Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ጥሬና ብስል!

ከቦሌ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ከተማው ሳይፈርስ፣ ሰላም ሳይደፈርስ፣ በሽታ ሳያጠቃን፣ እግር መጓዝ ሳይታክተው ታክሲ ጠፋ ተብሎ አካባቢው ይታመሳል። የአራት ኪሎ ታክሲ ፈላጊዎች ዓይን ወዲያና ወዲህ ይቃብዛል። የታክሲ ዘር ግን ጠፍቷል። ከሰማዩ በቀር ሰማያዊ ቀለም ራሱ የሸፈተብን ይመስላል። የማይሸፍትብን ግን ምን ይሆን? የማያድምብን ማን ይሆን? የማናድምበትስ? የማንነጫነጭበት ሕግና ሕግ አስከባሪስ? ጥያቄ ብቻ። ‹‹ኧረ ዛሬስ በጤና አይመስለኝም፣ ኧረ አገሩ ሰላም አይመስለኝም…›› ትላለች አንዲት ጠና ያለች ሴት በነጠላ ፊቷን እየሸፈነች። ‹‹ምንድነው ቀኑ ዛሬ? የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ነው እንዳይባል በቀደም አለፈ…›› አንድ ወጣት ግራ ተጋብቶ ይናገራል። ‹‹ታዲያ ለዓድዋ ዘመቻስ ቢሆን የተመምነው የዛሬ 128 ዓመት ነው። ያኔ የተጓዝነው በእግር፣ ያሸነፍነው በባዶ እጅ፣ ወኔ ውሎ ይግባና፡፡ ታክሲ ጥበቃና ዓድዋን ምን አገናኛቸው?›› ብሎ ሌላው ሲናገር፣ ‹‹ምን ይታወቃል? ዘንድሮ እኮ ወራሪው በየአቅጣጫው ነው። የዓድዋን ድል መታሰቢያ ባከበርን ማግሥት አናዳጆች ተነስተውብን እንደሆነስ…›› ትላለች ሴትዮዋ። ሽሙጥ መሆኑ ነው!

‹‹ጉድ ፈላ በአንድነታችን ስንወደስ የኖርን ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ተጠማምደናል እያልሽ ነው? እንዴት እንዲህ ትያለሽ?›› ወጣቱ ነገር ሲያበላሽ፣ ‹‹ያላልኩትን አለች እያለ ያነካካኛል እንዴ ይኼ? ምነው ሰው እንዲህ ነገር ለማቀጣጠል ከክብሪትና ከቤንዚን ቀደመ?›› ብላ አንገቷን ወዘወዘችበት። ‹‹እህ ወደን መሰለሽ? ትብታባችን እያደር ባሰበታ። ሸምጋዩም ያለዘበ እየመሰለው እሳት ላይ ቤንዚን ያርከፈክፋል። በቀናነት የታሰበውና የታለመው ዕቅድ ሳይቀር ድምፁ ሳይሰማ መጣ ተብሎ ድምፁ ሳይሰማ ይሸኛል። ሥራችን ሁሉ በአሉታዊ ጎኑ ብቻ ይተረጎማል። ሲተረጎምም ያለ ሞጋችና አሳማኝ ምክንያት ይታጠፋል። እስኪ በየት አገር ነው ወላጅ ሕፃን ልጁን ጡት ነከሰ ብሎ ወተት የሚነፍገው?›› እያለ ፈንጠር ብሎ የቆመ ጎልማሳ የሚገባንም የማይገባንንም ስንክሳር እያጣመረ ይናገራል። በዚህ መሀል አንድ ሚኒባስ ብቅ አለች። ተረኞቹ ተሳፋሪዎች ተሠልፈን ገባን። አንድ መንገድ፣ አንድ አማራጭ፣ አንድ ሐሳብ፣ ግን ብዙ ተጓዥ!

ጉዞ ጀምረናል። ‹‹ካልተሳፈሩበት ቶሎ ተሽቀዳድሞ፣ ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ እንዳልተባለላችሁ፣ ዕድሜያችን ቆሞ ሥራችን ቆሞ ምነው ጠፋችሁ ዛሬ? ለማን ተዋችሁን?›› ጋቢና የተሰየሙ አዛውንት ሾፌሩን ይጠይቃሉ። ‹‹ኧረ ተውኝ አባት። ምቀኛ ብቻ እኮ ነው የከበበኝ እኔንማ…›› ሾፌሩ የቆረቆረው ነገር እንዳለ ያስታውቃል። ‹‹ምቀኛ ከሩቅ አይመጣ…›› አዛውንቱ በጥበብ ያወጣጡታል። ‹‹ታዲያስ እኔ ዛሬ ስብሰባ እንደሚደረግ አልሰማሁም፣ የነገረኝ የለም። ገና ለገና ሥራዬን በትጋት ስለምሠራና ጥሪት ለመያዝ ስለምባክን የመንግሥት ወገን ነው ለማስባል አትንገሩት ተብሎ ይኼው ከስብሰባ አስቀሩኝ…›› ሲላቸው፣ ‹‹አሃ ምቀኝነቱ እርስ በርስም ነው?›› አሉት። ‹‹አይገርምም? ቆይ ግድ የለም…›› ሾፌሩ የእኛ መቸገር ሳይቸግረው የእሱ ስም በአግቦ ሽሙጥ መበላቱ ያብከነክነዋል። የአካባቢው ተወካይ ሆኖ በሰሞኑ ስብሰባ አለመገኘቱ አናዶት የታክሲ ጠባቂዎች መጉላላት ግን ግድም አልሰጠው፡፡ ‹‹ያ መከረኛ አበል ስንቱን አበላሸው…›› ስትል ያቺ ሴት ከመሀል ወንበር ሰማናት፡፡ ሊጀመር ነው!

 ‹‹ድሮስ ለእኛ ማን ያስባል? ሁሉም ለራሱ ጥቅም ብቻ ነው የቆመው…›› ትላለች አንዲት ወጣት። ‹‹የጥቅም ጉዳይ ከተነሰማ በዚህ ሁላችንም ብንሆን አንታማም፡፡ እርግጥ ነው የጥቅሙ ዓይነትና የሚገኝበት መንገድ ይወስነዋል፡፡ ለምሳሌ እኔ በቀደም ዕለት የምኖርበት ወረዳ ከቤት ካርታ ጋር በተያያዘ ሄድኩ፡፡ ለጊዜው የመሬትና የንብረት ጉዳይ ስለታገደ ዕግዱ እስኪነሳ ይጠብቁ ተባልኩ፡፡ ዕግዱ ሲነሳ ለማወቅ ስልክ ቁጥራችሁን ስጡኝ ስል የእርስዎን ይስጡኝ አለኝ አንድ ጮሌ፡፡ ከሰጠሁት በኋላ በዋትስአፕ ነው የምደውልልዎት አለኝ፡፡ ምክንያቱን ስጠይቀው ጉዳዬን አስጨርሶ ለማጠናቀቅ የምከፍለውን የገንዘብ መጠን የሚነግረኝ በዋትስአፕ እንደሆነ ሲነግረኝ ደነገጥኩ…›› ብለው አንዲት እናት ከሾፌሩ ጀርባ ሆነው አጠገባቸው ላለ ወጣት ሲነግሩት ሰማን፡፡ በገጠማቸው ጉዳይ እየተገረምን ሳለ፣ ‹‹በቀደም ዕለት የክፍላተ ከተሞች ስብሰባ ሲካሄድ ጠርተውኝ ብገኝ ኖሮ ይህንን ጉድ እዘረግፈው ነበር…›› ብለው ሲስቁ አብረናቸው ሳቅን፡፡ ‹‹እንዲህ ዓይነት ጉድ የተሸከመች አገር ውስጥ መኖር ዕርግማን ነው…›› የሚሉት አዛውንቱ ሲሆኑ፣ ሾፌሩ ግን እንደ ማኩረፍ እያደረገው መሪውን መዘወር ቀጠለ፡፡ ጎበዝ ጥቅም እንዲህ ነው!

ጉዟችን ቀጥሏል። ወያላው በገዛ እጁ መድረኩን አጣቦ መፈናፈኛ ጠፍቶት አንዳችንን ካንዳችን ገንዘብ ያቀባብለናል። ‹‹አተርፍ ባይ አጉዳይ…›› ትላለች ከኋላ ወንበር። ሞተሩ ላይ ተቀምጦ ከሥር ወበቅ ከላይ ንፋስ እያጣፋው የተቀመጠ አንዱ ደግሞ፣ ‹‹ግን ይኼ ሁሉ ሰው ሲጓዝ የሚውለው ሥራ የለውም እንዴ?›› ብሎ ይጠይቃል። ‹‹ካልተቀመጡ ሥራ አይሠራም በቃ? የቢሮ ሥራ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ቀረ። ተቀምጦ መብላት ግን አሁንም ያለ መሰለኝ…›› ይላል ከመጨረሻ ወንበር አንዱ። ‹‹እናንተ ሥራውን ትላላችሁ ኢትዮጵያ ራሷ ድሮ የቀረችውን?›› ትላለች ሌላዋ። ‹‹እግዚኦ ይኼ  ጭፍን ጥላቻ፣ ፍረጃ፣ ድጋፍና ተቃውሞ በቃ እያደር ይባስበት?›› የሚለው ጎልማሳው ነው። ይህንን ሁሉ ወግ ሲታዘብ የቆየ ዝንጥ ብሎ የለበሰ ጎልማሳ፣ ‹‹አሁንና ድሮ እየተባባልን እርስ በርስ ከምንተራረብ በጊዜያችን ምን ሠራንበት ብለን ራሳችንን ኦዲት ብናደርግ፣ ለምን የኑሮ ውድነት መጫወቻ እንደሆንን በቀላሉ ይገባን ነበር…›› ሲለን ሰማነው፡፡ እውነቱን ነው!

‹‹ኤድያ ኢኮኖሚውን ግብርና እየመራው እንኳን ምሁር ገበሬም አልተከበረም…›› ብላ አዋቂ መስላ አንዷ ስትሰርብ፣ ‹‹እህቴ ዋናው የተነሳው ጉዳይ በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ የገጠመን ሳንካ እንጂ፣ የግብርና ኢኮኖሚ ትንተና አይደለም…›› ብሎ ቱግ አለ ያ ሞተር ላይ የተቀመጠው። ‹‹ምን ነበር ጥያቄው?›› ከመባሉ፣ ‹‹ጥያቄውማ ይኼ ሁሉ ሰው ቀኑን ሙሉ ሲጓዝ የሚውለው ምን እየሠራ ነው?›› ብሎ የራሱን ጥያቄ ደገመው። መልሱ ሁላችንንም ፈገግ አሰኘን።  ‹‹ለማንኛውም ወንድሜ የሰጠን ምሁራዊ ትንታኔ የእኔንም ጥያቄ ዳሰስ ያደረገ ስለሆነ እንጂ፣ ዋናው ጉዳይ አርፈን ሥራ ላይ ብናተኩር ኖሮ ሚሊዮኖች ተርበው ልመና አንወጣም ነበር፡፡ እኛም ኑሮ ተወደደ ብለን ሌላ ጉዳይ ያለ የተወጠረውን መንግሥት አናስጨንቅም ነበር፡፡ ጠግበን በልተን፣ ለብሰን አምሮብን፣ ለሌሎች መትረፍ የሚያስችል ደረጃ ላይ እንገኝ ነበር ነው መልዕክቱ…›› ብሎ ነገሩን ደመደመው፡፡ ተገቢ ነው!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹እኔ ኢትዮጵያዊ ባልሆን ይቆጨኝ ነበር…›› ብሎ አንዱ አዲስ አጀንዳ ጀመረ። ‹‹ብቻህን ደስ አይልም፣ ምነው በደንብ ዘርግፈው እንጂ ይውጣልህ…›› ከአጠገቡ የተቀመጠ የቲክቶክ ሱሰኛ መሳይ ቆሰቆሰው። ‹‹ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል…›› ብሎ ያኛው ሳይጨርስ፣ ‹‹መቼስ ቢሆን ሆድ ሞልቶ ያውቃል እንዴ?›› አንደኛዋ ስታቋርጠው፣ ‹‹አስጨርሱኛ፣ ስታስጨርሱኝ እኮ ነው የሚገባችሁ። እንዴ ወሬ እኮ ሥልጣን አይደለም ያልቃል፣ ሺሕ ዓመት አልገዛ ማለቴ አላወራ…›› እያለ ጥቂት በነገር አዋዛን። ‹‹እንዲያው ያን ጊዜ በአንድነት ነቅለን ወጥተን ዓድዋ ድረስ ተጉዘን በአንድ ክንድ ጠላትን አባረን ስናበቃ ምነው ዛሬ ለመከፋፈል እጅ ሰጠን? ምነው ዛሬ ለቁርሾና ለቂም ጆሮ ሰጠን? ምን ሆነን ነው የእነዚያን ጀግኖች ወኔ መላበስ አቅቶን በየገመገሙ እየተባላን የጠላት መሳቂያ የምንሆነው…›› ብሎ ሲብከነከን ሐዘን ይሁን ቁጭት ውስጣችን ቁጣ ተቀሰቀሰበት መሰል ዝም አልን፡፡ ያሰኛል!

‹‹ይቅርታ ወንድም፣ አንድም ይኼ የጅምላ ውክልና ነው እውነትን አጥርተን እንዳናይ እያጥበረበረን ያለው። ለምሳሌ ለእኔ ዓድዋ እንደ ማንኛውም የሰው ልጅ አሳፋሪ የጥፋት ፍጅት ይታየኛል ብል አትደንግጡ። ምክንያቱም እኔ በፖለቲካና በመልከዓ ምድራዊ ክልል በተወሰነ ዜግነት ብቻ አላምንም። የሰው ልጅ ዘር ነኝ ብዬ አምናለሁ። ተሸናፊውም አሸናፊውም የእኔ ወገን ነው ብዬ አምናለሁ። ‹ኢት ኢዝ ማይ ራይት›፣ ‹እንቢ!› ‹ዘራፍ!› የሰው ዘር አባል ነኝ ነው ፉከራዬ። በአጭሩ የእኔና መሰሎቼ አስተያየትና አቋም ታሳቢ ቢደረግ፣ ከተቻለ ደግሞ ሁላችንም በመላው የሰው ዘር አባልነት ብናምንና ኬላ ብንጥስ የሚሻለው እሱ ነው…›› ከመጨረሻ ወንበር አንገቱ ላይ እራፊ ጨርቅ የጠመጠመ ገጣሚ መሳይ ተናገረ። ሁሉም ተሳፋሪዎች ዓይናቸውን አጉረጥርጠው አዩት። አራት ኪሎ ደርሰን ወያላው ‹‹መጨረሻ…›› ብሎ ታክሲያችን ጥግ ስትይዝ አዛውንቱ፣ ‹‹እናንተ ልጆች እባካችሁ እውነት አጠራን እያላችሁ ተደናግራችሁ አታደናግሩ አደራ፣ አደራ፡፡ ምንም ቢሆን ምን ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም…›› እያሉ ወረዱ። ወጣቱ በተናገረው ነገር አፍሮ ይሁን እንጃ፣ ‹‹ከዓድዋ ወዲህ ነን ወይስ ወዲያ?›› እያለ ግራ ገብቶት ሲቆም፣ ‹‹አዬ ጉዳችን ይህ አጉል ዘመናዊነትና ጭሳ ጭስ ስንቱን አበላሸው…›› ሲሉ እኚያ እናት፣ ‹‹ጥሬና ብስሉ ተቀላቅሎ እኮ ነው መከራ የምናየው…›› የሚሉት አዛውንቱ ነበሩ፡፡ መልካም ጉዞ!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት