Monday, May 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው የገጠመው ተግዳሮትና የግማሽ በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ የተለያዩ ተግዳሮቶች እየገጠሙት ነው ቢባልም፣ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በ2016 ግማሽ የሒሳብ ዓመት ከ15.2 ቢሊዮን ብር በላይ የዓረቦን ገቢ ማሰባሰብ መቻላቸው ተጠቆመ፡፡

የኩባንያዎችን የ2016 ግማሽ የሒሳብ ዓመት አፈጻጸም የሚያመለክተው መረጃ በግማሽ ዓመቱ ያሰባሰቡት የዓረቦን መጠን፣ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ32 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ኩባንያዎቹ በ2015 የመጀመርያ ግማሽ ዓመት አሰባስበው የነበረው የዓረቦን መጠን 11.7 ቢሊዮን ብር በመሆኑ፣ የግማሽ ዓመቱ አፈጻጸም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ3.5 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ያመላክታል፡፡

በግማሽ የሒሳብ ዓመቱ የተሰበሰበው የዓረቦን መጠን በኢንዱስትሪው በከፍተኛነቱ የሚጠቀስ መሆኑን ያነጋገርናቸው የኢንሹራንስ ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች ይጠቅሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ በግማሽ ዓመቱ የተሰበሰበው የዓረቦን መጠን ይሰባሰባል ተብሎ ከታቀደው አንፃር ዝቅተኛ ስለመሆኑም ያብራራሉ፡፡ በግማሽ ዓመት ከ3.5 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው ዓረቦን መጠን ከዚህም በላይ ሊሆን ይገባ እንደነበር ያመለክታሉ፡፡

18ቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በግማሽ ዓመቱ ያሰባሰቡት የዓረቦን መጠን በዚህን ያህል ደረጃ ዕድገት ያሳዩበትም ዋነኛ ምክንያት፣ ከዋጋ ንረት ጋር ተያይዞ በተለያዩ የመድን ሽፋን አገልግሎታቸው ላይ ከዚህ ቀደም ሲያስከፍሉ በነበሩት ዓረቦን ላይ የተወሰነ ጭማሪ በማድረጋቸው የተገኘ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ባለፈው ዓመት ያደረጉትን የዓረቦን ጭማሪ ብሔራዊ ባንክ እንዲቀንሱ በማድረጉ የግማሽ ዓመቱ የዓረቦን አሰባሰብ ላይ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡

የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች መቀዛቀዝም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የዓረቦን አሰባሰብ የተጠበቀውን ያህል አለመሆኑን ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

በአገር ውስጥ ያለው አለመረጋጋትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ማነቆ የሆኑ ተግዳሮቶች መፈጠራቸው፣ ብዙዎቹን የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዕቅዳቸው ልክ እንዳይጓዙ ማድረጉንም እኚሁ የኢንሹራንስ ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡

የሩስያና የዩክሬን ጦርነት፣ በቅርቡ ደግሞ የእስራኤልና የሀማስ ጦርነቶች በተለይ የማረን የኢንሹራንስ ዘርፍን በዓለም አቀፍ ደረጃ የጎዳ መሆኑን አስታውሰው በኢትዮጵያም ከዚህ ዘርፍ የሚሰባሰበው የዓረቦን መጠን እየቀነሰ መምጣቱንም ጠቁመዋል፡፡

የኅብረት ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ኩባንያ የቦርድ ሊቀመንበር ወ/ሮ መሠረት በዛብህ እንደገለጹት ደግሞ፣ ከኅዳር 2016 ጀምሮ ኢንዱስትሪው ቀዝቅዞ ማለቁን ይጠቁማሉ፡፡

በግማሽ ዓመቱ የእርሳቸው ኩባንያ በግማሽ ዓመት ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ ዓረቦን በማሰባሰብ ከፍተኛ የሚባል አፈጻጸም ቢያሳይም ከኅዳር 2016 ወዲህ ግን አጠቃላይ ኢንዱስትሪው ላይ መቀዛቀዝ በመታየቱ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ላይም ተፅዕኖ ማሳረፉን ገልጸዋል፡፡

ኢንቨስትመንት በተቀዛቀዘ ቁጥር ኢንዱስትሪው ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉ አይቀርም ያሉት ወ/ሮ መሠረት ባለፉት ጥቂት ወራትም ይህ ተፅዕኖ በግልጽ መታየቱን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ባንኮች ላይ የተጣለው የብድር ገደብም የራሱ የሆነ ተፅዕኖ እንዳሳረፈም አመልክተዋል፡፡

የብድር ገደቡ በተለይ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች እንዳይፈጠሩና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን ስለሚያቀዛቅዘው አዲስ የኢንሹራንስ ደንበኞችን ለማፍራት ያለመቻሉ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ይህም ብዙዎቹ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የነበሯቸውን ደንበኞች ውል እያደሱ እንዲቀጥሉ በማድረጋቸው የተጠበቀውን ያህል ዕድገት ሊያመጣ አልቻለም፡፡

የኢንዱስሪው የዓረቦን መጠን ቢያድግም በተጠበቀው ደረጃ ላለመሆኑ እንደ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችለው ምክንያት ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የዓረቦን ዋጋ ከፍ ያለ ነበር፡፡

ነገር ግን ብሔራዊ ባንክ ይህንን የዓረቦን መጠን ከ30 እስከ 50 በመቶ ቀንሱ ስላለ በዚህ መሠረት ከ30 እስከ 50 በመቶ ቅናሽ በማድረግ ሽፋን እየሰጡ መሆኑ የዓረቦን ገቢው በታሰበው ደረጃ እንዳያድግ አድርጎታል፡፡

ሌላው ለኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ተግዳሮት ሆኖ ለተከታታይ ዓመታት የዘለቀው የዋጋ ንረት መሆኑን የገለጹት የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ የሥራ ኃላፊዎች ይህ የዋጋ ንረት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የጨመውን የዓረቦን ገቢ መልሶ እየወሰደው መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

በአገሪቱ እየተስተዋለ ያለው የዋጋ ንረት ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን በእጅጉ ስለመጉዳቱ የገለጹት እነዚሁ የሥራ ኃላፊዎች ይህም በሚከፍሉት የካሳ ክፍያ ላይ ጫና እያሳደረባቸው ነው፡፡

የግማሽ ዓመቱ የዓረቦን አሰባሰብ መጠን ሲታይ አሁንም ከፍተኛውን የገበያ ድርሻ በመያዝ መንግሥታዊው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በቀዳሚነት ተቀምጧል፡፡

ለዓመታት የኢንዱስትሪውን ከፍተኛ የገበያ ድርሻ ይዞ የቆየው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ በግማሽ ዓመቱ ከተሰበሰበው አጠቃላይ የዓረቦን ውስጥ ከ39 በመቶ በላይ የሚሆነውን ድርሻ ስለመያዙ ያመለክታል፡፡

ከግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ደግሞ አሁንም አዋሽ ኢንሹራንስ ቀዳሚ ሲሆን በግማሽ ዓመቱ ከተሰበሰበው ጠቅላላ የዓረቦን መጠን ውስጥ ከ9.2 በመቶ በላይ የሚሆነውን ይዟል፡፡ ኅብረት ኢንሹራንስ ሰባት በመቶ ድርሻ እንዳለው ተመላክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች