Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየግሉ ዘርፍ ሊከተለው የሚገባው የቢጃይ ናይከር (ኢንጂነር) መንገድ

የግሉ ዘርፍ ሊከተለው የሚገባው የቢጃይ ናይከር (ኢንጂነር) መንገድ

ቀን:

በቶፊቅ ሽኩሪ

የሰው ልጅ ሕይወቱን በተቃናና በቀለለ መንገድ ይመራ ዘንድ በሚያደርገው የዕለት ከዕለት ሩጫ ውስጥ ከእሱ ዘመን በፊት ስለነበሩ፣ በእሱም ዘመን በዙሪያው እየተከናወኑ ስላሉ፣ እንዲሁም ወደፊት ሊከናወኑ ስለሚችሉ ኹነቶች በቂ የሆነ ዕውቀትና ግንዛቤ ይኖረው ዘንድ አጥብቆ ይሻል። ታዲያ እነዚህ በየዘመናቱ የተከናወኑ ታሪካዊ ክስተቶችና ኹነቶች በዘመኑ በነበሩ የመረጃ መለዋወጫ ቋቶች ውስጥ በእልፍ ተሰድረው ከትውልድ ትውልድ በመተላለፋቸው፣ ትውልድ እነዚህን የመረጃ መዛግብት በማገላበጥና በመፈተሽ የሚፈልገውን መረጃ በዓይነትና በብዛት ለማግኘትም ዕለት ከዕለት ይታትራል። አሁን ባለንበት ዘመንና ጊዜ ታዲያ ከትውልዱ የሥልጣኔ ዕድገት ጋር ተያይዘው የሚመጡ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሰው ልጅ መረጃን ለማግኘትም ሆነ፣ በዓለም ዙሪያ ግንኙነትን ለመፍጠር የሚያደርገውን ሩጫ ቀላልና ቀልጣፋ ያደርግለታል።

በተጨማሪም ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበቱንም በአግባቡ እንዲጠቀም በመርዳት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። በዚህም ምክንያት ትውልድ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ከማኅበራዊ ሚድያዎች ጋር ያለው ትስስርና ቁርኝት በእጅጉ እየጨመረ መምጣቱ በብዙዎች ዘንድ የሚታመንበት ጉዳይ ሆኗል። አሁን ዘመኑ የደረሰበት የኢንተርኔት አገልግሎትን በመጠቀም ማንኛውም ሰው የፈለገውን መረጃ በፈለገው ሰዓት ከቤቱ ሆኖ ያገኛል።

- Advertisement -

ከመደበኛ መገናኛ ብዙኀን ይልቅም የማኅበራዊ ሚዲያ በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ እየሆነ ነው። በተለይም ስማርት ስልኮች ከተፈጠሩ ወዲህ የማኅበራዊ ሚዲያዎች አጠቃቀም በእጅጉን መጨመሩ የሚታይ እውነት ነው። ታዲያ ይህ የዘመኑ በረከት የሆነው የቴክኖሎጂ ውጤት በተለይ ፌስቡክ ባለሁለት ሥለት በማለት የሚጠሩት ሲሆን፣ ከፊሎች ቴክኖሎጂውን በአግባቡ ሲጠቀሙበት ከፊሎች ላልተገባ ድርጊት ሲጠቀሙበት እየተስተዋለ ነው፡፡ ይህም እንደ አገር ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳዳሩ እውነት ነው፡፡ በዚህ ማኅበራዊ ሚዲያ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ሲሠሩበት መታዘብ የተቻለ ሲሆን፣ በተወሰነ ደረጃ ግለሰቦችና ተቋማት አግልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበት ምርት የሚሸጡበት የዲጂታል ገበያ (Digital Market Place) በማድረግ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡

ማኅበራዊ ሚዲያን በተለይ ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንደ መሆኑ መጠን፣ ለሥራ ፈጠራ የሚያነሳሱ ብሎም የሚደግፉ አካላት ማግኘት እምብዛም አልተቻለም፡፡ በአንድም ይሁን በሌላ በተለይ የተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ የተወሰኑ ግለሰቦች ያላቸውን ሀብት ጥቂቱን እንኳን ለወጣቱ በመለገስ ሠርቶ ከማሠራትና የሥራ ዕድል ከመፍጠር ይልቅ፣ ያላቸውን ሀብትና ዝና የታይታ መድረክ ሲያደርጉት ይስተዋላል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ካላቸው ሀብት እያካፈሉ ወጣቱ ሐሳብ ይዞ በፋይናንስ እጥረት የተለጎሙ እጆች እንዲሠሩ፣ ብሎም ወጣቶች  ሐሳባቸውን እንዲገልጹና ተወዳድረው የሥራ መነሻ ካፒታል (Seed Capital) እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ በቅርብ ጊዜ ጥሩ ጅማሮ ያደረገው ባለፀጋ ቢጃይ ናይከር (ኢንጂነር) (የ2015 ዓ.ም. የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት በንግድና በሥራ ፈጠራ ዘርፍ ተሸላሚ መሆኑን ልብ ይሏል) ይጠቀሳል፡፡

ቢጃይ (ኢንጂነር) በ15 ሺሕ ብር በተገኘ ብድር በመነሳት የተለያዩ ማሽነሪዎች በማምረት ሥራውን የጀመረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም በተለይ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽኖች በማምረት ለአገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ ነው፡፡ እሱ መደበኛ ባልሆነ መንገድ በማኅበራዊ ሚዲያ ውድድር እያካሄደ ለሥራ መነሻ ካፒታል እየሰጠ ይገኛል፡፡ የቢጃይ መንገድ በተለይ ወጣቶች ከመደበኛ የፋይናንስ ተቋማት ከፍተኛ መጠን ያለው ዋስትና (Collateral) ስለሚጠየቁ፣ በዚህ ችግር ሳቢያ ሐሳባቸውን ይዘው ለተቀመጡ ወጣቶችና ሥራ ፈጣሪዎች አዲስ ተስፋን የጫረ ክስተት ሆኗል፡፡ 

‹‹እኔ የምሰጠው 100 ሺሕ ብር (አሁን 500 ሺሕ ብር ደርሷል) ዘር ነው፣ ዘር ለገበሬ ሲሰጥ ማሳውን ይዘራዋል እንጂ አስፈጭቶ አይበላውም…›› በማለት ስለሥራው የሚገልጸው ቢጃይ፣  እስካሁን በዚህ የዘር ፈንድ ዘርተው የተሻለ ሀብት እንዲፈጥሩ ለማስቻል ወደ 2.5  ሚሊዮን ብር ገደማ በማውጣት የፈጠራ ሐሳብ ያላቸው ተወዳድረው ለሚያሸንፉ ይህ የዘር ፈንድ እንዲደረሳቸው ማድረግ ችሏል፡፡ ይህም በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ በአንድ በኩል በተቋሙ ማኅበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ተብሎ የተመደበ በጀት  በአግባቡ መጠቀም ከማስቻሉ በላይ፣ ለወጣቶች ከፍተኛ መነቃቃት አንዲፈጠር ያስቻለ ነው፡፡ ወጣቱ ማኅበራዊ ሚዲያውን በተሻለና በአዎንታዊ መንገድ መጠቀም እንዲችል ተጨማሪ ማሳያ መሆን ችሏል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በተሰጣቸው መነሻ ካፒታል ሐሳባቸውን ወደ መሬት አውርደው ሥራ የፈጠሩና ገበያንም ከዚሁ ከማኅበራዊ ሚዲያ ማግኘት የቻሉ ወጣቶችን በአንድ ወር ውስጥ ማየት ተችሏል፡፡

በተለይ የፈንድ ጉዳይ ሲነሳ ወደ መሬት ወርዶ በወጣቶች ሕይወት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲመጣና በአገራቸውም የልማትና የሰላም ግንባታ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ ወጣቶች ማፍራት ይቻል ዘንድ፣ ባለፉት ዓመታት አሥር ቢሊዮን ብር የኢትዮጵያ ወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ በመንግሥት ተመድቦ የወጣቱን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ሥራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ ይህ ፈንድ የታሰበለትን ዓላማ በቅጡና በሚገባው መንገድ ሳያሳካ፣ ለወጣቶች ዘላቂ የሥራ ዕድል ሳይፈጥርና ሕይወታቸውን ሳያሻሽል ቀርቷል፡፡ ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የገበያ ትስስር አለመፈጠር፣ በብድር አሰጣጥና አመላለስ ወቅት የነበሩ የአሠራር ግድፈቶች፣ በወጣቶች ዘንድ ስለቢዝነስና ሥራ ፈጠራ የነበረ የዕውቀት ማነስ፣ የላላ የቁጥጥር ሥርዓትና የተቋማት እርስ በእርስ አለመናበብ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በአገራችን አብዛኞቹ የግልም ይሁኑ የመንግሥት ተቋማት ይብዛም ይነስ ካገኙት ገቢ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን (Corporate Social Responsibility) ለመወጣት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ኅብረተሰቡን ሊጠቅሙ የሚችሉ፣ በተለይ በትምህርት መሠረተ ልማት ማስፋፋት፣ በጤና፣ በቤት ዕድሳት፣ ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ለኪነ ጥበብ ድጋፍ በማድረግ፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ በድንገተኛ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አደጋ ለደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ዕርዳታ፣ የመንገድ መሠረተ ልማት ዝርጋታና ሌሎች ሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ ይሳተፋሉ፡፡ ይህም ተሳትፎ በበጎ የሚታይ ቢሆንም ማኅበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ከያዙት በጀት ከፊሉን ለወጣቶች የሥራ ፈጠራ ቢያውሉት መልካም ነበር፡፡

አሁን አሁን እየተነቃቃ ባለው ማኅበራዊ ሚዲያ የተሻለ የሥራ ሐሳብ ኖሯቸው ዕድሉን ማግኘት ላልቻሉ ወጣቶች የሥራ ፈጠራ ካፒታል መነሻ የሚሆን ዘር ቢሰጣቸው፣ ወጣቶችን የበለጠ ተጠቃሚ ማድረግ ሲቻል ተቋማትም ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እግረ መንገድ መወጣት ያስችላቸዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም የሥራ ፈጠራ ውድድር ለማካሄድ ትልልቅ የአገሪቱ ሚዲያዎች እንደ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሌሎች ሚዲያዎች ብቻ ከመጠቀም ባለፈ፣ እንዲህ ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ለሰፊው ወጣት ተደራሽ በማድረግ የሥራ ፈጠራን ማበረታታት ተገቢ ይሆናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ውድድሮች በተለይ ለወጣቶች ከፍተኛ የሥራ ፈጠራ ተነሳሽነት (Entrepreneurial Motivation) ሲፈጥሩ ሐሳባቸው ተቀባይነት አግኝቶ ማሸነፍ ይችሉ ዘንድ፣ በማኅበራዊ ሚዲያው የሚታየው እርስ በእርስ መረዳዳት በራሱ አንድ የውድድሩ ድምቀት ከመሆን ባለፈ የመረዳዳት ባህልና ለወንድም ለእህት በጎ ማሰብን እንድንመለከት ያደርገናል፡፡

ይህንን ውድድር የበለጠ የግሉ ዘርፍ እንዲደግፍ ከሚያስገድዱ ምክንያቶች ዋነኛው፣ በተለይ በዚህ ዓመት በመንግሥት በኩል ምንም ዓይነት ይፋዊ ቅጥር በሌለበትና ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት  ተቋማት፣ የቴኪኒክና ሙያ ኮሌጆች ተመርቀው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ባለው የሥራ አጥ ቁጥር ላይ ሌላ የሥራ አጥ እየጨመረ ባለበት ሁኔታ መሆኑ ነው፡፡ በተለይ ከግሉ ዘርፍ አቅም ያላቸው ዜጎች ይህን ፈለግ በመከተል ለወጣቱ ተጨማሪ ተስፋን በመጫር የሥራ ፈጠራ ባህል እንዲዳብር ማድረግ፣ ቴክኖሎጂው ወደ አንድ ያመጣውን ወጣት ለማኅበራዊ ኃላፊነት ከሚመድቡት በጀት ከፊሉን እንዲህ ላለ ተግባር ማዋል ቢችሉ ለአገር የሚኖረው ፋይዳ አሌ የማይባል ነው፡፡

ይህ በኢንጂነር ቢጃይ የተጀመረው ወጣቶችን በማኅበራዊ ሚዲያ ሁሉን አሳታፊ በሆነ መንገድ በማወዳደር የሚሰጠው የዘር ፈንድ ተጠቃሚዎች፣ ገንዘቡን ከመጠቀም ባለፈ ሥራ ፈጥረው ዳግም ለሌሎች የሚያስተላልፉበት መንገድ ቢታይ መልካም ነው፡፡ እንዲሁም ገንዘቡን ከመስጠት ባለፈ በቂ ድጋፍና ክትትል ቢደረግ የተሻለ ለውጥ ማምጣት ያስችላል፡፡ ሌላው እንዲህ ዓይነት የዘር ፈንድ ለማግኘት ከሚደረጉ ውድድሮች ጀርባ መታዘብ የተቻለው ጉልህ ጉዳይ፣ ወጣቶች ዘንድ ያለው ከፍተኛ ተነሳሽነትና የሥራ ፈጠራ ነው፡፡ በተለይ በወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ የሚሠሩ መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በወጣቶች ዘንድ ያሉ ብዙ ያልተሠራባቸው ሐሳቦችን ከእነዚህ ውድድሮች ከሚደረጉባቸው ገጾች በመመልከት፣ ለሚያከናውኗቸው ሥራዎችና ወጣቶች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ለማሰማራት ጠቃሚ ግብዓቶች ማግኘት ያስችላቸዋል፡፡

ከዚህ ይበል ከሚያሰኝ የሥራ መነሻ ካፒታል (Seed Capital) ከመስጠት እኩል ልናየው የሚገበው በጎ ጉዳይ በመንግሥት አሥር ቢሊዮን ብር ተመድቦ በሚገባው ልክ ያልሄደውን የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ፣ በአሁኑ ወቅት አቅም ያላቸው አካላት በተለይ የግሉ ዘርፍ  ይህንን በጥናት ላይ የተመሠረተ አሠራር ወደ ተግባር አስገብተው ወጣቶች የራሳቸውን ሥራ እንዲሠሩ ተገቢውን ድጋፍ ቢያደርጉ ይመረጣል፡፡ በድጋፍ ውጤታማ ሆነው ከግሉ ዘርፍ ያገኙትን ገንዘብ ለሌሎች የሚያስተላልፉበት የዝውውር ሥርዓት (Revolving Fund) ቢዘረጋ የራሱ የሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል ብዬ አምናለሁ፡፡

ለማጠቃለል ያህል በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችን ባለው የፀጥታ መደፍረስና የሰላም ዕጦት ባስከተለው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ሳቢያ የወጣት ሥራ አጦች (Unemployed Youths) ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ ስለዚህ በተለይ በግሉ ዘርፍ ውስጥ ያሉ አቅም ያላቸው ግለሰቦችና ተቋማት በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ከፈጠሩት የሥራ ዕድል ባሻገር፣ ካላቸው ላይ ወጣቱ ወደ ተስፋ መቁረጥ እንዳይገባ በተለይ ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የሥራ መነሻ ካፒታል ቢቸሩ እላለሁ፡፡ ለዚህም ክትትል በማድረግ የቢጃይ (ኢንጂነር) መንገድ በመከተል (Angel Investor) በመሆን አገራዊና ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ሊወጡ የሚገባበት ጊዜ አሁን ይመስላል፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት የተለያየ መሰናክሎችን አልፈው የተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የደረሱ ግለሰቦች፣ ወጣቶችን በየአዳራሹ ብቻ በሚደረጉ የማነቃቂያ ዲስኩሮች (Motivational Discourse) ብቻ ከማነሳሳት በዘለለ ዘመን አመጣሹን ማኅበራዊ ሚዲያ በመጠቀም ብሔር፣ እምነት፣ አቋም፣ ወዘተ ሳይለዩ ወጣቶች በሐሳባቸው ብቻ ተፎካክረው የሚያሸንፉበት ሥርዓት በመዘርጋት፣ ጥቂት መነሻ ካፒታል እየሰጡና ክትትል እያደረጉ ለወጣቱ የሥራ እድል ፈጠራን በማስፋፋት አገራዊና ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ይወጡ ዘንድ እየተማፀንኩ ሐሳቤን በዚህ ላብቃ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው tofick1970@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...