Saturday, May 18, 2024

በአማራ ክልል ያገረሸው ውጊያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹ግማሾቹ ወንድሞቼ ፋኖ፣ ግማሾቹ ደግሞ የአገር መከላከያ ወታደሮች ናቸው፤›› ስትል ሐዘን በተቀላቀለበት ድምፅ ትናገራለች፡፡ ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገችው የባህር ዳሯ ነዋሪ፣ ‹‹እንዲህ ካለው ሕይወት ሞቶ መገላገል ይሻላል፤›› ስትል ነው ሳግ በተቀላቀለበት ድምፅ እያሳለፈች ያለውን ሕይወት ለሪፖርተር የተናገረችው፡፡

ከሰሞኑ በባህር ዳር አካባቢ ስለተፈጠረው ሁኔታ እንድታስረዳ የተጠየቀችው የባህር ዳሯ ነዋሪ፣ ያለው ሁኔታ የከፋ መሆኑን ትናገራለች፡፡ ‹‹ሌሊት አሥራ አንድ ሰዓት ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ ስነሳ በድንገት ድብልቅልቅ ያለ ተኩስ መስማት ጀመርኩ፡፡ ግቢያችንን ከፍቼ ስወጣ መንገድ ላይ ዝር የሚል ወፍ እንኳን የለም፡፡ በዋናነት ዓባይ ማዶ፣ ዘንዘልማ፣ ዳያስፖራ የሚባሉ ሠፈሮች እንጂ እኛ አካባቢ ውጊያ አልነበረም፡፡ ዳር ዳሩን እንጂ መሀል ከተማ አካባቢ ተኩስ አልነበረም፤›› በማለት ዓርብ የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ማለዳ ስለተጀመረው ውጊያ ተናግራለች፡፡

‹‹ፋኖዎቹ ከተማ ሊይዙ ሲሉ መለስናቸው ይላሉ፡፡ ፋኖዎቹ አንድ ነገር አደረጉ በተባሉ ቁጥር ሁሉ የሚመጣብን መከራ ከባድ ነው፡፡ በየቤቱ ይፈትሻሉ፣ ዱላና መከራው ብዙ ነው፡፡ ለእኛ ዋስ የሚሆነው ማን ነው? ማንንስ ነው የምናምነው? ወንድም ከወንድሙ እየተገዳደለ ነው፡፡ በአካባቢያችን ሥራ ቆሟል፡፡ ብዙ ሰው በእጁ ያለውን እያጣ ነው፡፡ ብዙ ሰው እየተራበ ነው፡፡ አንዳንዴ በዚህ ሁኔታ ከመኖር መሞት ይሻላል እላለሁ፤›› ስትልም የሰሞኑ ጦርነት የፈጠረባትን ስሜት አጋርታለች፡፡

በባህር ዳርና በዙሪያዋ ዓርብ ማለዳ የጀመረው ግጭት ቅዳሜ ቀጥሎ እሑድ አካባቢ ጋብ ማለቱን ነዋሪዋ ተናግራለች፡፡ ማክሰኞ የካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ትራንስፖርት፣ ሱቆችም ሆኑ ሌሎች እንቅስቃሴዎች ዳግም መጀመራቸውን ገልጻለች፡፡ የአካባቢው ሁኔታ እንደገና ሰላማዊ ቢመስልም ሁኔታው ወዴት እንደሚቀየር መናገር እንደማትችልና ሁሉም ሰው በሰቀቀን እንደሚኖር ነው የገለጸችው፡፡

ከአማራ ክልል በየቀኑ የሚሰሙ ዜናዎች አሳሳቢነታቸው እየጨመረ ነው፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር የቆየው ክልሉ አሁን ደግሞ በአንዳንድ አካባቢዎች እንቅስቃሴ ዝግ እየሆነ ነው፡፡ የሰሜኑ ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ  ጀምሮ ከግጭትና ከጦርነት ድባብ ተላቆ የማያውቀው የአማራ ክልል፣ ከሰሞኑ ደግሞ በየአካባቢው ጠንከር ያለ ውጊያ እያስተናገደ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ ዓለምን ለሁለት ዓመታት አስጨንቆ በቆየው ኮሮና ወረርሽኝ ተፅዕኖ የኢኮኖሚ ጉዳት እንደደረሰባት በተደጋጋሚ ይወሳል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በድርቅ ለተከታታይ ዓመታት ስትጠቃ ቆይታለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአንበጣ ወረርሽኝ በብዙ የአገሪቱ ክፍሎች ጉዳት ማድረሱ ተመዝግቧል፡፡

ይህ ድርብርብ ችግር እያለ የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነት፣ እንዲሁም የእስራኤልና የሐማስ ውጊያ ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣውን ጫና አበርትቶት ቆይቷል፡፡ ይህን ሁሉ ችግር ተቋቁሞ ለማለፍ የተገደደችው ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት ደግሞ ሌላ ዓይነት ውስጣዊ ቀውስ እያስተናገደች ነው የምትገኘው፡፡ በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ተባብሶ መቀጠሉ ወይም በፍጥነት በሰላማዊ መንገድ ዕልባት አለማግኘቱ፣ ኢትዮጵያ የገጠሟትን ውስብስብ ውጫዊና አገራዊ ፈተናዎች የበለጠ እንደሚያከፋው እየተፈራ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ብዙዎች ከሚያነሱት ሥጋት በተቃራኒው በአማራ ክልሉ ጦርነት ተካፋዮቹ ኃይሎች ስለድልና አሸናፊነት በመናገር ላይ ነው የሚገኙት፡፡ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምርያ ኃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው፣ ‹‹በትንሽ መስዋዕትነት ከፍተኛ ድል አስመዝግበናል፤›› ሲሉ ነበር የተናገሩት፡፡ ኮማንደሩ ይህን ቢሉም በተቃራኒው ከመንግሥት ጋር የሚዋጋው የፋኖ ኃይልም ቢሆን ከፍተኛ ድል ስለማስመዝገቡ ነው የሚናገረው፡፡

ኮማንደር ዋለልኝ ከትናንት በስቲያ ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በሰጡት መግለጫ፣ የፌዴራልና የክልል ፀጥታ ኃይሎች በከፈሉት መስዋዕትነት በክልሉ ያጋጠመው አደጋ ተቀልብሷል ብለዋል፡፡ መንግሥት በተደጋጋሚ የፋኖ ኃይሎችን ስለመደምሰሱና የክልሉን ፀጥታ ሙሉ ለሙሉ ስለማረጋገጡ ሲናገር እንደሚደመጠው ሁሉ፣ በተቃራኒው የፋኖ ኃይሎች ድል ማስመዝገብም ተደጋግሞ ይነገራል፡፡

ኮማንደር ዋለልኝ፣ ‹‹በባህር ዳር ከተማ ጠላት ለማድረስ የፈለገውን አደጋ በተቀናጀ ጥረት እንዳይሳካ አድርገናል፤›› ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ እሳቸው ይህን መግለጫ እየሰጡ ባሉበት ወቅት የፋኖ ኃይሎች የሸዋ ሮቢት ከተማን በቁጥጥራቸው ሥር ስለማስገባታቸው እየተዘገበ ነበር፡፡

በአማራ ክልል ላለፉት ስድስት ወራት የቀጠለውን ግጭትና ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አልተቻለም፡፡ ከብዙ አቅጣጫ በሰላም ይፈታ የሚለው ውትወታ ቢቀጥልም እስካሁን አልተሳካም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አሁን ያለው ግጭትና መገዳደል እስከ መቼ ይቀጥላል የሚለው አለመታወቁ ሥጋቱን ከፍ አድርጎታል፡፡

ሸዋ ሮቢት ከተማ ለአንድ ሳምንት ሄድ መለስ በሚሉ ውጊያዎች ማሳለፏን ነዋሪዎቿ ይናገራሉ፡፡ በከተማው መደበኛ እንቅስቃሴ መስተጓጎሉም ተነግሯል፡፡ በተለይ ቅዳሜና እሑድ የነበረው ውጊያ ከበድ ያለ እንደ ነበር የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ የፋኖ ኃይሎች ወደ ከተማዋ ገብተው እንደ ነበር ተናግረዋል፡፡

ከየካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ሸዋ ሮቢትን አቋርጦ የሚደረገው ከደብረ ብርሃን እስከ ደሴ ያለው መንገድ ከትራንስፖርት እንቅስቃሴ ዝግ መደረጉን መንግሥት አስታውቆ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎም የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ይህን ቀጣና ‹‹ፅንፈኞች›› ከሚላቸው ኃይሎች የማፅዳት ዘመቻ እየወሰደ መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡

ሪፖርተር ያናገራቸው አንድ የሸዋ ሮቢት ነዋሪ በከተማዋና በዙሪያዋ የተኩስና የጦርነት እንቅስቃሴ መከሰት ከጀመረ ስምንት ቀናት እንደተቆጠረ ተናግረዋል፡፡ ስለደረሰው ቁሳዊም ሆነ ሰብዓዊ ጉዳት እንደማያውቁ የተናገሩት ነዋሪው፣ ባለፉት የሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት የነበረው ውጊያ ከበድ ያለ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በፋኖና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ጠንከር ያለ ውጊያ በእነዚህ ቀናት መደረጉን በመጥቀስ፣ የፋኖ ኃይሎች ከተማዋን ይዘዋል የሚል ነገር መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ሦስት ሰዎች በሸዋ ሮቢት ውጊያ ስለመሞታቸው ዘግበዋል፡፡ እንደ ዙ 23 ያሉ ከባድ መሣሪያዎች ጭምር በከተማው በተካሄደው ውጊያ ጥቅም ላይ መዋላቸውንም ገልጸዋል፡፡ ከእንቅስቃሴ ውጪ ሆኖ በሰነበተው በሸዋ ሮቢትና በአካባቢው ያገረሸው ውጊያ የአካባቢውን ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ እንደከተተው ነው የመገናኛ ብዙኃኑ የዘገቡት፡፡

የዓድዋ ድል በዓል በአዲስ አበባ ሲከበር ንግግር ያደጉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የውስጥ ባንዳ፣ ፀረ ሰላምና ፀረ ልማት ብለው ስለፈረጇቸው ወገኖች በስፋት ተናግረዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት ለብዙ ሰዎች ጥያቄ የሚሆንባቸው ጉዳይ አገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በሚነሱ ግጭቶች እየታመሰች እንዴት፣ የተለያዩ የልማት ውጥኖችን ማሳካት ተቻለ የሚለው ነው፡፡ ይህ የሆነው ነውጠኞች እየተሹለከለኩ እንታገልለታለን የሚሉትን ሕዝብ ከመረበሽ፣ ከመዝረፍና የሽብር ወንጀል ከመፈጸም ባለፈ የሚመኙትን አገረ መንግሥት የማፍረስና የታላላቅ የልማት ዕቅዶችን የማደናቀፍ ዕቅዶቻቸውን ማሳካት እንዳይችሉ፣ ሠራዊታችንና የፀጥታ ኃይሎቻችን እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ በማድረግ የጠላቶቻችንን እኩይ ዓላማ ማምከን በመቻላቸው ነው፡፡ በ48 ሰዓታት ውስጥ፣ በጥቂት ቀናት ተዋግተን መከላከያን በመደምሰስ አዲስ አበባ እንገባለን የሚሉ ሕልመኞች ተመተው፣ አዲስ አበባ በርካታ የልማት ውጥኖች ዕውን የሚሆኑባት ከተማ ሆናለች፤›› በማለት የተናገሩት ፊልድ ማርሻሉ፣ ጠላቶች ያሏቸው ኃይሎች ሕልም ስለመምከኑ አብራርተዋል፡፡

በዚያው ንግግራቸው ግን መከላከያውም ሆነ አገሪቱ የተጋፈጡትን አደጋ አውስተዋል፡፡ መከላከያውንም ሆነ አገሪቱን የሚከፋፍል አደጋ ጠላት ያሏቸው ኃይሎች መፍጠራቸውን ተናግረዋል፡፡ በውጭ ኃይሎች ይደገፋሉ ያሏቸውና ‹‹ባንዳ›› ብለው የፈረጇቸው ቡድኖች በነፃ አውጪ ስም እንደሚንቀሳቀሱም አስረድተዋል፡፡ አገሪቱን ብቻ ሳይሆን መከላከያውን ለመበታተን እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡

እንደ ፋኖ ያሉ የታጠቁ ቡድኖችን በሰፊው በመርገም በተከበረው 128 ኛው የዓድዋ ድል በዓል ላይ ፊልድ ማርሻሉ መከላከያው የገጠመውን አደጋን በተመለከተ ሲናገሩ፣ ‹‹በውጭ ኃይሎች የተገዙ ባንዳዎች ዋነኛ ጠላት አድርገው የሚፈርጁት የገዛ አገራቸውን መከላከያና የፀጥታ ኃይል ነው፡፡ እዚያም እዚህም እሳት እየለኮሱ በሥምሪት እንዲወጠርና ኃይሉ እንዲበታተን ተረባርበዋል፡፡ ውስጣዊ አቅሙን ለማዳከም፣ በከበባ አጥቅተው ትጥቁን ዘርፈው ባዶ እጁን ለማስቀረትና አገሪቱ የውጭ ጠላት ቢመጣ የምትከላከልበት አቅም እንዳይኖራት ለማድረግ መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፍተውበታል፤›› ብለዋል፡፡

ፊልድ ማርሻሉ የጠቀሱት ሥጋት በመከላከያ ተቋም ብቻ የሚገደብ ሳይሆን፣ መላው አገሪቱንም የሚያሠጋ መሆኑ በብዙዎች ይወሳል፡፡ በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ያለማቋረጥ በየቦታው የተፈጠሩ ግጭቶች ለኢትዮጵያ ህልውናም አሥጊ መሆናቻው ተደጋግሞ ተወስቷል፡፡ በአማራ ክልል አሁን ተባብሶ የቀጠለው ጦርነትም ቢሆን የዚህ ሥጋት አንድ አካል ሆኖ ነው የሚቀርበው፡፡

ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በወጣው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ከሕግ ውጪ በሲቪሎች ላይ የሚፈጸም ግድያ በአማራ ክልል መከሰቱን ይፋ አድርጓል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በመርአዊ ከተማ በመንግሥት ኃይሎች መፈጸሙ የተነገረው የንፁኃን ዜጎች ግድያ ብዙዎችን ማስደንገጡ ይታወሳል፡፡ ከዚያ ቀደም ብሎም የአገር ውስጥና የውጭ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች በአማራ ክልል የሚካሄደው ጦርነት ከፍተኛ የቁስና ሰብዓዊ ውድመት ምንጭ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ሪፖርት አድርገዋል፡፡

በአማራ ክልል ላለው ቀውስ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈለግ ብዙዎች ውትወታ እያደረጉ ነው፡፡ አሜሪካን ጨምሮ የአውሮፓ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁሉን አቀፍ ሰላማዊ ንግግር እንደሚያስፈልግ በተደጋጋሚ ሲያሳስቡ ቆይተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -