Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለጋራ አጀንዳ መቆም የሚጠበቅባቸው የሴት አደረጃጀቶች

ለጋራ አጀንዳ መቆም የሚጠበቅባቸው የሴት አደረጃጀቶች

ቀን:

ለኢትዮጵያ ሴቶች ድምፅ ለመሆንና ያሉባቸውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችል ‹‹የሴቶች ንቅናቄ ግንባታ፣ አጀንዳ ቀረፃና ሥልታዊ አሠራር›› በሚል መሪ ቃል የኢትዮጵያ ሴቶች ጉባዔ ተካሂዷል፡፡

ለጋራ አጀንዳ መቆም የሚጠበቅባቸው የሴት አደረጃጀቶች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በተካሄደው መርሐ ግብር የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ በአገራችን በተለያዩ ዘመናት የኢትዮጵያ የሴቶች እኩልነትን ለማረጋገጥና የሴቶች መብቶችን ለማስጠበቅ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ የሴቶች ማኅበራትና ድርጅቶች ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ሴቶች በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊና በኢኮኖሚያዊ የሚገጥማቸውን የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ ተግዳሮቶችን ለመፍታት አያሌ ትግሎች ተደርገዋል፡፡

የሴቶችን ጥቄያዎች ወደሚመለከታቸው ውሳኔ ሰጪ እንዲሁም ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት በማቅረብና ትኩረት እንዲሰጠው በማድረግ ረገድ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሚኒስትሯ እንደገለጹት፣ ባለፉት ዓመታት በመንግሥት የተወሰዱ የሕግ፣ የፖሊሲ፣ የመዋቅር፣ የአሠራር ማሻሻያዎችና ፕሮግራሞች በኢትዮጵያ የሴቶችን በኢኮኖሚያዊ፣ በማኅበራዊና በፖለቲካዊ ዘርፍ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዲያመጣ አስችሏል፡፡ በተጨማሪም የሴቶችን ጥያቄዎች ወደፊት ለማምጣትና ስለሴቶች መብት የሚታገሉ ማኅበራትና ድርጅቶች እንዲቋቋሙ ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩም አግዟል፡፡ ከዚህም በመነሳት ብዙ የሴቶች ጥያቄዎች የፖሊሲ ምላሽ እንዲያገኙ፣ ኅብረተሰቡም የሴቶችን መብቶች አስመልክቶ የተሻለ ግንዛቤና አረዳድ እንዲኖረው አስችሏል፡፡    

ይሁን እንጂ አሁንም ለረዥም ዘመናት የቆዩ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ በደሎችና የመብት ጥሰቶች ሙሉ በሙሉ ምላሽ ያላገኙ በመሆናቸው፣ የሴቶች ትግልና እንቅስቃሴ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ ይገባል፡፡ እንቅስቃሴው በሴቶች ማኅበራትና በተለያየ ደረጃ በተቋቋሙ የሴቶች መዋቅሮች እንዲሁም በእኛው በሴቶች ባለቤትነት ተይዞ ሊሠራበት የሚገባ ሲሆን፣ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የሴቶች ኅብረትና መደጋገፍን በተቀናጀ ሁኔታ መምራትና ማንቀሳቀስ የሚጠይቅ ተግባር መሆኑን ኤርጎጌ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

የፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ሊቀመንበር ተስፋነሽ በላይ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ በሴቶች ዙሪያ፣ በጎጂ ባህሎችና በመብቶቻቸው እንዲሁም  ጥቃቶችን በመከላከልና ወደ ሕግ በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡

የሴቶችን የዘመናት ጥያቄ ለመመለስና መብቶቻቸውን ለማረጋገጥ መዋቅራዊ ተቋሞች ተመሥርተዋል፡፡ እስከ ታች ቀበሌ ድረስ የሴቶች ጽሕፈት ቤቶች ተደራጅተዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም የሚታየው ለውጥ አጥጋቢ ባለመሆኑና ዛሬም በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚጎዱና ጥቃት የሚርስባቸው ሴቶች በመኖራቸው፣ ለእነርሱ ድምፅ ለመሆን አገራዊ የሴቶች ንቅናቄ መፍጠር ማስፈለጉን አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳባ ገብረ መድኅን በበኩላቸው፣ የሴት አደረጃጀቶችና መዋቅሮች የሴቶችን መብት ለማስከበርና ጥቃትን ለመከላከል በርካታ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ በዚህም ቀላል የማይባሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡

ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ በየራሳቸው ፕሮግራምና በየፕሮጀክቶቻቸው በመጠመዳቸው ለሴቷ መብት፣ እኩልነትና ጥቃት በአንድ ላይ በመቆም ድምፅ ለማሰማት አልቻሉም፡፡

ወ/ሮ ሳባ እንደሚገልጹት፣ የኢትዮጵያ ሴቶችን የዘመናት ጥያቄ ለመመለስ ሁሉንም የሴቶች አደረጃጀትና ማኅበራት የጋራ አጀንዳ እንዲኖራቸው ማድረግና እነዚህንም አጀንዳዎች በመለየት፣ በውይይት በማዳበርና መቅረፅ ወደ ትግበራ ምዕራፍ መግባት ከማኅበራቱ የሚጠበቅ ይሆናል ብለዋል፡፡

የዩኤን ውመን ፕሮግራም ኃላፊ ወ/ሮ የእልፍኝ አበጋዝ እንደተናገሩት፣ በአገራችን በፆታ እኩልነት ዙሪያ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ በፆታ እኩልነት ላይ ያተኮሩ ጥሩ ሕጎችና ፖሊሲዎች ወጥተዋል፡፡ ከላይ እስከ ታች የተዘረጋም መዋቅር አለ፡፡ ከቀድሞው ጋር ሲነፃፀር ብዙ ለውጦች ተገኝቷል፡፡

ሴቶች ወደ አመራር መጥተዋል፡፡ በትምህርትም፣ በጤናና በሌሎችም የሴቶች ተሳትፎ ዙሪያ የሚታዩ ለውጦች አሉ፡፡ ለዚህም መንግሥት በሠራው ሥራ ዕውቅና ማግኘት ይገባዋል የሚሉት ወ/ሮ እልፍኝ፣ ይህም ሆኖ ግን ዛሬም ሴቶች በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊና በአጠቃላይ በአገራችን የልማት ሥራዎች ላይ ከወንዶች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ጠቁመዋል፡፡

በሥርዓተ ፆታ እኩልነት ዙሪያ በተናጠል በርካታ ሥራዎች የተሠሩና ውጤትም የተገኙባቸው ቢሆንም፣ እነዚህ ስኬቶች ወደ ኋላ እየሄዱና ዛሬም ሥር የሰደደ የወንድ የበላይነትና ያልተፈቱ ችግሮች በመኖራቸው በአንድ ተቀናጅቶ ድምፅ ማስማት እንደሚጠበቅ አሳስበዋል፡፡

በፕላን ኢንተርናሽናል የሴቶች ፕሮጀክት አስተባባሪ ወ/ሮ ሩት ደስታ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሴቶች ንቅናቄ በኢትዮጵያ ቢጠናከር በማኅበረሰቡ ውስጥ በሴቶችና በልጃገረዶች ዙሪያ አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያግዝ ይሆናል፣ ለዚህም የኢትዮጵያ ሴት አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበርና የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ያከናወኗቸው ጅምር እንቅስቃሴዎች አበረታች ናቸው ብለዋል፡፡

እንደ ወ/ሮ ሩት፣ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ትብብር ለመፍጠርና ንቅናቄው ከፍ ያለ ሚና የሚኖረው ሲሆን፣ በሴቶችና ልጃገረዶች ዙሪያ የተረቀቁ ፖሊሲዎች እንዲፀድቁና ተግባር ላይ እንዲውሉ፣ ነባር ደንቦችና ሕጎችም እንዲተገበሩ መድረኩ ተጨማሪ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...