Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየኤርትራ ወታደሮች በሽግግር ፍትሕ በሚቋቋመው ልዩ ፍርድ ቤት ተጠያቂ እንዲሆኑ ጥያቄ ቀረበ

የኤርትራ ወታደሮች በሽግግር ፍትሕ በሚቋቋመው ልዩ ፍርድ ቤት ተጠያቂ እንዲሆኑ ጥያቄ ቀረበ

ቀን:

  • በሚቋቋመው ልዩ ፍርድ ቤት የውጭ አገር ባለሙያዎች እንዲካተቱ ተጠይቋል

በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ‹‹በጦር ወንጀልና ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የተሳተፉ›› የኤርትራ ወታደሮች ጉዳይ በሌሉበትም ቢሆን፣ በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በሚቋቋመው ልዩ ፍርድ ቤት ሊታይና ተጠያቂነታቸውም ሊረጋገጥ ይገባል ሲሉ ሰባት የመብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ጥያቄ አቀረቡ፡፡

የሰብዓዊ መብትና የሲቪክ ድርጅቶቹ የካቲት 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በዝግጅት ላይ ያለውን ረቂቅ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በተመለከተ ባወጡት መግለጫ፣ ይቋቋማል ተብሎ በሚጠበቀው እውነት አፈላላጊ ኮሚሽን አማካይነት፣ በውጭ ኃይሎች የተፈጸሙ ከባድ ወንጀሎች ይፋ ሊደረጉ፣ እውነቱ ሊታወቅና ሊሰነድ ይገባል ብለዋል፡፡

መግለጫውን በጋራ ያወጡት የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (CARD)፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች (LHR)፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት (NEWA)፣ ሴታዊት የኢትዮጵያ ሠራተኞች መብት ተሟጋች (ELRW)፣ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ (AHRE)፣ ሁሉን አቀፍ ራዕይ ለዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ (IVIDE) እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል (EHRDC) የተሰኙ ድርጅቶች ናቸው፡፡

- Advertisement -

ድርጅቶቹ ጉዳዩን ይመለከታል ተብሎ የሚጠበቀው ልዩ ፍርድ ቤት፣ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጽሙ በሌሎች አገሮችም እንደሚደረገው፣ ሁሉን አቀፍ የዳኝነት ሥልጣን (Universal jurisdiction) እንዲኖረው የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ሊዘጋጅ ይገባል ብለዋል።

የልዩ ፍርድ ቤቱን መቋቋም እንደሚደግፉትና በፖሊሲው ላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች ለልዩ ፍርድ ቤት መቋቋም አሳማኝ ቢሆኑም፣ የልዩ ፍርድ ቤቱ ሕገ መንግሥታዊነት በአግባቡ ሊታይ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

‹‹የዳኝነት ሥልጣንን ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ወይም በሕግ የመዳኘት ሥልጣን ከተሰጠው ተቋም ውጪ የሚያደርግ፣ በሕግ የተደነገገን የዳኝነት ሥርዓት የማይከተል ልዩ ፍርድ ቤት ወይም ጊዜያዊ ፍርድ ቤት አይቋቋምም›› የሚለውን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 78(6) መሠረት በማድረግ፣ ልዩ ፍርድ ቤቱ ሕገ መንግሥታዊ አይሆንም የሚል ክርክር ሊያስነሳ ይችላል ብለዋል።

የሚቋቋመው ልዩ ፍርድ ቤት የመጀመሪያ ደረጃና ይግባኝ ሰሚ ችሎቶች እንዲኖሩ በመግለጫቸው ጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪም በሁለቱም ደረጃ ባሉ ችሎቶች ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ የጦር ወንጀሎችን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ወንጀሎችንና ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመዳኘት ዕውቀትና ልምድ ያላቸው የውጭ አገር ባለሙያዎች በዳኝነት ቢመደቡ ለፍትሕ ሒደቱ ቅቡልነት፣ ለውሳኔዎች ጥራት፣ ለዕውቀት ሽግግርና በዘርፉ ለሥነ ሕግ ዕድገት ተመራጭ እንደሚሆን ድርጅቶቹ ሐሳባቸውን አቅርበዋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለተፈጸሙ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም በአገሪቱ የተከሰቱ ውስብስብ ግጭቶችንና ቁርሾዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ያለመው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ረቂቅ ተዘጋጅቶ በቅርቡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ፣ የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ.ር) ሰሞኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ ድርጅቶቹ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሰነዱ ለሕዝብ ይፋ ተደርጎ ውይይትና ትችት እንዳልቀረበበት፣ ረቂቅ ፖሊሲውን በሚመለከት ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ለጋሾች ጋር ከተደረጉ አጫጭር ውይይቶች በስተቀር በቂ ውይይት አለመደሩጉን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ረቂቅ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሰነዱ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ከመፅደቁ በፊት፣ ለሕዝብ ይፋ ተደርጎ በባለድርሻ አካላት አስተያየት እንዲሰጥበት ድርጅቶቹ ጠይቀዋል፡፡ በረቂቅ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ላይ በቂና ፍሬያማ ውይይት እንዲደረግ አስቀድሞ ረቂቅ የፖሊሲ ሰነዱ ለሕዝብ ይፋ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን፣ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ምሁራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ረቂቅ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሰነዱን በዝርዝር ተመልክተው ከመፅደቁ በፊት አስተያየታቸውን እንዲያቀርቡ ዕድልና በቂ ጊዜ እንዲሰጣቸውም ድርጅቶቹ ጠይቀዋል፡፡

ለሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው አፈጻጸም መንግሥት ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ግዴታውን እንዲወጣ የጠየቁት ድርጅቶቹ፣ በአሁኑ ወቅት በርካታ የአገሪቱ ክፍሎች በማያባራ ግጭት ውስጥ መሆናቸውንና የቀሪዎቹ አካባቢዎች ፀጥታ አስተማማኝ ሁኔታ ላይ ነው ያለው ለማለት እንደሚቸገሩ አስታውቀዋል፡፡

በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የመከላከያ ሠራዊት ከፋኖና ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነግ ሸኔ) ታጣቂዎች ጋር ውጊያ ውስጥ መሆኑ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፀጥታ ሁኔታ የተረጋጋ ቢመስልም ምርጫ እስካሁን አለመካሄዱ በጋምቤላም ክልል በትጥቅ የተደገፉ ግጭቶች መታየታቸውንና በትግራይ በመሣሪያ ግጭት ባይኖርም ጦርነቱ የፈጠራቸው ቀውሶች ገና በቂ መፍትሔ አለማግኘታቸውን እንደ ሥጋት አውስተዋል፡፡

በመሆኑም መንግሥት ሕግና ሥርዓት የማስከበር ግዴታውን በአግባቡ ካልተወጣ በስተቀር፣ የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ ለማድረግ በጣም አዳጋች እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡

በአገሪቱ የሚታየው የግጭት አዙሪትና ፈር የለቀቀ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆኑት ሁሉ፣ ለሽግግር ፍትሕ አፈጻጸምም እንቅፋት እንዳይሆኑ፣ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ሊያረጋግጥ፣ ሰብዓዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሊኖረው እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

በኦሮሚያ ዜጎች በታጠቁ ኃይሎች ሲታገቱ፣ ሲገደሉና ደብዛቸው ሲጠፋ መንግሥት በተጨባጭ በቂ ዕርምጃ ሲወስድ አለመታየቱ፣ አንዳንድ የክልሉና የአካባቢ አስተዳደር የፀጥታ ኃይሎች ዜጎችን ሲያስሩ፣ ሲገድሉና አካላዊ ሰቆቃ ሲያደርሱ ይህንን ለማረም መንግሥት በተጨባጭ ዕርምጃ ሲወስድ፣ ወስዶም ከሆነ ለሕዝብ ሲያሳውቅ አልተስማም ሲሉ ድርጅቶቹ ወቀሳቸውን አቅርበዋል፡፡

በአማራ ክልል በበርካታ ቦታዎች ታጣቂ ኃይሎች በሚፈጽሙት የሽምቅ ጥቃት፣ በግልፍተኝነት በሲቪሉ ሕዝብ ላይ ጅምላ የበቀል ዕርምጃ የወሰዱ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ በተጨባጭ ተጠያቂ ሲደረጉ አልተሰሙም ሲሉ ድርጅቶቹ በመግለጫው አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም ድርጊቱን ከማውገዝ አንስቶ ለማስቆምና ለመከላከል መንግሥት ተግባራዊ ዕርምጃ ሲወስድ አለመታየቱ፣ በድሮንና በከባድ መሣሪያዎች ጥቃት ሲቪሎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት እየባሰ መምጣቱን፣ ለግጭቱ አባባሽ ምክንያቶች ጭምር መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹን መርምሮ ይፋ የሚያደርገው መንግሥታዊ ተቋም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ላይ ጭምር በአንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚሰነዘሩ ማስፈራሪያ መሰል ንግግሮች፣ ሕዝብ በሒደቱ ላይ የሚኖረውን አመኔታ የበለጠ ይሽረሽራል የሚል እምነት እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጠርጣሪ ዜጎችን ፍርድ ቤት ማቅረብ የተከለከለ ይመስል የፖለቲካ ተቃዋሚዎች፣ የሚዲያ ሰዎች፣ የፌዴራልና የክልል ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና የሚኒስትር ደኤታ ማዕረግ ያላቸው ኃላፊ ጭምር ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለረዥም ጊዜ ታስረው እንደሚገኙ ድርጅቶቹ ገልጸዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የሚታሰሩበት ቦታ መደበኛ ማረሚያ ቤት ወይም የተዘጋጀ የጊዜ ቀጠሮ ተጠርጣሪዎች ማቆያ ቦታ ሳይሆን፣ ‹‹ሐሩርና ንዳድ የበዛበት ወታደራዊ ማሠልጠኛ›› መሆኑ፣ ዜጎች ጉዳዩን የሕግ ማስከበር ሳይሆን ‹‹የበቀል›› አድርገው እንዲያዩት የሚጋብዝ፣ በመሆኑም፣ በገለልተኛ የፍትሕ ሒደት ፍትሐዊ ፍርድ የሚገያኙበት አሠራር እንዲዘረጋ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶቹ በመግለጫቸው አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...