Sunday, May 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ቅራኔዎች በሙሉ ሰላማዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

ታላቁ የዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓልን አስመልክቶ በዕለቱም ሆነ በዋዜማው በነበሩ ቀናት ጎልተው ከተሰሙ ጉዳዮች መካከል፣ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ህልውና የመጣባቸውን ጠላት ለመመከት ሲሉ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ማድረግ የተካኑበት እሴታቸው መሆኑ ተጠቃሽ ነበር፡፡ የአገር መሪም ሆነ በየቦታው ያለ አስተዳዳሪ፣ እንዲሁም መላው ሕዝብ በሰላሙ ጊዜ ስምምነት ባይኖራቸውም በአገር ጉዳይ ግን አንድ መሆን ያለና የነበረ ባህል እንደሆነ ተደጋግሞ ተጠቅሷል፡፡ በእርግጥም በአገር ጉዳይ አንድ መሆን አለመቻል ይዞት ሊመጣ የሚችለው መዘዝ እንደ ቀልድ የሚታይ አይደለም፡፡ በመደበኛው ሕይወት ሊስማሙ ያልቻሉ የውጭ ጠላት ሲመጣ አንድ ላይ መቆማቸው ለአገር ህልውና ዋልታና ማገር መሆኑ በስፋት ይነገራል፡፡ ጀምስ ብሩስ የተባለ አገር አሳሽም ይህንን ሀቅ በጉዞ ማስታወሻው ከትቦታል፡፡ ‹‹…በሰላም ጊዜ በአጥንት እንደሚጣሉ ውሾች እርስ በርሳቸው የሚናከሱት ኢትዮጵያውያን፣ የውጭ ጠላት ሲመጣ ግን በአንድነት ተሠልፈው ይደቁሱታል…›› ማለቱ በተደጋጋሚ የተነገረ ታሪክ ነው፡፡

በዚህ ዘመን ትውልድም በተደጋጋሚ የሚስተዋለው ልዩነት ግን ከጥንቱ ጋር ይመሳሰላል ለማለት እያዳገተ ነው፡፡ ቀደም ሲል በነገሥታቱ፣ በመሣፍንቱና በሰፊው ሕዝብ መካከል የሚኖረው ልዩነት አገርን በጋራ ከመጠበቅ አግዶ አያውቅም፡፡ ምናልባት አንዳንድ ግለሰቦች ለጥቅማቸው ሲሉ በባንዳነት ለጠላት ማደራቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በመንግሥት ላይ ያኮረፈ በሙሉ ለጠላት ሲወግን በየትኛውም የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ አልተሰማም፡፡ ቅሬታ ወይም ተቃውሞ ያላቸው ግለሰቦች ሸሽተው ጎረቤት ወይም ራቅ ያለ አገር ቢሄዱ እንኳን፣ ብሔራዊ ደኅንነትንና ጥቅምን አሳልፎ የሚያሰጥ ድርጊት ውስጥ ሲሳተፉ አይታወቅም፡፡ በጣም ጥቂት ግለሰቦች በአዋራጅ ድርጊት ውስጥ በመሳተፋቸው ዘር ማን ዘራቸው በኃፍረት አንገታቸውን መድፋታቸው ስለሚታወቅ፣ ብዙዎች ከእንዲህ ዓይነቱ አሳፋሪ ድርጊት ርቀው መኖራቸው አይዘነጋም፡፡ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የፖለቲካ ውጣ ውረድ ውስጥ ግን በነፃ አውጭነትም ሆነ፣ በሌሎች ዓላማዎች ከተሠለፉ ብዙዎች ውስጥ የተወሰኑት በክህደት ተግባራቸው ይታወቃሉ፡፡ በዚህ ድርጊታቸው ያተረፉት ንቀት ስለሆነ ቀና ማለት አይችሉም፡፡

አገርን ማክበር፣ ለህልውናዋ እስከ መጨረሻው መስዋዕትነት ድረስ ራስን ማዘጋጀት፣ በጨዋነትና በአስተዋይነት ለልማቷና ዕድገቷ የጋራ ራዕይ መያዝ፣ ለዜጎች መብትና ነፃነት ጥብቅና መቆም፣ ለብልሹ አሠራሮች መንስዔ የሆኑ ጉቦንና ሌብነትን ማጋለጥ፣ ለማሕበራዊ ፍትሕ መስፈን ግንባር ቀደም መሆን፣ ዜጎችን በብሔርና በእምነት መከፋፈልና ማጋጨትን በአንድነት ማውገዝና ማስወገድ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ፀር የሆኑ መሰናክሎችን ገለል ማድረግ፣ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች መኖርና መሥራት የሚገድቡ አላስፈላጊ ትርክቶችን ማስቆምና የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ያለ ልዩነት መቆም መቻል የግድ መሆን አለበት፡፡ እዚህ ላይ ልዩነቶች መኖር የለባቸውም እየተባለ አይደለም፡፡ ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ ለማስተናገድ የሚያስችል ባህርይ መላበስ ከተቻለ፣ ልዩነቶች በነፃነት የሚፎካከሩበት ምኅዳር መፍጠር አያቅትም፡፡ የልዩነት ሐሳቦች በነፃነት መንሸራሸር የሚችሉበት ዕድል ሲኖር የጉልበት መንገድ አማራጭ አይሆንም፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ እያቃተ ያለው አንዱ ችግር ልዩነትን ማስተናገድ አለመፈለግ ነው፡፡ ጉልበት አለኝ የሚል ሁሉ ከንግግር ይልቅ ጠመንጃ መነቅነቅ ይፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ሁሉም አስተሳሰቦች ወደ መነጋገሪያ መድረክ መጥተው የሚደመጡበት ሰላማዊና ዴሞክራሲያው ባህል ነው፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ስለንግግርና ድርድር አስፈላጊነት ከሚነገረው በላይ፣ ይህ ባህል አብቦና ጎምርቶ ሁሉም ሐሳቦች እንዲደመጡ ዕድል መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ሕዝብ ውስጥ ለዘመናት የሚብሰለሰሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከእነዚህ ችግሮች በጣም ብዙዎቹ በመንግሥትም ሆነ በፖለቲካው ውስጥ ባሉ ተዋናዮች ይታወቃሉ፡፡ ለአገር ህልውና ጠንቅ የሚሆኑ ድርጊቶች የሚበዙት እነዚህ የሚታወቁ ችግሮች ስለሚድበሰበሱ ነው፡፡ የፖለቲካ ተቀናቃኞችም እነዚህን የሚድበሰበሱ ችግሮች ከራሳቸው ፍላጎት ዓላማ አኳያ ብቻ ስለሚቃኙ፣ ሰላማዊ መፍትሔ ማግኘት ያለባቸውን ጉዳዮች የቅራኔ መፈልፈያ ያደርጋሉ፡፡ ቅራኔውን ከመጠን በላይ እያጦዙ ለአውዳሚ ግጭቶችና ጦርነቶች መቀስቀሻ ያደርጓቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት፣ ድርቅ፣ ረሃብ፣ ድህነት፣ ምስቅልቅልና የመሳሰሉ አስከፊ ነገሮች ብቻ እንዲበዙ ምክንያት ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያ ያለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን ጉዞ የሚያሳየውም ይህንን ነው፡፡ እንዲህ ባይሆን ኖሮ ኢትዮጵያ የረሃብና የችጋር ምሳሌ አትሆንም ነበር፡፡

ከእንዲህ ዓይነቱ አስከፊ አዙሪት ውስጥ መውጣት ባለመቻሉ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ትጥቅ አንግበው መንግሥትን የሚገዳደሩ በዝተዋል፡፡ ችግር ሲያጋጥም በሰከነ መንገድ ተቀምጦ የሚያነጋግር የተገነባ ባህል ስለሌለ፣ ያኮረፈ ሁሉ በፍጥነት የሚታየው ጦር መነቅነቅ ብቻ ነው፡፡ ከውጭ ወራሪዎችና ተስፋፊዎች ጋር ከተደረጉ ጦርነቶች ውጪ አብዛኞቹ የእርስ በርስ ነበሩ፡፡ ሌላው ቀርቶ ከአፄ ቴዎድሮስ ወዲህ ያለው ዘመነ መሣፍንትን ያስወገደው የማዕከላዊ መንግሥት ምሥረታ የሚያሳየው፣ በአንዱ እግር ሌላው ለመተካት የተኬደበት ርቀት በደም የታጀበ ነበር፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓተ መንግሥት መወገድ ጀምሮ ያለው ሒደትም፣ ፖለቲከኞች ‹‹ያለ ደም ሥርየት የለም›› ተባብለው የገቡበት የፖለቲካ ወጀብ ነው፡፡ የቀይና የነጭ ሽብር ዘመቻዎች፣ በኤርትራና በትግራይ የተካሄዱ ጦርነቶች፣ ከዚያ ወዲህ በተለያዩ ምክንያቶች የደረሱ ግድያዎች፣ እስሮች፣ ማሳደዶች፣ ግጭቶች፣ ጦርነቶች፣ ወዘተ አገሪቱን የደም ምድር አድርገዋታል፡፡ ይህ መራር የደም አዙሪት ማቆሚያ ያስፈልገዋል፡፡ በእዚህ ሁኔታ ለመቀጠል መሞከር የሚያስከትለው መዘዝ ከባድ ነው፡፡

ልዩነትን ያከበረ፣ በመግባባትና በመከባበር ላይ የተመሠረተና ስክነት ያለው ንግግር ያስፈልጋል፡፡ አገር የምትጠቀመው በዚህ መንገድ ከሚከናወን ንግግርና ድርድር እንደሆነ ይታመን፡፡ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ፣ አንዱ አንበርካኪ ሌላው ተንበርካኪ ለመሆን የሚደረግ ጥረት ፍሬ አልባ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ማዕከል የማያደርግ ፍላጎትም ሆነ ዓላማ ውጤቱ ጥፋት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ተሞክሮ ያልተሳካው በዜጎች መካከል ተገቢ ያልሆነ ክፍፍል በመፍጠሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊትና በዕድገት ትልቅ ደረጃ እንድትደርስ ማድረግ የሚቻለው፣ የአገር ጉዳይ የሚያገባቸው ወገኖች በእኩልነት ተነጋግረው የጋራ መግባባት ሲፈጥሩ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ዕሳቤ ሲኖር የአገሪቱ ሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነው ሕዝብ ዳኝነቱን በድምፁ ይሰጣል፡፡ የሕዝቡ የዳኝነት ድምፅ በነፃነት እንዲገኝ ምኅዳሩን በጋራ ማስተካከል የሚቻልበት ዓውድ መፈጠር አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ከፓርቲም ሆነ ከስብስብ በላይ የአገር ህልውና መቅደም ይኖርበታል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ፍላጎት ዕውን እንዲሆን፣ ቅራኔዎች በሙሉ ሰላማዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...