Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉበረመዳን 2016 ዋዜማ

በረመዳን 2016 ዋዜማ

ቀን:

ተሾመ ብርሃኑ ከማል

በመሠረቱ ረመዳን ማለት መፆም ማለት ሲሆን፣ ከሁሉም በላይ የፈጣሪ ትዕዛዝ ነው፡፡ የመፆም ትዕዛዝነቱም ለሙስሊም ብቻ ሳይሆን፣ በፈጣሪ አንድነት ለሚያምኑ ሁሉ ነው፡፡ ይህም አይሁዶችንና ክርስቲያኖችን ይጨምራል፡፡ በቁርዓን ውስጥ በተለይም በምዕራፍ ሁለት በቁጥር 183 ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ፆም በነዚያ ከእናንተ በፊት በነበሩት ሕዝቦች ላይ እንደተጻፈው በናንተም ላይ  ተጻፈ፤›› በማለት መፆም በሙስሊሞችና ከኢስላም በፊት በነበሩ በፈጣሪ አንድነት በሚያምኑ ሁሉ መደንገጉን ይገልጻል፡፡  መፆም ግን ምግብን ቀን ባለመብላትና መጠጥን ባለመጠጣት ብቻ የሚገለጥ አይደለም፡፡ ከክፉ ነገር ራስን መጠበቅንም ይጨምራል፡፡ በሐሰት እየመሰከሩ፣ እየቀጠፉ፣ እየዋሹ፣ የሰው ሥጋ በሐሜት እየቦጨቁ ከምግብና ከመጠጥ መታቀብ ፆመኛ እንደማያደርግ በብዙ አንቀጾች ተጠቅሷል፡፡ በዚህ ረገድ በምዕራፍ ሁለት ከቁጥር 183 እስከ 187 የተደነገገውን መመልከት ይጠቅማል፡፡ 

ከዚህም በተጨማሪ፣ ቀለል ባለ አፈታት ረመዳን ማለት የሚያቃጥል ጥም፣ በፀሐይ ኳ ብሎ የከነነ መሬት ማለት ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህም በጥም እየተቃጠሉና የሚያነድ ፀሐይ ጨረርን እየተቀበሉ ፀሐይ ከመውጣቷ ትንሽ ቀደም ብሎ ካለው ሰዓት ጀምሮ ፀሐይ ሙሉ በሙሉ እስክትጠልቅ ባለው ጊዜ ምንም ዓይነት ምግብ ሳይመገቡ ጊዜውን ፈጣሪን በማስታወስ፣ ከክፉ ነገሮች ሁሉ በመራቅ ደግ ተግባር በማከናወን፣ ራስን በተለይም ምላስን ከመጥፎ ቃላት በመጠበቅ ቸር ቸሩንና ገር ገሩን እንድትናገር በማድረግ ማሳለፍ ነው፡፡ ሙስሊሞች በመጠማትና በመራብ ከቶ ምንም የሌላቸውን ወይም ጥቂት ቀምሰው ቀን ለመግፋት የሚጥሩትን ያስታውሳሉ፡፡ ለእነዚህም ሰዎች ሐዘኔታን ያሳያሉ፡፡ የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው ይጸልያሉ፣ ካላቸውም ያካፍላሉ፡፡ 

- Advertisement -

ረመዳን የሚፆምበት፣ ሙስሊም መሆን የሚገለጥበት፣ ለእምነት ያለው ታማኝነት የሚያመለክቱበት፣ ደግነትና መስዋዕትነት የሚስተዋሉበት ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ ትርጉም ያለው ወር ነው፡፡ ሙስሊሞች በረመዳን ወር አዘውትረው በመጸለይ፣ መልካም ተግባር በማከናወን፣ ከተከለከሉ ነገሮች ሁሉ ራሳቸውን በመጠበቅ፣ ፈጣሪ ለሰው ልጅ የቸረው ፀጋ የላቀ መሆኑን በመገንዘብ፣ ስለሚያሳልፉ የእሱን በረከት ያገኛሉ፡፡ ሙስሊሞች በረመዳን ወር መፈጸም ከሚገባቸው ዋና ዋና ትዕዛዛት አንዱ ምፅዋት ለሚገባቸው የኅብረተሰቡ ክፍሎች በታዘዘው መጠን መስጠት ነው፡፡ ነቢዩ ሙሐመድም (ሱዓወ) ‹‹ሀብት ምፅዋት በመስጠት ይጨምራል እንጂ አይቀንስም›› በማለት ያስገነዝባሉ፡፡

የዘንድሮ የረመዳን በዓል ከመጋቢት ሁለት ወይም ሦስት ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል በፆም ይከበራል፡፡ በረመዳን ወር ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በርካታ በረከት የሚያስገኙ መልካም ነገሮች የሚከናወኑበት ወር ነው፡፡ ረመዳን በዓረብ የወራት ቀመር (ሂጅር) መሠረት ዘጠነኛው ወር ሲሆን፣ በዚህ ወር በመጨረሻው የወር ሲሶ (በሃያኛው ቀን) ፈጣሪ ለነቢዩ ሙሐመድ ቁርዓን ያወረደበት ነው፡፡ ረመዳን የመጀመሪያው የቁርዓን አንቀጽ የወረደበት ወር በመሆኑም በዓለም የሚገኙ ሙስሊሞች ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት ትንሽ ቀደም ብሎ ጀምሮ ፀሐይ እስክትጠልቅ ባለው ጊዜ በፆም፣ በጸሎት፣ ጥሩ ነገር በመሥራት፣ በምግባራቸው አርዓያ ሆነው በመገኘት ያከብሩታል፡፡ 

የረመዳን ወር የሚፆምበት የሚጸለይበትና ፈጣሪ ፀንቶ የሚዘከርበት ወር ብቻ ሳይሆን ሰዎች ተዋደው፣ ተፋቅረው፣ ተሳስበውና ተከባብረው እንዲኖሩ በፈጣሪ መታዘዛቸውን ለማስመስከር እጅግ በጣም ትልቅ አጋጣሚ ነው፡፡ ኢስላም ዘር፣ ቀለም፣ ፆታ፣ ብሔር ብሔረሰብ፣ ሃይማኖት ሳይለይ የሰላም ሃይማኖት፣ የመከባበርና የመቻቻል ሃይማኖት መሆኑን ከቤተሰብና ከጎረቤት ጀምሮ ያለው ሰው ሁሉ መልካም ምሳሌ ሆኖ በመገኘት የበለጠ የሚረጋገጥበት ነው፡፡ 

ረመዳን በዋነኛነት ከማንኛውም ወር ሁሉ በበለጠ መልኩ ራስን ለሥነ ሥርዓት በማስገዛት፣ በሰላምና በመቻቻል ማለፍ ያለበት ወር መሆኑን በሃይማኖቱ ጥልቅ ዕውቀት ያላቸው አባቶች አበክረው ያሳስባሉ፡፡ ሁከትን መፈጸም ቀርቶ ማሰብ ትክክል አይደለም፡፡ አንድ ሙስሊም በግሉ የረመዳን ፆምን በሰላም፣ በፀጥታ፣ በክብር፣ በጸሎት ለማሳለፍ እንደሚፈልገው ሁሉ በአካባቢው ከሚኖር ጎረቤቱ ጀምሮ እስከ ቀበሌው፣ ከዚያም ወረዳውና ክልሉ ያለው ኅብረተሰብ እንደሱ ሰላም፣ ፀጥታና ክብርን የተጎናፀፈ ወር ለማሳለፍ እንደሚሻ ለሴኮንዶች እንኳን አይዘነጋም፡፡

ጀላሉዲን ሩሚ ‹‹ለፈጣሪ ፍላጎት ራሳችንን ለማስገዛት ፈቃደኞች ሆነን ስንገኝ ብቻ እውነተኛ ነፃነት እንደሚገኝ፣ ራስን ለፈጣሪ ማስገዛት ማለት ከአጥፊ ፍላጎትና አምሮት፣ ከትርጉም አልባ ባዶ ስሜት፣ ከንቱ ከሆነ አስተሳሰብ፣ ከነሆለለ ሕይወት፣ ከፈተናና ከባርነት ነፃ ያወጣናል፤›› በማለት ያስገነዝበናል፡፡  

በመሠረቱ፣ በመቻቻልና በሰላም አብሮ ለመኖር በፍቅር መኖርን ይጠይቃል፡፡ ፍቅር የሚጀምረው ደግሞ ከአዕምሯችን ነው፡፡ ስለፍቅር ስንጨነቅና ስለፍቅር ተግተን ስንሠራ አፍቃሪ እንሆናለን፡፡ አፍቃሪ ስንሆን ስለራሳችንና ስለሌሎች የነበረን አመለካከት ይቀየራል፡፡ ሌሎችን ስናፈቅር ከሌሎች ፍቅርንና መፈቀርን እናገኛለን፡፡ የምንሰጠው ፍቅር ከፍ እያለ በሄደ መጠን የምንቀበለው ፍቅርም እያደገ ይሄዳል፡፡ 

ቅዱስ ቁርዓን የሚያስተምረው ኅብረተሰቡ የዘር፣ የፆታ፣ የሃይማኖት፣ የዜግነትና፣ የቀለም ልዩነት ሳያደረግ ከሁሉም ጋር ተቻችሎ እንዲኖር፣ በጥልቅ ሃይማኖታዊ ስሜት፣ በፍቅር፣ በመደጋገፍ፣ የሰውን ታላቅነት ተቀብሎ አስፈላጊውን ሁሉ ክቡር መስጠት በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተቸገሩን በመርዳት እንዲያሳልፈውና ከፈጣሪ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲያድስ ነው፡፡ 

ሌሎች ለሙስሊም ወንድሞቻቸው ሊያደርጉት የሚገባ

የእስልምናና የክርስትና ሃይማኖቶች ተከታዮች ኢትዮጵያውያን የአንድ አገር ሕዝቦች ናቸውና ከመሬቷ የበቀለውን ይመገባሉ፡፡ ለልብስ የሚሆነውንም በሥራቸው ለውጠው ይለብሳሉ፡፡ በአገራቸው ተወልዶ ያደገውንና ለመብል የታዘዘውን እንስሳ የፈጣሪን ስም አንስተው በማረድ ይመገባሉ፡፡ አንድ አየር ይተነፍሳሉ፡፡ አንድ ብርሃን ይጋራሉ፡፡ በአንድ ምድር ቤታቸውን ሠርተው ይኖራሉ፡፡ በአንድ መንግሥት ይተዳደራሉ፡፡ ባህላቸው፣ ቋንቋቸው ቢለያይ እንኳን በኢትዮጵያዊነታቸው አንድ ናቸው፡፡ ይህንን ሁሉ በጋራ ሲያደርጉ የሚለያዩት (እምብዛም የተለያዩ ባይሆኑም) በአንድ ሃይማኖት ብቻ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ የአይሁድ እምነት የሚከተለውንም ሆነ የበሃኡላህን፣ ካለም የዞሮአስተሩን፣ የታኦውን፣ የሂዱስታኑን የሚመለከት ነው፡፡

በዚህ ረገድ በተለይም ሙስሊም ሃይማኖትን እንደዘር፣ እንደቀለም፣ እንደጎሳ ወዘተ የተለያየ ያደረገው ራሱ ፈጣሪ ስለሆነ ሌሎች የፈለጉትን እንዳይከተሉ ሊከለክላቸው እንደማይገባ በተለያዩ አንቀጾች አዟል፡፡ ስለዚህም አንድ ሙስሊም፣ ሰዎች የተለያየ ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን የተለያየ አመለካከት እንዳላቸውና በያዙት ሃይማኖትና የመቀጠሉ ጉዳይ የራሳቸው ምርጫ መሆኑን፣ የሚፀድቀውንና የማይፀድቀውን የሚለየው ራሱ ፈጣሪ እንደሆነ ግልጽ በቁርዓን አሥፍሯል፡፡ 

መሠረታዊ ሀቁ ይህ ከሆነ የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮችም ሙስሊም ወንድማቸው ነውና በሰላም በመፆም ፈጣሪውን ማወደስና ማክበር ይችል ዘንድ በልዩ ልዩ መንገዶች መርዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሃይማኖታቸው ለሰው ሁሉ ሊያደርጉት የሚገባ ጥሩ ነገር ሁሉ የማድረግ ሃይማኖታዊ ግዴታ አለባቸውና፡፡ 

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በዚህ የረመዳን ወር ማስታወስ ያለባቸው ሌላው ዋነኛው  ቁም ነገር ኢትዮጵያውያን ሁሉ በራሳቸው ታሪክ፣ ባህል፣ ልምድ፣ ብሔር፣ ብሔረሰብና ክልል ኩሩ የመሆናቸውን ያህል ከሌሎች አገሮች በሚነሳ ማዕበል የማይናጡ ጠንካራ ሕዝቦች መሆናቸውን ነው፡፡ በኢትዮጵያውያን መካከል የእምነት ልዩነት ቢኖርም ሰብዓዊ ፍጡር መሆናቸውን፣ ተመሳሳይ ባህል፣ ተመሳሳይ ታሪክ፣ ተመሳሳይ ልምድና ተመሳሳይ ሥነ አዕምሮ የሚጋሩ መሆናቸውም የበለጠ ቢያዳብር እንጂ አያቀጭጭም፡፡ 

በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ሙስሊሞች

በአሁኑ ጊዜ፣ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ሙስሊሞች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ ለሕዝቦች በሰላም አብሮም መኖርና መከባበር ጠንክረው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይም እንደቱርክ፣ ሊባኖስ፣ ግብፅ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ፓኪስታን፣ ናይጄሪያ፣ ማሌዢያ፣ ያሉ የተለያየ ሃይማኖት የሚገኝባቸው አገሮች በመጫወት ላይ ያሉት ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ይህም ሆኖ ከሃይማኖታዊ ምክንያት ይልቅ ፖለቲካዊ አመለካከት እያየለ አልፎ አልፎ ችግር መስተዋሉ አልቀረም፡፡ ይህም በአገራችን ሙስሊም፣ ክርስቲያንና ኦሪታውያንን እርስ በርስ በማለያየትና አንዳቸውን ከሌላቸው በማበላለጥ ይጠቀሙበት እንደነበረው ዓይነት መሆኑ ነው፡፡ ኢስላምን በሚመለከት በአልመኢዳህ (5፡48) «ወደ እናንተም መጽሐፉን ከበፊቱ ያለውን መጽሐፍ አረጋጋጭና በእሱ ላይ ተጠባባቂ ሲሆን በእውነት አወረድን፡፡ በመካከላቸውም አላህ ባወረደው ሕግ ፍረድ፡፡ እውነቱም ከመጣልህ በኋላ ዝንባሌዎችን አትከተል፡፡ ከአንተ ለሁሉም ሕግና መንገድን አደረግን፡፡ አላህ በሻ ኖሮ አንድ ሕዝብ ባደረግሁት ነበር፡፡ ግን በሰጣችሁ ሕግጋት ሊሞክራችሁ (ለያያችሁ)፡፡ በጎ ሥራዎችንም ለመሥራት ተሽቀዳደሙ፣ መመለሻችሁ በጠቅላላ ወደ አላህ ነው፡፡ በእሱም ትለያዩበት የነበራችሁትን ነገር ይነግራችኋል፤» ተብሎ በግልጽ ሠፍሯል፡፡ ነቢዩ መሐመድም (ሱዓወ) ከክርስትናና ኦሪት ሃይማኖት ተከታዮች ጋር ተከባብረው አብረው ኖረዋል፡፡ አቡዳውድ የተባሉት የነቢዩ ሙሐመድ ሐዋርያ እንደጠቀሱት «ማንኛውም ሙስሊም ያልሆነ ዜጋን የጎዳ እኔን እንደጎዳ ይቆጠራል፤» በማለት በመጀመሪያው የሙስሊም ዓለም የሃይማኖት ነፃነትና ብዝኃነትን ያረጋገጡትም እሳቸው ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር እንኳንስ በተመሳሳይ እምነትን ጥላቻን ማናፈስ በተለያየ ሃይማኖት ላይ ተመሳሳይ ችግር መፍጠር እንኳን ትክክል አለመሆኑን ነው፡፡

በረመዳን ወር መከናወን ያለባቸው ተግባራት

በረመዳን ወር መከናወን ከሚገባቸው በርካታ ቁም ነገሮች የመጀመሪያው ዝልቅና ባለው መንገድ  ራስን ለለውጥ ማዘጋጀት ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች በረመዳን ወር ራሳቸውን ከአልኮል መጠጥ፣ ከሲጃራ፣ ከዝሙት፣ ከሸፍጥ፣ ከማታለል፣ ከሙስና፣ በምላሳቸው መጥፎ ነገር ከመናገር፣ ከምቀኝነት፣ ከቅናት፣ በሥልጣን ያላግባብ ከመጠቀም፣ የሰውን ሀብት ከመመኘት፣ በሐሜት በአሉባልታ የሰውን ስም ከማጥፋት ወዘተ ለመቆጣጠር ይሞክሩና ረመዳን ሲያልፍ ወደ ነበሩበት ይመለሳሉ፡፡ ይህም ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› እንደሚባለው መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ፆም ሲያዝ የተጠቀሱትንና ሌሎችም ያልተጠቀሱ ብዙ መጥፎ ባህርያትን አሽቀንጥሮ በመጣል በመልካም ለመተካት ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ መነሳት (መነየት) ይገባል፡፡ ይህን ትልቅ ተግባር ለማከናወንም ከድሮ መጥፎ ባህሪ ራስን ማላቀቅና ለማላቀቅም ቆርጦ መነሳት በተለይም ከራስ ጋር ምሕረት በሌለው ሁኔታ መታገልና ራስን ድል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን ከሌብነትና እሱን ከመሳሰሉ ከላይ የተጠቀሱ ድክመቶች ነፃ መሆን ይቻላል፡፡ 

አንዳንድ ሰዎች ለፈጣሪ ከሚያደርጉት ይልቅ ለታይታ ወይም ለፖለቲካ የሚያደርጉት ጎልቶ የሚታይበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህም በአለባበስ፣ በአነጋገር፣ በአካሄድ፣ በአገላለጥ፣ የሌላውን ሰው ዕይታ ለመሳብ ጥረት በማድረግ ወዘተ የሚገለጥ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ በአንደበቱና በድርጊቱ ባለጌና አጭበርባሪ፣ ከዋጋው በላይ ዋጋ ጨምሮ የሚሸጥ፣ ከጥራት ደረጃው በላይ የጥራት ደረጃ አለ ብሎ መናገር ብቻ ሳይሆን ጥራት የሌለውን አለው ብሎ የሚናገር፣ ሚዛን የሚያጎድል፣ የሰው ሐቅ የሚወስድ፣ ያልተደረገውን ተደረገ፣ ያልሆነውን ሆነ የሚል፣ የተናገረውን የሚክድ ወዘተ ጺሙን ቢያጎፍር፣ ልብሱን አሳጥሮ ቢለብስ፣ ቢጠመጥም፣ ሐዲስንና ቁርዓንን ቢያነበንብ፣ በሙስሊሙ ኅብረተሰብ በተሰበሰበበት ቢሰብክ፣ በአለባበስ ነቢዩ ሙሐመድን (ሱዓወ) መስሎ በተግባር ዜሮ የሆነ ሰው፣ እንደምን ከላይ በሚታይ ነገር እሳቸውን መምሰል ይቻላል? ይህስ አዋራጅ ምፀት አይሆንምን? ስለሆነም እንዲህ ካለው አስከፊና አደናጋሪ ነገር ለመራቅ ራስን ማስገደድ ይገባል፡፡ 

ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በማንኛውም ሥፍራ መልካም ሥነ ምግባርን ማሳየት አለበት፡፡ የራሱ ግለሰባዊና ከባቢያዊ ሰላም እንዲጠበቅ የሚፈልገውን ያህል የሌሎችንም ግላዊና ከባቢያዊ ሰላም መጠበቅ አለበት፡፡ ለምሳሌ በረመዳን ምክንያት አካባቢውን በድምፅ መበከል አይገባውም፡፡ ሌሊት ሲነሳ ጎረቤቱ በአንድ ግድግዳ የተያያዘ ወይም በቅርብ ርቀት የሚገኝ የሌላ እምነት ተከታይ ከሆነ የእሱን መብት አጥብቆ ሊያከብርለት ግድ ነው፡፡ ይህን ካላደረገ ከፆም የሚያገኘው በረከት አይሟላም፡፡ በተለይም የቴሌቪዥንን፣ የቴፕን የዲቪዲን የቪሲዲንና የመሳሰሉትን ድምፅ ማጉያዎች ለራስ በሚመጥን መልኩ መክፈት ሲገባ በማስጮህ ቁርዓን፣ ወይም መንዙማ ወይም ስብከት በማሰማት ሙስሊምነትን ለመግለጥ መሞከር ውጤቱ መመፃደቅ ከመሆን አይዘልም፡፡ ሁሉም ነገር የሚያምረው በመጠኑ ሲሆን ነው፡፡ በረመዳን ወር ልብን ከምን ጊዜውም በበለጠ ማለስለስ በእጅጉ ተፈላጊ ነው፡፡ 

በረመዳን የሚስተዋሉ የጋራ ስህተቶች

በረመዳን ወር ብዙ ሰዎች በጥሩ ምግብ ላይ ያተኩራሉ፡፡ በሌላ ጊዜ የማይበላው ሁሉ በረመዳን ወር ለመግዛት ጥረት ይደረጋል፡፡ ሥጋው፣ ሾርባው፣ ሳምቡሳው፣ ኬኩ፣ ተምሩ፣ ወዘተ. በብዛት የሚገዛው በዚህ ወር ነው፡፡ አንዳንድ ቤቶች የሚቀርበው ከሚባለው በላይ ነው፡፡ ይህም የምግብ ብክነትን ያስከትላል፡፡ ማባከን ደግሞ በኢስላም የሚፈቀድ አይደለም፡፡ 

ሌላው የሚስተዋል ስህተት ደግሞ አንዳንድ ሰዎች የሌሊቱን ምግብ (ሰሑር) ከጥዋት ሶላት በፊት ትንሽ ቀደም ብለው መመገብ ሲኖርባቸው በስንፍናም ሆነ በሌሎች ልዩ ልዩ ምክንያቶች ተራዊሕን (ከዒሻ በኋላ) ከሰገዱ በኋላ ማለትም ከምሽቱ ሦስት ሰዓት እስከ አራት ሰዓት ባለው ጊዜ መመገባቸው ነው፡፡ 

ምንም እንኳን ሙስሊሞች እንፆማለን ብለው የሚያስቡትና ለመፆም የሚዘጋጁት ፆም ከመግባቱና ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ቢሆንም አንዳንድ ሰዎች ነገ በአንደበታቸው መናገር ሳያስፈልጋቸው በውስጣቸው እፆማለሁ ብለው አያስቡም (ኒያ አያደርጉም)፡፡ አለማድረጋቸው በፆማቸው ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል፡፡ ይሁንና አንዳንድ ሊቃውንት በየዕለቱ በተለይም ከተራዊሕ ጸሎት በኋላ ማድረግ ይገባል ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ የሌሊት ሰሑር ምግብ ከመመገባቸው ቀደም ብሎ ወይም ሲቀርብ እንደሚፆሙ ማሰብ ይኖርባቸዋል ማለት ይገልጻሉ፡፡ ከዚህም ሌላ ፆም ሲጀምሩ ወሩን እፆማለሁ ብለው ካሰቡ በየዕለቱ ማሰብ አያስፈልጋቸውም የሚሉ ሊቃውንት አሉ፡፡ ዋናው ቁም ነገሩ እፆማለሁ ብሎ ማሰቡ ላይ ስለሆነ ሁሉም እንደ አስተምህሮቱ ትዕዛዙን መፈጸም ነው፡፡ 

የተራዊሕን ሶላት በሚመለከት ከሚቀጥለው ቀን አንስቶ መጀመር እንዳለበት የሚገልጹ አሉ፡፡ የተራዊሕ ሶላት ማለት ከዒሻ ሶላት በኋላ ያለ በረመዳን ወር የሚሰገድ የስግደት ጊዜ ሲሆን በዚህ የሶላት ጊዜ ከአቅሙ በላይ ችግር ካላጋጠመው በስተቀር ሁሉም መስጊድ ተገኝቶ መስገድ ይኖርበታል፡፡ እናም አንዳንድ ክፍሎች መጀመር ያለበት ረመዳን በገባ በሁለተኛው ቀን ነው የሚሉት፣ የረመዳን ቀን በዋለ ማለትም ረመዳን በተጾመበት ቀን ከ12 ሰዓት ማታ ጀምሮ ማለትም ከመቕሪብ ሶላት ቀጥሎ ሁለተኛው ቀን ስለሚውል ሌላ ሁለተኛ ቀን መጠበቅ ወደ ሦስተኛው ቀን እንዲሸጋገር ያደርጋል የሚሉ አሉ፡፡  

ብዙዎች በፆም በስህተት ቢበላ ወይም ቢጠጣ ፆምን ያፈርሳል ብለው ያምናሉ፡፡ ነገር ግን ሰውየው የበላው ወይም የጠጣው ሳያስበው፣ በስህተት ከሆነ ፆሙ አይፈርስም፡፡ በዚህም ምክንያት የፈረሰውን ፆም ለመተካት ሌላ ትርፍ ፆም መፆም አያስፈልገውም፡፡ ይህም ሆኖ አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች ሰዎችም መመገባቸውን እንዳይቀጥሉ ሊነግሯቸው ይገባል ሲሉ ሌሎች ደግሞ አይገባም ይላሉ፡፡ ዋናው ቁም ነገር የፆም ቀን መሆኑን ፍፁም በመርሳት ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ሳያስታውሱ ከበሉ ፆማቸው የማይፈርስ መሆኑ ነው፡፡  ይሁንና ብዙ ጊዜ እንዲህ ያለው ስህተት የሚፈጸመው ወደ ሚበሉና ወደ ሚጠጡ ሰዎች በመሄድና በፆም ላይ መሆንን በመርሳት የሚከሰት ስለሆነ ሙስሊሞች በረመዳን ወር ምላሳቸውን ብቻ ሳይሆን እግራቸውንም መሰብሰብ፣ ወደ ሚሄዱበት ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ 

ወጥ፣ ሾርባ፣ ወይም ሌላ የሚበስል ምግብ ሲሠራ መቅመስ ክልክል መሆኑን የሚያምኑ እንዳሉ ሁሉ መቀመስ እንዳለበትም የሚያምኑ አሉ፡፡ በአብዛኛው ግን በቂ ጨው መኖሩና አለመኖሩን ለማወቅ መቀመስ መብላት ስላልሆነ አያፈርስም ይላሉ፡፡ አንዳንድ ባለሙያዎች ግን ጨውም ሆነ ሌላ ቅመም በቂ መሆኑንና አለመሆኑን በሽታ ስለሚያውቁ ከጥርጣሬ ነፃ ይሆናሉ፡፡ 

ብዙ ሰዎች በፆም ቀን ባህላዊም ሆነ ዘመናዊ ጥርስ መፋቂያ መጠቀም የተከለከለ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን ነቢዩ ሙሐመድ (ሱዓወ) ራሳቸው በመፋቂያ ይጠቀሙ እንደነበር ይታወቃል፡፡ 

አንዳንድ ሰዎች የፆሙን ጊዜ ለማራዘም ሲሉ የመቕሪብን አዛን በመጎተት፣ የሱብሒን ደግሞ ቀደም ብለው በማወጅ ይጠቀማሉ፡፡ ከዚህም አልፎ በእኛ አገር ኢማሞች ወይም አንዳንድ ትልልቅ ሰዎች እስኪመጡ ድረስ የስግደት ሰዓት የሚጓተትበት ሁኔታ ይታያል፡፡ በሌላ አነጋገር እነሱ ትክክለኛውን የጸሎት ጊዜ ጠብቀው መገኘት ሲኖርባቸው ሰዓቱ እነሱን ይጠብቃቸዋል፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡ ማንኛውም ነገር መከናወን የሚኖርበት በሰዓቱ ነው፡፡ የተሻለ በረከት የሚገኘውም ከሰዓቱ ዝንፍ ሳይሉ መጠቀም ነው፡፡ 

ብዙ ሰዎች በረመዳን ፆም ከሚስት ጋር ግንኙነት ማድረግ እንደማይፈቀድ ያምናሉ፡፡ ይህም ስህተት ነው፡፡ እርግጥ ነው በፆም ሰዓት አይቻልም፡፡ ነገር ግን በመቕሪብ ሶላትና በፈጅር (ጥዋት) ሶላት መካከል ባለው ጊዜ ይቻላል፡፡ 

ሰዎች ረመዳን የፆም ብቻ ሳይሆን የጸሎት መሆኑን በመዘንጋት ቀኑን ሙሉ ተኝተው ማታ ይነሳሉ፡፡ አንዳንዱም ሌሊቱን ሲበሉ አሳልፈው ቀኑን ይፆማሉ፡፡ ይህ የሰዓት ልውውጥ ማድረግ እንጂ መፆም እንዳልሆነ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ ሌላውን ሁሉ ትልቅ መልካም ተግባር ትተን ለወንድም ወይም ለእህት ወይም ለወዳጅና ለሌላው ፈገግታ መስጠትና ሰውን የሚያደናቅፍ ነገር ከመንገድ ማስወገድ፣ እንደ በሰደቃ የሚገኝ በረከት  ከሆነ፣ ቀን የሚተኛ ሰው ያን በረከት የት ሊያገኘው ይችላል? ዋናው ቁም ነገር በመራብ፣ በመጠማት፣ ምላስን በመቆጣጠር፣ ስሜትን በመቆጣጠር፣ ከመጥፎ ነገሮች ሁሉ ራስን በመቆጠብ፣ ለሰውና ለእንስሳት ጥሩ ሆኖ በመገኘት፣ ሕይወት ባላቸውና በሌላቸው ነገሮች ላይ ሳይቀር ያላግባብ ባለመጠቀም ራስን በፆም መፈተን መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ቀን ሲበሉ አድረው ቀን መተኛት ለፈጣሪ መገዛት ሊሆን አይችልም፡፡ በፈጣሪ መገዛታቸውን ለማረጋገጥና ተጨማሪ በረከት ለማግኘት የሚሻ ሁሉ በቀን ልዩ ልዩ ጠቀሜታ ያላቸውን ነገሮች ማከናወን ይኖርበታል፡፡ 

አንዳንድ ሰዎች በረመዳን ፆም እቤት ስለሚውሉ ወይም አብዛኛውን ጊዜ ወደ መስጊድ መሄድ ስለሚያዘወትሩ ወደ ዘመዶቻቸው ቤት የሚሄዱት ከተፈታ በኋላ ነው፡፡ ይህም ቢሆን በመጠየቅ ሊያገኙት ይችሉት የነበረውን የረመዳን በረከት ያስቀርባቸዋል፡፡ ስለዚህ ሰዓታቸውን በማቻቻል ቢጠይቁ ይመከራል፡፡

ሌላው የሚስተዋል ስህተት በቁርዓን ንባብ ላይ ነው፡፡  ቁርዓን መቅራት የሚችሉ ሙስሊሞች በረመዳን ጊዜ ቁርዓንን ቢያንስ አንድ ጊዜ አንብበው ቢጨርሱ ከፍተኛ በረከት ያገኛሉ፡፡ ሆኖም በአንድ ሌሊት በሁለት ሌሊት ወይም በሳምንት ጨርሶ ቁጭ ከማለት ይልቅ በቀን የተወሰነ ክፍል በማንበብ ወሩን መዝለቅ ይመረጣል፡፡ ይህም ሆኖ በአንድ ቀን መጨረስ የተከለከለ ሲሆን በሦስትና በአራት ቀናት እየከፋፈሉ የተቻላቸውን ያህል ቢጨርሱ ግን ክልክል የለውም፡፡ በረከቱንም ይጨምረዋል፡፡ ሆኖም ሌሎች በረከት የሚያስገኙ ተግባራት ለምሳሌ የታመሙ ሰዎችን መጠየቅ፣ የሞቱ ሰዎችን መቅበር፣ ሐዘን የደረሰባቸውን ማፅናናት፣ የተቸገሩትን መርዳት የመሳሰሉት ዓበይት ኢስላማዊ ተግባራት እንዳይቀሩ ሁለትና ሦስት ጊዜ ሊበቃ ይችላል፡፡

በረመዳን ወር ትልቁ ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባው ጉዳይ ለፈጣሪ ሲሉ ወይም በጎ ተግባር በማከናወን የፈጣሪን ውዴታ ለማግኘት ሲሉ ያደረጉትን ነገር ‹‹ለእከሌ ወይም ለእከሊት፣ ለእንቶኔ ወይም ለእንቶኒት፣ ለእንስሳ ወይም ለግዑዝ እንዲህ ያለ መልካም ተግባር አከናወንኩ፤›› ብሎ ለሁለተኛ ወይም ሦስተኛ ሰው መንገር ጉራ ይሆናል፡፡ በፈጣሪና በአድራጊው መካከል የተደረገ መሆኑን ያስቀራል፡፡ ጉራ ደግሞ የሠሩትን መልካም ሥራ ከማጥፋቱም በላይ ተጠያቂነትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ወደ ገነት የሚወስደውን መንገድ ያደናቅፋል፡፡

በአጠቃላይ፣ የረመዳን ወር ወደ ፈጣሪ የበለጠ በመጠጋት በመጭው ዘመን ምሕረት እንዲያደርግ የሚለመንበት፣ በቀጣይ የሕይወት ዘመን መልካም ተግባር ለማከናወን ኃይልና ዕውቀት እንዲሰጥ የሚጠየቅበት፣ በፈጣሪ ፍቅርና አምልኮት በመላቅ እንዲሁም በእምነትና በዕውቀት ደረጃን አሳድጎ በመገኘት ከፍተኛ የበረከት መከር (መኸር) የሚሰበሰብበት ወዘተ. ነው፡፡ ስለሆነም ከዕውቀት ማነስ የተነሳ አንዳንድ የማይከለከሉ ነገሮች እንደሚከለከሉ ወይም የተከለከሉ ነገሮች እንዳልተከለከሉ አድርገው የሚናገሩ ስለሚኖሩ፣ ወይም የተለያዩ ኢስላማዊ አስተምህሮዎች ስላሉ በቅርብ የሚያገኙትን አዋቂ የሃይማኖት አባት ጠይቆ ወይም  ልዩ ልዩ ኢስላማዊ ጽሑፎችን  አንብቦ መረዳት ይጠቅማል፡፡ ጥርጣሬ፣ ሥጋዊ ፍላጎት፣ ምኞት፣ እራሮት የመሳሰሉ መንፈስን የሚያደፈርሱና የሚበክሉ ስሜቶች ሊወገዱ የሚችሉትም በተጠቀሱት መንገዶች ነው፡፡ ጠያቂው ከተጠያቂው ወይም ከጽሑፍ ምንጩ ባገኘው መረጃ መሠረት ተግባሩን ካከናወነ በቂ ነው፡፡

የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ለሙስሊሞች ሊሰጡት የሚገባ ድጋፍ

ሙስሊሞች ወርኃ ረመዳንን ራሳቸውን ለሥነ ሥርዓት በማስገዛት ያሳልፋሉ ሲባል በሰዎች ውስጥ የሚገኝን የስግብግብነት፣ የራስ ወዳድነት፣ የምቀኝነት፣ የተንኮል፣  የጠብ ጫሪነት፣ የትንኮሳ፣ የሌሎችን መብት የሚፃረር ተግባር፣ ከመሳሰሉት መጥፎ ባህሪያትን ሁሉ በመቆጣጠር ራሱን ለፈጣሪ ያስገዛል ማለትን ይጨምራል፡፡

ቅዱስ ቁርዓን የሚያስተምረው ሙስሊሙ ኅብረተሰብ የዘር፣ የፆታ፣ የሃይማኖት፣ የዜግነትና፣ የቀለም ልዩነት ሳያደርግ ከሁሉም ጋር ተቻችሎ እንዲኖር፣ በጥልቅ ሃይማኖታዊ ስሜት፣ በፍቅር፣ በመደጋገፍ፣ የሰውን ታላቅነት ተቀብሎ አስፈላጊውን ሁሉ ክብር መስጠት በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተቸገሩን በመርዳት እንዲያሳልፈውና ከፈጣሪ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲያድስ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ፣ ዘረኛነት፣ የፆታና የሃይማኖት ትምክህተኛነት፣ ዜጎች ባልሆኑ ላይ የዜግነት የበላይነት ማሳየት፣ በጥላቻ ስሜት በመሞላት፣ በንፉግነት ኢስላማዊ ግዴታን መወጣት አይቻልም እንደ ማለት ነው፡፡

ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በረመዳን ወር እንደዚህ ያለውን የላቀ ኢስላማዊ  ሥነ ምግባርን ሲያሳይ በአካባቢው የሚገኙ የሌሎች እምነት አባቶችና ተከታዮች የላቀ ከበሬታን ይሰጡታል፡፡ በልዩ ልዩ አገሮች የሚገኙ የክርስትና እምነትና የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች «የእንኳን አደረሳችሁ» መልዕክት የሚያስተላልፉ ከመሆናቸውም በላይ ለዚህ ወር ትኩረት በመስጠት ስለዓለም ሰላም፣ አብሮ መኖር፣ መቻቻል፣ የእርስ በርስ መተሳሰብና ፍቅር እንዲሰፍን ያስተምራሉ፡፡ በሃይማኖቶች መካከል የአስተምህሮት ልዩነት ቢኖርም ሁሉም ከፈጣሪ ጋር የተያያዘ በመሆኑ እንደሚያመሳስላቸው አበክረው ያወሳሉ፡፡ እንደኩዌት ባሉ አገሮች አብያተ ክርስቲያናት፣ ሙስሊሞች ፆም እንዲይዙባቸው ወይም ፆመው ከዋሉ በኋላ እንዲያፈጥሩባቸው ይጋብዛሉ፡፡ ከሙስሊሞች ጋርም አብረው አንድ ማዕድ ይመገባሉ፡፡ «በአንድ ማዕድ ስንበላ የበለጠ አንድ እንሆናለን፤» በማለትም ሐዋሪያው ጳውሎስ ሰዎች ለሰላምና ለፍቅር ተቀራርበው መጣር እንዳለባቸው ማስተማሩን በተግባር ያሳያሉ፡፡ እንዲህ በሚያደርጉ አገሮች በተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ 

ዘጠና በመቶው ክርስቲያን በሚኖርባት ደቡብ ሱዳንና ዘጠና በመቶ የሚሆነው ሙስሊም ኅብረተሰብ በሚኖርባት ግብፅ የረመዳን ፆም በመተሳሰብ፣ እርስ በርስ መልካም ምኞት በመገላለጽ እንዲቀበሉትና እንዲያሳልፉት ጥረት ይደረጋል፡፡ በዘር፣ በፆታ፣ በቋንቋ መለያየት ምክንያት ኅብረተሰቡ መለያየት እንደሌለበት ሁሉ በሃይማኖትም መለያየት እንደሌለበት መንግሥታቱ ይመክራሉ፡፡ 

የአፍሪካ አሜሪካውያን ሙስሊሞች ምሁር የሆኑት ሸኽ ኻሊድ ያሲን «የሙስሊሞችና ሙስሊሞች ያልሆኑ ሕዝቦች በሰላም አብረው መኖር» ሃይማኖታዊ ኃላፊነታቸው መሆኑን በሚመለከት ባስተላለፉት መልዕክት «ካለን የተቀራረበ ሃይማኖታዊ ትስስርና የአስተሳሰብ መርህ አኳያ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች መቻቻልንና ወንድማማችነትን አጥብቀን ልንተገብር ይገባል፤» በማለት በናይጀሪያ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች የሚታየው አለመግባባት ወንድማማችነት በተመላበት ሁኔታ እንዲወገድ አሳስበዋል፡፡

ሸኽ ኻሊድ ያሲን፣ በሁለቱ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የሚታየውን ሃይማኖታዊ መሠረት የሌለውን አለመግባባት ለማስወገድ ይቻል ዘንድ የሁለቱ ሃይማኖት መሪዎች ቁልፍ ሚና መጫወት እንደሚገባቸው ጠቅሰው፣ በሁለቱ እምነት ተከታዮች ዘንድ ያለውን ሃይማኖታዊ ትስስርና ዝምድና ለማናጋት የሚጥሩትን ሁሉ ሁለቱም ወገኖች ሊያጋልጡት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ «ሴረኞችና ቆሻሻ የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው መጥተው በስግብግብነት የተሞላ ሕልማቸውን ዕውን ለማድረግ ሲሉ የተለያያ እምነት፣ ዘርና ክልል ባለው ሕዝብ ውስጥ የጥላቻና የጠላትነት መርዛቸውን ከመርጨታቸው በፊት አፍሪካውያን ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች በወንድማማችነትና በመቻቻል ለዘመናት ኖረዋል፤» በማለት የተለያየ ሃይማኖት፣ ዘር፣ ቀለም ወይም ሌላ መኖር ለግጭት ምክንያት መሆን እንደሌለበት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ 

የተለያየ እምነት፣ ዘር፣ ብሔር ብሔረሰብ፣ ቀለም ወዘተ ያላቸው ሰዎች በፈጣሪ ዘንድ አንድ መሆናቸውን የሚቀበል ሙስሊም በረመዳን ወር የበለጠ ማሰብ የሚኖርበት ሰዎች በሰውነታቸው አንዳቸው ሌላቸውን ሳይጎዱ በፍቅር፣ በመተሳሰብ፣ በመግባባት፣ በስምምነት፣ በወንድማማችነት ስሜት እንዴት እንደሚኖሩ በማሰብ መሆን እንዳለበት ቅንጣት እንኳን የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በዚህ የረመዳን ወር ማስታወስ ያለባቸው ዋነኛውና ዓብይ ቁምነገር ኢትዮጵያውያን ሁሉ በራሳቸው ታሪክ፣ ባህል፣ ልምድ፣ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ክልል፣ ኩሩ የመሆናቸውን ያህል ከሌሎች አገሮች በሚነሳ ማዕበል የማይናጡ ጠንካራ ሕዝቦች መሆናቸውን ነው፡፡ በኢትዮጵያውያን መካከል ያለው የሃይማኖት ልዩነት፣ ሰብዓዊ ፍጡር መሆናቸውን፣ ተመሳሳይ ባህል፣ ተመሳሳይ ታሪክ፣ ተመሳሳይ ልምድ፣ ተመሳሳይ ሥነ አዕምሮ የሚጋሩ መሆናቸውን የበለጠ ቢያዳብር እንጂ የሚያቀጭጭ ከቶ አይደለም፡፡ «ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች በመሆናቸው ሰብዕናቸውን አዳበሩ፤» ልንለው እንችላለን፡፡ አይሁዶችም፣ ክርስቲያኖችም እንደዚሁ፡፡

መደምደሚያ

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅም በተያዘው የረመዳን ወር ልዩ ትኩረት ቢሰጠው ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለም ሕዝብ ይጠቅማል፣ በተለይም ከኢትዮጵያ ተጨባጭ እውነታ ጋር ይመሳሰላል ብሎ ያሰበውን ፈትሑላህ ጉለን «የነፍሳችን ሐውልት» በሚል ካዘጋጁት መጽሐፍ ያገኘውን እንደሚከተለው ያቀርበዋል፡፡  

«መፆም ለመክሳት ሲባል ወይም ከምግብና ከመጠጥ ራስን ለተወሰነ ጊዜ ለመከልከል ሲባል የሚደረግ በፍፁም አይደለም፡፡ በየዕለቱ የሚደረጉ ጸሎቶች ለመቀመጥና ለማጎንበስ ታስበው የተዘጋጁ የአካል ማሠልጠኛ ስፖርቶች አይደሉም፡፡ ምፅዋት መስጠት ካለው ገቢ ትንሽ ግብር መክፈል ወይም በማያውቁት አገር የሚገኙ ለማያውቋቸው ችግረኛ ሰዎች ከችግራቸው ፋታ እንዲያገኙ ሲባልና፣ ለማይታወቅ ዓላማ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ሐጅ መሄድ ሲባል ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ በመጓዝ ያጠራቀሙትን የአገር ውስጥ ገንዘብ ወደ ውጭ ምንዛሪ ለውጦ ማጥፋት አይደለም፡፡ ወይም ወደ ሐጅ ለጸሎት የሚሄዱበትን መሠረታዊ ምክንያት አውቀው ካልሄዱ በስተቀር «ሐጅ» የሚለውን ስምና ከዚያ ጋር የሚገኘውን ዝና ለማግኘት ከመሆን አይዘልም፡፡ እነዚህ ሁሉ ድርጊቶች በምሕዋራቸው ዙሪያና በተዘረጋላቸው መስመርና መንፈስ በተግባር ካልዋሉ በስተቀር ከሌላው የዕለት ተዕለት ተመሳሳይ ሥራ እንደምን ተለይተው ሊታዩ ይችላሉ? በአምልኮ ተግባር ውስጥ ቁጥርን ለማብዛት መንቀሳቀስ ከልጅነት ጨዋታ ጋር የሚመላለስ ነው፡፡ መንፈሳዊ ጥያቄ ለማቅረብ ካልሆነ በስተቀር በከንቱ መጮህና ማንቧረቅ የድምፅ ሳጥንን ከማለማመድ/ከማሠልጠን የተለየ ሊሆን አይችልም፤» በማለት ያስረዳሉ፡፡

ረመዳን ሙባረክ – የተቀደሰና የተባረከ ረመዳን!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...