Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናዕንባ ጠባቂ ተቋም ቤቶች ኮርፖሬሽን ባወጣው የመኖሪያ ቤቶች ጨረታ ላይ የሕጋዊነት ጥያቄ...

ዕንባ ጠባቂ ተቋም ቤቶች ኮርፖሬሽን ባወጣው የመኖሪያ ቤቶች ጨረታ ላይ የሕጋዊነት ጥያቄ አነሳ

ቀን:

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የ1997 ዓ.ም. የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) ዕጣ ያልወጣላቸው ቆጣቢዎች ያቀረቡለትን አቤቱታ መሠረት በማድረግ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ከሦስት ሺሕ ቤቶች በላይ በሽያጭ ለማስተላለፍ ያወጣው ጨረታ ላይ የሕጋዊነትና የፍትሐዊነት ጥያቄ አነሳ። 

የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ጥር 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ማስታወቂያ አጋጠመኝ ያለውን የፋይናንስ አቅም ችግር ለመፍታትና ተጨማሪ ወጪ ቆጣቢ ቤቶችን ለመገንባት፣ ከከተማው የዲዛይንና ግንባታ ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን 3,146 የመኖሪያ ቤቶችንና 306 የንግድ ሱቆችን በጨረታ ለመሸጥ ማቀዱን መግለጹ ይታወሳል።

በ1997 ዓ.ም. ተመዝግበው ከስቱዲዮ እስከ ባለሦስት መኝታ ቤት ድረስ ቤቶች ለማግኘት እየቆጠቡ ያሉ 959 ነዋሪዎች፣ እያንዳንዳቸው ምን ያህል እንደቆጠቡ የሚገልጽ ሙሉ ስማቸው ከፊርማቸው ጋር ያረፈበትና በድምሩ 144,820,085.43 ብር መቆጠባቸውን ከሚያሳይ ሰነድ በማያያዝ፣ ኮርፖሬሽኑ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን ለመሸጥ የጀመረውን ሒደት እንዲያሳግድላቸው የሚጠይቅ ደብዳቤ ለዕንባ ጠባቂ ተቋም ጨረታው ይፋ በተደረገበት ዕለት ማስገባታቸውን መዘገባችን አይዘነጋም። 

- Advertisement -

አቤቱታቸውን የተቀበለው ዕንባ ጠባቂ ተቋም የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በዋና ዕንባ ጠባቂ እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር) ተፈርሞ በወጣ ደብዳቤ፣ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በሰባት የሥራ ቀናት ውስጥ ምላሹን እንዲያሳውቀኝ ሲል አራት ጥያቄዎችን አቅርቧል። 

አንደኛ ኮርፖሬሽኑ የመኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ በሽያጭ የማስተላለፍ ሕጋዊ መሠረት ያለው ስለመሆኑ በማስረጃ ተደግፎ እንዲቀርብ ብሏል። 

ሁለተኛ መኖሪያ ቤቶቹ በጨረታ ለሽያጭ ሲቀርቡ የ1997 ዓ.ም. እና የ2005 ዓ.ም. የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎችን ቅድሚያ በመስጠት፣ በልዩ ሁኔታ ተሳታፊ ያልተደረገበት ምክንያት እንዲገለጽ ጠይቋል። 

ሦስተኛ ኮርፖሬሽኑ የመኖሪያ ቤቶችን ከዕጣና ከምደባ ውጪ በጨረታ ሽያጭ ለማስተላለፍ ሲወስን፣ በ1997 ዓ.ም. እና 2005 ዓ.ም. ተመዝግበው ቤት እየተጠባበቁ ያሉ ነዋሪዎች ጉዳይ ላይ ግልጽና የመጨረሻ ውሳኔ ያልተሰጠበትን ምክንያት እንዲገለጽ የሚል ጥያቄ አቅርቧል። 

አራተኛ ኮርፖሬሽኑ ቤቶችን በጨረታ ለመሸጥ ሲወስን ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የከተማው ነዋሪዎችን አቅም ባገናዘበ መንገድ የጨረታ መነሻ ዋጋና የአከፋፈል ሥርዓት ሊታይ ያልቻለበትን ምክንያት በመግለጽ፣ ኮርፖሬሽኑ ምላሹን በሰባት የሥራ ቀናት ውስጥ እንዲሰጥ ሲል በደብዳቤ ጠይቋል። 

ዕንባ ጠባቂ ተቋም ለኮርፖሬሽኑ ደብዳቤ የላከበት ይህ ጉዳይ የ1997 ዓ.ም. የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎቹ በመረጧቸው 16 የኮሚቴ አባላት ተወካዮቻቸው በኩል፣ በኅዳር ወር 2015 ዓ.ም. ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት በምርመራ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል። 

የአቤቱታው ምርመራ ኮርፖሬሽኑ የመኖሪያ ቤትና ንግድ ቤቶችን በጨረታ ለተጠቃሚዎች ለመሸጥ ባወጣው ጨረታ መነሻ ምክንያት ቅሬታው የቀጠለ በመሆኑ፣ ጉዳዩን ማጣራት አስፈላጊ መሆኑን ደብዳቤው ያብራራል። 

አቤቱታ አቅራቢ ተመዝጋቢዎቹ በኅዳር ወር ለዕንባ ጠባቂ ተቋም ካስገቡት ደብዳቤ በተጨማሪ፣ የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤትና የከንቲባ ልዩ ጽሕፈት ቤት ገቢ ባደረጉት የጥያቄ ደብዳቤ፣ በአስተዳደሩ ‹‹ብቁና ንቁ›› የተባሉ ቆጣቢ ነዋሪዎች ኅዳር 6 ቀን 2015 ዓ.ም. በወጣው የ14ኛ ዙር ዕጣ ሙሉ በሙሉ እንደሚካተቱ ቢገለጽም፣ ዕድሉን ባለማግኘታቸው እስካሁን የከተማ አስተዳደሩን ይሁንታና ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

‹‹የከተማ አስተዳደሩ እያደረሰብንና እያለፍንበት ያለውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሞራላዊ ምስቅልቅልና ተስፋ አስቆራጭ ቤት የማግኘት ችግር ተቋቁመን፣ እስካሁን ይሁንታ እየተጠባበቅን በመሆኑ፣ የከንቲባ ልዩ ጽሕፈት ቤት የመፍትሔ ምላሽ ይስጠን፤›› ሲሉ በደብዳቤያቸው ጠይቀዋል። 

ደብዳቤውን ለከተማው የቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ፣ ለከተማና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ ለአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት፣ ለፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ገቢ ማድረጋቸውንም ሪፖርተር ባደረገው ማጣራት ማረጋገጥ ችሏል። 

የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽንን በተመለከተ ለዕንባ ጠባቂ ተቋም በኅዳር ወር ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ ተቋሙ  ምርመራ ማድረጉን በመግለጽ፣ ተመርምሮ የተሰጠውን ውሳኔ ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ ምላሹን አሳውቋቸዋል። 

በኮርፖሬሹኑ የጽሑፍ ምላሽ ሦስት ዋና ዋና ጉዳዩች የተነሱ ሲሆን፣ አንደኛ ኮርፖሬሽኑ በ2005 ዓ.ም. ለቆጣቢዎች ከተላለፉ 18,630 ቤቶች፣ የ1997 ዓ.ም. ተመዝጋቢዎች ብቻ እንዲስተናገዱ መደረጉን ገልጿል።

አስከትሎም በ14ኛው ዙር ዕጣ ያልደረሳቸው ነባር የቤት ተመዝጋቢዎች በቀጣይ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ያለ ሲሆን፣ በመደምደሚያው ደግሞ በ14ኛ ዙር ዕጣ የ1997 ዓ.ም. ብቁ ተመዝጋቢዎች ሙሉ በሙሉ ይስተናገዳሉ የሚል ገለጻ በኮርፖሬሽኑ በኩል አልተሰጠም ብሏል። 

ከዚህ ምላሽ በኋላ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የ1997 ዓ.ም. ተመዝጋቢዎች ቤት ደርሷቸው ሳይጠናቀቁ የ2005 ዓ.ም. በዕጣው የሚካተቱ ከሆነ ምርመራው እንደሚቀጥል በደብዳቤ አስታውቋል። 

የአቤቱታው ሒደት በዚህ ሁኔታ እያለ ነው ኮርፖሬሽኑ ከጥር 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ይፋ ባደረገው ማስታወቂያ፣ 3,452 ቤቶች (3,146 የመኖሪያ ቤቶችና 306 የንግድ ሱቆችን) በጨረታ ለመሸጥ የጨረታ ሰነዶችን ሽያጭ ከተጠቀሰው ቀን ጀምሮ ለተከታታይ 20 ቀናት እንደሚያካሂድ ይፋ ያደረገው። 

በኮሚቴ የተወከሉት ተመዝጋቢዎችም ይህ ‹‹እኛን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዳ ስለሆነ፣ በእናንተ በኩል ይህንን እንድታስቆሙልንና ቤቶቹ ለእኛ ለሕጋዊ ተመዝጋቢ ጠባቂዎች እንዲተላለፍ እንዲወሰንልን፤›› ሲሉ ጥያቄያቸውን በጽሑፍ አቅርበዋል።

ባለፈው ሳምንት ደግሞ ኮርፖሬሽኑ ከኅብረተሰቡ በቀረበልኝ ጥያቄ መሠረት ነው በማለት የጨረታ ሰነድ ለመግዛት ያስቀመጠውን የጊዜ ገደብ በ13 ቀናት አራዝሞ፣ እስከ ከነገ በስቲያ መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ተጫራቾች ሰነዱን መግዛት እንደሚችሉ አሳውቋል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በሌላ በኩል የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ፣ ኮርፖሬሽኑ ስለጨረታው ማብራሪያ እንዲሰጥ ጥያቄ ማቅረቡ ታውቋል። 

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ከሪፖርተር ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ቢደረግላቸውም፣ ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ምላሻቸውን ለማካተት የተደረገው ጥረት አልተሳካም። 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...