Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለአዋሽ ኢንሹራንስ አዲስ ሥራ አስፈጻሚ ተሾመ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከግል ኩባንያዎች ከፍተኛውን የገበያ ድርሻ የያዘው የአዋሽ ኢንሹራንስ አ.ማ. የዳይሬክተሮች ቦርድ ከዚህ ዓለም በሞት በተለዩት ኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ምትክ አዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰየመ፡፡

የኢንሹራንስ ኩባንያውን ከአራት ዓመታት በላይ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሲያገለግሉ የነበሩትን አቶ ጉዲሳ ለገሠን ተክተው፣ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ኩባንያውን እንዲመሩ የተሰየሙት አቶ ጂባት ዓለምነህ ናቸው፡፡ ቦርዱ ከትናንት በስቲያ ባካሄደው ስብሰባ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንዲያገለግሉ የተሰየሙት አቶ ጂባት፣ ይህንን ኃላፊነት እስከተረከቡበት ጊዜ ድረስ በምክትል ሥራ አስፈጻሚነት (ኦፕሬሽን ቺፍ) ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

አዲሱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሹመታቸው እስኪፀድቅ ድረስ፣ በተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚያገለግሉ መሆኑን የሚያመለክተው የኩባንያው መረጃ፣ አቶ ጂባት የአዋሽ ኢንሹራንስ አ.ማ. ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው በቋሚነት እንዲያገለግሉ፣ ቦርዱ ሹመቱ ይፀድቅለት ዘንድ በሕጉ መሠረት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚያመለክት መሆኑም ታውቋል፡፡ አቶ ጂባት በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ23 ዓመታት በላይ በሥራ የቆዩ ሲሆን፣ ሥራ የጀመሩትም በአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ውስጥ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ኩባንያውን ከተቀላቀሉ በኋላ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሠሩ ሲሆን፣ የተለያዩ ቅርንጫፎችን በሥራ አስኪያጅነት መርተዋል፡፡ በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ደግሞ የኩባንያው የካሳ ክፍል ዳይሬክተር በመሆን ለረዥም ጊዜ ሠርተዋል፡፡

ላለፉት አራት ዓመታት ደግሞ በምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ የኩባንያው ሦስተኛ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን የተሰየሙት አቶ ጂባት፣ በትምህርት ቤት ዝግጅታቸው በፋይናንስና ዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ የቢኤዲግሪ፣ እንዲሁም በዴቨሎፕመንት ስተዲስ የኤምቢኤ ዲግሪ አላቸው፡፡

አዋሽ ኢንሹራንስ አ.ማ. በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙ 18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በኢንዱስትሪው ከግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ኩባንያው የ2015 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙ እንደሚያሳየው፣ ዓመታዊ የዓረቦን አሰባሰብ ምጣኔውን ከ2.44 ቢሊዮን ብር በላይ አድርሷል፡፡ ይህም በኢንዱስትሪው ከግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከፍተኛውን የዓረቦን መጠን በማሰባሰብ ቀዳሚ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ከ28 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ገበያ ላይ የቆየው አዋሽ ኢንሹራንስ የተከፈለ ካፒታል መጠኑን ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን፣ የተፈረመ ካፒታሉ ደግሞ አራት ቢሊዮን ብር ነው፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች