Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየቀድሞ የሐረር ሙዚቀኞች አዲስ መንገድ

የቀድሞ የሐረር ሙዚቀኞች አዲስ መንገድ

ቀን:

ድምፃውያኑን መርዓዊ ዮሐንስ፣ ወጋየሁ ደግነቱ፣ ጌታቸው ተሰማ፣ ግርማ ንጋቱ፣ ንግሥት አበበ፣ መሠረት በለጠና ሌሎችንም ታዋቂ ድምፃውያንና ከያንያንን ያፈራ ነው፡፡ የቀድሞ የሐረርጌ ክፍለ ሀገር የኪነት ቡድን፡፡

የቀድሞ የሐረር ሙዚቀኞች ማኅበር ሊቀመንበር አርቲስት ሰለሞን ሽፈራው እንደሚናገረው፣ የኪነት ቡድኑ በሙዚቃውም ሆነ በሌሎች የኪነ ጥበብ ዘርፎች ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ ነው፡፡

የቀድሞ የሐረር ሙዚቀኞች አዲስ መንገድ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የቀድሞው የምሥራቅ ዕዝ ኦርኬስትራ

በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የጦር አካዴሚ፣ ሦስተኛ ክፍለ ጦርና ምሥራቅ በረኛ ‹ሰጎን› በሚል መጠሪያ የሚታወቁት የሙዚቃ ቡድኖች በደርግ ዘመን በአንድ ተጠቃለው ‹‹የምሥራቅ ዕዝ ኦርኬስትራ›› በመባል እንደ አዲስ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የምሥራቅ ዕዝ ኦርኬስትራ ሁለት ዓይነት ተልዕኮ ይዞ ይንቀሳቀሱ የነበረ ሲሆን፣ ቀዳሚው ሠራዊቱ የሚገኝበት የግዳጅ ቀጣና ድረስ በመሄድ በማዝናናትና ወኔውን በመቀስቀስ ለጦር ዝግጁ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው በበዓላት ወቅት በየቴአትር ቤቶች፣ ሲኒማ ቤቶችና በየክፍላተ አገሮች በመዘዋወር ሲሆን የጦር ሠራዊቱን በመዘዋወር ኅብረተሰቡን በሙዚቃ የማስደሰትና የማዝናናት ዓላማ ነበረው፡፡

በ1983 ዓ.ም. የደርግ ሥርዓት ወድቆ ኢሕአዴግ አገሪቱን ሲቆጣጠር ይህ የኪነት ቡድንም እንደማንኛውም የሠራዊቱ አባላት የመበተን ዕጣ እንደደረሰበትና የኪነት ቡድኑ አባላትም ለረዥም ጊዜ ከሙያቸው ርቀውና ተበታትነው መቆየታቸውን አርቲስቱ ይገልጻል፡፡

የቀድሞ የሐረር ሙዚቀኞች አዲስ መንገድ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የቀድሞ የሐረር ሙዚቀኞች ማኅበር አባላት

በ2008 ዓ.ም. የቀድሞ የምሥራቅ ዕዝ ኦርኬስትራ አባል አርቲስት ግርማ ከበደ (ዲናሬ) ኅልፈተ ሕይወትን ተከትሎ የቀድሞ የምሥራቅ ዕዝ ኦርኬስትራ አባላት በመሰባሰብ ይህን ማኅበር እንደ አዲስ ለመመሥረት ችለዋል፡፡

እንደ ሊቀመንበሩ አገላለጽ አርቲስት ግርማ ከበደ (ዲናሬ) ጦሩን ያነቃቃ፣ በሙያው ለአገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ፣ በማናቸውም የጦር ዓውደ ውጊያዎች በመገኘት የዜግነት ግዴታውን የተወጣ ነው፡፡ በሞተ ጊዜ ግን ዘመድና ወገን እንደሌለው ማዘጋጃ ሊቀብረው ሲል የቀድሞ ጓደኞቹና የሙያ ባልደረቦቹ ተጠራርተው ቀጨኔ መድኃኔዓለም እንዲቀበር ማድረጋቸውን ያወሳል፡፡ በዚህም መነሻነት የተጀመረ ግንኙነት ማኅበሩ እንዲመሠረትና ዛሬ በተለያዩ ሁነቶችና ዝግጅቶች ላይ በመገኘት የሙዚቃ ሥራዎችን ለሕዝብ እንዲያቀርብ ሆኗል፡፡

ማኅበሩ በአሁኑ ወቅት 42 አባላት ያሉት መሆኑን የሚናገረው አርቲስት ሰለሞን፣ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ፣ አራት ኪሎ ላይ ቢሮ ከመስጠት ባሻገር ሌሎችንም አስፈላጊ ድጋፍና ዕገዛዎች እያደረገላቸው ይገኛል፡፡ ማኅበሩ በሰሜኑ የአገራችን ጦርነት ወቅት የተለያዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ማቅረቡንና መከላከያ ሚኒስቴርም ደጀንነታቸውን በመመልከት ማኅበሩን ሊያጠናክሩ የሚችሉ የሙዚቃ መሣሪያዎችን በድጋፍ መልክ አበርክቶላቸዋል፡፡

አርቲስቱ እንደሚናገረው፣ ማኅበሩ በተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት ድጋፍ የሙዚቃ መሣሪያዎችን ለማሟላት ጥረት እያደረገ ቢገኝም ዛሬም የሳውንድ ሲስተም ችግር አለበት፡፡ በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ የሙዚቃ ሥራዎችን እንዲያቀርቡ ሲጋብዙም አባላቱ ከኪሳቸው እያዋጡ ሳውንድ ሲስተም ለመከራየት ተገደዋል፡፡

ማኅበሩ በአሁኑ ወቅት በባንድ ደረጃ የተሟላ ኦርኬስትራ ያለው ሲሆን፣ በድምፃውያን ደረጃ እነ መሠረት በለጠ (ጉምጉም)፣ ግርማ ንጋቱ (ፌዴራል ፖሊስ ሙዚቀኛ)፣ መሰሉ ተሰማ (ብሔራዊ ቴአትር ሙዚቀኛ)፣ ወደሬ ታደሰ (አገር ፍቅር ቴአትር ሙዚቀኛ) የመሳሰሉትን አንጋፋ አርቲስቶች ያቀፈ ነው፡፡

የምሥራቅ ዕዝ ኦርኬስትራ የማይረሳና በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ትልቅ አሻራ ያሳረፈ የኪነት ቡድን ነው የሚለው አርቲስቱ፣ ይህ በቀድሞው የኦርኬስትራው አባላት የተቋቋመው ማኅበር ከውዝዋዜ ጀምሮ ለአገር የኪነ ጥበብ ዘርፍ ከፍ ያለ ሚና የሚያበረክቱ የሙዚቃ ሰዎችን ለማፍራት ዓላማ አንግቦ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡

አሥር አለቃ ጊሹ አደአ በምሥራቅ ዕዝ ኦርኬስትራ ባለሙያ የነበረና በአሁኑ ወቅት ደግሞ በቀድሞ የሐረር ሙዚቀኞች ማኅበር በኦሮምኛ ድምፃዊነት እያገለገለ የሚገኝ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ድምፃዊው እንደሚናገረው፣ የደርግ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ የምሥራቅ ዕዝ ሲፈርስ፣ እኛም ተበታትነንና በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሠማርተን ቆይተናል፡፡ ይህ ማኅበር እንደ አዲስ ሊመሠረት የቻለውም የቀድሞ የሙያ ባልደረባችን የሆነው ግርማ ከበደ (ዲናሬ) ኅልፈተ ሕይወትን ተከትሎ ለቀብር በተሰበሰብንበት ቦታ ሲሆን፣ ለአገር ታላቅ ውለታ የዋሉና ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ግለሰቦች የትም ሜዳ መውደቅ የለባቸውም በሚል ዓላማ ማኅበሩ ሊመሠረት ችሏል፡፡

ማኅበሩ የዛሬ ቁመናውንና የመሰባሰቢያ ቢሮ ከማግኘቱ በፊት በአራዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፣ ከዚያም በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት አዳራሽ እየተገናኙ ማኅበሩን የማጠናከርና የማደራጀት ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአርቲስት አበበ ኃይሌን ‹‹አማሬሳ›› የተባለውን ሙዚቃ በተጋበዘበት መድረክ እያቀረበ እንደሚገኝ የሚናገረው አርቲስቱ፣ የማኅበሩ መመሥረት ከኪነት ሥራው ባሻገር የታመመን በመጠየቅና የተቸገረን በመርዳት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡

አርቲስት ማሙሽ ዮሴፍ በቀድሞ የሐረር ሙዚቀኞች ማኅበር ኦርጋኒስት ሲሆን ከ1976 ዓ.ም. ጀምሮ በሐረርጌ ክፍለ ሀገር በምሥራቅ ዕዝ ኦርኬስትራ በኦርጋኒስትነት አገልግሏል፡፡ የዚህ ማኅበር መመሥረት ትርጉሙ የላቀ ነው የሚለው አርቲስቱ፣ የቀድሞ የሐረርጌ ክፍለ ሀገር ሙዚቃንና አርቲስቶችን በሕዝብ ዘንድ እንዲታወሱ ከማድረግ ባሻገር፣ በተለያዩ ዝግጅቶችና ክብረ በዓላት በመገኘት ለኪነት አፍቃሪው ማኅበረሰብ ሥራዎችን በማቅረብ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡

የሐረር የኪነት ቡድን በማኅበር መልክ ዳግም መመሥረቱ በአባላቱ ዘንድ እንደታላቅ ስኬት የሚቆጠር ነው፡፡ ማኅበሩ በዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች እየተጠናከረ ሲሄድ አሁን ካለበት በተሻለ ደረጃ ጥበባዊ ዕሴቱ የጎላ ሥራ ለሕዝብ ማድረስ የሚችል መሆኑንም አርቲስቱ ይናገራል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...