Tuesday, May 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቢጂአይ ኢትዮጵያ የባንክ ሒሳቦችና ንብረቶች ላይ እንዳይንቀሳቀሱ በፍርድ ቤት ዕግድ ተጣለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ቢጂአይ ኢትዮጵያ እስከ መጋቢት 17 ቀን 2016 .ም. የሚቆይ ዕግድ ተጥሎበታል

ፐርፐዝ ብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አክሲዮን ማኅበር የቢጂአይ ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርን ንብረትና የባንክ ሒሳቦች በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዕግድ ተጣለ፡፡

ፐርፐዝ ብላክ የካቲት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በከፍተኛ ፍርድ ቤት የፍትሐ ብሔር ምድብ ችሎት፣ የቢጂአይ ኢትዮጵያ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችና የባንክ ሒሳቦች እንዳይንቀሳቀሱና ገንዘብ እንዳይሰወርብኝ ብሎ ባቀረበው የዕግድ አቤቱታ መሠረት፣ ፍርድ ቤቱ አቤቱታውን ተቀብሎ የባንክ ሒሳቦችና የማይንቀሳቀሱ የቢጂአይ ኢትዮጵያ ንብረቶች እንዳይሸጡና እንዳይለወጡ እስከ መጋቢት 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ የሚቆይ ዕግድ ጥሏል፡፡

መዝገቡ ለችሎት ሊቀርብ የቻለው፣ ፐርፐዝ ብላክ በጠበቆቹ አማካይነት የካቲት 27 ቀን 2016 ዓ.ም.  በተጻፈ አቤቱታ መሠረት ሲሆን፣ ክስ እስከሚያቀርብ ድረስ ቢጂአይ ኢትዮጵያ 1.5 ቢሊዮን ብር እንዳይሰወር፣ እንዲሁም የማይንቀሳቀስ ንብረቱ እንዳይሸጥ አስቸኳይ ዕግድ ይሰጥልን በሚል በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግና  የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር  ሰሚ ችሎት የሰጠውን አስገዳጅ ውሳኔ መሠረት በማድረግ  አቤቱታ ስላቀረበ  ነው።

የአቤቱታው ይዘትም፣ በአመልካችና በተጠሪ መካከል ሐምሌ 2015 ዓ.ም. በተፈረመ የሽያጭ ውል፣ የቢጂአይ ዋና መሥሪያ ቤትና ተጨማሪ ይዞታውን በአጠቃላይ ስፋቱ 29,896.51 ካሬ ሜትር  የሆነ ቦታ ላይ ያረፈ ንብረት አምስት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ እሴት ታክስን ሳይጨምር ለመግዛት ተዋውለው እንደነበር፣ ግዥው የተፈጸመው በሒደት በሚደረግ የክፍያ ሥርዓት እንደ መሆኑ፣ ፐርፐዝ ብላክ የመጀመሪያውን 20 በመቶ ማለትም 1.15 ቢሊዮን ብር ከእነ ተጨማሪ እሴት ታክሱ መክፈሉን በአቤቱታ አቅርቧል።

ቢጂአይ በውሉ አንቀጽ 2 እና 3  እንደተመለከተው ሁለተኛ ዙር ክፍያ የሚከፈለው በቅድሚያ የካፒታል ትርፍ ታክስና ከዕዳና ዕገዳ ነፃ ስለመሆኑ ማስረጃ ሲያቀርብ በመሆኑ፣ ይህን እንዲፈጽም ቢጠየቅም፣ ይህንን ለማድረግ ካለመፈለጉም ባሻገር ያለምንም በቂና አሳማኝ ምክንያት  በመካከላቸው ያለውን ውል  አንቀጽ ስድስት መሠረት በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ቀርቦ ውሉን መፈረም ሲገባው፣ ውሉን ማቋረጡን የፐርፐዝ ብላክ አቤቱታ ይገልጻል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ መሬቱን ለሦስተኛ ወገን ለመሸጥ እንቅስቃሴ ስለመጀመሩ መረጃ እንደደረሰው፣ ፐርፐዝ ብላክ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት የፍትሐ ብሔር ምድብ ችሎት አቤቱታ አቅርቧል።

በመሆኑም ቢጂአይ የውል ግድዴታውን አሟልቶ ባለመፈጸሙ  የተነሳ ፐርፐዝ ብላክ የመጀመሪያ ደረጃ 20 በመቶ  ከፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ ይህን አቤቱታ እስካቀረበበት የካቲት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ በማሰብ፣ ሕጋዊ ወለድ ዘጠና በመቶ ታስቦ 69 ሚሊዮን ብር፣ ለልዩ ልዩ ወጪ  የሚከፈል ክፍያ 250 ሚሊዮን ብር፣  ለዳኝነት የሚከፈል 50 ሚሊዮን ብር፣ በድምሩ አንድ ቢሊዮን 519 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ክርክር በመኖሩ፣ ቢጂአይ ወደፊት ንብረት የማሸሽና የመሰወር ድርጊት ሊፈጽም ስለሚችል ፐርፐዝ ብላክ ክስ እስኪመሠርት ድረስ በአስቸኳይ የዕግድ ትዕዛዝ ይሰጥልኝ ሲል አቤቱታውን ለከፍተኛው ፍርድ ቤት የፍትሐ ብሔር ምድብ ችሎት ማቅረቡን ሪፖርተር የደረሰው ሰነድ ያሳያል። 

ፍርድ ቤቱም አቤቱታውን ካየ በኋላ፣ ቢጂአይ ኢትዮጵያ በብሔራዊ ባንክ ሥር የሚተዳደሩ ሁሉም ባንኮች ውስጥ  ባሉት የባንክ ሒሳቦች፣ ፐርፐዝ ብላክ የጠቀሰው የገንዘብ መጠን፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 የቤት ቁጥር 017፣ ስፋቱ 29,896.51 ካሬ ሜትር የሆነው ይዞታ ሳይሸጥ ሳይለወጥ ወይም በማንኛውም ሁኔታ  ለሦስተኛ ወገን ሳይተላለፍ ታግዶ እንዲቆይ የዕግድ ትዕዛዝ  ሰጥቷል፡፡

ዕግዱ የሚቆየው እስከ መጋቢት 17 ቀን 2016 ዓ.ም መሆኑን የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ያሳያል፡፡

ቢጂአይ ኢትዮጵያ በዋና መሥሪያ ቤት የሽያጭ ሒደት አፈጻጸም ከፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ጋር የተከሰተውን አለመግባባት በተመለከተ፣ የካቲት 28 ቀን 2016 ዓ.ም. መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በመግለጫው ወቅት አጠቃላይ የስምምነት ሒደቱ ምን እንደነበርና ችግሩ የተፈጠረበት ወቅት መቼ እንደሆነ በማብራራት፣ በቀጣይ ከፐርፐዝ ብላክ ጋር ያለውን የስምምነት ሒደት ከተጠናቀቀ በኋላ አዲስ ገዥ የማፈላለግ ጨረታ እንደሚያወጣ፣ የቢጂአይ ኢትዮጵያ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ በኃይሉ አየለ ተናግረዋል፡፡ ፐርፐዝ ብላክ  ለሽያጩ የመክፈል  አቅሙን የሚያሳይ ማስረጃ  ሊያሳይ ባለመቻሉ ምክንያት ውሉ እንደተቋረጠ ቢጂአይ ኢትዮጵያ ገልጿል።

ቢጂአይ በመግለጫው፣ ‹‹ፐርፐዝ ብላክ በአንድ ወቅት ጥሩ የፋይናንስ ሒደት ላይ እንደነበረ ዓይተናል፡፡ ይሁንና  ከዚያ በኋላ ያለው የፋይናንስ  አቅሙን ሊሳይ ባለመቻሉ ምክንያት ለውሉ ሽያጭ መቋረጥ አንዱ ምክንያት ነው፤›› ሲሉ የሕግ ክፍል አቶ ነጋ ምሕረቴ  ተናግረዋል፡፡

‹‹በሁለቱ  ወገኖች መካከል በስምምነት ላይ የተመሠረተ የፊርማ ውል ባለመኖሩ ምክንያት  ወደ ሰነዶች በመሄድ መፈራረም እንዳልተቻለ፣ ፐርፐዝ ብላክ ያቀረበው ምክንያት መርህ አልባና ላለመፈራረማችን ምክንያት ራሱ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የሽያጭ ውሉን   ለመፈራራረም ባለው ሒደት ከስምንት ወራት በላይ እንደፈጀ  የገለጹት አቶ ነጋ፣ ‹‹በሽያጭ ውሉ ላይ የደብዳቤና የሰነድ ስምምነቶች  ለብዙ ጊዜያት ብናደርግም፣ የቁርጠኝነት ማነስ በፐርፐዝ ብላክ በኩል በመኖሩ  መስማማት አልተቻለም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹ከአንድም ሁለቴ ውሉን እንቋጨው የሚል ጥያቄ ለፐርፐዝ ብላክ ብንልክም፣ ካስቀመጥነው ጊዜ ባነሰ ሰዓት የድጋሚ ይብራራልን መልስ ይሰጠን ብለዋል፤›› በማለት አቶ ነጋ ተናግረዋል።

ሦስተኛ ወገን በሽያጭ ውሉ ላይ በመግባቱ ምክንያት ነው ውሉ የተቋረጠው  የሚለውም ከእውነት የራቀ እንደሆነ አብራርተዋል።

የሽያጭ ውሉን በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ለማስመዝገብ የካፒታል ገቢ ግብር ክሊራንስ ማቅረብ አንዱ ቅድመ ሁኔታ ሲሆን፣ በሽያጭ ሒደቱ ላይ ፐርፐዝ ብላክ በካፒታል ገቢ ግብር ክሊራንስ ላይ ያሉትን ጥያቄዎች ለማስተናገድ የሁለቱም ድርጅቶች የሕግ ቡድን ወደ ገቢዎች ሚኒስቴር ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጽሕፈት ቤት ሄደው ማብራሪያ ማግኘታቸው በቢጂአይ መግለጫ ተብራርቷል፡፡

የካፒታል ገቢ ግብር ክሊራንስ ለማግኘት፣ የታክስ ባለሥልጣኑ ከሌሎች ሰነዶች በተጨማሪ፣ በቢጂአይና በፐርፐዝ ብላክ መካከል የተፈረመ የሽያጭ ውል እንዲቀርብ ይጠይቃል። ይህም የግብር ባለሥልጣኑ የሚከፈለውን ትክክለኛ ግብር እንዲወስን ያስችለዋል ሲሉ አቶ ነጋ አስረድተዋል፡፡ 

‹‹በድርድሩ ሒደት ቢጂአይና ፐርፐዝ ብላክ  በተለያዩ ጉዳዮች ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ፣ ፐርፐዝ ብላክ በተስማሙባቸው ጉዳዮች ላይ ሳይቀር አዳዲስና የመጀመሪያውን ስምምነታቸውን የሚቃረኑ ሐሳቦችን ይዘው ይቀርቡ ነበር። ይኼንንም ለድርጅቱ በተደጋጋሚ በየጊዜው አሳውቀናል፤›› ብለዋል። 

ቢጂአይ ክሊራንስ እንዳያገኝ እንቅፋት የሆነው በሽያጭ ውሉ ላይ ስምምነት አለመደረሱና ፐርፐዝ ብላክ ውሉን ባለመፈረሙ ነው ሲል ቢጂአይ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡

ፐርፐዝ ብላክ በፍርድ ቤት የቢጂአይ የባንክ ሒሳቦችና ንብረቶችን ማሳገዱን በተመለከተ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ በኃይሉ፣ ‹‹ቢጂአይ ኢትዮጵያ በፍርድ ቤት በተያዘ ጉዳይ ላይ አስተያየት አይሰጥም፤››  ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች