Saturday, May 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የውጭ አገር ሥራ አገናኝ ኤጀንሲዎች የተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያ ጉዳይ ለገንዘብ ሚኒስቴር ቀረበ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት አገናኝ ኤጀንሲ አሠሪዎች ፌዴሬሽን፣ በሥሩ የሚገኙ ሦስት የኤጀንሲዎች ማኅበራት አባላት የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) ከፋይ ሆነው ይቀጥሉ ወይም ይነሳላቸው የሚል ውሳኔ ለመስጠት፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ጥናት ቀርቦለት ግምገማ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ። 

የውጭ አገር ሥራ አገናኝ ኤጀንሲዎች የተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያ ጉዳይ ለገንዘብ ሚኒስቴር ቀረበ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ መዝገቡ አሰፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ዘርፍን የሚመለከት በአምባሳደር የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሟል። 

‹‹እዚያ ኮሚቴ ውስጥ መብቶቻችንንና የማኅበሮቻችን አባላት መብትን የሚጥሱ አንዳንድ ነገሮች ሲነሱ ለኮሚቴው ጉዳዩን እናነሳለን፤›› ብለዋል። 

ፌዴሬሽኑ ከኮሚቴው ጋር ባደረጋቸው ውይይቶች ስለተነሱ ጉዳዩች ሲጠቅሱም፣ ‹‹ብዙ ጊዜ ዜጎቻችን ወይም ኤጀንሲዎች በትክክል የሚያገኙትን፣ ለኮሚሽንና ለሠራተኞች ምልመላ ወጪ የሚያደርጉትን ገንዘብ (Recruitment Cost) በአግባቡ ለምን አያሳውቁም? የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ ጥናት አድርገናል፤›› ብለዋል። 

አቶ መዝገቡ ይህንን የገለጹት ባለፈው ሳምንት ‹‹ዳግም ተሃድሶ ለፌዴሬሽኑ ጥንካሬና ለዜጎች ደኅንነት›› በሚል መሪ ቃል ከአባላቱ ጋር ባደረገው ጉባዔ በተለይም ሪፖርተር ላቀረባቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ ነው። 

ምክትል ፕሬዚዳንቱ ኤጀንሲዎች ስለሚያወጧቸው ወጪዎችና ከተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያ ጋር ተያይዞ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹ጥናት ስናደርግ የምናስመጣቸው ኮሚሽን ብቻ አይደለም፣ የአውሮፕላን የበረራ ቲኬት አለ፡፡ የዜጎችን የምልምላ ሒደት የምናሟላበት፣ የውጭ ጉዳይ፣ ለሠራተኛና ለማኅበራዊ፣ ለሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ለኤምባሲዎች የሚከፈል አለ። እነዚህ ሁሉ አንድ ላይ ነው የሚመጡት። ኮሚሽናችንንና ለአገልግሎት የምናስመጣውን ለይተን ነው መክፈል ያለብን። አሁን ባለው አሠራር አንድ ላይ ነው እንድንከፍል የሚደረገው፤›› ብለዋል፡፡ 

ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዘርፉ ኮሚቴ ጋር የተለያዩ ውይይቶችን ማድረጉን የገለጸው ፌዴሬሽኑ፣ አባላቱ ኤጀንሲዎቹ የተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያ፣ ከኮሚሽንና ከአገልግሎት ወጪዎቻቸው ጋር ተደምሮ መከፈል የለበትም የሚለውን ማንሳቱን አስታውቋል፡፡  

‹‹በጥናትና በባለሙያ የተደገፈ ጥናት አቅርበናል። ከዚህ በፊትም አሁንም በድጋሚ ይህ ነገር ታይቶ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይ እንሁን? ወይስ አይሆንም? የሚለው በጥናት ተሠርቶ ሲወጣ ወደፊት የሚደበቀውና የሚሸሸው ነገር ይቀራል፣ ይቀንሳል የሚል እምነት አለን፤›› ሲሉ አቶ መዝገቡ ተናግረዋል፡፡ 

‹‹በፌዴሬሽኑ በአጠቃላይ በዘርፉ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ተወያይተንበታል፡፡ መፍትሔ ለማምጣት ደግሞ ከመንግሥት ጋር መሥራት እንዳለብን ተማምነናል ብለዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዘርፉ ጉዳዩች ኮሚቴ በኩል ለፌዴሬሽኑ የሚሆን ነገር በጎ ምላሽ ነው ወይ ያገኛችሁት የሚል ጥያቄ የተነሳላቸው ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹ገና በሒደት ላይ ያለ ነገር ነው፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር አጥንቶ ይህ ነገር እውነት ስለሆነ የተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይ መሆን አለባችሁ ሊለን ይችላል፡፡ የሚሰበስቡት ምንድነው የሚለውን ዓይቶ ውሳኔ በቅርቡ የሚሰጠው በእሱ ነው፡፡ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እየተገመገመ እየታየ ያለ ጉዳይ ነው፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። 

‹‹የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ነቢል መሐመድ ባለፈው ሳምንት በፌዴሬሽኑ ጉባዔ መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር የተጠቀሰውን የግብር ጉዳይ አስመልክተው፣ ‹‹ግብርን በሚመለከት  በጣም ብዙ ነገር ላይ ደርሰን፣ በመጨረሻ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንደገና እንዲታይና ለገንዘብ ሚኒስቴር እንደሚተላለፍ ቃል ተገብቶልናል። የግብር ጉዳይ መስመር እየያዘ ይገኛል፤›› ብለዋል። 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች