Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር ገፍቶ የማስወጣት ትግል ከጥንት ጀምሮ ይመጣ የነበረው ከዓባይ ተጋሪ አገሮች ነበር›› ዳር እስከዳር ታዬ (ዶ/ር)፣ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከሰሞኑ ‹‹የሁለቱ ውኃዎች ዓብይ ስትራቴጂ›› የተባለ ጥናታዊ መጽሐፍ ይፋ አድርጓል፡፡ ሁለቱ ውኃዎች እነማን ናቸው ብቻ ሳይሆን፣ መሪ ስትራቴጂክ ዕቅድ ማዘጋጀቱ ለምን እንዳስፈለገ የተቋሙ ባልደረባና ተመራማሪ ዳር እስከዳር ታዬ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡ ተመራማሪው ከዚህ ቀደም በእስያ ፓስፊክ ጉዳዮች የሠሩ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ በአሜሪካና በአውሮፓ ጉዳዮች መሪ ተመራማሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ስለኢትዮጵያ የሥጋት ሁኔታዎች፣ እንዲሁም ስለሶማሌላንድ ስምምነት በርካታ ሐሳቦችን ያነሱበት ዮናስ አማረ ከእሳቸው ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

ሪፖርተር፡- ‹‹የሁለቱ ውኃዎች መሪ ስትራቴጂክ ዕቅድ›› በመጽሐፍ አሳትማችኋል፡፡ ሁለቱ ውኃዎች እነማን ናቸው? መጽሐፉ በዋናነት የሚያጠነጥንባቸው ጉዳዮችስ ምንድናቸው?

ዳር እስከዳር (ዶ/ር)፡- የሁለቱ ውኃዎች ዓብይ ስትራቴጂ ብለን ያዘጋጀነው መጽሐፍ ብዙ ጉዳዮችን ይዟል፡፡ እኛ እንደ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ሐሳብ አመንጪ ተቋምነታችን በተደጋጋሚ ከውጭ የሚመጡ ሥጋቶቻችን ምንድን ናቸው፣ እነሱን መፍታት ያለብን እንዴት አድርገን ነው የሚሉ ጥያቄዎችን መሠረት በማድረግ ነው የተነሳነው፡፡ እሱን ስናይ ደግሞ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ችግሮች ከውኃ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ወደኋላ ለብዙ መቶ ዓመታት ተመልሰን ብንገመግም፣ የኢትዮጵያ ችግሮች ከእነዚህ ሁለት የውኃ አካላት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በሰሜን ምዕራብ በኩል ዓባይ አለ፣ በሰሜን ምሥራቅ በኩል ደግሞ ቀይ ባህር አለ፡፡ እነዚህን ነው የስትራቴጂክ ዕቅዱ ዋና ማጠንጠኛ ውኃዎች ያልናቸው፡፡ ቀይ ባህር ወደኋላ ብንሄድ በየትኛውም ዘመን የዓለም ልዕለ ኃያላን አገሮች ዓይን ማረፊያ የሆነና እስካሁንም ሆኖ የቀጠለ ነው፡፡ ከሮማዊያን ጀምሮ፣ ኦቶማን ቱርኮች፣ አሜሪካም ሆኑ ቻይና ፍላጎት የሚያሳዩበት ስትራቴጂካዊ የውኃ አካል ነው፡፡ ለእኛ ደግሞ በተለይ የዓባይን ምንጭ ለመቆጣጠር የሚፈልግ ኃይል በዚህ መስመር ሲመጣብን ቆይቷል፡፡ የዓባይ ውኃን በተመለከተ እኛ ውኃውን አመንጪ የራስጌ አገር ነን፡፡ ግብፅ ደግሞ ውኃውን ተጠቃሚ የግርጌ አገር ናት፡፡ በተፈጥሮ ወይም በጂኦግራፊ አቀማመጥ ውኃው ከኢትዮጵያ ወደ ግብፅ የሚፈስ በመሆኑ፣ ውኃውን ኢትዮጵያ ከተጠቀመች እኛ እንጎዳለን የሚል ጥርጣሬና ሥጋት ሁሌም አለ፡፡ በዚህ ምክንያት እኛ ውኃውን ከተጠቀምን እነሱ ይጎዳሉ የሚለው ግምት ለዘመናት ሰፍኖ ቆይቷል፡፡ በዚህ የተነሳ ለዘመናት ብዙ ችግሮች ሲመጡብን ነበር፡፡

ለዚህ መፍትሔ ለመስጠት ከፍ ያለ ዕይታ ይፈልጋል፡፡ ጉዳዩ ትልቅ ስትራቴጂ ይጠይቃል፡፡ ትልቅ ወይም ዓብይ ስትራቴጂ ስንል ደግሞ በአንድ መሥሪያ ቤት ወይም ተቋም ብቻ የሚፈታ ችግር ሳይሆን የተለያዩ ተቋማትን በማስተባበር፣ የተለያዩ የሀብት ምንጮችን በማሰባሰብ የሚከናወን ጉዳይ መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡ ሁሉንም ወገን በማስተባበር ነው ይህን ጉዳይ በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው፡፡ ሁለቱ ውኃዎች ዓባይና ቀይ ባህር ለኢትዮጵያ ወሳኝ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ እስከ ዛሬ ባለው ብቻ ሳይሆን የወደፊቱ መፃኢ የኢትዮጵያ ሁኔታ ከእነዚህ ውኃዎች ተነጥሎ የሚታይ አለመሆኑን መገመት ይቻላል፡፡ ማደግ ካለብን በዋናነት ውኃ መጠቀም ይኖርብናል፡፡ ዕድገት በመሠረታዊነት ውኃና የኃይል ምንጭ ይፈልጋል፡፡ ውኃና ኢነርጂ ለማግኘት ስናስብ ደግሞ ዓባይ ቀድሞ ይመጣል፡፡ ዓባይ ከውኃ ምንጭነቱ ባለፈ ኢነርጂም ይሰጠናል፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ወንዞች ያሏት ቢሆንም፣ በውኃ ፍሰትም ሆነ በኢነርጂ ማመንጨት አቅሙ ዓባይን የሚያክል የለም፡፡ ኢትዮጵያ ማደግ ካለባት የሁለቱም ምንጭ የሆነውን ዓባይን በደንብ መጠቀም አለባት፡፡

ኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው ዕድገትን ለማስመዝገብ ለመልማት ወሳኝ በሆኑት ሁለቱ የዓባይና የቀይ ባህር ውኃዎች ላይ ትኩረት አድርጋ መሥራት ይገባታል በሚል መነሻ ነው ይህ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ የተዘጋጀው፡፡ የኢትዮጵያን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታትም በእነዚህ ላይ አተኩሮ መሥራት ወደ መፍትሔው ለመጠጋት ያግዛል ተብሎ ነው የተዘጋጀው፡፡

ሪፖርተር፡- ዓባይ ኢትዮጵያውያን እጅ ላይ ያለ፣ ለብቻቸው መቆጣጠርና መወሰን ሚችሉበት ሀብት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ቀይ ባህር ግን ብዙ የዓለም ኃያላን አገሮች የሚያንዣብቡበት፣ ተገዳዳሪ የሆኑ ኃይሎች የተሠለፉበትና ፉክክር የበዛበት ዓለም አቀፍ የውኃ አካል ነው፡፡ በቀይ ባህር ጉዳይ የጂኦ ፖለቲካው ፍጥጫና የራስን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚደረገው ፉክክሩ ከፍተኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ወደብ አልባ አገር ነች፡፡ ከዚህ አኳያ ለሁለቱም ውኃዎች በእኩል ደረጃ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ማውጣቱ ትንሽ አይከብድም?

ዳር እስከዳር (ዶ/ር)፡- በእርግጥ ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ እኛ የቀይ ባህር ተጋሪ አገር አይደለንም፡፡ ግን ከቀይ ባህር ተነጥለን መኖር የምንችል አገር አይደለንም፡፡ ቀይ ባህርም በለው፣ ባብኤል መንዶብ ወይም የኤደን ባህረ ሰላጤ ለእኛ በጣም ቅርብ የሆኑ አካባቢዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ የውኃ አካላት ተነጥለን መኖር አንችልም፡፡ ሌላውን ትተን የወጪና የገቢ ንግዳችንን እንኳን ብናይ ከ90 በመቶ በላይ በዚሁ መስመር የሚደረግ ነው፡፡ ስለዚህ ምንም ነገር በዚያ ቢፈጠር ተፅዕኖው በእኛ ላይ ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ በጂቡቲ ወደብ ላይ የሆነ ነገር ቢፈጠር በሚቀጥሉት ቀናት እዚህ መርካቶ የሸቀጦች ዋጋ ላይ ሊኖረው የሚችለው ልዩነት ከፍተኛ ነው፡፡ የቀይ ባህር ተጋሪ አይደለንም፣ ነገር ግን ይህ ባህር ለእኛ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ወደ እዚያ ልንሄድ የምንችልበትን መንገድ በሙሉ ማፈላለግ አለብን፡፡

አገሮች ከባህር ጋር ለመገናኘት ብዙ መንገዶችን ይፈልጋሉ፡፡ እኛ ወደብ አልባ አገር ብንሆንም፣ ጥሩነቱ ግን ሙሉ ለሙሉ አማራጭ የሌለን የታነቅን አገር አይደለንም፡፡ ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ እንደተከበበችው ስዋዚላንድ ዓይነት አገር አይደለንም፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፡፡ ጎረቤቶቻችን ቢደማመሩ የሚበልጥ የቆዳ ስፋት አለን፣ ወደ 120 ሚሊዮን ሕዝብም ያለን ነን፡፡ ከዚያ በተጨማሪም ከባህር ጋር ልንገናኝባቸው የምንችልባቸው ሦስትና አራት አገሮች በዙሪያችን አሉ፡፡ ከእነዚህ አገሮች ጋር በመደራደር፣ በሰጥቶ መቀበል፣ በተለያዩ መንገዶች ወደ ባህር የምንደርስባቸውን አማራጮች ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ጠንካራ ፉክክር የሚጠይቅ ነው፡፡ ሆኖም በቅጡ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ጥናቱን ስንሠራም ይህን በደንብ አስበነዋል፡፡ በዙሪያችን ያሉት አገሮች ሉዓላዊ ናቸው፡፡ በቀይ ባህር እንኳን የባህር በር ይኑረን ብለን ቀርቶ በቀይ ባህር ፎረም ውስጥ እንሳተፍ ስንል ተቃውሞ የተነሳው ከማን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ እዚሁ ከጎረቤቶቻችን ነበር ቀድሞ ተቃውሞ የተሰማው፡፡ ከዚህ አንፃር ጉዳዩ አስቸጋሪና ፈታኝ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ሆኖም ጨርሶ ደግሞ ችላ የምንለው አይደለም፡፡ ዛሬ እንለፈው ብለን ዝም ብንል ጫናው በየቀኑ እየጨመረ እንደሚሄድ ማሰብ አለብን፡፡ ስለዚህ አሉ የምንላቸውን አማራጮች መፈለግ የተሻለ ነው ብለን ነው የምናምነው፡፡

ሪፖርተር፡- የባህር በር ጉዳይም ይሁን ሌላ ብሔራዊ አጀንዳ ሲታሰብ ጥናቶችን፣ ዕቅዶችንና ስትራቴጂዎችን ቀድሞ ማውጣት አስፈላጊ ነው ይባላል፡፡ ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገውን ስምምነት በድንገት ‹‹ሰበር ዜና›› ከማድረግ ከዚያ ቀደም ብሎ ስትራቴጂውን ማውጣት አስፈላጊ አልነበረም?

ዳር እስከዳር (ዶ/ር)፡- እሱ ላይ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ ሆኖም ይህን ለመመለስ አንድ ምሳሌ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2011 ጃንዋሪ ነበር የዓረብ አብዮት የተነሳው፡፡ እኛ ግን ታላቁ ህዳሴ ግድብን የጀመርነው ከሁለት ወራት በኋላ እ.ኤ.አ. በማርች 2011 ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ሁለቱን አገናኝተው ኢትዮጵያ የግብፅን መዳከም ዓይታ ግድቡን ጀመረች በሚል በዓረቡ ዓለም ይወራል፡፡ ይህ ግን ትክክል አይደለም፡፡ እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 2010 የዓባይ ተፋሰስ አገሮች የትብብር ማዕቀፍ (ኮመን ፍሬምወርክ አግሪመንት) የተባለው ስምምነት ተፈርሞ ነበር፡፡ ይህ የሚያሳየው መንግሥት የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ቀድሞ ሲሠራ እንደነበር ነው፡፡ የሕግ ድጋፍ ለማግኘት ሲጥር ነበር፡፡ የፕሮጀክት ጥናትም ሲያደርግ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የግድቡ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ከመጣሉ በፊት ይህን ዓይነት ፕሮጀክት ሊሠራ ነው ተብሎ አልተነገረም ነበር፡፡

አሁንም ተመሳሳይ ነገር ነው የሆነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድንገት ተነስተው የባህር በር አላሉም፡፡ ኃላፊነቱ ለእኛ ተሰጥቶን ቀድመን ጥናት ስንሠራ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ በእኛ መሥሪያ ቤት ሁለት ዓይነት የጥናት አሠራር ነው ያለው፡፡ እኛ እንደ ተመራማሪ ለኢትዮጵያ ፈተና ናቸው መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል በምንላቸው ጉዳዮች ላይ በራስ ተነሳሽነት ጥናት እንሠራለን፡፡ በተመሳሳይ ደግሞ በዚህ ጉዳይ ላይ መፍትሔ ብታፈላልጉ ተብሎ ከመንግሥት በሚመጣ ጥያቄ ጥናት የምንሠራበት ሁኔታም አለ፡፡ የአሁኑን ጥናት በጦርነቱ ጊዜ ነበር ስንሠራው የነበረው፡፡ ከፕሪቶሪያ ስምምነት በፊት ጥናቱን ጨርሰናል፡፡ ተቋማችን ብዙ ዓይነት ጥናቶችን ይሠራል፡፡ ሆኖም የስትራቴጂ ተቋም በመሆኑ ሁሉም የሚሠራቸው ጥናቶች ለሕዝብ ይፋ ይሆናሉ ማለት አንችልም፡፡ መንግሥት ሲናገረው ነው ወይ አጀንዳ አድርጋችሁ ያመጣችሁት? እናንተ ለምን ቀድማችሁ አላጠናችሁም? የሚል ጥያቄን እንሰማለን፡፡ ግን ደግሞ የህዳሴ ግድብ ሲሠራ እንደነበረው ሁሉ በዚህ ጉዳይ ማጥናት ከጀመርን ቆይተናል፡፡

የባህር በሩ ጉዳይ በኅዳር ወር ነበር አጀንዳ የሆነው፡፡ በኅዳር ወር አጀንዳ የሆነ ጉዳይን በዚህ በአጭር ጊዜ አጥንተን በየካቲት በዚህ ደረጃ በመጽሐፍ ልናሳትም አንችልም፡፡ በዚህ ሁኔታ የሕግ፣ የታሪክ፣ የጂኦ ፖለቲካ ትንታኔ የያዘ መጽሐፍ በዚህ አጭር ጊዜ ማሳተም ይቻላል ብሎ የሚያስብ ሰው አለ ብዬ አልገምትም፡፡ ጉዳዩ ቀድሞ ሲሠራ የነበረ ነው፡፡ ሆኖም ውሳኔ የሚሰጡ አካላት አሉና በዚህ ቀን ይውጣ ብለው ሲወስኑ ጊዜውን ጠብቆ የወጣ ነው፡፡ በየትም አገር እንደተለመደው መረጃ ለሕዝብ ይፋ ሳይሆን የሚቆይበት ጊዜ እንዳለ ሁሉ፣ ለሕዝብ ይፋ የሚደረግበት ራሱን የቻለ አሠራር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ውኃን የተመለከተ ስትራቴጂ ከዚህ ቀደም የለም ነበር ይባላል፡፡ ይህ ምን ያህል እውነትነት ያለው ነው?  

ዳር እስከዳር (ዶ/ር)፡– የውኃ ልማት ስትራቴጂ ተብሎ በዚህ ደረጃ የተዘጋጀ ነበር ብዬ አላስብም፡፡ ሆኖም የተፋሰስ ልማቶችን የተመለከቱ ዕቅዶች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ በዓባይ ተፋሰስ ላይ የሆነ ዓይነት ፕሮጀክት መገንባትን የተመለከቱ ሐሳቦች ነበሩ፡፡ በዚህ ቦታ ላይ ግድብ፣ በዚህ ቦታ ላይ መስኖ የሚሉ የፕሮጀክት ሐሳቦች ነበሩ፡፡ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ እንግሊዞቹ ሳይቀር ጣናን የመጠቀም ዕቅድ ነበራቸው፡፡ ከምኒልክ ዘመን ጀምሮ የቆዩ የፕሮጀክት ሐሳቦች ሲቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ አንድ ጉዳይ የፖለቲካ ትኩረት የሚሻበት የራሱ ወቅት አለ፡፡ ውኃን በተመለከተ ወደ ፖለቲካ አጀንዳነት በማምጣት ረገድ መጽሐፋችን ላይ እንደጠቀስነውም የአሁኑ የመጀመሪያው ነው፡፡

በአንድ መሥሪያ ቤት ወይም በተወሰኑ ተቋማት ብቻ በፕሮጀክት መልክ ቀርፀህ ልታስኬደው ትችላለህ፡፡  ሆኖም ግን ዓባይን የመሰለ የውኃ ሀብት ጉዳይ በዚህ መልክ ማስኬድ አይቻልም፡፡ በአጠቃላይ የእኛን የውኃ ሀብት በዚያ መንገድ ማስኬድ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም እንደ ዓባይ ያሉ የውኃ ሀብቶች በጣም ውስብስብ ከሆኑ የፖለቲካ ጉዳዮች ጋር የተቆራኙ ናቸው፡፡ በታችኞቹና በላይኞቹ የተፋሰሱ አገሮች መካከል ብዙ የፖለቲካ ውዝግብ አለ፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ ትልቅ ስትራቴጂ መቅረፅ ይፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ግድብ ለመገንባት ብታስብ ብር ብቻ ወይም ቴክኒካዊ ዕውቀት ብቻ አይደለም የሚያስፈልግህ፡፡ ብዙ የፖለቲካ ውሳኔዎች፣ የፖለቲካ ስምምነቶች፣ ድጋፍ ማግኘት፣ አገሮችን ማሳመን ሁሉ ይጠይቃል፡፡ ይህ ደግሞ ሰፋ ያለ ስትራቴጂ ማየትን የሚጠይቅ ነው፡፡

እኛ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ከእነዚህ ሁለት ውኃዎች ጋር የተቆራኘ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ የደረስነው ውኃዎቹ በጣም አስፈላጊ ስለሆኑና በአመራርም ደረጃ እንደ ስትራቴጂ ተይዘው በትኩረት መሠራት ስላለባቸው ነው፡፡ ከዚህ በፊት ብዙ ስትራቴጂዎች ሲወጡ እናስታውሳለን፡፡ የትምህርት፣ የከተማ ልማት፣ ወዘተ እየተባለ ብዙ ስትራቴጂዎች ወጥተዋል፡፡ በእነዚያ ስትራቴጂዎች የውኃ ጉዳይ ይህን ያህል ትኩረት አግኝቶ አያውቅም፡፡ ለምሳሌ የግብርና ልማት ስትራቴጂውን በምታይበት ጊዜ ትኩረት የሚሰጠው በዋናነት ለመሬትና ለጉልበት ነው፡፡ እሱን በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር፡፡ ቀይ ባህርን በተመለከተ የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር አንድ በማድረግ የባህር በር እንድታገኝ ያደረገው ከፍተኛ ጥረት ተሳክቶለት ነበር፡፡ ደርግ እሱን ለማስጠበቅ ብዙ ጥረት አደረገ፡፡ ኢሕአዴግ ሲመጣ ግን ሙሉ ለሙሉ አጀንዳው ተዘግቶ ነበር፡፡ እንኳን የፖሊሲ ጉዳይ ሊሆንና ስትራቴጂ ሊዘጋጅለት ቀርቶ አጀንዳው ራሱ በአጀንዳነት እንዳይነሳ ተዘግቶ ነበር፡፡ ስለዚህ አሁን የቀይ ባህርና የዓባይ ውኃን ያስተሳሰረ ስትራቴጂ ይዘን መምጣታችን አዲስ ነገር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቀይ ባህርና ዓባይን ምን አገናኛቸው?

ዳር እስከዳር (ዶ/ር)፡- አንድ በዚህ ጥናት ላይ የተሳተፈ ባልደረባችን ደጋግሞ ዓባይ ራሱ እኮ ወደ ቀይ ባህር ነው የሚፈሰው  ይለን ነበር፡፡ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ዓባይ ወደ ቀይ ባህር ነው የሚፈሰው የሚል አባባል አለ፡፡ ይህ የሁለቱን ትስስር ለማሳየት የሚባል እንጂ ዓባይ ወደ ሜዲትራኒያን እንደሚፈስ የታወቀ ነው፡፡ ለእኛ ሁለቱም ወሳኝ ናቸው፡፡ ዓባይ ለመጠጥ፣ ለግብርናና ለሌላም የሚሆን ንፁህ የውኃ ሀብት ነው፡፡ ከእኛ አልፎ የግርጌ አገሮችን በእጅጉ የሚጠቅም ሀብት ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ይህንን ሀብት መጠቀም እኛም እንፈልጋለን፡፡ ይህን ለማድረግ ስንነሳ ግን ቀድመው ውኃውን የሚጠቀሙ አገሮች ይህን ለመዝጋት ሲሞክሩ ነው የሚታየው፡፡ ይህን ደግሞ የሚያደርጉት ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር እንድትርቅና እንድትነጠል ለማድረግ ነው፡፡

ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር ገፍቶ የማስወጣት ትግል ከጥንት ጀምሮ ይመጣ የነበረው ከዓባይ ተጋሪ አገሮች ነበር፡፡ በአንድም በሌላ መንገድ ድጋፍ እያደረጉና እያስተባበሩ ነው ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር እንድትገፋ ያደረጉት፡፡ በጣም የቅርቡን እንኳን እንደ ምሳሌ ብጠቅስ የኤርትራ ታጣቂዎች ለነፃነት ለሚያደርጉት ትግል ከፍተኛ ድጋፍ ከማን ይደረግላቸው እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ ከቀይ ባህር ኢትዮጵያ እንድትገፋ የማድረጉ አሻጥር ይመጣ የነበረው ከዓባይ ተጋሪ አገሮች ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ወደ ቀይ ባሀር እንመለስ ስንል ከፍተኛ ተቃውሞ በጎረቤቶቻችን ዘንድ እንዲነሳ የሚያደርጉት እነዚሁ የዓባይ የታችኞቹ ተጋሪ አገሮች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሁለቱ ውኃዎች ተያያዥ ናቸው፡፡ ሥጋት በመደቀን ደረጃ ከታየ ሁለቱም ውኃዎች ተመሳሳይ ሥጋት ነው ሲደቅኑብን የኖሩት፡፡ እነሱን ተከትሎ ብዙ ጫናና ሥጋት ሲገጥመን ነው የኖረው፡፡ በታሪክ ካየነው ደግሞ ወደ ቀይ ባህር በተጠጋን ቁጥር የተሻለ አቅም ይኖረናል፡፡ ይህንን የሚያውቁ የዓባይ ተጋሪ አገሮች በአንድም በሌላም ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር እንድትገፋ ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡ ሁለቱ ነገሮች የተያያዙ ናቸው የሚባለው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ የወደፊት ጉዟችንን ስናስብ ለምሳሌ የዛሬ አምስት፣ አሥር ወይም ሃያ ዓመት ኢትዮጵያ እንዴት ትሆናለች ብለን ለመገመት አሁን ያለውን የኢትዮጵያን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጨባጭ ሁኔታ ማየት ይኖርብናል፡፡ ከተሜነት እየተስፋፋ ነው፣ ኢኮኖሚው እየተንቀሳቀሰ ነው፣ ለዚህ ሁሉ ሁለቱም የውኃ አካላት በጣም ያስፈልጋሉ፡፡ ዓባይ በኢነርጂና በውኃ ምንጭነቱ ያስፈልገናል፡፡ ዕድገት ያለ ዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጥ አይታሰብምና ቀይ ባህር ደግሞ ለወጪና ገቢ ንግድ ያስፈልገናል፡፡ የእኛ አገር ኢኮኖሚ ደግሞ በገቢ ንግድ ጥገኛ ነው፡፡ በአንድ አገር ወደብ ላይ ጥገኛ ሆነን የባህር በር ሳይኖረን ኢኮኖሚው በዘላቂነት ሊያድግ ይችላል ብለን ማሰብ አንችልም፡፡ የሆነ ቦታ ላይ ሲደርስ ንዝረት (ሾክ) እንዳይገጥመው ስለሚፈለግ ከወዲሁ የባህር በር ጉዳይ አስፈላጊ አድርገን ማንሳት ይኖርብናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገውን የቅርብ ጊዜ የመግባቢያ ስምምነት አንዳንዶች የንግድና ኢኮኖሚ አድርገው ያቀርቡታል፡፡ በሰጥቶ መቀበልና አብሮ በማደግ ላይ የተመሠረተ ይሉታል፡፡ ይሁን እንጂ ጉዳዩ የኢኮኖሚ ብቻ ከሆነ ለምን ከፍተኛ ተቃውሞ አስነሳ የሚሉም አሉ፡፡ ስምምነቱ የባህር ኃይል ከመገንባት፣ እንዲሁም እንደ አገር ለሶማሌላንድ ዕውቅና ከመስጠት ጋር የተያያዙ ፖለቲካዊ አጀንዳዎች የያዘ በመሆኑ አይደለም ወይ ከባድ ተቃውሞ የተነሳው?

ዳር እስከዳር (ዶ/ር)፡- ለረጅም ጊዜ የቆየ ነባር አሠራርና አመለካከትን ስትነካ ብዙ ጩኸት እንደሚነሳ ይታወቃል፡፡ በምሥራቅ አፍሪካም አንድ የቆየ ልማዳዊ ገጽታ ሰፍኗል፡፡ ሶማሊያ እየተሻሻለች ያለች አገር ብትሆንም ብዙ ችግር ያለባት ተጋላጭ አገር ነች፡፡ ሶማሌላንድ ደግሞ ውጤታማ የመንግሥት መዋቅር ቢኖራትም ዕውቅና የሌላት አገር ናት፡፡ ይህ ነባራዊ ሁኔታ እንዳለ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ወገኖች አሉ፡፡ እኛ ደግሞ የባህር በር ያስፈልገናል ብለን ተነስተናል፡፡ ኤርትራ፣ ጂቡቲም ሆነች ሶማሊያ ጉዳዩ ሲነገራቸው አይሆንም ካሉ ያለን አማራጭ ወደ እዚህ መዞር ነው፡፡ ወደ እዚህ ስንዞር ደግሞ ከሶማሌላንድ ጋር ድርድር ማድረጋችን ከፍተኛ ተቃውሞ ሊገጥመው እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊ ሆነህ ስታስበው በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ከተነሳው ተቃውሞ ይልቅ ኢትዮጵያ ያለባት ችግር ይበልጣል፡፡ እኛ በአንድ አገር፣ በአንድ ወደብና ደካማ በሆነ መሠረተ ልማት ላይ ጥገኛ ሆነን መቀጠል አንችልም፡፡ ስለዚህ አማራጭ መፈለግ አለብን፡፡ አደጋ ሊኖረው ቢችልም እሱን መከተል ይኖርብናል፡፡ ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገው ስምምነት ወደብ ለመጠቀም ብቻ ቢሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ተቃውሞ አይነሳም ነበር፡፡ ከበርበራ ወደብ 19 በመቶ ድርሻ እስከ መግዛት ደርሰን ነበር፡፡ ለወደብ ብቻ ቢሆን ኖሮ ተለምነን ነበር እንድንጠቀም የሚጋብዙን፡፡  

ሪፖርተር፡- የእናንተ ተቋም አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ከውጭ ግንኙነትና ከደኅንነት ጋር የተያያዙ በርካታ ሰነዶችን ያዘጋጃል፡፡ ብዙ ጉዳዮችን እንደምታጠኑም ይታወቃል፡፡ በዋናነት ኢትዮጵያ አሁን ምን ዓይነት የሥጋት ሁኔታዎች ውስጥ ነው ያለችው የሚለውን በጥቂቱ ቢያነሱልን?

ዳር እስከዳር (ዶ/ር)፡- የኢትዮጵያ ሥጋቶችን ስናይ ውስጣዊም አለ፣ ከውጭ የሚመጣም አለ፡፡ ውስጣዊ ብቻ ነው እንደማልለው ሁሉ ከውጭ ብቻ የሚመጣ ነውም አልልም፡፡ ግን ውስጣዊውና ውጫዊው ሥጋት አንዱ ከሌላው የሚመጋገብ መሆኑን እገነዘባለሁ፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ እነዚህ ሁለት ውኃዎች ናቸው ብዙ ጦስ እያመጡብን ያሉት፡፡ አርፈን ብንቀመጥና ምንም አንነካም ብንል ያን ያህል ሥጋት ላይገጥመን ይችላል፡፡ ሥጋቶች ግን አሉብን፡፡ ከሥጋት ነፃ የሆነ አገር የለም፡፡ ሆኖም አገሮቹ የሚለያዩት ያንን ሥጋት ለመመከት ባላቸው ዝግጁነትና በገነቡት አቅም ነው፡፡ እሱን ደግሞ መንግሥት እየሠራበት ነው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የሚገጥመን የሥጋት ዓይነት የባህር በር ለማግኘት ከምናደርገው ጥረት ጋር፣ እንዲሁም ከውኃ አጠቃቀም ፍላጎታችን ጋር በተያያዘ ለውጥ ይኖረዋል ተብሎ ነው የሚገመተው፡፡ አዳዲስ አሠላለፍና ወዳጅነትን እያየን ነው፡፡ ምን ያህል ነው የሥጋት መጠኑ የሚለውን ወደፊት የምናይ ነው የሚሆነው፡፡ አዲሱ ነገር የሚሆነው ከውኃ ጥቅሞቻችን ጋር በተያያዘ ዝምተኛ ፖሊሲያችንን እየተውን ከመምጣታችን ጋር በተያያዘ ብዙ ለውጥ ይኖራል፡፡ ኢትዮጵያ ሁሌም እንደሚባለው ገለልተኛ አገር፣ በሌሎች አገሮች ጉዳዮች ጣልቃ የማትገባ ጭምት ተደርጋ ነው በውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ የምትሳለው፡፡ አሁን ግን ይህ እየተቀየረ እኛም ፍላጎት አለን፣ በፍላጎቶቻችን ዙሪያ ተባብረን እንሥራ የሚል ፖሊሲ መጥቷል፡፡ ይህ አቋም ምናልባት አንዳንድ ነገሮችን ይዞ ይመጣል የሚል ግምት አለ፡፡ እሱን እንግዲህ እየተከታተሉ መልስ መስጠት ይጠበቃል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርብ በምን ጉዳዮች ምን ዓይነት ሰነዶችን ይፋ ታደርጋላችሁ፡፡ ከእናንተ ምን ይጠበቅ?

ዳር እስከዳር (ዶ/ር)፡- እኔ በተቋሙ በጥናት ኤክስፐርትነት ነው የምሠራው፡፡ ከምንሠራቸው ጥናቶች ውስጥ የትኛው ነው ቅድሚያ ይፋ መሆን ያለበትና የሌለበት የሚለውን የሚወስነው አመራሩ ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን ወሳኝ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቋማችን እያጠና ነው የሚገኘው የሚለውን መውሰድ ይቻላል፡፡    

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ግጭቶች በሰብዓዊ ዕርዳታ ሥራዎቻችን ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተፅዕኖና እየተከሰተ ያለውን ሥቃይ እያየን ነው›› ሆላንደር ሆላንደር፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያና የጂቡቲ ዋና...

ከበርካታ የአፍሪካ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ለአሜሪካ የቅርብ ወዳጅ እንደሆነች ይነገርላታል፡፡ ክፍለ ዘመንን የተሻገረው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ሰሞኑን ዲፕሎማቲክ ግንኙነት የጀመሩበትን 120ኛ ዓመት ክብረ በዓላቸውን...

‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖሩንን እንቅስቃሴዎች ሊያግዙ የሚችሉ ተቋማት ያስፈልጉናል›› ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር)፣ የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያንና የምሥራቅ አፍሪካን የፋይናንስ ተቋማት መሠረት በማድረግ በየዓመቱ የሚካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ፣ በበርካታ አጀንዳዎች አማካይነት በተለይ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓቶችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ጎን...

‹‹ኢትዮጵያ ብዙ ፈተና እየገጠማት ቢሆንም ከፈተናው ውስጥ ቀስ እያልን እንወጣለን ብዬ አስባለሁ›› ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር

ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ መካሄዱን ተከትሎ  በቀደሙት ጊዜያት ከተቋማዊ ስሙ ባለፈ በሚያከናውናቸው ተግባራት፣ ተቋሙን ይመሩት በነበሩ ኮሚሽነሮች፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ተቋማዊ ባህሪው ከአስፈጻሚው...