Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፐርፐዝ ብላክ ቢጂአይ ኢትዮጵያ የሽያጭ ውሉን ካልፈረመ ክስ ሊመሠርት እንደሚችል ገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ትሬዲንግ አክሲዮን ማኅበር ከቢጂአይ ኢትዮጵያ ጋር ያደረገው የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ሽያጭ ውል በድንገት በመቋረጡ፣ ክስ እንደሚመሠርት አስታወቀ፡፡

ፐርፐዝ ብላክ ሜክሲኮ ከተግባረዕድ ኮሌጅ አጠገብ የሚገኘውና ከቢጂአይ ኢትዮጵያ ለመግዛት የተስማማውን የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ሽያጭ፣ ቢጂአይ ኢትዮጵያ ድንገት በለቀቀው መግለጫ የሚቋረጥ ተራ ውል ባለመሆኑ፣ የሽያጭ ውሉ በድጋሚ ካልተፈረመ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስደው ትናንት ማክሰኞ የካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ሰንጋተራ የነጋዴዎች ኅብረት ሕንፃ ላይ በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤቱ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ቢጂአይ ኢትዮጵያ ከፐርፐዝ ብላክ ጋር ያደረገው የሽያጭ ውል ማሰሪያ ድርድር ሒደት መቋረጡን ያስታወቀው ሰኞ የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ነበር። 

ቢጂአይ ኢትዮጵያ የሽያጭ ውል ፊርማ በተዋዋይ ወገኖች መካከል እንዲኖርና የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ሽያጭ ዕውን እንዲሆን ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን በመግለጽ፣ ‹‹በፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ትሬዲንግ አክስዮን ማኅበር በኩል ግብይቱን ለማጠናቀቅና የሽያጭ ውሉን ለመፈረም ፍላጎትና ቁርጠኝነት ባለመኖሩ ምክንያት፣ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ሽያጭ ሒደቱን ለማቋረጥ ተገደናል፤›› ሲል አስታውቋል። 

‹‹ስለዚህም በተዋዋይ ወገኖች ቀደም ሲል በተፈረመው የቀብድ ውል ውስጥ በተገለጹት ድንጋጌዎች መሠረት የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ሽያጭ በይፋ ተቋርጧል፤›› ብሏል። 

ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ሐምሌ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. የቢጂአይ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃን ለመግዛት ጨረታ በማሸነፍ፣ አምስት ቢሊዮን ብር ክፍያን በሁለት ዓመት ለመፈጸም ውል መፈጸሙ ይታወሳል፡፡

የፐርፐዝ ብላክ የሕግ ክፍል ኃላፊ ኤርሚያስ ብርሃኑ (ዶ/ር) ጋዜጣዊ መግለጫውን በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት፣ በውሉ መሠረት ክፍያው የሚጠናቀቀው በሦስት ዙር በመሆኑ፣ ፐርፐዝ ብላክ በውልና ማስረጃ ያልፀደቀ የመጀመሪያ ክፍያ 1.15 ቢሊዮን ብር በመክፈል፣ የክፍያው በሒደት እንደሚፀድቅ የውሉ አካል በማድረግ መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡

የመጀመሪያው ስምምነት ውልና ማስረጃ በማቅረብ ከፀደቀ በኋላ፣ ፐርፐዝ ብላክ ሁለተኛውን ዙር 2.5 ቢሊዮን ብር ክፍያ ለመክፈል በማቀድ፣ ሁለተኛውን ክፍያ ለመፈጸም በቢጂአይ በኩል ከግብር ነፃ ሰነድ (ታክስ ክሊራንስ)፣ ሕንፃው ከዕዳና ዕገዳ ነፃ ስለመሆኑ ማስረጃ ማምጣት እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል፡፡ ይሁንና ቢጂአይ የግብር ሰነዶቹን አሟልቶ ማቅረብ አለመቻሉን ጠቁመዋል፡፡

ከታክስ ክሊራንስ በተጨማሪ ቢጂአይ ኢትዮጵያ መጀመሪያ የነበረው የሽያጭ መጠንና አሁን ያለው የሽያጭ ልዩነት በዚህ መሀል ያለውን ክፍያ (ካፒታል ጌይን ታክስ) መክፈል እንደሚጠበቅበት በመግለጽ፣ ቢጂአይ የሚጠበቅበትን ክፍያ ባለመክፈሉና ቦታው ያረፈበትን ሕጋዊ ካርታ ለማምጣት ፈቃደኛ አለመሆኑን አክለዋል፡፡

ቢጂአይ ኢትዮጵያ ወደ ግብር ሰነድ መሟላትና ወደ ሽያጭ ፊርማ ከመሄዱ በፊት ገዥው (ፐርፐዝ ብላክ) 2.5 ቢሊዮን ብሩን መክፈል አለበት ሲል፣ በሌላ በኩል ግን ፐርፐዝ ብላክ በበኩሉ 2.5 ቢሊዮን ብር ከመክፈሉ በፊት የግብር ሰነዶቹ ተሟልተው መቅረብ አለበት ብሏል፡፡

ሪፖርተር በሁለቱ መካከል የተደረገውን የውል ስምምነትና አሁን የተፈጠረውን ውዝግብ በተመለከተ ለቢጂአይ ኢትዮጵያ ጥያቄ ቢያቀርብም፣ በድረ ገጹ ላይ ይፋ ካደረገው መረጃ ውጪ ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት እንደማይችል፣ የቢጂአይ ኢትዮጵያ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ በኃይሉ አየለ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የፐርፐርዝ ብላክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አፈጻሚ ፍሰሐ እሸቱ (ዶ/ር) በአሁኑ ጊዜ አሜሪካ አገር እንደሚገኙ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገለጸ ሲሆን፣ ሐሙስ የካቲት 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱና መግለጫም እንደሚሰጡ የፐርፐዝ ብላክ የሕግ ክፍል ኃላፊ ኤርሚያስ (ዶ/ር) ጋዜጣዊ መግለጫውን በሰጡበት ወቅት ገልጸዋል።

ፐርፐዝ ብላክ ከጠቅላላው አምስት ቢሊዮን ብር ውስጥ 1.15 ቢሊዮን ብር የከፈለ መሆኑን፣ በሁለተኛ ዙር መክፈል የነበረበት የ2.5 ቢሊዮን ብር ጊዜ አልፏል ሲል ቢጂአይ ገልጿል፡፡ ኤርሚያስ (ዶ/ር) የሽያጭ ውሉ እንዲፈርስ ፐርፐዝ ብላክ ፍላጎት እንደሌለውና የተከፈለው ገንዘብ እንዲመለስ ጥያቄ የማቅረብ ዕቅድ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ቢጂአይ በአቋሙ ከቀጠለ ፐርፐዝ ብላክ ወደ ክስ እንደሚሄድ አቶ ኤርሚያስ ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር ያገኘው የውል ስምምነት ሰነድ እንደሚገልጸው፣ ‹‹ሽያጩ ፍፃሜ የሚያገኘው (Transaction Closing) ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት አስተዳደርና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የተሟላ ሰነድ ሲቀርብ›› ብቻ ነው፡፡

ይሁን እንጂ የሁለተኛው ዙር የ2.5 ቢሊዮን ብር ክፍያ መፈጸም ያለበት ሰነዶቹ ከመሟላታቸው በፊት ነው? ወይስ በኋላ? የሚለው ጉዳይ አወዛጋቢ ሆኖ በመቀጠሉ ቢጂአይ ኢትዮጵያ በቅርቡ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች