Tuesday, May 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሰንሻይንና የቻይናው ሲሲሲሲ የአየር መንገድ ሠራተኞች ቤቶችን በ460 ሚሊዮን ዶላር ሊገነቡ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ35 ዓመታት በላይ የዘለቀው ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ኩባንያ፣ ከቻይናው ሲሲሲሲ ኩባንያ ጋር በመሆን ከ460 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ይጠይቃል የተባለውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ቅዳሜ የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. በይፋ እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡ ኩባንያው ያጠናቀቃቸውን ከአምስት ሺሕ በላይ ቤቶችንም በይፋ እንደሚያስረክብም ገልጿል፡፡

ሰንሻይንና የቻይናው ሲሲሲሲ የአየር መንገድ ሠራተኞች ቤቶችን በ460 ሚሊዮን ዶላር ሊገነቡ ነው | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ፕሬዚዳንት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዛሬው ዕለት በይፋ ሥራው ከሚጀመረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አምስት ሺሕ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ውስጥ 2,500 የሚሆነውን ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ይገነባዋል፡፡ ቀሪዎቹ 2,500 ቤቶች ደግሞ በቻይናው ሲሲሲሲ ኩባንያ ይገነባሉ ብለዋል፡፡ ኩባንያዎቹ የዚህን ፕሮጀክት ግንባታ ሥራ የተረከቡት አየር መንገዱ ያወጣውን ጨረታ በጋራ በማሸነፋቸው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሁለቱ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች የሚገነባው የአየር መንገዱ የሠራተኞች የመኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት፣ ይፋዊ የሥራ ማስጀመርያ ሥነ ሥርዓት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በተገኙበት ይከናወናል ተብሏል፡፡

በሁለቱ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች የሚገነቡት የመኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት የሚገኘው ለሚኩራ ክፍለ ከተማ ውስጥ ሲሆን፣ ግንባታውም በሦስት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡

የአየር መንገዱ ሠራተኞች አምስት ሺሕ የመኖሪያ ቤቶች 16 ሕንፃዎች ሲኖራቸው፣ እያንዳንዳቸው ሕንፃዎች 20 ወለል እንደሚኖራቸው ተገልጿል፡፡

ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ገንብቶ ያጠናቀቃቸውን 5,000 የመኖሪያ ቤቶች ለባለቤቶቹ በዛሬው ዕለት በይፋ ያስረክባል ተብሏል፡፡

ኩባንያው በሪል ስቴት ግንባታ ውስጥ መሳተፍ ከጀመረ ወዲህ ለተጠቃሚዎች ያስተላለፋቸውን ቤቶች ቁጥር፣ ከ11,500 ሺሕ በላይ እንደሚያደርሰው የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

ከመኖሪያ ቤቶቹ ርክክብ ጋር ተያይዞ የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ኩባንያ 35 ዓመት ጋር ክብረ በዓሉን የሚያከብር ሲሆን፣ በዚህ በዓል ላይ ኩባንያው ለ20 ሠራተኞች የመኖሪያ ቤቶች ሽልማት እንደሚያበረክት ታውቋል፡፡

ኩባንያው በየአምስት ዓመቱ ለትጉህ ሠራተኞቹ መኖሪያ ቤቶች እንደሚሸልም፣ ዘንድሮም በተለያዩ የኩባንያው ፕሮጀክቶች ውጤታማ ሥራ ላከናወኑና በትጉህነታቸው ለተመረጡ 20 ሠራተኞች እንደሚሸልም፣ እስካሁን 65 ቤቶችን ለሠራተኞች በሽልማት ያበረከተ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡

ሰንሻይን ሪል ስቴት አሁን በእጁ ያሉ የሪል ስቴት መኖሪያ ቤቶችን አጠናቆ ያስረከበ በመሆኑ፣ ከዚህ በኋላ ወደ ሌሎች አዳዲስ ግንባታዎች እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

ከእነዚህ መካከል በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል የተባለውና ከአዲስ አበባ አስተዳደር ጋር በ70/30 መርሐ ግብር መሠረት ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው ነው የተባለ የሪል ስቴት ግንባታ፣ በመሀል አዲስ አበባ የሚከናወን መሆኑን አቶ ሳሙኤል ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ሳሙኤል ገለጻ፣ በ70/30 የግንባታ መርሐ ግብር ከአስተዳደሩ ጋር በመተባበር ከሚገነባቸው ቤቶች ውስጥ 30 በመቶ ለአስተዳደሩ በነፃ የሚተላለፍ ነው፡፡ 70 በመቶው ደግሞ ኩባንያው ለቤት ገዥዎች የሚሸጠው ነው፡፡ የግንባታ ጊዜውም ከሦስት እስከ አራት ዓመታት ይፈጃል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች