Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜና‹‹ፖለቲከኞች በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ የግል ፍላጎትና ዓላማ ለማስፈጸም መሞከር ፍጹም...

‹‹ፖለቲከኞች በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ የግል ፍላጎትና ዓላማ ለማስፈጸም መሞከር ፍጹም ስሕተት ነው›› ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ

ቀን:

ፖለቲከኞች በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ ጣልቃ እየገቡ የግል ፍላጎትና ዓላማ ለማስፈጸም መሞከር ተቀባይነትም የለውም ሲሉ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ተናገሩ፡፡

የቅዱስ ፓትርያርኩ 11ኛ ዓመት በዓለ ሢመት የካቲት 24 ቀን 2016 ዓ.ም. በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሲከበር ቅዱስነታቸው ባደረጉት ንግግር፣ ፖለቲከኞች ባልዋሉበትና ባልተፈቀደላቸው ሌላው ቀርቶ የተቋቋሙበት ሕገ መንግሥቱ እንኳ የማይፈቅድላቸውን በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ ጣልቃ እየገቡ የግል ፍላጎትና ዓላማ ለማስፈጸም መሞከር ፍጹም ስሕተት ነው፣ ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለራሳቸው ለፖለቲከኞቹም አይበጅም ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የሃይማኖት አባቶች ከፖለቲካ ገለልተኛ በመሆን ሁሉን በፍቅርና በእኩልነት ማቀራረብ ይገባቸዋል ያሉት ፓትርያርኩ፣ የሃይማኖት አባቶች በፖለቲከኞች ላይ ያላቸው ሥልጣንና መብት ማስተማርና መምከር እንደሆነ፣ ያም ሆኖ አንዱን በመደገፍ ሌላውን በመንቀፍ ሳይሆን ሁሉም እኩል ልጆቻችን መሆናቸውን አውቀን በፍቅር በመመልከት መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

- Advertisement -

ፖለቲከኞች ሲጋጩብንም የማስታረቅና የማቀራረብ፣ የመምክርና የማሳመን እንጂ ወደ አንዱ ተለጥፎ ሌላውን ዘልፎ መናገርን የቆምንለት ቅዱስ ወንጌል አይፈቅድልንም በማለት ያስገነዘቡ ሲሆን፣ በዚህ መንፈስ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት ተናበው ቢሠሩ በአገር ላይ ሰላም ይሰፍናል ልማት ይፋጠናል ብለዋል፡፡

ዓለም ሲሳሳት ከመገሠጽ ይልቅ አብሮ ማጨብጨብ ተለማምደናል፤ ባናጨበጭብም ዝምታን መርጠናል ነገር ግን ኃላፊነቱን የተረከብነው ጥፋት ሲፈጸም ዝም ብሎ ለማየት አልነበረም፣ ከዓለሙ ጋር አብሮ ለማጨብጨብ ወይም አድማቂ ለመሆንም አልነበረም፣ ከቅዱስ ወንጌሉ መሠረተ ሐሳብ ፍንክች ሳንል የእውነት፣ የፍትሕ የሰላም፣ የፍቅር፣ የዕርቅ የይቅርታ የአንድነት፣ የስምምነት ጠበቃ መሆናችንን ማሳየት ነበረብን፣ ሰውን ሁሉ በእኩልነት በመቀበልና የሁሉም እኩል አባቶች መሆናችንን በተግባር ማስመስከር ይገባን ነበር፣ የተዛባውን በማረም ትውልዱን ለማዳን ያደረግነው ጥረት የሚያረካ እንዳልሆነ ታዛቢው ሁሉ አይቶብናል በማለት ምክርና ተግሳጽ አስተላልፈዋል።

ባለፉት ዓመታት እጅግ በጣም አስቀያሚ ነገሮችና ፈተናዎች በቤተ ክርስቲያናችን ተከስተዋል፣ አሁንም አልቆሙም። በየአካባቢው መብቱ ተነፍጎ በቀየው እንዳይኖር በልዩ ልዩ ምክንያት እየተፈናቀለ ያለውን ሕዝባችን ለማጽናናትና ለመደገፍ በአንድነት መቆም ይገባናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ልጆችዋን የመንከባከብ የመጠበቅና ዕንባቸውን በማበስ ፍትሕንና ርትዕን የማንገሥ ኃላፊነት አለባት፡፡ ይህንን ኃላፊነት በአስተውሎት ልትወጣው ይገባል፡፡

ቅዱስነታቸው ‹‹የዘመናችን ትውልድ ከተግባር ይልቅ አስመሳይ ሆኖ መታየትን ከቅድስና ይልቅ ነውረ ኃጢአትን፣ ከትሕትና ይልቅ ትዕቢትን የተለማመደ ለሃይማኖትም ሆነ ለማኅበረሰብ ጤና ያልተመቸ ትውልድ እንደሆነ በግልጽ ይታያል›› ሲሉ ተግሳጽ አሰምተዋል።

በበዓለ ሢመቱ ላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ምዕመናንና የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮች  በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋን ጨምሮ ተገኝተዋል፡፡ የአሜሪካው አምባሳደር በተለይ በቅርቡ በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ገዳም በግፍ በተገደሉ መነኮሳት የተሰማቸውን ሐዘን በኤምባሲያቸው የማኅበራዊ ትስስር ገልጸዋል፡፡ አሜሪካ የሃይማኖት አባቶችንና የሲቪል ምዕመናንን ግድያ ታወግዛለችም ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...