Tuesday, May 21, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የሴራ ፖለቲካ ልፊያ ትርፉ ተያይዞ መውደቅ ነው!

ኢትዮጵያ ውስጥ አንዱ ሌላውን ጠልፎ ለመጣል የተደረጉ የሴራ ፖለቲካ ልፊያዎች ጦሳቸው ዛሬም አገርን እየለበለበ ነው፡፡ የሴራ ፖለቲካ ማዕከላዊ ማንጠንጠኛው ሥልጣን ሲሆን፣ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት መሆን የሚገባው ሕዝብ ደግሞ የሴረኞች መቀለጃ ነው፡፡ ለዚህ ማስረጃ የሚሆነው ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ዴሞክራሲ የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ በሕዝብ ላይ ለመቀለድ ማገልገሉ ነው፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ሥርዓት ይቃወሙ የነበሩ የዘመኑ ወጣቶች ከመሬት ለአራሹ እኩል ሲያቀነቅኑ የነበሩት፣ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የማነፅን አስፈላጊነት ነበር፡፡ የንጉሠ ነገሥቱ ሥርዓት በየካቲት 1966 ዓ.ም. ግብታዊ አብዮት ከተወገደ በኋላ የተፈለፈሉት የፖለቲካ ኃይሎችም ሆኑ ነፃ አውጭዎች፣ ከመጠሪያቸው ጋር ተቆራኝቶ የዘለቀው ዴሞክራሲ ከግብራቸው ጋር ሲመሳሰል አልታየም፡፡ ብዙዎቹ ሕዝባዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊ፣ ሪፐብሊካዊና የመሳሰሉ ተራማጅ መለያዎች ቢያነግቡም ከመጠሪያቸው ጋር የሚያመሳስላቸው አንዳችም ነገር አልነበረም፣ ዛሬም የለም፡፡ የሁሉም መነሻና መድረሻ እስኪመስል ድረስ ሴረኝነት ነበር የሚገልጻቸው፡፡

አሁንም ሆነ በፊት በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ንድፈ ሐሳባዊ መሠረቶች ላይ ንባቡም ሆነ ትርጓሜው አንድ ነው፡፡ ተግባር ላይ ሲገባ ግን ‹‹ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ›› እንደሚባለው፣ ከውስጣዊ አደረጃጀት እስከ ውጫዊ መስተጋብር ድረስ የብዙዎቹ ባህሪ አንድ ዓይነት ነው፡፡ በሐሳብ መለያየት ሞት አይደለም በሚባልበት ዓለም ውስጥ፣ አንዱ የሌላውን ሐሳብ በጨዋነትና በስክነት ለማስተናገድ ይተናነቀዋል፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው መንበሩ እንዳይነቀነቅበት አንዳችም ዓይነት ተቃውሞ መስማት አይፈልግም፡፡ ለሥልጣን የሚታገለውም እንቅስቃሴውን ሲያካሂድ ተቃውሞ እንዲቀርብበት አይሻም፡፡ ሥልጣኑን የሚዘውረው ተቃውሞን አዳፍኖ የሚፈልገውን ዓላማ ለማሳካት እንዳሻው መሆን ስለሚፈልግ አምባገነን ይሆናል፡፡ ሥልጣን ፈላጊው የውጭውን ቀርቶ በውስጥ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ ስለማይፈልግ በየጊዜው ማሊያውን እየቀያየረ ይበታተናል፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ ፓርቲዎች፣ ግንባሮችና ጥምረቶች በየተራ ታይተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ መከራ ሊያበቃ ካልቻለባቸው ምክንያቶች መካከል ዋነኛው በአገርም፣ በፓርቲም፣ በተለያዩ ተቋማትም ሆነ ማኅበራት ለሥልጣን ሲሉ ብቻ ሁከት የሚፈጥሩ መብዛታቸው ነው፡፡ ሕግና ሥርዓት በማንበር ዓላማን ማሳካት የሚያስችል ምኅዳር መፍጠር ሲቻል፣ በሁሉም ቦታ የበላይ ለመሆን የሚደረገው ግብግብ ለሕዝብ ሞት፣ ስደትና መከራ ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ ሕግና ሥርዓት መከበር ካልቻለ ሴራ የበላይነቱን እየያዘ ሥርዓተ አልበኝነት ይበራከታል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን የያዘ ግለሰብም ሆነ ስብስብ በሕጉ መሠረት ብቻ ኃላፊነቱን ካልተወጣ ተቃውሞ መቀስቀሱ አይቀሬ ነው፡፡ የመንግሥት ሥልጣን በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ እንዲመራ የሚያዘው በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ደግሞ የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ከላይ እስከ ታች ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ሆኑ ሹማምንት በዚህ መሠረት ኃላፊነታቸውን ካልተወጡ፣ ሕግ አውጭው አካል ፓርላማ በሕግ በተሰጠው ሥልጣን የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት፡፡

ገዥውን ብልፅግና ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግ የማክበር ግዴታ አለባቸው፡፡ ይህ ግዴታ የሚመነጨው ኢትዮጵያ ውስጥ ሕጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር ማድረግ ስላለባቸው ነው፡፡ በዚህም መሠረት በጋራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤትም ሆነ በተለያዩ መንገዶች በሚያደርጓቸው መስተጋብሮች፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ለዴሞክራሲያዊ ፉክክር እኩል እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ ገዥው ፓርቲ ቢያስቸግር እንኳ ሁሉንም ሕጋዊ አማራጮች በመጠቀም መፈተን አለባቸው፡፡ የሐሳብ ልዕልና የበላይነቱን እንዲይዝ ሲፈለግ በጉልበት የሚያምኑትን ማሳፈር የግድ መሆን ይኖርበታል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሁሉንም አማራጮች ዘጋግቶ ጉልበትን ለማፅናት የሚደረግ ሙከራ ለጊዜው የሚሠራ ቢመስልም፣ እየዋለ ሲያድር እንደማያዋጣና ለችግር እንደሚዳርግ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ጉልበተኛ ወይም መሰሪ ባለመምሰል በሴራ ፖለቲካ የአገርን ዕድል ማበላሸትም አያዋጣም፡፡ ለዘመኑ የዕድገት ደረጃም አይመጥንም፡፡

በአሁኑ ዘመን የኢትዮጵያ ፖለቲካ አሠላለፍ የተለያዩ ጎራዎች መኖራቸው ተገቢ ነው፡፡ ይህ አሠላለፍ ግን አንዱ የሌላውን ህልውና እየካደ እንዳይጓዝ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ሰላማዊና ሕጋዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እየተዳከመ በየቦታው አመፅ የሚስፋፋው፣ ካለፉ አስከፊ ድርጊቶች ለመማር ፈቃደኝነት በመጥፋቱ ምክንያት እንደሆነ መተማመን ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ በነፃነትና በእኩልነት የሚፎካከሩበት እንዲሆን ለሁሉም ሐሳቦች ዕድል መሰጠት አለበት፡፡ አንዱ አውራ ሌላው ጫጩት የሚሆንበት የፖለቲካ ጉዞ ያተረፈው ግጭትና ውድመት ብቻ ነው፡፡ ትጥቅ አንግበው የሚፋለሙም ሆኑ በሰላማዊው ምኅዳር ውስጥ ያሉት በእኩልነት እንዲስተናገዱ የሚያስችል የጋራ መግባባት መፈጠር አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ምድር አንድ ጥይት ሳይተኮስ በሕዝብ ድምፅ ብቻ ሥልጣን መያዣ ሥርዓት መበጀት ይኖርበታል፡፡ ይህ ዕውን ይሆን ዘንድ ደግሞ የሴራ ፖለቲካ ከሥሩ ተመንግሎ መውደቅ አለበት፡፡

በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖረው ሕዝብ አጥብቆ የሚመኘው ሰላም ሰፍኖ በነፃነትና በእኩልነት መኖር ነው፡፡ በነፃነትና በእኩልነት ለመኖር የሚያስችል ሥርዓት የሚገነባው ከሴራ የፀዳ የፖለቲካ ሥራ ሲከናወን ነው፡፡ ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ችግሮች ደረጃ በደረጃ ተፈተው ሕዝብ የሚፈልገው የኑሮ ሥርዓት እንዲዘረጋ ግን፣ በግራም ሆነ በቀኝ የተሠለፉ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው ራሳቸውን ከአገር በታች ማድረግ መልመድ አለባቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ባህል ሊኖር የሚችለው ራስን ከአገርና ከሕዝብ ፍላጎት በታች የማድረግ ፈቃደኝነት ሲኖር ነው፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ግን ዴሞክራሲያዊ ዕሳቤ መዳበር አለበት፡፡ የፖለቲከኞች ግንኙነት በሕግና በሥርዓት ላይ ተመሥርቶ መከናወን የሚችለው ዴሞክራትነት በተግባር ሲረጋገጥ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ማስመሰል በሕዝብ ላይ መከራ መቆለልና አገርን የማትወጣው ማጥ ውስጥ ከመክተት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ የሴራ ፖለቲካ ልፊያ ትርፉም ተያይዞ መውደቅ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...