Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግል ባለሀብቶች በደረቅ ወደብ ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችል ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በደረቅ ወደብ ልማትና አገልግሎት ላይ ተሰማርተው መሥራትና የመጀመርያውን ፈቃድ ለሚፈልጉ መውሰድ ለሚፈልጉ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች፣ ፈቃድ ለማውጣት የሚጠበቅባቸውን መሥፈርት የሚዘረዝር መመርያ ተረቀቀ፡፡

በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ አስተያየት እንዲሰጥበት የተሠራጨው መመርያ እንደሚገልጸው፣ የደረቅ ወደብና ተርሚናል ማልማት የሚፈልግ ባለሀብት ማሟላት ከሚገባቸው መሥፈርቶች አንደኛው ከባህር ወደብ ጋር በሚያገናኝና ከባድ ተሽከርካሪዎችን በሚያስተላልፉ ዋና መንገዶች ጋር ተገናኝቶ ማልማት ነው፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2011 ዓ.ም. ያፀደቀው የአሥር ዓመቱ የሎጀስቲክስ ስትራቴጂን መሠረት በማድረግ፣ በርካታ የሎጂስቲክስ የሥራ ዘርፎችን ከመንግሥት ብቸኛ አገልግሎት ሰጪነት በማላቀቅ፣ የግሉንም ዘርፉ የማካተት ሥራዎቹ አንደኛው አካል ነው የደረቅ ወደብን አገልግሎት ፈቃድ ለግሉ ዘርፍ ለመስጠት እየተሠራ ያለው፡፡

ከስትራቴጂው በማስቀጠልም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2012 የሎጂስቲክስ ፖሊሲውን ሲያፀድቅም፣ የደረቅ ወደብ ልማትና አገልግሎት ለግል ባለሀብት ክፍት እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ልዩ ተርሚናል፣ የሎጂስቲክስ ፓርክና የሎጀስቲክስ ሀብ የተካተቱበት የደረቅ ወደብና ተርሚናል አገልግሎቶች ማሟላት የሚገባቸውን በርካታ መሥፈርቶች ዘርዝሯል መመርያው፡፡ አብዛኛው በመሠረተ ልማት ደረጃ ማሟላት ያለባቸውን ነገሮች የደረደረ ሲሆን መሥፈርቱ፣ የደረቅ ወደቡን ከባህር ወደብ ጋር ከሚገናኝ ዋና መንገድ ጋር ማገናኘትም የመሥፈርቱ አካል ነው፡፡

የተርሚናል ዓይነቶቹ አምስት ሲሆኑ፣ የኮንቴይነር ተርሚናል፣ የደረቅ ብትን ጭነት ተርሚናል፣ የጥቅል ዕቃ ተርሚናል፣ የተሽከርካሪ ተርሚናል፣ እንዲሁም የኢንተርሞዳል ተርሚናል ናቸው፡፡

በርካታ የመሠረተ ልማት መሥፈርቶችን ከማሟላታቸው ባሻገር፣ አምስቱም ዓይነት ተርሚናሎች እንደ ቅደም ተከተላቸው የቆዳ ስፋታቸው 2.5፣ ሁለት፣ ሦስት፣ 1.5 እና አራት ሔክታር መሆን አለባቸው፡፡

ከደረቅ ወደብ ውስጥ የሚገኘው የሎጀስቲክስ ፓርኩ በትንሹ 33 ሔክታር ላይ ያረፈና ዘጠኙ ሔክታር የለማ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ከ48 ያላነሱ ባለሙያዎች ያሉበት፣ እያንዳንዳቸው በአራት ሔክታር ላይ የተሠሩ ከሦስት ያላነሱ መጋዘኖች ያሉበት፣ እንዲሁም በርካታ የአደጋ መከላከያና ሌሎች መሠረተ ልማት የተሟሉበት መሆን ይጠበቅበታል የሚለማው የሎጀስቲክስ ፓርክ፡፡

ከፍተኛውን የቆዳ ስፋት እንዲይዝ ታስቦ የተቀመጠው የሎጀስቲክስ ሀብ ልማቱ ሲሆን፣ እሱም በትንሹ ከ80 ሔክታር ባላነሰ ቦታ ላይ የተሠራና 34 ሔክታሩ በአስፋልት ኮንክሪት የተገነባ የኮንቴይነር፣ የደረቅ ብትን ጭነት፣ የጥቅል ዕቃ፣ የተሽከርካሪና የኢንተርሞዳል ተርሚናሎች ያሉት መሆን እንደሚጠበቅበት መመርያው ይዘረዝራል፡፡ የሎጂስቲክስ ሀብ ከ100 ያላነሱ ከባድ ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ የሚያቆም መሆን እንዳለበትም ተቀምጧል፡፡

የቀድሞ የትራንስፖርት ሚኒስትር ደኤታና የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው አገልግለው የነበሩት በአሁን ጊዜ በግል ሥራ ሎጀስቲክስ ማማከር ላይ የሚገኙት የኋላሸት ጀመሬ (ኢንጂነር) አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ሲሰጡ እንደገለጹት፣ በደረቅ ወደብ ላይ የሚሰጡ አገልግሎቶች ደረጃቸውን የበጠቁና አገልግሎቶችም የካርጎ ፍሰቱን የሚያሳልጡ እንዲሆን በማሰብና ወደቦቹ የተሻለ አደረጃጀት እንዲኖራቸው እንደሚገባ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል መሥፈርቶቹ ሊጠብቁ የቻሉት፡፡

የኋላሸት (ኢንጂነር) አክለውም የባለሙያ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ ትልልቅ የሎጀስቲክስ ኩባንያዎች የመሬት አገልግሎት የሚሳለጥላቸው ከሆነ በደረቅ ወደብ አገልግሎት ላይ ሊሰማሩ እንደሚችሉ ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡ እርሳቸው በኃላፊነት ቦታ ላይ ሳሉም ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር በዚህ ዘርፉ ላይ የግል ባለሀብቶች ሊሰማሩ እንደሚችሉ በማሰብ በኢንቨስትመንት ማበረታቻው ደንብ ላይ እንዲካተት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ባለሀብቱን ለማነቃቃት ማበረታቻው እንዲገባ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች