጦሩን ትጥቅ ሳያስፈታ ደብቆ ያቆየው ሕወሓት ነው በሚል ወቀሳ ይቀርባል፡፡ ሁለቱ ወገኖች ከሚሰጧቸውና እርስ በርስ የመወቃቀስ ይዘት ካላቸው አመክንዮዎች በዘለለ ደግሞ፣ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታቱ ሥራ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ ተፈጻሚ እንዳልሆነ በርካቶች ይናገራሉ፡፡

ይህን ምክንያት የሚያቀርቡ ወገኖች ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት ሥራው በትግራይ ሸማቂዎች ብቻ የተገደበ ሳይሆን በጋምቤላም፣ በቤኒሻንጉልም፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎችም የሚሠራ ሰፊ አገር አቀፍ ዕቅድ መሆኑን ያነሳሉ፡፡ ይህን ዜጎችን ከመሣሪያ በመነጠል ሥልጠና ሰጥቶ ወደ መደበኛ ሕይወት እንዲገቡ የማድረግ ጥረት የሚጠይቅ ሥራን ደግሞ፣ መንግሥት ብቻውን መወጣት እንደማይችል ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ለዚህ የፕሪቶሪያ ስምምነት አካል ለሆነ ጉዳይ የውጭ የልማት አጋሮች፣ በተለይም ድርድሩ ላይ የነበሩ አደራዳሪዎች እንደሚደግፉት ብዙ ተስፋ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፣ ድጋፉ በተባለው ልክ አለመገኘቱ ለትግበራው እንቅፋት መሆኑ ይነገራል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም (አምባሳደር) ከሰሞኑ ስብሰባ ቀደም ብሎ፣ መንግሥት ለስምምነቱ መተግበር ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹በተናጠል የሚደረግ የሰላም ስምምነት ትግበራ የለም፤›› ሲሉ የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ ተመሳሳይ የትግበራ ተነሳሽነት በተቃራኒው ካሉ ወገኖች እንደሚጠበቅ ነው የተናገሩት፡፡

ወደ 15 አንቀጾችን ይዞ የቀረበው ባለዘጠኝ ገጹ የፕሪቶሪያ ስምምነት በአንቀጽ ስድስት ላይ ነበር ትጥቅ የማስፈታትና መልሶ ማቋቋም ጉዳይን ያስቀመጠው፡፡ ስምምነቱ በተፈረመ በአምስት ቀናት ልዩነት የፈራሚዎቹ ወገኖች ወታደራዊ መሪዎቻቸው ተገናኝተው በትጥቅ ማስፈታቱና መልሶ ማቋቋሙ ቅደም ተከተል ላይ ስምምነት እንደሚያደርጉ ሠፍሯል፡፡ የሕወሓት ታጣቂዎች ቀላልና ከባድ መሣሪያ የሚፈቱበትንና ወደ መልሶ ማቋቋሙ ሥልጠና የሚገቡበትን ጊዜ ከአንድ ወር ያልበለጠ መሆን እንደሚኖርበትም የጊዜ ገደብ አስቀምጧል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ያቋቋመው የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽንና ሌሎችም አካላት በአገሪቱ  በአጠቃላይ 371 ሺሕ ተዋጊዎች መኖራቸውን ግምታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ 70 በመቶ በትግራይ የሚገኙ ናቸው፡፡ እነዚህን ተዋጊዎች አሠልጥኖ መልሶ ለማቋቋም ደግሞ ከ550 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ይገምታሉ፡፡

መንግሥት ባለፈው ዓመት ይፋ እንዳደረገው ከሆነ ትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎችን ያዳረሰውን ጦርነት ውድመት መልሶ ለመጠገን ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ብሏል፡፡ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር) ዓምና በነሐሴ ወር ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ተዋጊዎችን ትጥቅ ለማስፈታትና መልሶ ለማቋቋም የሚያስፈልገው ከ500 እስከ 700 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት በጀት በዚህ ውስጥ የሚካተት ነው ብለው ነበር፡፡

ወደ 28 ሚሊዮን ዕርዳታ ጠባቂ ሕዝብ ተፈጥሮባታል በሚባለው ኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት እስከ 35 በመቶ በሚደርስ ከፍተኛ አኃዝ ላይ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ በፕሪቶሪያ ስምምነት የሰሜኑ ጦርነት ይቁም እንጂ በአማራ ክልል ትኩስ ውጊያ እየተካሄደ መገኘቱ፣ እንዲሁም የኦሮሚያ ግጭት አለማብቃቱ ተደማምሮ ቀውሱን የበለጠ እንዳያባብሰው እየተሠጋ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ተዋጊዎቹን ትጥቅ ለማስፈታትና መልሶ ለማቋቋም የተያዘው ዕቅድም በቀላሉ እንደማይሳካ የሚገምቱ ብዙ ናቸው፡፡ በፕሪቶሪያው ድርድር ወቅት ለትጥቅ ማስፈታቱና ለመልሶ ማቋቋሙ ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡ በርካታ ለጋሾች ቢኖሩም፣ ቃል በተገባው ልክ ድጋፍ ያደረጉ አለመኖራቸው ይነገራል፡፡

ይህን ጉዳይ የሚከታተሉ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የፖለቲካ ተንታኝ ግን፣ ለዚህ ሥራ ለመርዳት ቃል የገቡ ወገኖች በመንግሥት በኩል እንደ ቅደም ተከተል ያስቀመጡት ሁኔታ ባለመሳካቱ እጃቸውን መሰብሰባቸውን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹የውጭ ድጋፍ ሰጪዎች መንግሥት በመጀመሪያ የቀጠለውን ጦርነት እንዲያስቆም ይፈልጋሉ፡፡ የሚለግሱት ገንዘብ በቀጥታ ለታለመለት ታጣቂዎችን ትጥቅ አስፈትቶ መልሶ ለማቋቋም ሥራ መዋሉን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ፤›› ሲሉ የፖለቲካ ተንታኙ ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ገንዘቡን ከመልቀቃቸው በፊት በአማራ፣ በኦሮሚያና በሌሎችም አካባቢዎች እንደ ትግራይ ሁሉ ጦርነት እንዲቆም መጠየቃቸውን አስረድተዋል፡፡

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽነር ተሾመም (አምባሳደር) ቢሆኑ ለሪፖርተር እንደተናገሩት ከሆነ፣ ሥራው ከፍተኛ የሆነ ሀብት ይፈልጋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያን የተረጋጋች ከማድረግ አኳያ ይህ ሥራ ፋይዳው በጣም ከፍተኛ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ ኮሚሽናቸው ለጦርነት፣ ለጥፋትና ለውድመት ተሰባስበው የነበሩ ሰዎችን አሠልጥኖና አዕምሮአቸውን ቀይሮ ወደ ሰላም የማሰማራት ሥራ እንደሚያከናውን ነበር የተናገሩት፡፡

ይህ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም አስፈላጊና ፋይዳው ትልቅ ነው የተባለ ሥራ ግን በተለያዩ ምክንያቶች እንቅፋት እየገጠመው መሆኑ ነው የተነገረው፡፡ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ትግበራ የሚከታተለው የቁጥጥር፣ ክትትልና ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ በታኅሳስ ወር ከስምምነቱ ፈራሚ አካላት ጋር የጋራ ስብሰባ በማድረግ ባወጣው መግለጫ፣ ትጥቅ የማስፈታቱና መልሶ ማቋቋሙ ሥራ መዘግየቱ እንዳሳሰበው ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ በወቅቱ ባወጣው መግለጫ ላይ የአፍሪካ ኅብረት ለትጥቅ ማስፈታትና ለመልሶ ማቋቋም ያግዛል በሚል አንድ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ከአደጋ መጠባበቂያ በጀቱ ላይ ቀንሶ መስጠቱ መሰማቱ አይዘነጋም፡፡

ከሰሞኑ ደግሞ የአውሮፓ ኅብረት 16 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል መግባቱ ትልቅ ዜና ሆኖ ነበር፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) በኩል የሚደረግ ሲሆን፣ በስምንት ክልሎች የሚገኙ ከ370 ሺሕ ያላነሱ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም እንደሚውል ተጠቁሟል፡፡

የድጋፍ ስምምነቱ በተደረገ ወቅት የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታዋ ሰመሪታ ሰዋሰው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት አቅሙ በሚፈቅደው ልክ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታትና መልሶ የማስፈሩን ሥራ እንደሚደግፍ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ለዚህ ሥራ የሚያስፈልገውን ወጪ 15 በመቶ እንደሚሸፍን ነው ያስታወቀው፡፡

ይሁን እንጂ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽነሩ ተሾመ (አምባሳደር) የአውሮፓ ኅብረቱ ድጋፍ በዓይነቱ የመጀመርያው ትልቅ የሚባል ድጋፍ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ የአውሮፓ ኅብረትን እግር ተከትለው ሌሎች ቃል የገቡ ለጋሾች ድጋፋቸውን እንዲሰጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የትጥቅ ማስፈታቱና መልሶ ማቋቋሙ ሥራ በዋናነት በመንግሥት እንደሚመራ ይታወቃል፡፡ መንግሥት ከተለያዩ አካላት ሀብት አሰባስቦ ታጣቂዎችን ትጥቅ አስፈትቶ፣ ወደ ማሠልጠኛ ጣቢያዎች አስገብቶና ሥልጠና ሰጥቶ ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲገቡ ማድረግ ይጠበቅበታል ይባላል፡፡ እስካሁን ባለው ሒደት ግን የተጠበቀው ድጋፍ በአግባቡ ባለመገኘቱ ሥራው በተባለው ጊዜ መካሄድ አልቻለም ነው የሚባለው፡፡

ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ትግርኛ ክፍል ጋር ረጅም ቃለ ምልልስ ያደረጉት የመከላከያ ሚኒስትሩ አብረሃም በላይ (ዶ/ር)፣ ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሰጡት ማብራሪያ ባይኖርም፣ ስለፕሪቶሪያ ስምምነት ጉዳዮች አተገባበር ሐሳቦች አንስተው ነበር፡፡ በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል የውዝግብ መነሻ የሆኑና በፕሪቶሪያው ስምምነት ላይ አጨቃጫቂ ቦታዎች ተብለው የተቀመጡ አካባቢዎችን ችግር ለመፍታት በመንግሥት በኩል የተያዘውን ዕቅድ በሰፊው ያብራሩት አብረሃም (ዶ/ር)፣ ተፈናቃዮችን መልሶ ስለማስፈር፣ ከመከላከያ ውጪ ያሉ የታጠቁ ኃይሎችን ስለማስወጣት፣ እንዲሁም በየአካባቢው ራሱ ሕዝቡ በሚያካሂደው ምርጫ የአስተዳደር መዋቅሮችን ስለመገንባትና በመጨረሻም በሕገ መንግሥቱ መሠረት በሕዝበ ውሳኔ ጉዳዮቹን ስለመቋጨት በሰፊው አብራርተዋል፡፡

ይህን ተከትሎ በሕወሓት በኩል እስካሁን ትጥቅ ሳይፈቱ በጦር ካምፕ አስቀምጧቸዋል ስለሚባሉ ታጣቂዎች ጉዳይ መንግሥት የያዘው አቋም አለመታወቁ፣ በአንዳንዶች ዘንድ ጥርጣሬን እየፈጠረ ነው፡፡ በተለይ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ ከመንግሥት ጋር በነበረ ንግግር ወቅት፣ ‹‹ታጣቂዎቻችንን ትጥቅ ያላስፈታነው ለሥራው የሚያስፈልገው በጀት ስላልተገኘ ነው፤›› የሚል አስተያየት ሰጥተዋል መባሉ ከፍተኛ መነጋገሪያን ፈጥሮ ነበር፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፣ ከአንድ ወር ቀደም ብሎ በሰጡት መግለጫ፣ ታጣቂዎችን በካምፕ ሰብስቦ ውድ የክልል በጀትን መቀለቢያ ከማድረግ፣ በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች ፈጥኖ መድረስ ይበጃል የሚል ወቀሳ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ላይ መሰንዘራቸው ውዝግብ አስነስቶም ነበር፡፡

የትግራይ ክልል ታጣቂዎችን ለክፉ ቀን በሚል ትጥቅ ሳያስፈታ ደብቆ አቆይቷል የሚለው ጉዳይ፣ በፌዴራል መንግሥትና በክልሉ መካከል ለረጅም ጊዜ መወዛገቢያ ሆኖ ነው የቆየው፡፡

ስለዚሁ ጉዳይ አስተያየት የተጠየቁት ስሜ አይጠቀስ ያሉት የፖለቲካ ተንታኝ ግን፣ ጉዳዩ የገንዘብ እንጂ ታጣቂ ደብቆ የማቆየት አለመሆኑን ነው የሞገቱት፡፡ ‹‹በጀቱ ሳይለቀቅና ሳይገኝ ታጣቂዎቹን አሠልጥኖ ወደ መደበኛ ሕይወት የመመለሱ ሥራ አይካሄድም፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ በትግራይ ክልል ሙሉ ቁጥጥር አለው፡፡ የታጠቁ ኃይሎች ለክፉ ቀን በሚል በካምፕ ተሰብስበው ተቀምጠዋል የሚለውን ራሱ ማጣራት ይችላል፡፡ ለእኔ ከዚህ ይልቅ ገንዘቡ ባለመገኘቱ ነው ሥራው ያልተጀመረው፤›› የሚል ምልከታቸውን አጋርተዋል፡፡

ይህ ትጥቅ የማስፈታትና መልሶ የማቋቋም ጉዳይ ውዝግብ ደግሞ የአፍሪካ ኅብረት በሚያስተናግደው የፕሪቶሪያው ስምምነት አተገባበር በሚገመገምበት ስብሰባ ላይም አንዱ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ እንደሚቀርብ ነው የተገመተው፡፡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ (አምባሳደር) በተጨማሪ፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ከስብሰባው መካሄድ ቀድመው ይፋ አድርገዋል፡፡ ሆኖም ስብሰባው ስለሚያተኩርባቸው ነጥቦች ፍንጭ አልሰጡም፡፡ በስብሰባው የሁለት ቀናት ቆይታ ምን ዓይነት ጉዳዮች በውይይት ርዕስነት እንደተነሱ ለማወቅ ሪፖርተር ጥረት ያደረገ ቢሆንም፣ ዝርዝር መረጃዎችን ማግኘት ሳይቻል ቀርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -