Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹ንብ ባንክን ካለበት ችግር ለማላቀቅ የምንሠራው ሥራ እንደሚሳካልን 101 ከመቶ እርግጠኛ ነኝ›› አቶ ሺሰማ ሸዋነካ የንብ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ገጥሞታል የተባለውን ችግር ተከትሎ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኩል የተለያዩ ውሳኔዎች መተላለፋቸው ይታወሳል፡፡ የተለየዩ ዕርጃዎንችም ወስዷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ባንኩን ወደ ቀድሞ አቋሙ ሊመልሱ ያስችላሉ የተባሉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡ ለዚህም በቀዳሚነት አዲስ የተመረጡት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት እያደረጉ ነው የተባለው እንቅስቃሴ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ ከዚህ አኳያ ባንኩ ገጥመውት ነበር በተባሉ ችግሮች፣ ለመፍትሔ እየተወሰዱ ባሉ ጉዳዮች ዙሪያና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በሚመለከት ከአዲሱ የንብ ኢንተርናሽና ባንክ የዳይሬከተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሺሰማ ሸዋነካ ከዳዊት ታዬ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡    

ሪፖርተር፡- ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ የግል ባንኮች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን ባንኩ የተለያዩ ተግዳሮቶች ገጥመውታል፡፡ ችግሩ ሥር እየሰደደ በመምጣቱም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጣልቃ እስከ መግባት ደርሷል፡፡ በባንኩ ላይም ምርመራ ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ ንብ ባንክ በዚህን ያህል ደረጃ ስሙን ያስነሳው ችግር ምንድነው? ገጥመውት የነበሩትን ችግሮች በዝርዝር ቢገለጹልን?

አቶ ሺሰማ፡- ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኢትዮጵያ ቀዳሚ ከሚባሉት ባንኮች አንዱና በዋናነት በነጋዴዎች የተቋቋመ ባንክ ነው፡፡ ባንካችን በፅኑ መሠረት ላይ የተገነባና ላለፉት ከ24 ዓመታት በላይ ለኅብረተሰቡ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ትልቅ ተቋም ነው፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ነጋዴዎች እምነት የተጣለበትና በዋናነትም የነጋዴዎች ባንክ የሆነው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ምንም እንኳን አሁን የገጠመው ጊዜያዊ ተግዳሮት ቢኖርም፣ ይህንን ተግዳሮት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደምንወጣው እርግጠኞች ነን፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በባለአክሲዮኖች ታኅሳስ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ላይ በተከታታይ ባደረገው ምርመራ፣ ባንኩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልተለመደ መልኩ የመልካም አስተዳደር (Corporate Governance) ችግር እየተስተዋለበት መምጣቱን ገልጿል፡፡ የባንኩን የገንዘብ አከል ንብረት ሥጋትና (Liquidity Management) ጤናማና ተገቢ በሆነ ሁኔታ የማስተዳደር ችግር እየገጠመው ስለመሆኑ ለመገንዘብ መቻሉንም አስታውቋል፡፡

በዚሁ በመግለጫው፣ የባንኩ ቦርድ ከጠቅላላ ጉባዔው የተሰጠውን አደራ፣ እንዲሁም በብሔራዊ ባንክ የኩባንያ አስተዳደርና አግባብነት ካላቸው ሌሎች ተዛማጅ መመርያዎች መሠረት፣ ለአንድ ዓላማና የባንኩን ዘለቄታዊ ጥቅም መሠረት ባደረገ መልኩ ኃላፊነቱን መፈጸም ሲገባው፣ በቦርድ አካላት መካከል ጤናማ ያልሆነና የባንኩን ጥቅም መሠረት ያላደረግ መከፋፈል ከመፈጠሩም በላይ ልዩነቱ የባንኩን የዕለት ተዕለት የሥራ ክንውን ወደሚያውክበት ደረጃ ተሻጋግሯል ሲል መግለጹ ይታወሳል፡፡ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መግለጫ ላይ ቦርዱና ከፍተኛ አመራሩ የባንኩን የአደጋ ሥጋት (Risk Management) በአግባቡ ማስተዳደር፣ የማኔጅመንቱን የሥራ አፈጻጸም በመገምገም ለውጥ እንዲመጣ በማስቻልና ባንኩ ሕግ አክብሮ እንዲሠራ በማድረግ ረገድ ኃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት አልቻሉም ሲል በዕለቱ ለባለአክሲዮኖች ገልጾ ነበር፡፡

በመግለጫው ላይ ሌላው የተገለጸው ጉዳይ አንድ ባንክ አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት ከተለያዩ አካላት ማለትም ከደንበኞችና ከባለአክሲዮኖች ቅሬታ ወይም አቤቱታ ሊቀርብበት የሚችል ቢሆንም፣ በንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ላይ የነበረው ሁኔታ ከዚህ ወጣ ያለ መሆኑን ነው፡ ተደጋጋሚ ሊባል በሚችል ደረጃ ቅሬታና ጥቆማ የሚቀርብበት ባንክ እንደነበር፣ በዚህ አኳኋን የሚቀርቡ ቅሬታዎችና ጥቆማዎችን በተመለከተ ብሔራዊ ባንክ ማጣራት በማድረግ እንደ አስፈላጊነቱና እንደ አግባቡ ምላሽና የማስተካከያ ዕርምጃ እየወሰደ ቆይቷል፡ ሆኖም የቀድሞ ቦርድና ከፍተኛው አመራር የሚጠበቅበትን ባለመወጣቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያደረገለትን ድጋፍ በአግባቡ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

እንደሚታወቀው በባንክ አሠራር ውስጥ ከሚጠቀሱ ቁልፍና ወሳኝ ተግባራት መካከል አንዱ ሊያጋጠም የሚችልን ገንዘብ አከል እጥረት ሥጋት (Liquidity Management) ጤናማና ብቃት ባለው ሁኔታ የበላይ አመራሩ ማስተደደር የሚያስችል ሥርዓት ዘርግቶ ተፈጻሚ ማድረግ ቢሆንም፣ ማኔጅመንቱ ከዚህ በተለየ ሁኔታ ይህንን ተግባር ለመወጣት ሳይችል መቅረቱን በመግለጫው አመላክቷል፡፡

እንግዲህ በመግለጫው ተጠቅሶ እንደነበረው ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች እንዲከሰቱ በመሠረታዊነት አስተዋፅኦ ካደረጉት ምክንያቶች ዋነኛው የባንኩ የቀድሞ ቦርድና ማኔጅመንት የሚጠበቅባቸውን ተግባርና ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለመቻላቸው ነው፡፡ በዚህም ባንኩ ለተለያዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ለከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት እንዲዳረግ በማድረግ የባንኩ ጤናማ አካሄድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ከዚህም በላይ የባለአክሲዮኖችና የአስቀማጮችን (Shareholders & Depositiors) ጥቅም የሚነካ ድርጊት ሆኖ በመገኘቱ፣ ብሔራዊ ባንክ ታኅሳስ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. የተካሄደው የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ከነበሩት አጀንዳዎች አንዱ የነበረው ባንኩን በቀጣይ ሦስት ዓመታት የሚመራ ቦርድ የመምረጥ ሒደቱን አስተባብሮ በሕጉ መሠረት እንዲከናወን አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- አዲሱ ቦርድ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ ያለውን በባንኩ ውስጥ ተፈጠረ የተባለውን ችግር እንዴት ገመገመው?

አቶ ሺሰማ፡ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ችግሮች ነበሩ፣ አሁን ግን እየተስተካከሉ ነው፡፡ የባንኩ ችግር ብዙ ነው፡፡ በተለይ የሊኪውዲቲ (የጥሬ ገንዘብ) ችግር ጎልቶ ታይቷል፡፡ ይህ የሊኪውዲቲ ችግር በአገር ደረጃ የሚታይ ነው፡፡ የንብ ባንክ የሊኪውዲቲ ችግር ወጥቶ ስለታየ ነው እንጂ፣ የሁሉም ባንኮች ተግዳሮት ነው፡፡ ይህንን ማስተካከል ይኖርብናል፡፡ ለማስተካከል ደግሞ 24 ሰዓታት እየሠራ ነው፡፡ ጠዋትም ሆነ ማታ ይህንኑ ነው የምናስበው፡፡ አሥራ ሁለቱም የቦርድ አባላት እንደ አንድ ሆነው ጠንክረው ከሠሩ ችግሩን በአጭር ጊዜ እንወጣዋለን የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባንካችሁ ላይ ባካሄደው ምርመራ ተፈጠረ ያላቸውን ችግሮች በዝርዝር ለባንካችሁ ባለአክሲዮኖች አሳውቋል፡፡ ነበሩ ያላቸውን ተግዳሮቶች እንዲታረም ያደረጋቸው ጥረቶች ሊሳኩ እንዳልቻሉ ሁሉ ጠቅሷል፡፡ የዕርምት ዕርምጃዎች ባለመወሰዳቸው ባንኩን አደጋ ላይ ስለመጣሉም ገልጿልና አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ቦርድ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተጠቀሱ ችግሮችን ለመፍታት ምን እያደረገ ነው? ባንኩ ገብቶበታል ከተባለው ችግር ለማውጣት አዲሱ ቦርድ እየሠራ ያለው ሥራስ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ሺሰማ፡- አዲሱ ቦርድ ባንኩ ያለበትን ከፍተኛ ተግዳሮት በመገንዘብ ፈጥኖ ወደ ሥራ በመግባት በአጭር ጊዜ ውስጥ የተለያዩ ዕርምጃዎችን ወስዷል፡፡ እንደ ማሳያ አዲሱ የዳይሬክተሮች ቦርድ ከቀድሞ ቦርድ ርክክብ ከፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ በንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኩል ያሉትን ችግሮች ለማወቅና መፍትሔ ለማበጀት ተከታታይ ውይይቶችን አካሂዷል፡፡ የቦርዱን ሥራ ለማስጀመር እንዲረዳ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ ምርጫ አካሂዷል፣ የደንበኞችን አመኔታ በአጭር ጊዜ ለመመለስ የሚያስችል የ90 ቀናት ዕቅድ ሁሉም የቦርድ አመራር ተሳትፎበት ከተዘጋጀ በኋላ፣ በዳይሬክተሮች ቦርድ ውይይት ፀድቆ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የቦርዱ ንዑሳን ኮሚቴዎች ተሰይመው ሥራቸውን ጀምረዋል፡፡ ከሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር በተለያየ ጊዜ ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡ በተጨማሪም በንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት በተለያየ ደረጃ ከሚገኙ የሥራ አመራር አባላት፣ አዲስ አበባ ከሚገኙ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የ90 ቀናት ፍኖተ ካርታ በሚመለከት ውይይት ተካሂዷል፡፡ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ፣ ምክትል ገዥና ሌሎች አመራሮች ጋር ጥልቅ ውይይት በማካሄድ በቀጣይ የRecovery Plan እና ሌሎች አስፈላጊ ዕቅዶች ተዘጋጅተው እንዲቀርቡ በተሰጠ አቅጣጫ መሠረት ይኸው ተፈጽሟል፣ ለብሔራዊ ባንክም ተልኳል፡፡

እንዲሁም፤ የባንኩን የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በማሰናበት የባንኩን ሥራ በጊዜያዊነት እንዲያስተባብሩ አቶ መልካሙ ሰለሞንን በተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚነት መድቧል፡፡ ከላይ በገለጽኳቸው መድረኮች መረዳት የተቻለውና አስቸኳይ የመፍትሄ እርምጃዎች የሚሹ ጉዳዮችንም ለመለየት ተችሏል፡፡ ዝርዝር መርሃ ግብር በማዘጋጀት ለዚሁ የሚሆኑ የመፍትሔ ርምጃዎች እየወሰድን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ እያደረጋችሁት ያለው ጥረት በትክክል ባንኩን ከችግር ለማውጣት ያግዛል? ባሰባችሁት ልክስ ይሳካልናል ብላችሁ ታስባላችሁ?

አቶ ሺሰማ፡- ምን ልናደርግ እንዳሰብን ቀደም ብዬ ገልጬልሃለሁ፡፡ ባንኩን ካለበት ችግር ለማላቀቅ የምንሠራው ሥራ እንደሚሳካልን በእርግጠኝነት ልገልጽልህ እፈልጋለሁ፡፡ 101 ከመቶ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ምክንያቱም በመርካቶ ያደረግነው ካምፔን ራሱ ወደ ስኬት የምንራመድ መሆኑን አመላክቶናል፡፡ በዘጠና ቀን ውስጥ እንሠራለን ብለን ካስቀመጥናቸው ሥራዎች መካከል ቀዳሚው የባንኩን ሊኪውዲቲ ችግር መቅረፍ ነው፡፡ ባንኩ በጣም ጠንካራ ባንክ ነው፡፡ በሁሉም ረገድ ጥንካሬውን በእርግጠኝነት መግለጽ እችላለሁ፡፡ ነገር ግን ባንኩ ሊኪውዲቲ ችግሩ ከተፈታ በኋላ ወደ መደበኛው ሥራ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ባንኩ ነበረበት ተብሎ  የሚገለጹ ችግር የሊኪውዲቲ ችግር ብቻ አይደለም፡፡ ከብድር ጋር ተያይዞ በተለይም ብድር ከማስመለስ ጋርም ተያያዥ የሆኑ ችግሮች አሉ፡፡ የተበላሸ የብድር ምጣኔውም ጨምሯል፡፡ መጨመሩም ሌላው ችግር ነው፡፡

አቶ ሺሰማ፡- እሱም ቢሆን ከአንዱ ወደ አንዱ የተጋባ ነው፡፡ አንድ ድክመት ወደ ሌላ ድክመት ይጋባል፡፡ ከእሱ ጋር የተያያዘ ነው እንጂ ቀደም ሲል ጥሩ ደረጃ ላይ ነበር፡፡ አሁን እሱ ላይ ብቻ ትኩረት ስለተደረገ ነው፡፡ የባንክ ሥራዎች እርስ በርስ የተያያዙ ናቸው፡፡ አንደኛው ሲጎትትብህ ሌላኛው የመበጠስ ወይም የመለጠጥ ነገር ይኖራል፡፡ ከዚህ አንፃር ነው እንጂ የተበላሸ የብድር ምጣኔውም ብዙ ችግር የለውም፡፡ ማኔጅ ይደረጋል፡፡ በእኔ እምነት በዘጠና ቀን ውስጥ ማኔጅ እናደርገዋለን፡፡ ከዘጠና ቀን በኋላ ብሔራዊ ባንክን አሳምነን ኖርማል ቢዝነስ እንጀምራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ችግሩን ለመፍታት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጣልቃ በመግባት የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ ይህ እርምጃው ባንኩን ምን ያክል ታድጐታል ማለት ይቻላል?

አቶ ሺሰማ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዚህ ረገድ ዘርፈ ብዙ ድጋፎች አድርጎልናል፡፡ በተለይም ሙያዊ ድጋፎቹ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ከምንም በላይ ስራችንን በመልካም ሁኔታ ለማከናወን እንድንችል አቅጣጫዎችን በማመላከትና የመፍትሔ እርምጃዎቻችን የባንኩን ጤናማነት ያረጋገጡ እንዲሆኑ በክትትል ሥራቸው እየደገፉን ይገኛሉ፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢው አዲሱን ቦርድ ቢሯቸው ድረስ አስጠርተው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ሌሎች የብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ሰፊ ጊዜ ወስደው ምክርና መመሪያ ሰጥተውናል፡፡ እንዲሁም መከተል የሚገባንን አቅጣጫ አሳይተውናል፡፡

ለዚሁም የብሔራዊ ባንክ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ለሚያደርጉልን ድጋፍ በባንኩ ቦርድ፣ ማኔጅመንትና ሠራተኞች ሥም ከፍ ያለ ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ባንኩን ወደቀድሞው ከፍታው ለመመለስ ይወሰዳሉ ተብለው ከሚጠበቁ እርምጃዎች መካከል ከፍተኛ የባንኩ አመራሮች በመመዘን እንደ አዲስ ምደባ ማድረግ የሚል ነው፡፡ ይህንን ምን ያህል ሄዳችሁበታል?

አቶ ሺሰማ፡- በመጀመሪያ ቦርዱ እያንዳንዱ እንቅስቃሴው የሚመራው በተቀመጠው የ90 ቀናት ፍኖተ ካርታ መሠረት ሲሆን፤ ይህንን ጥያቄ በተመለከተ በዚሁ ዕቅድ ላይ በዝርዝር የተመለከተ ስለሆነ በቅድሚያ የዋና ሥራ አስፈጻሚ ሹመት ከተከናወነ በኋላ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክን ችግሮች በመተለከተ በዝርዝር ካቀረባቸው ጉዳዮች ውስጥ ነባሩን ማኔጅመንት የሚመለከት ነው፡፡ ከዚሁ ጋር አይይዞም የነባሩን ከፍተኛ ማኔጅመንት አባላት ይዞ ለውጥ ሊመጣ ይችላል ብዬ አላምንም በማለት ሥጋቱን ገልጿል፡፡ እምነት የለኝም ብሏል፡፡ ከዚህ ከብሔራዊ ባንክ ምልከታ አንፃር እስካሁን ምን ዕርምጃ ወስዳችኋል? እስካሁን የተሰማው የፕሬዚዳንቱ መሰናበት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አካሄዳችሁ ምን ይሆናል፡፡ አዲስ የስትራክቸር ለውጥስ ይደረጋል?

አቶ ሺሰማ፡- ይህንን ጉዳይ  በተመለከተ ቀደም ብዬ በዝርዝር ገልጫለሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ስትራክቸሩ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆንና የተለጠጠ እንዳይሆን እንፈልጋለን፡፡ ውጤታማ የሆነና ይህንን ችግር በቀጥታ ለመፍታት የሚያስችል እንዲሆን ይደረጋል፡፡ ሪቫይዝድ የሆነ ስትራቴጂክ ዕቅድ አለው፡፡ ከእርሱ ጋር የተጣጣመ ስትራክቸር እንዲኖረን እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ባንኩ በቅርቡ የተገበረው ነው የተባለ የሦስት ዓመት ስትራቴጂ ዕቅድ አለ፡፡ ይህን ትከልሱታላችሁ ወይስ ታስቀጥሉታላችሁ? በሌላ በኩል ግን ይህ ዕቅድ የተለጠጠ ነውም ይባላልና በዚህ ረገድ ምን ታደርጋላችሁ?

አቶ ሺሰማ፡- ማንኛውም ቢዝነስ ካለበት ሁኔታ አንፃር ሪቫይዝ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ተለዋዋጭ ፕላን ማዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡ ለጊዜው የዚህን ዓመት ዕቅድ እንዲከለስ እያደረግን ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ሌሎቹ ፕላኖች ክለሳ ይደረጋሉ፡፡

ሪፖርተር፡- አዲሱ ቦርድ ባንኩን ከገባበት ችግር ለማውጣት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ገልጸውልናል፡፡ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋርም እየመከረ ነው፡፡ የ90 ቀናት ፍኖተ ካርታ ነድፎ ይህን በመተግበር ላይ እየዋለም ነው ተብሏል፡፡ ከዚህ አንፃር በ90 ቀን ውስጥ ምን እናሳካለን ብላችሁ ታምናላችሁ? በተከታታይ ባደረጋችሁት የውይይት መድረክ ላይ ምን አገኛችሁ?

አቶ ሺሰማ፡- በ90 ቀናት የውይይት ፍኖተ ካርታ ላይ በተመለከተው መሠረት በመጀመሪያ ባንኩ ከነበረበት የገንዘብ አከል እጥረት ሥጋት (Liquidity Management)ችግር ይወጣል፡፡ በተከታታይ ከተደረጉ ውይይቶች በባንኩ ውስጥ ነበሩ የተባሉ ችግሮችን ለመለየት ችለናል፡፡ ከአሠራር ጋር የነበሩ ክፍተቶችን ለይተናል፡፡ ከገንዘብ አከል ሥጋት ችግር ጋር በተያያዘ የነበሩ ዋና ዋና ችግሮችን ለይተናል፡፡ በማኔጅመንት አካባቢ የነበሩ ክፍተቶችንም ተረድተናል፡፡ ከሌሎችም ከባለድርሻ አካላት፣ ከሠራተኞችና ከሚመለከታቸው ጋር ባደረግናቸው ውይይቶች አንኳር አንኳር የሚባሉ በርካታ ችግሮች እንደነበሩ ለመረዳት ችለናል፡፡ ይህንንም በመከተል ተገቢውን የማስተካከያ ዕርምጃዎች እየወሰድን ባንኩን ከነበረበት ከፍታ ላይ ለማድረስና የቀድሞውን ስምና ዝናውን ለመመለስ እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ለአንድ የቢዝነስ ተቋም ዕድገት ወሳኝ ሚና የሚኖራቸው ሠራተኞች ናቸው፡፡ ከእናንተ ባንክ አኳያ በነበረው ችግር አንፃር ብዙ ሠራተኞች ብዥታ ውስጥ ገብቶ እንደነበርም ይታመናል፡፡ ሠራተኛው ከነበረበት ብዥታ ወጥቶ ተግቶ እንዲሠራና የእናንተን ዕቅድ ለማስፈጸም እንዲችል ምን እያደረጋችሁ ነው?

አቶ ሺሰማ፡- በእርግጥም ሠራተኛ ለአንድ ድርጅት እንደ ጀርባ አጥንት የሚታይ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ሊባል ይችላል፡፡ ባንካችን አሁን ሰባት ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል አለው፡፡ አጠቃላይ ካፒታሉ ደግሞ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ሠራተኛው ከሌለ ይህ ሁሉ ዋጋ የለውም፡፡ ምንም ዓይነት ካፒታልና አሴት ቢኖርም፣ ሠራተኛውን ካልያዝክ ውጤት አይኖርም፡፡ የሠራተኛው አዕምሮ ከሁሉም የበለጠ ነገር ነው፡፡ አስተዋጽኦ የላቀ ነው፣ ይህንን እንረዳለን፡፡ ሠራተኛው የተረጋጋ የሥራ ድባብ ይፈልጋል፡፡ እኔ ያነጋገርኳቸው አብዛኛዎቹ ሠራተኞች ባንካቸውን ይወዳሉ፡፡ እስከ ሃያ ዓመት ያገለገሉ ሁሉ አሉበት፡፡ ስለዚህ የሠራተኞችን ሞራል ከፍ እያደረግን ነው፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው ችግራቸው ከየት መነጨ? ከተባለ የማኔጅመንት ስታይሉና ባህሉ (ካልቸሩ) የተበላሸ ስለነበር ነው ማለት ይቻላል፡፡ የተበላሸ ባህል ስለመኖሩ እነሱም የገለጹት ነገር አለ፡፡ ይህንን ባህል ስንለውጥ ወደ ቀደመው መተማመናቸው ይመልሳሉ፡፡ አሁንም በመመለስ ላይ ነው፡፡ የበለጠ ኮንፊደንሳቸው እንዲመለስም እናደርጋለን፡፡ በዚህም ሠራተኛው ደስተኛ ይሆናል፡፡ ድርጅቱም ሠራተኛውን ይንከባከባል፣ ሠራተኛውም ድርጅቱን ይንከባከባል፡፡   

ሪፖርተር፡- አዲሱ ቦርድ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ምን ያህል ቁርጠኛ ሆኖ እየሠራ ነው? በኃላፊነት ዘመኑ ባንኩን ምን ደረጃ ላይ አደርሰዋለሁ ብሎ ያስባል? የእርስዎስ ምኞት?

አቶ ሺሰማ፡- አዲሱ ቦርድ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት የባንኩን ስምና ዝና ወደነበረበት ከፍታ ለመመለስ በቁርጠኝት እየሠራ ይገኛል፡፡ በተለይ በዚህ ወቅት ቦርዱ ሙሉ ጊዜውን ለባንኩ ትንሣኤ በመሰዋት የተከሰተውን ችግር በአጭር ጊዜ ለማስወገድ ቀን ከሌት እየሠራ ነው፡፡ ለዚህም ይህንን ጊዜ ‹አንድ ልብ መካሪ አንድ ቃል ተናጋሪ› ሆነን እንደምንወጣው ቅንጣት ታክል ጥርጥር የለንም፡፡ባንኩ አሁን የገጠመውን ተግዳሮት የተረዳን በመሆኑ በፍጥነት እንደምንፈታው በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እወዳለሁ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅድሚያ የጋራ ቤታችን የሆነውን ባንካችንን አሁን ካለበት ተግዳሮት ለማላቀቅና ወደነበረበት ከፍታ ለመመለስ ተግተን እየሠራን እንገኛለን፡፡

በቅርቡ ባካሄድናቸው ውይይቶችም ከሠራተኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ያገኘናቸው ግብረመልሶች አበረታች ሆነው ነው ያገኘናቸው፡፡ በዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካል ለባንኩ ስኬት ‹እኔም ድርሻ አለኝ› በሚል ስሜት እንደሚሰራ አረጋግጦልናል፡፡ ለዚህም ሁሉንም እናመሰግናለን፡፡ በመሆኑም ባዘጋጀነው የ90 ቀናት ፍኖተ ካርታ መሠረት ባንካችንን በአፋጣኝ አሁን ካለበት ሁኔታ በማላቀቅ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደነበረበት ደረጃ የመመለስ ትልም ይዘን እየሰራን እንገኛለን፡፡ እናሳካዋለንም፡፡ አንድ የግልህ ድርጅት ችግር ላይ ካለ አይደለም ቀን ሌሊትም እንቅልፍ አይወስድህም፡፡ እኔ በግሌ አሁን የምሠራው ልክ እንደ ግል ድርጅቴ ነው፡፡ ጥቅም አግኝቼበታለሁ ብዬም አይደለም፡፡ አንድ ትልቅ ዛፍ ጫካ ውስጥ ቢወድቅ ብዙዎቹን ደፍጥጦ ነው የሚወድቀው፡፡ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው እንደዚያ ነው፡፡ ዛፉ ካዘመመ እንኳን ስንቶቹን ነው የሚጫነው፡፡ ስለዚህ ከዚያ አንፀር ነው እኔ የማየው፡፡ ይህንን ማስተካከል ያለብንም እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ሁሉ ከግምት አስገብተው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርታችኋል፡፡ ከዚህ ጉባኤ ምን ትጠብቃላችሁ?

አቶ ሺሰማ፡- እንደጠቀስከው ጠቅላላ ጉባዔው መጋቢት 14 ቀን 2016 ቀን በሚሊኒየም አዳራሽ ለማካሄድ ጠርተናል፡፡ በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ የባንኩን ካፒታል ለማሳደግ ታስቧል፡፡ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ቀደምትና አንጋፋ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሆኖም በኢንደስትሪው ካሉ ባንኮች ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቆየት አሁን ያለውን ካፒታል ከፍ ለማድረግ ዕቅድ ይዘናል፡፡ ካፒታል ደግሞ ተጨማሪ ስራዎችን ለመስራት አንዱና ዋነኛው ግብዓት መሆኑ ይታወቃል፡፡

በሌላ በኩል ቀደም ሲል በሰኔ 2018 ዓ.ም. ተከፍሎ እንዲጠናቀቅ በባለአክሲዮኖች ተወስኖ የነበረውን ያልተከፈለ ካፒታል መጠን ሙሉ በሙሉ በመጪው ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ተከፍሎ እንዲጠናቀቅ እንዲሁም ባለአክሲዮኖች አሁን ያለውን የትርፍ ድርሻቸውን በባንኩ የካፒታል ማሳደጊያነት እንዲያውሉ እንጠይቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በምታደርጉት ጠቅላላ ጉባዔ ዓላማው በዋናነት ካፒታል ማሳደግ ላይ ትኩረት የሚሰጥ ነው፡፡ ነገር ግን ባንኩ ላለበትና ካለበት ችግር ለመውጣት ካፒታል ማሳደግ ብቻውን መፍትሔ ይሆናል? ሌሎች ሊወሰዱ የሚገባቸው ዕርምጃዎች የሉም? አሁን ባሰባችት መጠን ካፒታል እንዲያድግና የቀድሞ ካፒታሉን ከፍሎ ለመጨረስ የጊዜ ገደቡን ማሳጠሩ ተግዳሮት አይሆንም? ባለአክሲዮኑ ይህንን ካፒታል በምትፈልጉት የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማሟላት አይቸገርም?

አቶ ሺሰማ፡- እንደገለጽከው ካፒታል ማሳደግ በራሱ ብቻውን ችግር ማቃለያ ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን ካፒታል ማሳደግ ለአንድ የፋይናንስ ተቋም እጅግ አስፈላጊው ነገር ነው፡፡ በተለይ በአሁኑ ሰዓት እንደ ንብ ላለ ባንክ በጣም ያስፈልገዋል፡፡ ከሊኪውዲቲ (ከጥሬ ገንዘብ) ችግር ለመውጣት፣ በዓለም አቀፍ ባንኮችና ተቋማት ዘንድ የበለጠ እምነት ለመጨመር ሁሉ ካፒታል ማሳደጉ እጅግ ጠቃሚ መሆኑ ጥያቄ ውስጥ መግባት የለበትም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ባለአክሲዮኖች የድርጅቱ አለኝታ መሆናቸውን ለመግለጽ እንዲህ ያለው ዕርምጃ አስፈላጊ ነው፡፡ የችግሩ የመጀመሪያው ገፈት ቀማሾች እነሱ ናቸው፡፡ ድርጅቱ የሆነ ነገር ቢሆን ንብረታቸውን የሚያጡትም ባለአክሲዮኖች ናቸው፡፡ ስለዚህ ድርጅታቸው ችግር ሲያጋጥመው ቀድመው የመጀመሪያ ደራሾች እነሱ መሆን አለባቸው፡፡ ካፒታል ማሳደግ ብቻውን መፍትሔ ባይሆንም ካፒታል ማሳደግ የሚሰጠው ብዙ ጠቀሜታ አለ፡፡ ካፒታል ማሳደጉ ባለሀብቶች የሚያገኙትን የትርፍ መጠንን ሁሉ ያሳድጋል፡፡ የትርፍ ክፍፍል ይጨመራል፡፡ ድርጅቱ የሚያድገው ባለው አቅም ነው፡፡ ስለዚህ ለጊዜው በ2018 ዓ.ም. እንዲጠናቀቅ ታቅዶ የነበረው የተፈረመ ካፒታል በ2016 ዓ.ም. እንዲጠናቀቅ ባለአክሲዮኖች ያፀድቁልናል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ መግለጽ የምፈልገው ይህ ባንክ መደገፍ አለበት፡፡ መቀጠል ያለበት፣ መዝለቅ ያለበት ባንክ ነው፡፡ አሁን ጊዜያዊ ችግር ገጥሞታል፡፡ ይህ ባንክ በኢትዮጵያውያን የተመሠረተ ነው፡፡ በነጋዴዎች የተመሠረተ ነው፡፡ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የተውጣጡ ባለአክሲዮኖች አሉት፡፡ ወደ 5,500 ባለአክሲዮኖች አሉት፡፡ ስለዚህ ነጋዴዎች በሙሉ ለባንካቸው ድጋፍ መስጠትና ማበረታታት፣ ወደ ቀድሞ ቦታ እንዲመለስ ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ባንኩን በፕሬዝዳንትነት የሚመራው ጠንካራ ባለሙያ እየፈለጋችሁ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ ጥረታችሁ በአጭር ጊዜ ይሳካል ብላችሁ ታምናላችሁ?

