Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊሕፃናትም የሚጠለፉበት ሕገወጥ ስደት በዓመት ከ25 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ሕፃናት ድንበር አቋርጠዋል

ሕፃናትም የሚጠለፉበት ሕገወጥ ስደት በዓመት ከ25 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ሕፃናት ድንበር አቋርጠዋል

ቀን:

መዳረሻቸውን የመን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እንዲሁም ሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅና የአውሮፓ አገሮች አድርገው ጉዞን በየብስና በባህር ካደረጉ በርካታ ወጣቶች የበረሃና የባህር ሲሳይ የሆኑት ቀላል አይደሉም፡፡

ሕፃናትም የሚጠለፉበት ሕገወጥ ስደት በዓመት ከ25 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ሕፃናት ድንበር አቋርጠዋል | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉ ስደተኞች ፎቶ ከፌዴራል ፖሊስ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ

ከተመኙት አገር ለመድረስ ዓመታት ፈጅተውም የተመኙትን ሥራና ሕይወት ሳያገኙ ከዚህም ከዚያም ሳይሆኑ የቀሩትም በርካቶች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የዚህ ችግር ሳይፈታ ከዚህ ቀደም በብዛት በወጣቶች ይፈጸም የነበረው ሕገወጥ ስደት፣ ዛሬ ላይ ወደ ሕፃናቱም ተጋብቷል፡፡

ከዚህ ቀደም በተለይ ሴት ወጣቶችን ለችግር፣ ለእንግልት፣ ለመደፈር፣ ለሕመምና ለሞት ሲዳርግ የነበረ ሕገወጥ ስደት፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሕፃናት ላይ መስተዋል ጀምሯል፡፡

- Advertisement -

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በሳምንቱ በማህበራዊ ትስስር ገጹ እንዳሰፈረውም፣ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የተሰማሩ ሦስት አዘዋዋሪዎችን ከ117 ኮብላዮች ጋር በቁጥጥር ሥር አውሏል፡፡

በቁጥጥር ከዋሉት የአብዛኛቹ ዕድሜ ከ15 ዓመት ያልበለጠ ታዳጊ ወጣቶች ሲሆኑ፣ ከኦሮሚያ ክልል ከተለያዩ አካባቢዎች በሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ወደ ውጭ ሀገር ለመውጣት ሶማሌ ክልል ቶጎ ውጫሌ ሲደርሱ መያዛቸውንና ለሶማሌ ክልል ፖሊስ ተላልፈው መሠጠታቸውን አስታውቋል፡፡

ሕፃናት በቤተሰባቸው አሊያም በጓደኛና በደላላ ግፊት ድንበር አቋርጠው ሲሰደዱ እየተስተዋለ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ሕፃናት ከወላጆቻቸው ጋር አብረው የሚሰደዱ መሆናቸው ቢታወቅም፣ የአሁኑን ለየት ያደረገው ብቻቸውን የሚሰደዱ ሕጻናት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ነው፡፡

ዓለም አቀፍ ፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም)፣ ሴቭ ዘ ችልድረንና ዩኒሴፍ ድንበር አቋርጠው የሚሰደዱ ሕፃናትን ለመታደግና ትብብራቸውን ለማጠናከር ከየካቲት 19 እስከ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ በአዲስ አበባ ቀጣናዊ ውይይት አድርገዋል፡፡

በድህነት፣ በረሃብ፣ በግጭት፣ በወጣት ሥራ አጥነትና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚከሰቱ ቀውሶች፣በርካታ ኢትዮጵያውያን ልጆችና ወጣቶች የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ከቀያቸው እየተሰደዱ ነው፡፡

ዓለም አቀፍ ድርጅቶቹ እንደሚሉት፣ በኅዳር 2016 ዓ.ም. 285 ሺሕ ኢትዮጵያውያን በስደተኞች መተላለፊያቱ በሚታወቀውና በተለመደው በምሥራቅ መውጫ ተሰደዋል፡፡

የምሥራቅ መውጫ የአፍሪካ ቀንድ አገሮችን፣ የመንና ሳዑዲ ዓረቢያን የሚያገናኝ ሲሆን፣ በዚህ መውጫ የሚሰደዱም መዳረሻቸውን ሳዑዲ ዓረቢያ ወይም ገልፍ አገሮች የሚያደረጉ ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2022/23 በርካታ ሕፃናት በዚህ መውጫ ተሰደዋል፡፡ በ2023 ብቻ 25,600 ሕፃናት ማለትም በአጠቃላይ በዓመቱ ከተሰደዱት ዘጠኝ በመቶ ሕፃናት ከአገራቸው ተሰደዋል፡፡ ከእነዚህ ሕፃናት መካከል 11,400 ወይም አራት በመቶ ያህሉ ሴት ልጆች ናቸው፡፡

በ2021 እና 2022 በዚሁ መውጫ ከቤተሰብ የተለዩ ወይም አብሯቸው የሚያውቁት ሰው የሌለ ሕፃናት ስደተኞች ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል፡፡ እንደ ድርጅቶቹ መግለጫ፣ ብቻቸውን የተሰደዱ ሕፃናት ቁጥር በእነዚሁ ዓመታት ከ7,300 ወደ 14,900 አድጓል፡፡ ብቻቸውን የተሰደዱ ሴት ልጆች ቁጥርም ከ1,700 ወደ 4000 ደርሷል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ሁሪያ ዓሊ እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ ችግር ምክንያት በርካቶች ከቀያቸው ይሰደዳሉ፡፡ በዚህ ውስጥ ደግሞ ደላሎች ያላቸው ሚና የጎላ ነው፡፡ የቤተሰብ ግፊትና ልጅን ልኮ ተጠቃሚ የመሆን ምኞትና ፍላጎትም ተጠቃሽ ገፊ ምክንያቶች ናቸው፡፡

ደኅንነቱ በተጠበቀ መንገድ ከሚሄዱት በተቃራኒ በኢመደበኛ መንገድ የሚፈልሱት ለፆታዊ ጥቃት፣ አካላቸው ለመጉደል፣ አካላቸው ለመሰረቅ፣ ተገደው ወደ ውትድርናና ወደማይፈልጉት ሥራ ለመግባት ይዳረጋሉ፡፡

በራሳቸው የመወሰን አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑት ሕፃናት በቤተሰብ፣ በአካባቢ ሰዎችና በደላሎች አማካይነት የሚሰደዱ ሲሆን፣ ሕፃን በመሆናቸው ብቻ የተለየ የችግር ተጋላጭነት ይገጥማቸዋል፡፡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱም ከሌሎች የከፋ ነው፡፡

ህፃናት ለዳግም ስደት፣ ለጉልበት ብዝበዛ፣ ለአካላዊና ፆታዊ ጥቃት እየተጋለጡ መሆኑን በማስታውስም፣ የህፃናት ህገ ወጥ ፍልሰት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል። ኢትዮጵያም ብሔራዊ የህፃናትና የፍልሰት ፖሊሲ እያዘጋጀች መሆኑንም አክለዋል።

በምስራቅና በአፍሪካ ቀንድ በሚገኙ ሀገራት መካከል ደህንነቱ የተጠበቀ የድንበር ተሻጋሪ ህፃናት አያያዝን በተመለከተ ለመምከር በተዘጋጀው መድረክ የተገኙት በኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቢባቶ ዋኔ በበኩላቸው፣ በህገወጥ መንደግ የተሰደዱ ህጻናት ሰብዓዊ መብታቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ ቀያቸው ለመመለስና ከቤተሰብ ለማቀላቀል የሚከናወኑ ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

የሴቭ ዘ ችልድረን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስተር ዣቪየር ጆበር እንደሚሉትም፣ በስደተኛ ሕጻናት ላይ እየደረሱ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ተጋግዞ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

በምሥራቅ በር ለሚሰደዱ ሕፃናት የሕፃናት ጥበቃ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ ምልሰትና በዘላቂነት መልሶ ከቤተሰብ ለማዋሃድ ሥራ ድጋፍ በመስጠትና መብታቸው እንዳይጣስ ጥበቃ በማድረግ ይሠራል ብለዋል፡፡

በጂቡቲ፣ በሶማሊያ፣ በየመን ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ወደ ተለያዩ አገሮች የሚሰደዱ ሕፃናትን ለማዳንና ሕገወጥ ፍልሰትን ለማስቀረት ፣ በመንግሥትና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለዓመታት የዘለቀ ሥራ ቢሠራም፣ ችግሩን ማስተንፈስ አልተቻለም፡፡

እ.ኤ.አ. በ2023 ብቻ ከኢትዮጵያ ወደ የመን የተሰደዱ ወንዶች ቁጥር በ113 በመቶ ሲጨምር፣ የሴቶቹ በ27 በመቶ አድጓል፡፡ በቦሳሶ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ድጋፍ ካገኙ ስደተኞች 58 በመቶ ሕፃናት ነበሩ፡፡ አይኦኤም ከደረሳቸው ስደተኞች ውስጥም ከአሥሩ አንዱ ሕፃን ነው፡፡

በጅቡቲ ተይዘው ከሚገኙ ስደተኞች ውስጥም 19 በመቶው ሕፃናት ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕፃናት ስደትም ከ2022 እስከ 2023 ባለው ጊዜ በ20 በመቶ ጨምሯል፡፡

በርካታ ሕፃናት በሕገወጥ የስደት ጉዞ የሚገጥሙ ችግሮችን የማያውቁ በመሆናቸውም፣ በሰው ለመነገድ፣ ለጥቃትና ለብዝበዛ አጋልጧቸዋል፡፡ በደረሱበት የሚታሰሩ መሆኑ ደግሞ ችግሩን ያጎላዋል፡፡

ህገወጥ የህፃናት ፍልሰትን በብሄራዊ የህጻናት ጥበቃ፣ አያያዝ ስርዓትና በብሄራዊ ስደት ፖሊሲዎች ውስጥ ለማካተት እንደ ግብዓት ያገልግላል በተባለው የውይይት መድረክ፣ የዓለም አቀፉ የህፃናት መርጃ ድርጅት፣ ዩኒሴፍ፣ የዓለም አቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የጅቡቲ፣ የሶማሊያ እና የመን ተወካዮች ተሳትፈዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...