Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከሳበኝ የክር ጥበብ የተቀዳ መክሊት

ከሳበኝ የክር ጥበብ የተቀዳ መክሊት

ቀን:

ወጣት ዳግም ገብሬ ይባላል፡፡ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ በ2012 ዓ.ም. በአርቴክቸር የሙያ ዘርፍ የዲግሪ ትምህርቱን ያጠናቀቀ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ‹‹ሳበኝ የክር ጥበብ›› የሚል መጠሪያ ያለው ድርጅት አቋቀሞ እጅ ጥበብ ውጤቶችን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

ወጣት ገብሬ እንደሚለው፣ የእጅ ሥራ ውጤቶችን የሚሠራው ሚስማርና ክር በመጠቀም ነው፡፡ ሳባ ክር፣ ወርቀ ዘቦና ለሐበሻ ቀሚስ ጥለት የሚያገለግሉ ክሮችን ከሚስማር ጋር በማዋሃድ የሰዎችን ፎቶና ሌሎችንም ምሥሎች በመሥራት ውጤታማ ለመሆን ችሏል፡፡

ከሳበኝ የክር ጥበብ የተቀዳ መክሊት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በክር ጥበብ ከተሠሩት መካከል

ይህ ሥራ በኢትዮጵያ ብዙ ያልተለመደና ውበት ያለው መሆኑን የሚናገረው ወጣቱ፣ ወደ ገበያ ለመግባት አራት ዓመታት እንደፈጀበትና በአሁኑ ወቅት ሥራው በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘ ይግለጻል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ክርና ሚስማር ተጠቅሞ የሚሠራቸውን ጥበቦች ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ገበያ በትዕዛዝ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ይህንን ጥበብ ለሌሎች ለማስተላለፍም ለአምስት ወጣቶች የሙያ ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡

‹‹በተመረቅኩበት የትምህርት መስክ የመንግሥት ሥራ ለመቀጠር ከመጠበቅ የራሴን ፈጠራ ይዤ በመውጣት ውጤታማ ሆኛለሁ፤›› የሚለው ወጣቱ፣ ቀደም ሲል ሥራዎቹ የሚሠራውም ሆነ የሚሸጠው መንገድ ዳር የነበረ ሲሆን፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የነበሩት ወ/ሮ ሒሩት ካሰው ሥራውን ዓይተው ደብዳቤ በጻፉለት መሠረት በወረዳ 02፣ (ኮተቤ አካባቢ) 60 ካሬ የሚሆን የወርክሾፕ ቦታ ተሰጥቶት በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በቶሞካ ካፌ፣ ሊኦፖል ሆቴልና በተለያዩ ዓውደ ርዕዮች ላይ በመሳተፍ የጥበብ ሥራዎቹን ለሕዝብ ዕይታ ማቅረቡንና ሥራው እየታወቀና በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነት እያተረፈለት መምጣቱንም ይናገራል፡፡

በአገራችን ለጥበብና ለሙያተኛው ያለው የቆየ አመለካከት እየተለወጠና ትውልዱም የጥበብ አፍቃሪ እየሆነ መጥቷል የሚለው ወጣት ዳግም፣ ሥራውን እንዲገፋበትና በሙያውም ውጤታማ እንዲሆን የረዳው ሰዎች በየጊዜው የሚሰጡት አስተያየት እንደሆነ ይገልጻል፡፡

አንድን የፎቶ ምሥል በክርና በሚስማር ተጠቅሞ ለመሥራት በአብዛኛው ከሦስት እስከ አምስት ቀናትን የሚፈጅና ሽያጩም እንደሚሠራው ሥራ በካሬ የሚሠላ በመሆኑ በገቢ ደረጃ ጥሩ የሚባል መሆኑን ያስረዳል፡፡

‹‹ጥበቡን ለገንዘብ ብዬ አልጀመርኩትም፡፡ ስለሚያስደስተኝና ውስጤ ያለ በመሆኑ ያንን ለማውጣት ነው የሞከርኩት፡፡ እስካሁን ያልተሞከሩ ሥራዎችን በመሥራት በዓለም አቀፍ መድረኮች ዕውቅና ሊያሰጡኝ የሚችሉ ሥራዎችን ለመሥራት ዘወትር እታጋለሁ፤›› የሚለው ወጣቱ፣ ሩሲያና እንግሊዝ በዚህ ጥብብ የታወቁ መሆናቸውንም ይገልጻል፡፡፡

እንደ ወጣት ዳግም፣ ጥበብ የአዕምሮና የሰውነት ጤና ነው፡፡ የጥበብ ጥሪ ችላ የሚባልም አይደለም፡፡ ገንዘብ አልተገኘበትምና እተወዋለሁ ቢሉ እንኳ እንቅልፍ አያስተኛም፤›› የነፍሱን ጥሪ ተከትሎ በመሄዱ አንድም መክሊቱን፣ ሁለትም ገንዘብ አግኝቶበት ራሱንና ቤተሰቡን እየደገፈበት ይገኛል፡፡

ወጣቶች የሰው ድጋፍና ዕገዛ ሳይጠብቁ ውስጣቸው አለ ብለው የሚያምኑበትን ጥበብ ለማውጣት መጣር ይኖርባቸዋል፡፡፡ ከግለሰብም ሆነ ከመንግሥት ድጎማ እናገኛለን ብለው ከመጠበቅ፣ እርሳስ በ5 ብርም ቢሆን ገዝተው ሥራቸውን ከፍ ለማድረግና  ራሳቸውን ለማሳወቅ መጣር ይኖርባቸዋል በማለትም ይመክራል፡፡

‹‹እኔ አሁን ለደረስኩበት ደረጃ የሰው ድጋፍ ሳይሆን አንድም በጥረት፣ ሁለትም በእግዚብሔር ዕርዳታ ነው፤›› የሚለው ዳግም፣ በያዙት ሥራ ላይ ማተኮር እንጂ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለባቸው ይናገራል፡፡

ወጣት ሔርሜላ ታደሰ፣ የሳበኝ የክር ጥበብ ድርጅት አባል ስትሆን፣ በወጣት ዳግም፣ ክርንና ሚስማርን በመጠቀም የተለያዩ ምሥሎችን የመሥራት ሥልጠና ያገኘችና ወደ ሙያው የተቀላቀለች ናት፡፡ ‹‹ይህ ሙያ ቤት ስለሚያሳምርና ጥበባዊ እሴቱም የጎላ በመሆኑ፣ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አለው፤›› የምትለው ሔርሜላ፣ እሷም ከትምህርቷ ጎን ለጎን ይህንን የዕደ ጥበብ ሥራ እየሠራች ትገኛለች፡፡

እነዚህ የጥበብ ውጤቶችም ወደ ተለያዩ አገሮች ለሽያጭ እንደሚቀርቡ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ሳዑዲ ዓሪቢያና ሌሎችም አገሮች በትዕዛዝ ሠርተው ያስረከቧቸው መኖራቸውን ትገልጻለች፡፡  

‹‹ሳበኝ የክር ጥበብ›› ድርጅት በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች የተለያዩ የኮሙዩኒኬሽን አውታሮችን በመጠቀም ሥራዎቹን እያስተዋወቀና እያስፋፋ ይገኛል፡፡ ከድርጅቱ እሷና ሌሎችም አባላት ሙያውን በማዳበርም ሆነ በገቢ ደረጃ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውንም ተናግራለች፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...