አቶ ሺሰማ፡- አዎ! በእርግጠኝነት! ባንኩን የሚመጥን ዋና ሥራ አስፈጻሚ በአጭር ጊዜ ለመምረጥ ዕቅድ አስቀምጠን እየሠራን ነው፡፡ እንደሚታወቀው ባንኩ ሀገራችን ውስጥ ካሉት ባንኮች አንጋፋና ቀዳሚ ከሚባሉት መካከል አንዱ በመሆኑ፤ በርካታ ባለሙያዎች ወደባንኩ መምጣት እንደሚፈልጉ ተረድተናል፡፡ በርካታ ማመልከቻዎችም እየተቀበልን ነው፡፡ እንግዲህ የምልመላ ስራውን እንዳጠናቀቅን ከእነዚህ ባለሙያዎች መካከል የምንሾም ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከንብ ባንክ ጉዳይ ወጣ እንበልና በግልዎ ወቅታዊውን የኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ እንዴት ይገመግሙታል?

አቶ ሺሰማ፡- ጥያቄው በሰፊው ሊብራራ የሚችል ነው፡፡ ብዙ ሐሳቦችንም መሰንዘር ይቻላል፡፡ በአጭሩ ለመግለጽ ዕድገት እያሳየ ያለ ዘርፍ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ባንኮችን ሁኔታ ወደኋላ መለስ ብለን ካየንና አሁን የደረሱበትን ደረጃ ስናመዛዝን ዕድገቱ በግልጽ ይታያል፡፡ ለምሳሌ የዛሬ 25 ዓመት አካባቢ አዳዲስ ባንኮች ሲመሠረቱ ንብ አንዱ ነበር፡፡ በወቅቱ ባንኩን ለማቋቋም የሚያስፈልገውን አሥር ሚሊዮን ብር ካፒታል ለማሟላት በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ በወቅቱ እኔ የአጅፕ ፋይናንስ ማናጀር ነበርኩና ብዙ ባንኮች የሚፈለገውን ካፒታል ለመሙላት ዕገዛ ሲጠይቁን እንደነበር ሁሉ አስታውሳለሁ፡፡ ያኔ 10 ሚሊዮን ብር ለመሙላት ችግር እንዳልነበር፣ አሁን የባንክ መመሥረቻ የካፒታል መጠን እያደገ መጥቶ አምስት ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህ የካፒታል መጠን በዚህን ያህል ደረጃ አድጎ እዚህ መድረሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በሌሎች የባንክ ዘርፍ እንቅስቃሴ ብዙ ለውጦች አሉ፡፡ ዕድገት አለ፡፡ ከዚህ አንፃር ከዚህም በኋላ ይህ ዘርፍ እያደገ ይሄዳል፡፡ የአገራችን ባንኮች ብራይት ፊቸር ይኖራቸዋል ብዬ ነው የማስበው፡፡ በተለይ የካፒታል ማርኬት መመሥረት ለባንኮች አዲስ የሥራ መስክ ይፈጥርላቸዋል፡፡ ባንኮች የኢንቨስትመንት ባንክ ሆነው እንዲሠሩ ተጨማሪ ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ በእኔ እምነት ግን ብዙዎቹ የአገራችን ባንኮች ወደ ውህደት ቢገቡና አቅማቸውን አጠንክረው ቢሠሩ ደግሞ የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን የውህደት ሐሳብ ብዙዎች እያነሱት ያሉት ጉዳይ ነው፡፡ እርስዎ እንዲህ ያለውን ሐሳብ ይጋሩታል ማለት ነው?

አቶ ሺሰማ፡- በትክክል፡፡ በተለይ አነስተኛ አቅም ያላቸው ባንኮች ወደዚህ ቢገቡ ይመረጣል፡፡ ቢያንስ በምሥራቅ አፍሪካ ከዚያም አልፎ በአፍሪካ ደረጃ ጠንካራ ተወዳዳሪ ባንኮች እንዲኖሩን ከተፈለገ መዋሃድ የግድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ንብ ባንክ? እየመጣ ያለውን ዓለም አቀፍ ባንክ ውድድርን እንዴት ለመወጣት እየተዘጋጀ ነው? እንደ አንድ የቦርድ ሊቀመንበርስ በዚህ ጉዳይ ምን ያስባሉ?

አቶ ሺሰማ፡- ይኼ ቦርድ አንድ ወሩ ነው፡፡ ነገር ግን መሆን ያለበትን አጥንተን የሚሆነውን እናደርጋለን፡፡ በዚህ ረገድ በእልህ የምንሠራው ነው፡፡ እንደሚታወቀው ንብ ባንክ የነጋዴዎችም ባንክ ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን ባንክ ነው፡፡ ነጋዴዎች ደግሞ ለማደግ ትልቅ አቅም አላቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ደንበኞቹን በሙሉ አቅፎ ትልቅ ቦታ እንደሚደርስ እርግጠኛ ነኝ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች