Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለአርሶ አደሮች ምርት የአደጋ ዋስትና ኢንሹራንስ መርሐ ግብር ይፋ ተደረገ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) በሰው ሠራሽና በተፈጥሯዊ አደጋዎች ሳቢያ፣ በአርሶ አደር ሰብል ላይ ሊደርስ የሚችል የምርት ጉዳት ለመደገፍና ለማጠናከር ያግዛል ያለውን፣ የግብርና መድን መርሐ ግብር ይፋ አደረገ።

የተመድና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ሰኞ የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው መርሐ ግብር፣ በአገር አቀፍ ደረጃ አነስተኛ ገበሬዎችን የሚደግፉ የኢንሹራንስ ተቋማት ሽፋንና ተደራሽነት እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል፡፡

መርሐ ግብሩ ሁለት ሚሊዮን ዶላር በሚጠጋ ገንዘብ የሚከናወን መሆኑን፣ በአገሪቱ የግብርና የአደጋ ሥጋቶች የሚቀንሱበትና አደጋ በሚደርስበት ወቅት ጉዳቱን ሊጋራ የሚቻል የኢንሹራንስ ሽፋን መስጠት የሚያስችል አቅም መፍጠር የያዘ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዩኤንዲፒ ሁሉን አካታችና ዘላቂ ልማት ዘርፍ ቡደን መሪ አቶ ግዛቸው ሲሳይ  እንደገለጹት፣ ይፋ በተደረገው ፕሮግራም አማካይነት የመድን ኢንዱስትሪዎች ለግብርናው ዘርፍ የበለጠ ተደራሽ እንዲሆኑና ኅብረተሰቡ ለግብርና ኢንሹራንስ ያለው ግንዛቤ እንዲጨምርና ወደ ኢንሹራንስ ገብቶ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማመቻቸት ሥራ ይከናወናል፡፡

በየዓመቱ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት አርሶ አደሮች የሚያጋጥሟቸው እንደ ጎርፍ፣ ድርቅና ጦርነት የኢንሹራንስ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ያሉት አቶ ግዛቸው፣ በድርቅ ምክንያት ዕርዳታ እየተለመነ መቀጠል የለበትም ብለዋል፡፡ ዕርዳታ ከመለመን አስቀድሞ አርሶ አደሮችን በኢንሹራንስ መደገፍ ቢቻል ኅብረተሰቡን ከልመና መታደግ ይቻላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የግብርና ኢንሹራንስ በዕርዳታ ሰጪ ተቋማት ላይ የተመረኮዘ እንጂ በመንግሥት በሚደረግ ድጎማና የግብርና ፖሊሲ አማካይነት አለመሆኑን የተናገሩት ደግሞ፣ በዩኤንዲፒ የግብርና ኢንሹራንስ ከፍተኛ ባለሙያ ብፅዓት ደብረ ወርቅ ናቸው፡፡ ለኢንሹራንስ ዘርፍ እንደ መነሻ የሚያገለግል ጥራት ያለው መረጃ፣ የተመሰከረላቸውና ዕውቅና ያላቸው ባለሙያዎች፣ እንዲሁም የግብርና ምርቶች የኢንሹራንስ ዋጋ ግምት ለማውጣት የሚረዱ ጥናቶች እንደሌሉ ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ የተዘጋጀው የግብርና አደጋ ሥጋት ኢንሹራንስ መርሐ ግብር በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኘውን የግብርና ኢንሹራንስ ሽፋን ተደራሽ፣ ተመራጭና ተመጣጣኝ በማድረግ አዳዲስ የኢንሹራንስ ዓይነቶችን ወደ አርሶ አደሩ በማስፋፋት ድህነትን የሚቀንስና ሥጋትን የሚከላከል ነው ተብሏል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ለሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ተጋላጭ በሆነችው ኢትዮጵያ በተለይ ድርቅ፣ ጦርነት፣ ጎርፍና ወረርሽኝ መጨመራቸውን ገልጸዋል፡፡ ይፋ የተደረገው የግብርና ሥጋት መድን መነሻ ፕሮግራም በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እያለፉ ያሉትን የኅብረተሰብ ክፍሎች በመደገፍ፣ በተደጋጋሚ የሚቀርብ የዕርዳታ ፍላጎትን ለመቀነስ ያግዛል ብለዋል፡፡

ለአምስት ዓመታት የሚተገበረው የድጋፍ ፕሮግራም በአደጋ ተጠቂ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ፣ ሥራውም በሳይንሳዊ ፈጠራና ቴክኒክ የሚተገበሩ የኢንሹራንስ ምርቶችን ለአርሶ አደሮች በማስተዋወቅ ግንዛቤያቸውን መጨመርና አደጋዎችን መቋቋም እንዲችሉ ማድረግን ያለመ ነው ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች