Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትበሃምሳ ዓመት ቅብብል ያፈራነው ልምሻ

በሃምሳ ዓመት ቅብብል ያፈራነው ልምሻ

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

በደርግ ዘመን ጀምሮ፣ በሕወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን ጣሪያ የነካው የትምህርት ውድቀት የልሂቅ ዕድገትን አለምሽሿል፡፡ የለብ ለብ ትምህርት፣ የመንግሥት ፖለቲካ የሚያቦካው አሳሳችና ሐሳዊ ትምህርት፣ ሁለቱ አንድ ላይ ወጣቱን ሳይማር የተመረቀ/ሳይማር ተማርኩ የሚል አስመሳይ እንዲሆን እያደረገ ማውጣቱ፣ ያልተማረው ባለ ወረቀትም ካሽመደመደው አላዋቂነት ለመውጣት የረባ የራስ በራስ ጥረት አለማድረጉ፣ በተቃራኒው ለመቀጨጭ እጅ መስጠት መበራከቱ፣ በድህረ ሕወሓት/ኢሕአዴግ የለውጥ ጊዜ ላይ ትልቅ የስንቅ ጉድለትና የልምሻ ዕዳ አቆይቷል፡፡ የፖለቲካውን ሜዳ መካን በመካን አድርጓል፡፡ የሕዝቡንና የወጣቱን ህሊና የሚመራ የበሳል ፖለቲካ ማዕከል አሳጥቷል፡፡

የሽምድምድ ትምህርት ውጤት የሆነው ወጣት ራሱን ተመሪ፣ ጎልማሳ ፖለቲከኞችን መሪ አድርጎ ሊያከብር አልቻለም፡፡ ለዚህ የሚያበቃ ምን አግኝቶ! ትምህርት ቤት ገብቶ የወጣው ወጣት ስለ1960ዎች ትውልድ የለውጥ ትግል በቃርሚያ ያገኘው ዕውቀት በድንቁርናና በሽርዳዳ የተሞላ፣ ‹‹ሸ›› እና ‹‹ቸ›› በሚባሉ ፊደሎች ከመጣላት ጋር አያይዞ ያንኳሰሰ፣ ንቀትን የሚያጎለብትና ከማን አንሼ ባይነትን የሚያፋፋ ነበር፡፡ ‹‹ቀይ ሽብር›› እና ‹‹ነጭ ሽብር›› ይባል የነበረው ክፉ ጊዜ ካለፈ በኋላ ስለነበረው የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም አገዛዝ ቢሰማ፣ ‹‹ታላቁ ቆራጡ ኮሙዩኒስት መሪያችን›› እያሉ የማወደስና እያወደሱም የማንከት ሥርዓት እንደነበረ ነው፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግና ሻዕቢያ የጠመንጃ ‹ባለ ድል›› ሆነው በ1983 ዓ.ም. ግንቦት ቢመጡ፣ አንደኛው ‹ኤርትራ የብቻዬ፣ ኢትዮጵያ የጋራችን› በተሰኘ ጥፋት ዝና ያተረፈ፣ ሕወሓት ኢትዮጵያን በማጥቃትና በማስጠቃት መወገዝ የለማበት፡፡ ኦና የነበረውን ኢሕአዴግነት የሞሉት ቡድኖች ቢመዘኑ፣ ለሕወሓት የበላይ ሥልጣንና ለብሔርተኛ ፖለቲካው ሠግደው ሎሌ ገዥነትንና በሊታነትን የተቋደሱ፡፡ ሕወሓትና እነሱ ተቀናብረው የቀነበሩበት ሥርዓት ለውሸት ልክ የለው! ‹‹የብሔሮች እኩልነት የተረጋገጠበት… የብሔር ጭቆና ላይመለስ የተሰናበተ… የካቲት 11 የሕወሓት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ልደት! …ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. የአዲሲቱ ኢትዮጵያ ታሪክ የጀመረበት…›› እያሉ እስከ ማናፋት ምላሱ የወፈረ፡፡

- Advertisement -

ከእነሱ በተቃራኒ ተቃዋሚ ነን የሚሉት ቡድኖች፣ ታሪካቸው በመዳፋትና በመንኮታኮት የተሞላ ነው፡፡ ገና ብቅ ከማለታቸው ገዥውን ቡድን ‹‹ፀረ ኢትዮጵያ! የኢትዮጵያን ጥቅም የማያስጠብቅ!››፣ ወዘተ በማለት እየኮነኑ ሸረኛ ጥቃትን በራሳቸው ላይ የሚጠሩ፣ ካቄመ የማይለቅ አመለኛ ቀንዳም ገዥን እንዴት በዘዴ መያዝ እንዳለባቸው የማያውቁ፣ ያወቁ መስለው በይፋ ለስለስ ያለ አቋም ቢይዙ፣ ኮናኝ ውንጀላቸውን በሹክሽክታ ሲያራምዱ በቀላሉ የሚያዙ ነበሩ፡፡ እናም በሰርጎ ገብ ከፋፋይነት በሐሜትና በአንጃ ለመቆራረስ፣ ተከስሶ በእስርና በዕገዳ ለመጎሳቆል፣ ተናቁሮ ለመሰንጠቅና ለማለቃቀስ ቅርብ ነበር ኑሯቸው፡፡

ግልብ ግንዛቤም ያጠቃቸው ነበር፡፡ መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም የነገሠበትና በማርክሲዝም ይነግድ የነበረው አገዛዝ ወታደራዊ ቢሮክራሲያዊ ሰንሰለቱ በ‹ኢሕድሪ› መንግሥትነቱም ሆነ በ‹ኢሠፓ› ፓርቲነቱ ውስጥ ቁልጭ ብሎ የሚታይ ሆኖ ሳለ፣ በኢሕአዴግ ዘመን የነበሩት ተቃዋሚዎች ደርግን ‹‹ሶሻሊስት/ኮሙዩኒስት/ማርክሲት›› ብሎ ከመግለጽ ያለፈ የሥርዓት ግንዛቤ እጅግም አልነበራቸውም፡፡ ከ1997 ዓ.ም. የምርጫ ቅስቀሳ እስከ 1998 ዓ.ም. በነበረ እንቅስቃሴያቸው የታየባቸው ጀብደኛነት ያጋለጠውም የኢትዮጵያ አገረ መንግሥትም ሆነ የራሳቸው አዘላለቅ በሕወሓት/ኢሕአዴግ ቁጥጥር ውስጥ መሆኑን በደንብ የተገነዘበ ብልህ የፖለቲካ ቅያስ እንዳልነበራቸው ነበር፡፡ እናም በአጥለቅላቂ የሕዝብ ድጋፍ የደመቁትን ያህል ‹‹የአህያ ባል ከጅብ አያስጥል›› የሚል መተረቻ ሆነው ተሰባበሩ፡፡ ከእነሱ የተራረፉትና ነፍስ ዘራን/አገገምን ያሉትም ቢሆኑ ትርጉም ያለው ትምህርት ከ1997-1998 ዓ.ም. ውድቀት ተምረው የአተያይና የትግል ጥበበኛነት አላሳዩም፡፡

ብቅ ጥልቅ እያለና አቅም እያጠራቀመ በሄደው ከ2006 እስከ 2010 ዓ.ም. በነበረው የወጣቱ ግብታዊ ትግል ውስጥም መግለጫ ከማውጣት ያለፈ ሚና አልነበራቸውም፡፡ ይህ ጉዳይ ከተመልካችነት ያለፈ ምን ሚና ነበራችሁ ብሎ እነሱን መጠየቅ የሚሻ አይደለም፡፡ የነበረው የትግሉ ዕድገት አጠቃላይ ባህርይ ግብታዊ (ሕዝብን ከሕዝብ ያያያዘ የትግል መሪነትና አነቃናቂነት ያልታየበት)፣ በአያሌው የተነጣጠለ፣ የመንግሥት ጥፋትና ተንኳሽነት ያልተጠበቀ ቁጣ እየወለደ፣ ቁጣ ለማስቆም የሚወሰድም የድቆሳ ዕርምጃ ሌላ ቁጣ እየወለደ ይካሄድ የነበረ ነው፡፡ በኦሮሚያ ወጣቶች ትግል ውስጥ አንዱ ሁነኛ መፈክር ‹‹ኦሮሚያ ለኦሮሞ›› የሚል ነበር፡፡ በአማራ አካባቢ ጎንደር ብልጭ ያለው ‹በኦሮሚያ የሚፈሰው ደም የእኛም ነው› ያለ የትግል ድምፅም ግብታዊ ወለድ አስተዋይነት ነበር፡፡ ከተደራጀ እንቅስቃሴ የመጣ ቢሆን ኖሮ ከዚያ በኋላ የነበረው የሕዝቦች ትግል የጋራ የፖለቲካ ጥያቄዎችንና አርቆ አስተዋይ ብስለትን ሲያንፀባርቅ ለማየት በቻልን ነበር፡፡ ‹‹ኦሮ-ማራ›› የምትባለዋ ‹‹ቅንጣቢ ምሪትም›› ግብታዊ ወለድና ብስለት የሚጎድላት ነበረች፡፡ ከውጭ ትግሉን እየመራን ነው የሚሉ ቡድኖች በሚዲያና በስልክ ያደርጉ የነበሩትም አስተዋፅኦ፣ ግብታዊ እንቅስቃሴ በሒደት ግብታዊ ‹‹መሪዎችን›› የመፍጠሩ አንድ መገለጫ ከመሆን የዘለለ አልነበረም፡፡ እንደ ጃዋር መሐመድ ያሉ ፖለቲከኞች ማውደምና ማቃጠልን በትግል ታክቲክነት እንዲጠቀሙ ለወጣቶቹ የሰጡት ምሪትም ቢሆን፣ ተሬዎች በግብታዊ ቁጣ ለሚወስዱት ዕርምጃ ልሂቃዊ ቡራኬ ከመስጠት በቀር፣ አዲስ የትግል ሥልት የማስያዝ ሚና የለበትም፡፡

ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ወርዶ ዓብይ አህመድ በመጣበት ጊዜ የነበረው የወጣቶች እንቅስቃሴ ያልተያያዘ/የጋራ መሪ የለሽ ነበር፡፡ ‹‹የቄሮ ትግል››፣ ‹‹የፋኖ ትግል›› እንደ ተባለ ሁሉ የሲዳማውም የጉራጌውም ወጣት የራሱን ስም እየለጠፈ ሲያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ የዝናና የአካባቢያዊ ጥያቄዎች ፉክክር ያየለበት ነበር፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ለውጥ ወደ እዚህ በታየው በነፃ የመተንፈስ ጊዜ፣ ወጣቱ በህቡዕ ትግል መሪነት አግዛችሁኛል ብሎ ከአገር ውስጥ ‹‹ፓርቲዎች›› ስማቸውን ያነሳሳቸው አለመኖራቸውና እነሱም ከዳር ተመልካችነት ያለፈ መላወስ አለማሳየታቸው፣ ቡድኖቹ በለውጥ አማጭነት ንቁ ሚና እንዳልነበራቸው ሌላ ማረጋገጫ ነው፡፡ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. አብዮት አደባባይ ቦምብ ፍንዳታ ከተከሰተ በኋላ የሶማሌው አብዲ ዒሌ ሕዝብ የሚያጨራርስና አገር የሚንድ ቀውስ በክረምት ባነሳሳ ጊዜ እንኳ፣ በሁለት ጎራ ተኮልኩለው የነበሩት ቡድኖች ባንነውና የጎራ ሠፈራቸውን ተሻግረው፣ መፋጀትንና መፈራረስን የማስቀረት ትብብራዊ ሥራ ውስጥ አልገቡም፡፡

በሕወሓት/ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎች የዳር ተመልካችነት የተገለጸው የፖለቲካ አመራር ባዶነት፣ በግብታዊው የወጣቱ ታጋይነት ላይ የሚጋጩ ተፅዕኖዎችን አሳድሯል፡፡ በኢሕአዴግ ጊዜ በትምህርት ቤት ያለፈው ወጣት ትውልድ፣ ደርግ አፍርቶት ከነበረው ወጣት ጋር በተልኮሰኮሰ ትምህርትና አቅሙን የማይናገር ምስክር ወረቀት በመሸከም ተመሳሳይ የነበረ ቢሆንም፣ በብሔርተኛ የአስተሳሰብ ሙሽት የተጣበበ ነበር፡፡ ከሠፈርተኛ ክፍልፋይነት ባሻገር ‹ብሔርተኛ› እና ‹ነፍጠኛ› በሚሉ ትልልቅ ጎራዎች ውስጥ እንዲሰማራ የተደረገና ብሔር አነካኪ ንቁሪያዎችንና ፀቦችን የተለማመደ ነበር፡፡ መሪ ማጣቱ እነዚህን ችግሮች ተሻግሮ በሰፊው የተያያዘ እምቢታ የማቀጣጠል ዕድሉን አሳንሶበታል፡፡ ችግሩ አሸልቦ እንዲቆይም አድርጓል፡፡ ከዚያም በላይ፣ ከድፍን የኢትዮጵያ ፍቅርና ከብሔርተኛነት ውጪ የመጣ አዲስ የፖለቲካ ዕይታ አልነበረምና በእነዚህ በተከፋፋሉ ነባር ጎራዎቹ ውስጥ ተኮልኩሎ እያለ፣ በነፃነትና በኑሮ መሻሻል የተሞላ ሕይወትን አገኛለሁ ብሎ እንዲያልም ሆነ፡፡

እንደዚያም ሆኖ፣ በሁለቱም ጎራዎች ውስጥ ያሉ ብዙኃን ወጣቶችና ጎልማሶች በአያሌው ለዓብይ አህመድ አዲስ መንግሥት ድጋፋቸውንና አክብሮታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በዓብይ መንግሥት ላይ ተስፋቸውንም አሳርፈዋል፡፡ በአዲሱ መንግሥት ተስፋ ከማድረግ በታች ግን፣ ካለ ፖለቲካ ፓርቲ መሪነት ወጣቱ ያካሄደው ትግል የለውጥ ምዕራፍ ለመክፈት መቻሉ፣ ወጣቱ ልብ ውስጥ የጫረው የመታበይ ዝንባሌም ነበር፡፡ በአገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የናቀና ከዚህ ቀደም ‹‹አታጋዮች›› የባረኩለትን የማውደም/የማቃጠልና መንገድ የመዝጋት የትግል ሥልት ይዞ፣ መሪ ሳይሻው ራሱ ለራሱ ትግል የማካሄድ መተማመንና ኩራትም ተፈጥሮ ነበር፡፡ ከግብታዊ ትግል ‹‹ስኬት›› የፈለቀች ኩራትና በዓብይ መንግሥት ላይ ተስፋ ማድረግ፣ 2010 ዓ.ም. ጳጉሜዎች ላይና የ2011 ዓ.ም. መጥባት ላይ ከተከሰቱ ትልልቅ የጎራ ሠልፎች ጋርም ተዛምደው ነበር፡፡ ጳጉሜን ውስጥ በኢትዮጵያ ድፍን ፍቅር ጎራ ውስጥ ያሉ፣ በዝናና በ‹ኢሳት› በኩል ለሚያውቁት ‹አርበኞች ግንቦት 7› ያሸበረቀና የሕዝብ አጀቡ የበዛ አቀባበል አደረጉ፡፡ መስከረም 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ላይ የዳውድ ኦነግን ለመቀበል የተካሄው መሰናዶ ደግሞ፣ በሽብርቅም በደጋፊም የፊተኛውን አቀባበል የመብለጥ ከፍተኛ ፉክክር የታየበት ነበር፡፡

በግብታዊ ትግል መመካት፣ ማውደምን አዋጪ የትግል ሥልት አድርጎ መያዝ፣ የዓብይን መንግሥት በጋራ መደገፍና በ‹ኦነግ› እና በ‹ግንቦት ሰባት› ረድፎች መሠለፍ፣ የእነዚህ የማይግባቡ ዝንባሌዎች አንድ ላይ መጎዳኘት መጪው የለውጥ ትግል እንዴት ያሉ አበሳኛ ፈተናዎች እንዳሉበት የሚጠቁም ነበር፡፡ አበሳ መገለጥ የጀመረውም ገና ወዲያው ነበር፡፡ በሽብርቅ ፉክክር ጊዜ በአተካሮ የተከሰተ ግብግብ ከኦነግ የአቀባበል ‹‹ድል›› በኋላ ደም ያፈሰሰ የደቦ ቅጣቱን አካሄደ፡፡ ለኦነግ ዳውድ የተደረገው ግዙፍ የኦሮሞዎች አቀባበል ኦነግ ተቀናንሶ ተሸራርፎ በርዝራዥ ለተረፈ የአሮጌ አቋም ቡድን እንደነበር ብዙኃኑ ግንዛቤ አልነበረውም፡፡ ያ አቀባበል፣ የቡድና ቡድኖቹን ልዩነት ጉዳዬ ያለም አልነበረም፡፡ በአጠቃላይ ለኦነግ ባንዲራና ለኦሮሞ ብሔርተኛ ትግል አክብሮት የሰጠ አቀባበል ነበር፡፡ አቀባበሉን ለኦነግ ብቻ የተደረገም አድርጎ ማጥበብ አሳሳች ነው፡፡ ግዙፉ አቀባበል ለብሔርተኛ ጎራው የተሰጠ አቀባበል ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ ትግሉን በደፈናው ተምሳሌቱ ያደረገው ይህ ሕዝብ-ገብ አመለካከት፣ ከኦነግ ካዘረዘሩት ስብርባሪ አቋሞችና ከኦሕዴድ ጋር ነገ መፋተጉም የማይቀር ነበር፡፡

‹‹ለግንቦት 7›› እና ‹‹ለኦነግ የተደረገውን አቀባበል የብሔርተኛውና የኢብሔርተኛው ሁለት ትልልቅ ጎራዎች ሠልፍ መገለጫ እንደነበር አድርገን ካየነው፣ መጪውን ትልቅ የፈተና ሥዕል ለማስተዋል ያመቸናል፡፡ ይኼውም፣ የዓብይ መንግሥትና የለውጡ እንቅስቃሴ ለመጎልበት ከፈለገ፣ ያፈጠጡበትን እነዚህን ሁለት ጎራዎች እየናደ የጋራ መገናኛ ባለው የለውጥ ዓላማ ዙሪያ መሰብሰብ መቻል አለበት፡፡ ካልቻለ ሁለቱ ጎራዎች በየፊናቸው በየራሳቸው ማዕቀፍ ውስጥ ለማስገባት ይጎትቱታል፡፡ ጉተታው ለሁለቱም አልሰምር ካላቸው ደግሞ ሁለቱም ጠምደው ይተናነቁታል፡፡ ሁለቱ ጎራዎች በሁለት በኩል በሚኖራቸው ፍልሚያም በእሳት አጥፊነት ከቦታ ቦታ ያባዝኑታል፡፡ 2010ን ሸኝተን 2011ን የተቀበልንበት የመስከረም ልምድ፣ ይህንን ሁሉ መጪ ጣጣ አመልክቶናል፡፡ በጊዜው ፈልፍሎ ለመረዳት አልቻልን እንደሆን እንጂ፡፡

ጣጣዎቹ በየፈርጁ ራሳቸውን ለመግለጥም ብዙ ጊዜ አልፈጁም፡፡ ሌሎች ጣጣዎችን ማየት ውስጥ ሳንገባ፣ ዓብይ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ውስጥ በገባ በሁለት ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ፣ በአብዮት አደባባዩ የድጋፍ ትዕይንት ላይ፣ ዓብይን ለመግደል የቦምቦች ውርወራ መከሰቱና ይህንን ለማክሸፍ ከሕዝብ በኩል የታየው ሕይወት የነጠቀ ቆራጥ ተጋዳይነት ብቻውን፣ ‹‹ለውጡን ለውጤ ያላችሁ ሁሉ በአዲሱ መንግሥት ዙሪያ ተጠምጠሙ!›› የሚል መልዕክት ያስተጋባ ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ችግሮች እያቃለሉ በለውጥ የመጓዝ ነገር፣ በተቃዋሚዎችም ብቻ የማይቻል፣ የኢሕአዴግንና የተቃዋሚዎችን ትግግዝ የሚሻ መሆኑ ከ1997 ዓ.ም. ምርጫና የለውጥ ዕድል መቀጨት ወደ እዚህ ጎልቶ የተነገረ ተግባር ነበር፡፡ ‹‹ዓብይ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ሲገባ›› የሚል አባባል የተጠቀምኩት ሥልጣኑ ተንሳፋፊ እንደነበር ለመግለጽ ነበር፡፡ ከቢሮው በስተቀር ሁሉም የመንግሥት አውታር በሕወሓት ዓይን – ጆሮ – ዕዝ ሥር እንደነበር ዕውቅ ነበር፡፡ ዓብይም በበስተኋላው ቀውስ ጊዜ ይህንኑ ነግሮናል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ሥራ ‹‹ነፍስ ሸጦ የማስተዳደር›› ያህል የሆነበትና ከሕዝብ ድጋፍ በቀር መተማመኛ የሌለው ሰው፣ ከሁሉ ቀድሞ የለውጥ ፖለቲካ ቡድኖች ሁሉ በዚህ መንግሥት ዙሪያ መሰባሰባችው ለለውጡ አንግብጋቢ መሆኑን መለፋፍ (ማለትም ተሰባስበው በተወሰነ የአጭር ጊዜ መርሐ ግብር በጋራ በሚታገሉላቸው በሚቀሰቅሱላቸውና በሚፈጽሟቸው ነገሮች ላይ ትልም እንዲያበጁ መጥራት) በተገባው ነበር፡፡ ዓብይ አህመድ ነገሮች ይወሳሰቡብኛል/የሽግግር መንግሥት ጣጣ ቀስ ብሎ ይመጣብኛል ብሎ ቸል ቢል፣ ለውጡ መውሸልሸል እንዳያገኘው የተቆረቆሩ ፖለቲከኞች ሁሉ ‹‹ፍኖተ ካርታ ይውጣ›› ከማለት ይልቅ ዓብይንና ለውጡን የሚደግፍ ስብሰባ ጠርተው ለውጡን የሚያግዝ (ሁከት/ግርግር የሚያቀልና ትልም የሚያጠራ፣ የዓብይን መንግሥት ከመተካት ሚና የተጠነቀቀ) አጭር መርሐ ግብር ነድፈው መንቀሳቀስና ሕዝብን ሁሉ የዚያ ትልም ተጋሪ ማድረግ በተገባቸው ነበር፡፡ የሚገባቸውን ያላደረጉት አስታዋሽ ሊቅ ቸግሮ አልነበረም፡፡ ገና ከመጀመሪያው ችግሮች ራሳቸው የሊቅ አፍ ሆነው ‹‹ኧረ የለውጥ አጋዥ ያለህ!›› የሚሉ ምላስ አውጥተው ነበር፡፡ ጩኸታቸውም ማብቂያ አልነበረውም፡፡

የአብዲ ዒሌ አገር የመናድና የጭፍጨፋ ቀውስ ሐምሌ ማለቂያ 2011 ዓ.ም. ላይ ተከፍቶ ነሐሴ ውስጥ በረደ፡፡ መስከረም 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ለኦነግ ግዙፍ አቀባበል በአዲስ አበባ ከተደረገ በኋላ፣ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ወጣቶች መሀል ግጭት ተከሰተ ተብሎ የተካሄደው (በተለይ የቡራዩና አካባቢው) የደቦ ቅጣትና የፀጥታ ኃይል ፈጥኖ የመድረስ ዳተኛነት ያሳየበት ልምድ፣ በዚያ ልምድ የተንፀባረቁትም የፖለቲካ ፍልሚያ መስመሮች፣ ጊዜ ሳይረፍድ ትኩስ በትኩስ አንድ ነገር አድርጉ ያሉ ነበሩ፡፡

ኦነግ ዳውድ በሰላም ከገባ በኋላ በአንድ በኩል የታጠቁ ተዋጊዎቹ ሠልጥነው ወደ ፀጥታ አውታሩ እንዲቀላቀሉለት እየጎተጎተ፣ በሌላ በኩል በየቦታው የጠመንጃ ቡድኖች ማሰማራት የያዘው ወዲያው ነበር፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ከአንዱ ወደ አንዱ እየተዛመቱ የብሔር ግጭት ይለኩሱ የነበሩ ቀውሶች፣ የትግራይና የአማራ ክልሎች በመሬት ጉዳይ የተያያዙት ንትርክ እየከረረ መምጣት፣ የብስጭትና የበቀል ስሜታቸውን ወደ ሌሎች አቅጣጫዎችም የሚረጩ ነበሩ፡፡ ሰኔ አጋማሽ 2011 ዓ.ም. የእርስ በርስ መተላለቅ ለማስነሳት ትልቅ አቅም የነበራቸው፣ በኢትዮጵያ መከላከያ ኤታ ማዦር ሹም ሰዓረ መኮንንና በእነ አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)  (የአማራ ክልል አስተዳደር ሰዎች) ላይ የተካሄዱ ሴረኛ ግድያዎች የፈጠሩት ክውታ፣ የዓመቱ ታላቅ የቀውስ ክስተት ነበር፡፡ ግን ‹‹የመንግሥት ግልበጣ! የሕወሓት ሥውር ሴራ! የአማራ ነፍጠኛን አደገኛነት ያሳዩ ግድያዎች! ወዘተ›› እያሉ ከመወነጃጀልና ‹‹ነገር ከማጋጋል እንታገስ!…›› ከማለት አልፎ የትብብር (ሶሊዳሪቲ) መድረክ እንኳ ለመፍጠር አልተሞከረም፡፡

ተከታዩ 2012 ዓመት ከ2011 የበለጠ ጣጣዎች እየተከታተሉ የታዩበትና የዓብይ መንግሥት የሕዝብ ድጋፍ ብዙ መበዝበዝ የደረሰበት ነበር፡፡ ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ጃዋር መሐመድ ‹‹በሌሊት ጥበቃዬ ተነሳ ልገደል ነው!…›› በሚል የቀሰቀሰው ቁጣ፣ ከጥቅምት 12 እስከ 14 ቀን በተለያዩ ሥፍራዎች በቅብብል ግድያዎችንና የንብረት ውድመቶችን ‹‹ኦሮሞ ያልሆኑ›› በተባሉ ሰዎች ላይ አስከተለ፡፡ የሰው ነፍስ እንደ ዶሮ የረከሰበት ጥቃት የቆመውም ከእነ ጃዋር ሠፈር ‹‹በቃችሁ! አቅማችሁን አሳይታችኋል›› ሲባል ነበር፡፡ የዓብይና የጃዋር ወዳጅነት በዚህ ዓይነት ቀውስ ከፈረሰ በኋላ የጃዋር የአንደበትና የተግባር ተራጋጭነት ልክ አልነበረውም፡፡ የዓብይ መንግሥት ፌዴራላዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ ድብቅ ዕቅድ ያለው ስለመሆኑ ከመናገር አንስቶ፣ የመንግሥትን ውጥረቶች ማባባስና ማበራከት ሁሉ ይካሄድ ነበር፡፡ ‹‹ክልል ልሁን…፣ ልዩ ወረዳ ልሁን…›› የሚሉ ጥያቄዎችን መንግሥት ታገሱ ሲል፣ እነ ጃዋር ደግሞ ‹‹መብታችሁ ነው! አይዟችሁ ከጎናችሁ ነን!›› እያሉ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩና በ‹ኦኤምኤን› ቀስቃሾች ነበሩ፡፡

ልብ በሉ! ትግል ተብሎ በሚካሄደው ጥቃት ውስጥ ሰዎች በብሔረሰባዊ ማንነታቸውና በፖለቲካ አቋማቸው ጠላት ተደርገው ይጠቃሉ፡፡ ከዚህ የከፋ ነገርም አለ፡፡ ‹‹አታጋዮች›› ቡራኬ የሰጡት ንብረት የማውደም የትግል ታክቲክ ‹‹ዕድገት አሳይቶ››፣ ሰውን ከሰውነት ደረጃ ወደ ግዑዝ ደረጃ አውርዶ፣ የሆነ ጥያቄ ተሰሚነት እንዲያገኝ ለማድረግ የሚወገርና የሚቃጠልም ሁነኛ ቁሳቁስ አድርጎታል፡፡ በሌሎች አገሮች ጎማ በማቃጠልና ዕቃ በመሰባበር ቁጣ ሲገለጽ ይታያል፡፡ የብሔርተኛ ጥላቻ ባነቀዘው በእኛ አገር ማን ጎማ ምናምን ለመፈለግ ይጨነቃል! ከጎማ ‹‹የረከሰ›› ጥላቻ ያረፈበት ሰው ሞልቷል፡፡ ይህንን ከሚያስተውሉ ፖለቲከኞቻችን በኩል ግን፣ ይህንን ጉድ የሚያረክስ/የሚያስቀር የተሰባሰበ ጥረት ብቅ አይልም፡፡

የጃዋርና የዓብይ የትቅቅፍ ጊዜ ማብቃት፣ የዓብይን መንግሥት ወደ ብሔርተኞቹ ሠፈር የመሳቡ ጥረት ተበጥሶ የዓብይን መንግሥት ‹‹የነፍጠኞች አገልጋይ፣ የፌዴራላዊነት ጠላት፣ የአሃዳዊነት ወኪል›› አድርጎ የመጥመድ እንቅስቃሴ የተከፈተበትም ጊዜ ነበር፡፡ ማስቆሚያ ያጣው ብሔርተኛ ግጭትና የሰዎች ጥቃት የደራበት፣ ከአማራ አካባቢ የመጡ ተማሪዎች ታግተው የጠፉበት (ኅዳር)፣ የሰኔ 2012 የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተንተርሶ ማንነት ላይ ያተኮረ የቅጣት ዶፍ ብዙ ቦታ ላይ የወረደበት፣ አዲስ አበባ ላይ ነውጥ ለመፍጠር የተቃጣበትም ዓመት ነበርና ይህ ቀውስ ባስከተለው ብስጭት፣ ኢብሔርተኛ ነኝ የሚለውም ሠፈር የዓብይን መንግሥት በአስጠቂነትና በ‹ዘር› ማጥራት ሥውር አጀንዳ ይበልጥ እየጠመደ መጥቷል፡፡ ከሁለት የፖለቲካ ሠፈር በኩል የዓብይ መንግሥት የሚወገዝበት ጊዜ ላይ መደረሱ፣ ‹‹የለውጡ አምባ የት ጋ ነው? በለውጡ ዙሪያ የሚሰባሰቡትስ እነማን ናቸው?›› የሚል ግራ መጋባትም ያስከተለ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ መላ ያጣ ቅዋሜ ከእነ ደም አፋሳሽነቱ፣ መሰባሰቢያ ጊዜን የማባከን ውጤት ነበር፡፡

በዚያም አልበቃም፡፡ ባለሦስት ስለት ግቦች (ኦሮሚያን ማፅዳት፣ አማራንና ኢብሔርተኞችን በዓብይ መንግሥት ላይ ማስነሳት፣ መንግሥት ሊቆጣጠረው የማይችል የእርስ በርስ መገዳደል ማራባት) የተጣመሩበት መሰሪነት በተለያየ መልክ ይካሄዳል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ብሔር ያነካኩ የቅብብል ግጭቶችና ግድያዎች፣ በታጣቂዎች የሚፈጸሙ ጭፍንና ጨካኝ ጥቃቶች፣ ከአካባቢ አካባቢ በደቦ የሚካሄዱ ፍርክሶች፣ ‹‹ጥያቄያችን ካልተመለሰ!›› የሚሉ ተቆጪዎች በእልህ መወጫነት በንፁኃን ላይ የሚያደርሷቸው የንብረት ጥቃቶችና ግድያዎች… ብዙ ብዙ ነበሩ፡፡ እነዚህን ግፎች ሁሉ የሚደግሷቸው ሰብዕና ላይ የደረሱ የጥርቅም ድቀቶችና በግልፍታ የሚፈጥኑ ዝቅጠቶች ናቸው፡፡ በዚያ ላይ ፀጥታ የማስከበር ዕርምጃ መዛል፣ የመንግሥት መፍትሔ ያጣ ዝምታ፣ የፖለቲካኞች መንግሥትን ከመወንጀል ያላለፈ መሐንነት፣ አንድ ላይ ብሶተኛ ማኅበረሰቦች ውስጥ የሚያደርሰው ተገንና ፍትሕ የማጣት ሐዘንና ብግነት አለ፡፡ እንዲህ ያለው የተጠቂነት ስሜት የበኩሉን እልህ፣ ጥላቻና በቀል ያጠራቅማል፡፡ በዚህ ላይ በመደበኛና በማኅበራዊ ሚዲያ የሚበተን እንካ ሰላንቲያና መርዘኛ ‹‹ንቃት›› ሲታከል በቀልና ቁርሾ ይፈላለጉና ደም ይቀባበላሉ፡፡ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ያስተዋልናቸው ሰው ይህን ያህል በሰው ላይ ይጨክናል!›› ያሰኙ ግፎች የዚህ ዓይነት ዝቅጠት ውጤት ናቸው፡፡

ሕወሓት ከአማራ ክልልና ከፌዴራል መንግሥት ጋር የገባው ቅራኔ ክረቱ አድጎ፣ የጥቅምት 24ቱ (2013) ግዙፍ ‹‹ጦርነት›› ሲከፈት ደግሞ ብቻውን ሌላ ታሪክ ይሆናል፡፡ ሕወሓት ባካሄዳቸው ወረራዎች በጥላቻና በቂም የታጠቡ ሰዎች ብዙ ዘግናኝ ነውሮች ሲሠሩ እንዳየን ሁሉ፣ አገር ለማዳን በተካሄደው አጠቃላይ እንቅስቃሴም ሕዝቦች ከባለ አገር እስከ ልሂቅና ወጣት አንድ ላይ ተምመው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እጅና ጓንት ሲሆኑ ለማየት ቻልን፡፡ መናቆር ተጠግኖ ወጣቶች በአገር ፍቅር ሲፈነቀሉ፣ ፆታ ሳይለዩ ለአገራቸው ለመሰዋት ሲገማሸሩ ታይቷል፡፡ አገር የማዳኑ ርብርብ የፈጠረውን ጥሩ አጋጣሚ፣ ሕዝብ-ወጣቶች-ምሁራን-የፖለቲካ ልሂቃንና መንግሥት የተቀናጁበት የኅብረት ማዕከልና ተዋረድ ለመፍጠር አለመጠቀማችን እየፈጩ ጥሬ የሚሆን ችግር ውስጥ አቆይቶናል፡፡ አገር የማዳኑ ርብርብ ጋብ ባለ ጊዜ የተለመደው ግጭትና የታጠቁ የጫካ ቡድኖች ጥቃት፣ ሕግና ሥርዓት የማስከበር ጉድለት፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ብሽሽቅ፣ የመንግሥት አንደበት ማጣትና የመፍትሔ እጥረት ተመልሶ ይመጣል፡፡ መንጨርጨርና ጥርጠራ ይራቡና በመንግሥትና በሕዝብ መካከል የትምምን ዕጦት ተመልሶ ፀሐይ ይሞቃል፡፡ ከሕወሓት ጋር የነበረው ጦርነት በድርድር ከተደመደመ በኋላ ሰነባብቶ የሆነውም ይኼው ነው፡፡

በፕሪቶሪያው ስምምነት የሰሜኑ ጦርነት ከቆመ በኋላ የእነ ኦነግ ሸኔ ተኳሽነትና ጥቃት ተመልሶ ማግጠጥ፣ አስተማማኝ የፀጥታ ዋስትና ማጣት፣ ከመንግሥት ዝምታ መውደድ ጋር የመንግሥት በአስጠቂነት መጠርጠር እንደገና ተመለሰ፡፡ በዚህ ላይ፣ የሕዝብ ትምምንን ከሚያዳብር ግልጽ አሠራር ይልቅ፣ ደባን ለሚጠረጥር ሐሜት የተመቸ የሽፍንፍን አሠራርና ትክክለኛ ጊዜን ያልጠበቀ ውሳኔና ውሳኔውን የማስፈጸም ሩጫ ተጨመረና በአማራ አካባቢ የፋኖዎችን የጠመንጃ ትግል ወለደ፡፡ የዓብይን መንግሥት በሥውር የአማራ ጠላትነት የሚጠረጥረው አማራ ብሔርተኛ ወጣት፣ ከማኅበራዊ ሚዲያ ጨለምተኛ ፖለቲካ በቀር የሚያምነው ‹‹አንቂ›› የለውም፡፡ ከማኅበራዊ ሚዲያ ውጪ ተገኔ የሚለው ሌላ ፓርቲ የለውም፡፡ ይህ ሳያንስ፣ የሕወሓት ሠራዊት ትጥቅ ባልፈታበት ሁኔታ የልዩ ኃይልና ኢመደበኛ ታጣቂዎች በመከላከያና በፖሊስ ተቋማት ውስጥ ተዘርዘሩ ብሎ ነገር፣ መንግሥትን ይበልጥ የሚያስጠርጥር እንጂ በመንግሥት ላይ ለመተማመን የሚያበቃ አይደለም፡፡ መንግሥትን እንደምን አምኖ! በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለው የአማራ መከራ እያበቃ መምጣቱን የሚያስተማምን ነገር አላየ! የማኅበራዊ ሚዲያ ‹‹ታማኝ አንቂዎቹ››ም የሚነግሩት ይህንኑ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ምን እስኪሆን ይጠብቃል! የጠመንጃ ችግር የለበት! ጠመንጃ ድሮም ለእሱ ብርቁ አይደለም! አሁንም በአገር ጥሪ ዘመቻው ከጠመንጃ ጋር ተገናኝቷል፤ የውጊያ ልምዱን አሟልቶታል፡፡ የተጠቂነት ብሶቱ፣ እልሁና መንጨርጨሩ በዋንጫ ሞልቶ ፈሷል፡፡ ከዚህ በላይ የትጥቅ ታጋይ ለመሆን ምን አንሶት!! እንዲያውም ሌሎቹን የሚያስንቅ መሆን የሚችል ነው!

ሕወሓት ኢትዮጵያን ለመበተን ገሃነም ድረስ ለመሄድ ቀውሶ የነበረ ነው፡፡ ፋኖዎች ደግሞ ከጠመንጃ ጋር የኢትዮጵያን ባንዲራና የኢትዮጵያን ፍቅር ማውለብለብ የሚችሉ ናቸው፡፡ በቤኒሻንጉልና በጋምቤላ የታዩት ባለጠመንጆች ያልበደላቸውን ‹‹መጤ›› በጥላቻ ብቻ ለመግደል ያላቅማሙ ናቸው፡፡ ኦነግ ሸኔ የሚባለውስ በኦሮሚያ ሥልጣን ላይ መውጣት የሚገባኝ ኦሮሞ እኔ ነኝ ከማለትና ኦሮሚያን ለኦሮሞ ብቻ ከማለት በቀር ንፁኃንን (ለአረጋውያንና ለሕፃናት እንኳ ሳይሳሳ) የሚገድለው ሌላ ምን ምክንያት ኖሮት! ከእኔ ሥልጣን ውጪ ኦሮሞ የልማት ዕድል ለምን በራለት ብሎና ኦሮሞ ያልሆነን አያሳየኝ ብሎ ሰላም መበጥበጥ የፖለቲካ ሕመም እንጂ ብሶት አይደለም! የአማራ ፋኖዎች ግን አማራ በተባሉ ላይ ትኩስ በትኩስ ከሚፈጸም ጥቃት የሚፈልቅ ብሶትና እልህ የታቀፉ!! እናም ፋኖዎች ወደ ትጥቅ ለመሄድ ከዚህ በላይ ተገቢ ምን ምክንያት ይፈልጋሉ!? እናም ‹‹ፕሮግራም/ዓላማ›› የሚባል ቅሌን ጨርቄን ሳያስፈልጋቸው ብሶትን በአፈሳ ይዘው ‹‹ኧረ ጎራ››ውን ከጠመንጃ ጋር አንግበው፣ የማኅበራዊ ሚዲያን አመራር ይዘው በየአካበቢያቸው የታጠቁ ተኳሾች ሆኑ፡፡ የማኅበራዊ ሚዲያ ኃላፊነት የጎደለው ስድድብ ፖለቲካ ሆኖ የዓብይ መንግሥትንና የመከላከያ ሠራዊትን ‹‹ባህርይ›› መግለጫ ሆነ፡፡ የሕወሓት የፕሮፓጋንዳና የሥነ ልቦና ውጊያ ሥልቶችም ተቀዱና ከኢትዮጵያ ባንዲራና ከኢትዮጵያ ድፍን ፍቅር ጋር ተጎዳኙ፡፡

በሕወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን ባለ ጋዜጣ ሆኖ ምኒልካዊነትንና የአማራ ብሔርተኛነትን ሊያዳቅል ይለፋ የነበረ፣ የዓብይ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ከመጣ ወዲህም ነጋድራስ የሚባል ድርጅቱን ከፋኖ ጋር ሊያያይዝ ይሞክር የነበርና በአዲስ አበባ ‹‹ቀበሌ 24›› ተከስቶ የነበረን ከእምነትና ከመሬት ጋር የተገናኘ ግጭትን የፖለቲካ መጠቀሚያ ሊያደርግ የሞከረ ሰው፣ ድምፁን አጥፍቶ ቆይቶ ካገነገኑ ፋኖዎች የቻለውን ያህል በሥሩ አደረገ፡፡ ‹‹ፖለቲካ››ንና እምነትን አንድ ላይ አሸራረበናም ቤተስኪያን ውስጥ ምሽግ ሠርቶ ተገኘ፡፡ በእሱ ቤት ሃማኖትና ፖለቲካን በህቡዕ አጋብቶ በአጭር ጊዜ አገር ምድር ድጋፍ ይዞ፣ በአጭር ጊዜ የአዲስ አበባ ቤተ መንግሥትን ሊነቀንቅ!! ፖለቲካንና ሃይማኖትን ያጋባ እንዲህ ያለ እንቅስቃሴን ብዙ ሃይማኖቶች ባሉበት አገር መቃጣት፣ የሃይማኖት ጦርነት መደገስ መሆኑን የእሱ ጭንጫ አዕምሮ በየት ተረድቶት!! እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባለች አገር አንድ ሃይማኖት በሠፈነበትም አገር ፖለቲካን ሃይማኖተኛ ማድረግ መዘዙ የማያልቅ መሆኑን ከታሪክ መቼ ተምሮ!!

ይኼኛው ጋላቢ ይህንን አደገኛ የፖለቲካ አላዋቂነት የተወሰኑት ፋኖዎች ላይ ሲለጥፍ፣ ሌላው ጋላቢ ደግሞ አማራን ያስጠቃው ብሔርተኛው ሥርዓት — ብሔርተኛው ሕገ መንግሥት — እስኪቀየር መታገል የሚል ዓላማ በጥቅሉ አስታጥቋቸዋል፡፡ ኑ እናሻሽል ተብለው እስኪጠሩ ድረስ ጫካ ይቆያሉ? ወይስ እነሱ የወደዱት ሕገ መንግሥት ‹‹ጥርት›› ብሎ መሟላቱን እስኪያረጋገጡ ከጫካ አይነቃነቁም? ወይስ በእነ ‹‹አሳምነው ብርጌድ›› መባዛት የጦርነት ገድላቸው ሰምሮ ኢትዮጵያን ነፃ አውጥተው በእነሱ አመራር ሥር የነፃነት ሕገ መንግሥቱ ይረቀቃል? ‹‹የምንዋጋው ለጥገና ለውጥ አይደለም›› ሲባል ይህንን ማለት ይሆን? ይህ ገና ተለይቶ አልታወቀም፡፡

የትግላቸውን ታክቲክ በማሳደግ ጮሌ አስተዋፅኦ ያደረገላቸው ምርጥ አማካሪ ግን ‹‹ከድርድር በፊት መከላከያ የአማራ ክልልን ለቆ ይውጣ›› የሚል ቅድመ ሁኔታን ያስታጠቃቸው ሰው ነው፡፡ የዚህች ቅድመ ሁኔታ ውስጠ ወይራ — ‹‹የጥሞና ጊዜ›› ወይም ‹‹ያለ ቅድመ ሁኔታ የተናጠል ተኩስ ማቆም መንግሥት አድርጓል›› የምትባለዋን ነገር ለእኛም አቃምሱን — ማለትም የአማራ ክልል ሥልጣንን በቅድሚያ አስረክቡን ነው፡፡ ይህ ከተሳካ ምክር አዋቂው ጋላቢ ከእነ ቢጤዎቹ መጥቶ በፋኖዎች ስም የአማራን ሕዝብ ሊፈናጠጥ መሆኑ ነው፡፡ ፖለቲካ፣ በኢትዮጵያ የትጥቅ ትግል ታሪክ እንዲህ ያለ የ‹‹9ኛ ሺሕ›› ቧልት ሆኗል፡፡ በሌላ አነጋገር ፖለቲካ ጥይት የሚተኩስ አስከሬን ሆኗል፡፡

ዛሬ ባለንበት የአስከሬን ጊዜ ቃታ መሳቡ በቶሎ የሚያቆምም አልመስል ብሏል፡፡ የፋኖ ጫካ መግባትና መሟሟቅ የኦነግ ሸኔ ደጋፊና ተመልማዮችን መበራከት እያገዘ ይገኛል፡፡ ‹‹ሸኔ›› በሦስተኛ አገር ለድርድር ሲቀርብ፣ ፋኖ ‹‹በምሕረት ግባ›› ከመባል አለማለፉ ክብረ ነክ ሆኖ፣ በሦስተኛ አገር ካልተደራደርኩማ በሚል ስሜት ውጊያ የሚያጧጡፍ ነዳጅ ሆኖትም ነበር፡፡ የዓብይ መንግሥትና እነዚህ ቡድኖች ቀጥታ ለሕዝብ የሚሠራጭ የድርድር ሒደት ቢያካሄዱና የሚጠይቋቸውን ጥያቄዎች ብንሰማቸው ብዬ እመኝና ለሕዝብ ብለው ከሆነም የሚታገሉት፣ የሕዝብን የተረጋጋ ኑሮ ማደፈራረስ እንደምን ለሕዝብ ጥቅም መንገብገብ እንደሆነ ብንጠይቃቸው፣ እነሱም በአብዛኛው በኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ ያለው ጉጉት፣ እንደ ሶማሌ ክልል ሕዝብ፣ መሪና ሕዝብ አንድ ልብ ሆኖና ሰላምን ተጎናፅፎ ልማት ውስጥ ከመሰማራት ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ቢያውቁ ብዬ እጓጓለሁ፡፡

ወይስ ኦሮሚያና አማራ ሰላምን እየናፈቁ ሶማሌ በአያሌ ሰላም በልማት የሚጣደፈው የዓብይ መንግሥት ለሶማሌ ‹‹ክልል›› እያደላ ይሆን? ይህንን ጥያቄ የሰነዘርኩት የነገሮችን የወለል ገጽታ እያዩ መፍረድ ምን ያህል ሊያሳስት እንደሚችል እንድናስተውል ብዬ ነው፡፡ የዓብይን መንግሥት ‹‹በኦሮሞ ላይ ጥቃት የሚፈጽም ነው/አማራን የሚያጠቃ ነው›› ብለው የሚወነጅሉ ሰዎችንና ይህንን የማንቀበል ሰዎችን የሚለያየን ነገሮችን በላይ ገጽታቸው የመፍረድና ከላይ ገጽታ አልፎ የማስተዋል ልዩነት ነው፡፡ የዓብይ መንግሥት ‹‹የአማራንም ሆነ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ጥቃት ማስቆም ስላልቻለ የአማራም ሆነ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፀር ነው›› ብሎ መደምደም፣ የዓብይ አህመድ አማካሪ የሆነው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ሸጧል/በዓብይ መንግሥት ውስጥ የተሾሙ አማራ ብሔርተኞች ፀረ-አማራ ሆነዋል ብሎ ከመወንጀል ጋር በስህተተኛነት ባህርዩ ተመሳሳይ ነው፡፡

በበኩሌ በዓብይ መንግሥትም ውስጥ ይሁን በብልፅግና ፓርቲ ውስጥ በብሔር የሚያስቡና የሚጠቃቀሙ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ይኼ መንግሥት እንደ መንግሥት ተቋም ለኢትዮጵያ እንጂ ለብሔር የቆመ እንዳልሆነም በእርግጠኝነት አውቃለሁ፡፡ የጥቃቱ ማብቂያ ማጣት በራሱ ለጥርጥሬ መመቸቱ ሳያንስ፣ ‹‹ለእከሌ ብሔር የሚያደላ›› ለሚል ሐሜት ከሚያጋልጥ ጥፋትም፣ ይኼው መንግሥት ንፁህ እንዳልሆነም አውቃለሁ፡፡ ለምሳሌ ብሔርተኛ አመጣሽ አደጋ አዲስ አበባ ላይ እንዳይደርስ በመፍራት አሮሚያ ወሰን ውስጥ በፍተሻ ማገት/ማጉላላት አንዱ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ጥፋት ፖለቲካዊ መዘዝ አለውና ብዙ ሰው አስከፍቷል፣ ብዙ ሰውም በቀላሉ የፌዴራሉን መንግሥት ‹‹በአማራ ላይ የመጣ›› ብሎ እንዲያስብ ጠቅሟል፡፡ መንግሥት በፀጥታ አጠባበቁ እጅግ በተሻለ ጥንቃቄ ሊሠራ ይገባውም እንደነበር አያከራክርም፡፡ ከአማሮች በኩል የፀጥታ አደፍራሽነት ሊከሰት ይችላል የሚል ፍርኃት የመጣውም፣ ከአማራ ብሔርተኛ ተኳሽነት መምጣት ጋር እንደሆነም አያከራክርም፡፡ የትግራይ ተኳሽነት በመንግሥት ላይ ይካሄድ በነበረበት ጊዜም የአደጋ ጣይነት ጥርጣሬ በትግራዊ ላይ ሁሉ አንዣቦ ነበር፡፡ የኦነግ ሸኔ አሸባሪ ጥቃትም፣ ወደ አዲስ አበባ የሚገባ ኦሮሞን ሁሉ አስጠርጥሮ አስፈትሿል፡፡

ኅብረ ብሔራዊ ዝምድናንና አመለካከትን ትቶ ወደ ብሔርተኛነት መኮማተር ዕይታን ያጠባል፡፡ የህሊናን ሚዛናዊነት ያዛባል፡፡ የሁሉን መከራ ከማየትና ስለሁሉም ወገን መከራ ከመብከንከን ያውካል፡፡ ተቆርቋሪነትን ወገን መራጭ/አድልኦኛ ያደርጋል፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ ባለው ሰላም ማጣት የሚጎዳው ኦሮሞ ብቻ የሆነ ይመስል፣ ያለውን መንግሥት የሚቃረኑ የኦሮሞ ብሔርተኞች የኦሮሞ ነገር ብቻ ነው የሚሸቀሽቃቸው፡፡ ‹‹ዛሬ የሚገደለውና የሚታሰረው ኦሮሞ ከበፊቱ ጊዜ የበለጠ ነው›› ከሚል መንደርደሪያ ተነስተውም፣ በኦሮሚያ ውስጥ ለኦሮሞ የቆመ መንግሥት የለም እስከ ማለት ድረስ ይስፈነጠራሉ፡፡ የአማራ ብሔርተኞችም ከሁሉ ገዝፎ የሚሸቀሽቃቸው የአማራ ሲዖል ነው፡፡ የትግራዩም ብሔርተኛ፣ ሌላውም ብሔርተኛ እንደዚያው ነው፡፡

ሁሉንም የአገር ልጆች ወገኖቹ አድርጎ የሚያይ ኢትዮጵያዊ መንሸቅሸቅ ያለበት በሁሉም ጉዳት ነው፡፡ ከሰውነት ዳር ወጥቶ አይገድሉ አገዳደል መግደል የሚያሰቅቅ የጉዳት ውጤት ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ጭካኔ የንፁኃን መገደልም የሚያንገበግብ ጉዳት ነው፡፡ የንፁኃን ጥቃት ጉዳታችን ነውና በተለያየ መልክ ለእነሱ መድረስ ኃላፊነታችን ነው፡፡ ወደ ሰው አራጅነት የወረዱ ብሔርተኞች ያስፈራሉ፡፡ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ኦሮሞንና አማራን በፌዴራሉ መንግሥት ላይ ለማስነሳት ለሚለፋ ፖለቲካ መሣሪያ ሆነው፣ የትኛውንም ጭካኔ ለመፈጸም የተመለመሉና የተሰማሩ አራጆች ያስፈራሉ፡፡ ምክንያቱም ነገም ስለሚገድሉና አገርን ወደ ሲዖልነት ስለሚወስዱ፡፡ የዚህ ዓይነት ዝቅጠት — የዚህ ዓይነት አይሞቱ ሞት — ሰዋዊ ማንነትን ሳያጡ የግድያ ተጠቂ ከመሆን ይበልጥ መንፈስን ያሸማቅቃል፡፡ ወደ ጥፋት መሣሪያነት የወረዱ (ርኅራኄያቸውንና አዕምሯቸውን የተነጠቁ) ወጣቶች መበራከት ብሔራቸው ከየትም ይሁን ከየት፣ ለሁላችንም የሞት ሞት ነው፡፡ ለእነዚህም ወገኖች በመድኅንነት መድረስም ኃላፊነታችን ነው፡፡ የመከራችንን ምንጭ የምንረዳውና የምናደርቀው ይህንን ትልቁን ጉዳችንን ለይተን ስናውቅ ነው፡፡

የሰብዕና ዝቅጠት ከብዙ አቅጣጫ ሊመጣ ይችላል፡፡ ብሔርተኛነት በጥላቻና በበቀል ከመመዝመዝ በጊዜ መመለሻ ካላገኘ፣ ሄዶ ሄዶ ተግባሩ ሁሉ በጥላቻና በጭካኔ ወደሚታዘዝ ጭፍን በቀለኝነት መውረዱ አይቀርም፡፡ በአገራችን የሆነውም ይኼ ነው፡፡ ብሔርተኛነት አመጣሽ በሆነ ጭካኔ የሚፈጸም ጥቃትን ለመቃወም ብሔርተኛ ተኳሽነት ውስጥ መግባት፣ የጥቃት ምንጭ ወደ ሆነው ወጥመድ መግባት ነው፡፡ በዚህ ወጥመድ ውስጥ የገባ ትግል ደግሞ እየተንጨረጨረ በሚያድግ የጥላቻ/የበቀል ስሜት መታኘኩና ሌሎቹ ብሔርተኞች በተንከባለሉበት የዝቅጠት ቁልቁለት መንከባለሉ አይቀርም፡፡ የመከላከያ ሠራዊትን ‹‹የአማራ ጠላት! ዘረኛ ወራሪ! የአንድ ቡድን ሠራዊት!›› ብሎ ማለትም የዝቅጠት መጀማመሪያ ነው፡፡ አማራን የሚወክለው የእኔ ትግል ብቻ ነው፣ የብልፅግና አማሮች አማራን የካዱ ናቸው/የእኔን ትግል የሚቃረን የአማራ ጠላት ነው ብሎ መግደል የጀመረ ትግል፣ ጥላቻው ሲፋፋ በጭፍን ንፁኃንን እንዳይገድል ምን ሊያግደው!? በየጥጋጥጉ የፋኖ ብሔርተኝነት ከወሮበልነት ጋር ተጋብቶ በዕገታ መዝረፍንና ‹እጅ ወደ ላይ› ብሎ መቀማትን ተያይዞትስ የለ!! የአማራ መንግሥታዊ ተቋማትን እየዘረፉና እያወደሙስ እንደምን ነው አማራን መጥቀም የሚቻለው!? አማራ ከፋኖ ጋር እንዲገጥም/አማራ ባለሀብት ፋኖን እንዲረዳ ጥሪ ማቅረብ፣ አማሮችን ለመግፋት የዋለውን ‹‹ብሔር ለብሔሩ›› የሚል አስተሳሰብን እንደምን ለመታገል ይጠቅማል? ጥሪያችሁ እኮ አገርህ አማራ ነው/ሌላው አገርህ አይደለም ብሎ የሚያውጅ ነው! የጥሪያችሁ መልዕክት ከዚህም ይከፋል፡፡ ‹‹በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ የምትገኙ አማሮች የፋኖን ትግል ተቀላቀሉ!›› ብሎ ጥሪ፣ ኢትዮጵያ አገራችሁ አይደለችም/ኢትዮጵያን ትታችሁ ወደ እኛ ኑ ብሎ ከመለፈፍ (ኢትዮጵያን የማፍረስ ጥሪ ከመጥራት) በምን ያንሳል!? የዞረበት ትግል ማለት እንዲህ ነው!!

የአማራ ሕዝብ ሆይ! ለጊዜው እዚያም እዚያም ድጋፍና አጀብ የበዛለት የብሶት ትግል ውሎ አድሮ በሚያበራክተውና በሚያንሰራፋው ችግር መድረሻ ማሳጣቱና ደም ዕንባ ማስለቀሱ አይቀርም፡፡ የአማራ ሕዝብና አዛውንቶች በጊዜ ነቅተው ሰላማዊ መፍትሔን ሙጥኝ እንዲሉ፣ ወጣቶቹ ፋኖዎችም ጅራትና ቀንዱ የማይታወቅ ፖለቲካ ነደፋቸውን ትተው፣ ለብሶት ያበቋቸውን ጥያቄዎች በመያዝ ወደ ጠረጴዛ እንዲመጡ እማፀናለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