Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየከተማ አስተዳደሩን የብቃት መለኪያ ፈተና የወደቁ ሠራተኞች ከደረጃቸው ዝቅ ያሉበት ድልድል ይፋ...

የከተማ አስተዳደሩን የብቃት መለኪያ ፈተና የወደቁ ሠራተኞች ከደረጃቸው ዝቅ ያሉበት ድልድል ይፋ ሊደረግ ነው

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሠራተኞችና አመራሮች የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ወስደው የወደቁ ከ7,500 በላይ ሠራተኞች፣ ከደረጃ ዝቅ ተደርገው የተመደቡበት የሥራ ዕርከን ድልድል መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ እንደሚደረግ፣ የከተማው የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ  አስታወቀ።

የከተማው አስተዳደር ታኅሳስ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባና በኮተቤ ዩኒቨርሲቲዎች አስፈጻሚነት፣ የክህሎትና የባህሪ ምዘና ፈተና ከሰጣቸው 15,151 ሠራተኞች ወይም ባለሙያዎች፣ እንዲሁም ዳይሬክተሮችና የቡድን መሪዎች 7,512ቱ መውደቃቸውን ይፋ ያደረገው ከሁለት ወራት በፊት እንደነበር ይታወሳል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ቢሮ ኃላፊ ጣሰው ገብሬ (ዶ/ር)፣ ‹‹ፈተና ያላለፉት ከደረጃ ዝቅ ብለው ነው የሚሠሩት። ድልድሉ ስለተጠናቀቀ ደብዳቤው በየተቋሙ ይሰጣል፤›› ሲሉ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

ጣሰው (ዶ/ር) የብቃት መመዘኛውን ውጤት ታኅሳስ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ባደረጉበት ወቅት፣ ፈተናው በሁለት የተከፈለ መሆኑንና አንደኛው የሠራተኛ ወይም ባለሙያ፣ ሁለተኛው ደግሞ የዳይሬክተሮችና የቡድን መሪዎች እንደነበረ ገልጸው ነበር። 

በወቅቱ ፈተናውን ከወሰዱ 10,257 ሠራተኞች ወይም ባለሙያዎች ፈተናውን ያለፉት 5,095 ወይም 50 በመቶ መሆናቸውን፣ ከ4,213 ዳይሬክተሮችና የቡድን መሪዎች ያለፉት 1,422 ወይም 34 በመቶ እንደሆኑ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

በታኅሳስ መጨረሻ ውጤቱን ባሳወቁበት ወቅት 441 የሚሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች በፈተናው ሳይገኙ መቅረታቸውን፣ እንዲሁም 681 ደግሞ በተለያዩ የደንብ ጥሰቶች ምክንያት ፈተናቸው እንዳልታረመላቸው ገልጸው እንደነበር ይታወሳል። 

ጣሰው (ዶ/ር) ትናንት ማክሰኞ የካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሪፖርተር በሰጡት መግለጫ፣ ፈተና ያመለጣቸውን እንዲሁም ስም በማሳሳትና ኮድ መጻፍ የሌለበትን በመጻፍ የመሳሰሉ የደንብ ጥሰቶችን በመፈጸማቸው ፈተናቸው ያልታረመላቸውን፣ ቢሯቸው ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር እንደገና እንዲፈተኑ ማድረጉን አስታውቀዋል። 

የብቃት ማረጋገጫ ፈተናውን የወደቁት 7,512 ሠራተኞችና አመራሮች ከደረጃ ዝቅ ተደርገው እንደሚመደቡ ያሳወቁት ጣሰው (ዶ/ር)፣ ‹‹ከሰኞ የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ቀናት የሚቆይ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየሰጠናቸው ነው፡፡ ሁለተኛው ዙር ሥልጠና ከመጪው ሳምንት ሰኞ መጋቢት 2 እስከ ዓርብ መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ይሰጣል፤›› ብለዋል። 

‹‹ዓርብ መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ምሽት ወደ ትግበራ እንዲገባ ይታወጃል፣ ሥልጠናው እንዳለቀ ወደ ትግበራ ነው የሚገባው፤›› ሲሉ ተናግረዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሠራተኞችና ለአመራሮቹ የሰጠውን የብቃት ምዘና ተከትሎ ጥር 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ለ11 ክፍላተ ከተሞችና ለሦስት ቢሮ ኃላፊዎች የሠራተኞች ድልድል እንደ አዲስ ተካሂዶ እስኪጠናቀቅ ድረስ፣ ‹‹ማናቸውም የመሬት አገልግሎቶች›› ለአጭር ጊዜያት ታግደዋል ሲል ማስታወቁ ይታወሳል። 

ሪፖርተር በመጪው ሳምንት ድልድሉ ይፋ ሲሆን የመሬት አገልግሎቶች መሰጠት ይቀጥላሉ ወይ ሲል ለጣሰው (ዶ/ር) ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል። 

የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ወስደው የነበሩት የአስተዳደሩ የመሬት ይዞታ ቢሮ፣ የመሬት ልማት አስተዳደር ቢሮና በከንቲባ ጽሕፈት ቤት ሥር የሚገኙ ሦስት ተቋማት በአጠቃላይ 3,861 ሠራተኞች የነበሩ ሲሆን፣ ከሳምንት በኋላ ውጤት ይፋ ሲደረግ ፈተናውን ያለፉት 1,680 ብቻ እንደነበሩ መገለጹ ይታወሳል።

ከመጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. አዲስ የሥራ ዕርከን ድልድል በኋላ የመሬት ሥራ አገልግሎት በቅርቡ እንደሚጀመር ሪፖርተር፣ በዘርፉ ከተሰማሩ ምንጮች ያገኘው መረጃ ያመላክታል። 

የከተማ አስተዳደሩ የፈተናው ውጤት ይፋ በተደረገ በቀጣዩ ቀን የመሬት አገልግሎቶችን በጊዜያዊነት ማገዱን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...