Monday, May 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በኪነ ጥበብ ፖለቲከኛን መስደብ ወይስ ፖለቲካን መብለጥ? አስቻለው ፈጠነ ከኢትዮጵያ ቪቪያን ቺዲዲ ከሴኔጋል    

በያሬድ ነጋሽ ሐሰን

ግብይት እንዲሳለጥ ዓይነተኛ ሚና ያላቸውና እንደየ ዘመኑ አገልግሎታቸው እየጎላ የሚመጡ መንገዶችን ይከተላል። ሻጭና ገዥ የሚገበያዩትን ንብረት፣ ጊዜ እንዳይወስድባቸው፣ ከጥራቱ እንዳይቀሸብባቸው፣ ከእምነት እንዳይጎድልባቸው የተለያየ የመገበያያ መንገድን ሲከተሉ መነሻውን ጥንት አድርገዋል። ለግብይት የሚሆነው ንብረት ዓይነቱ ለየቅል ነውና ‹‹ይኼ ንብረት ለፍጥነቱ በዚህ፣ ለክብደቱ በዛኛው ሽታ አለውና በዚያ ተሰባሪ ስለሆነ በዚህ ተቀጣጣይ ነውና በዚያ በጣሩን በዛኛው ፈሳሹን በዚኛው፤›› እያለ በመላ ሲገበያይ ሰንብቷል።

በተለያየ መንገድ ተጭነው ከሻጭ ወደ ገዥ በግብይት ሲጓጓዙ ከነበሩ ንብረቶች መሀል የአዕምሮ ንብረት የሆነው ሐሳብ አንደኛው ነው። ሐሳብ በየትኛውም መንገድ ለግብይት ሊቀርብ ይችላል፣ ሆኖም ያለ ድካም ይነገድ ዘንድ ሐሳብ የኪነ ጥበብ ጥገኛ ነው። በዚህ መነሻነት፣ በኮልታፋ አንደበት ‹‹የኪነ ጥበብ ሚና፣ ሐሳብን ከመነሻው ወደ ተፈለገው ሥፍራ የማጓጓዣ መንገድ ነው፤›› እያልን ቢሆንም፣ ‹‹በጠራና በነቃ አዕምሮ ሐሳባቸውን በኪነ ጥበብ አሸክመው ወደ ማኅበረሰብ ሲያጓጉዙ የነበሩ ሊቃውንት ስለኪነ ጥበብ ዓላማ ምን አሉ›› የሚለውን መመልከት ተገቢነት አለው።

እውነታን በጠራ መልኩ መመልከቻ መንገድ እያለን ይመስላል ፓብሎ ፒካሶ ‹‹የኪነ ጥበብ ዓላማ የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ የለበሰን አቧራ ማጠብ ነው፤›› ይለናል።

የሰው ልጅ በሁኔታዎች የተነሳ ውስን ሆኖ ሊመለከታቸውና ሊደርስባቸው የማይችለው ጉዳዮች በመኖራቸው፣ ሃንጋሪ ከፈረንሣይ ድቅል የሆነው ፎቶ ግራፍ አንሺ (Brassai) ‹‹የኪነ ጥበብ ዓላማ ሰዎች በራሳቸው ሊደርሱበት ከሚችሉት በላይ አሻግሮ የበቃ የግንዛቤ ደረጃ ላይ ማድረስ ነው፤›› ይለናል። ‹‹የተሳለ ስለትም በጊዜ ሒደት ይዝግ ይደንዛልና ሞረድ እንደሚፈልግ ሁሉ፣ የነበረው እንዳልነበረ ሆኖ ሰውም መነቃቃቱ ጠፍቶ የተዳከመ እንደሆን፣ በዚህ ጊዜ የኪነ ጥበብ ከፍተኛው ዓላማ ማነሳሳት ነው፤›› ይላል አሜሪካዊ ድምፃዊና የሙዚቃ ጸሐፊ (Bob Dylan)፡፡ ‹‹የላይ የላዩን ሳይሆን ውስጣዊ እውነታን መመርመሪያ መሣሪያ ነው፤›› ይለዋል አርስቶትል፡፡ ነገሩን በደረቁ ከምንመለከተው ግለሰቦች ‹‹የኪነ ጥበብ ዓላማ ነው›› በሚል ያስቀመጡትን ሐሳብ ከተጨባጭ እውነታዎቸ ጋር አያይዞ መመልከት ማለፊያ ነው፡፡

ክሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ በአውሮፓ የዳበረው፣ ሱሪሊዝም በተሰኘውና ሥውሩ የአዕምሮ ክፍላችን በተለያየ የጥበብ መንገድ አማካይነት መግለጥ ዓላማው ባደረግው እሳቤ ማዕቀፍ ውስጥ የኖረው ቤልጂየምአዊው (Rene Magritte)  ‹‹የጥበብ ዓላማ ሚስጥራዊ ሐሳቦችን ማስተላለፊያ ምስጢር ነው፤›› ማለቱን ስንመለከት፣ ይህ የኪነ ጥበብ ዓላማ በተለይም ከያኒውን የልቡን ስሜት ሥውር አድርጎ ለማስተላለፍ ምቹ በር ይከፍትለታል፡፡ አንድ ታሪካዊ ክስተት እናንሳ፡፡

ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ የልባቸውን ማንም በቀላሉ እንዳይረዳው አድርገው የመቅረብ የግጥም ተሰጥኦ የነበራቸው ቀደምት የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ከያኒና ዓርማ ነበሩ። ‹‹ውበትሽ ይደነቃል›› የተሰኘውን የክቡር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰን ተወዳጅ ሙዚቃ ለእንስቶቻችን ስንጋብዝ ከረምን፣ ሻምበል ግን ‹‹የምወዳት አገሬን በቆንጆ ሴት መስዬ፣ ለአገር የደረስኩት ድርሰት ነው፤›› ቢሉን ኃፍረት ቢጤ ሸነቆጠን። ከያኒው አይደለም ለተራ ሰው ይቅርና፣ በአገር ደረጃ የተቋቋመን የሳንሱር ተቋም፣ ምን እንደተናግሩ ሳይረዳ አደንዝዘው የልባቸውን መናገር ተክነውበታል፡፡

‹‹አልቻልኩም›› የተሰኘና ጨቅጫቃ ለሆነች ሚስት የተሰናዳ የሚመስል የሙዚቃ ሥራ አሰናድተው፣ በ1953 ዓ.ም. ዘመን መለወጫ መስከረም አንድ ጥላሁን ገሰሰ መድረክ ላይ እንዲጫወተው አደረጉ፡፡ ታኅሣሥ 1953 ዓ.ም. ላይ ብርጋዴር ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ (የክብር ዘበኛ አዛዥ)፣ ገርማሜ ነዋይ (የጅግጅጋ አውራጃ አዛዥ) እና የአፄ ኃይለ ሥላሴ ቀዳማይ ካቢኔ የነበሩት ሌ/ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ ለወራት ለብቻቸው ሲመክሩበት የከረመው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተደረገ (የታኅሣሥ ግርግር)።

ግርግሩ ተረጋግቶ የሁሉ ቀልብ ሲሰበሰብ፣ ‹‹አልቻልኩም›› በሚል ከወራት በፊት የተሠራው ሙዚቃ ዘፈኑ ለፍቅር አለመግባባት ሳይሆን፣ ሕዝቡ በአገዛዙ መማረሩን ለመግለጽና ለአመፅ እንዲነሳ ለመገፋፋት (ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው መነሻዎች እንደ አንዱ ተቆጥሯል) የተሸረበ መሆኑን ንጉሣውያኑ ደረሱበት። ‹‹የጥበብ ዓላማ ሚስጥራዊ ሐሳቦችን ማስተላለፊያ ምስጢር ነው፤›› ይሉት ዓይነት፡፡

ገጣሚውና ሙዚቀኛው ታሰሩ። በአፀፋውም ግጥሙ ማስተካከያ ተደርጎበት ‹‹ባትችለውም ቻለው›› በሚል ርዕስ በብዙነሽ በቀለና በተፈራ ካሳ በድጋሚ እንዲሠራ ተደረገ። (‹‹የከተማው መናኝ፣ ይነገር ጌታቸው 2013 ዓ.ም.፣ ጥላውን ገሠሠ የሕይወቱ ታሪክና ምሥጢር 2013 ዓ.ም. ዘከሪያ መሐመድ›› የሚለውን ይመለከተዋል፡፡)

አሜሪካዊው ሙዚቀኛ ቦብ ዲላን ‹‹የጥበብ ዓላማ ጊዜን ማቆም ነው፡፡›› ሲለን ጊዜን ማቆም የሚቻል ባይሆንም፣ በጊዜ ውስጥ ማቆሚያ አጥተው የነበሩ ቀውሶች በተጨባጭ ለደቂቃም ቢሆን ቆመው ተመልክተናል፡፡

በታኅሣሥ እ.ኤ.አ. 2012 በሰሜንና ደቡብ ማሊ ታጣቂዎች የተጀመረው የእርስ በርስ ጦርነት መላ በጠፋለት ወቅት፣ ተወዳጅ የሆነችው ማሊያዊት ድምፃዊት ኦሞ ሳንጋሬ ባማኮ ላይ ኮንሰርት አዘጋጀች፡፡ ከተማው ኦሞ ሳንጋሪን ለማድመጥ ተሰናዳ፡፡ ኦሞ ሙዚቃውን ጀምራ ሁለት ደቂቃ ሲሞላት ሙዚቃውን አቋርጣ ታላቅ ኃይለ ቃል አወጣች ‹‹ተመለከታችሁ ጦርነቱ ለሁለት ደቂቃ ቆሟል፣ ፈቃደኝነቱ ካለ ጦርነቱ በዘላቂነት በቀላሉ እንዲህ መቆም ይችላል፤›› ስትል ተደመጠች፡፡ ይህንን መሰል ድርጊት ታላቁ የሬጌ ሰው ቦብ ማርሌ በቬትናም አድርጎት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ኪነ ጥበብ ‹‹በጊዜ ውስጥ ወደ ተለያየ አቅጣጫ ይፈስ የነበረን የዓለም ሕዝብ አንዲት ቦታ ቆሞ ስለአንድ ጉዳይ ብቻ እንዲያተኩር አስገዳጅ ኃይል ተላብሳ ብቅ ብላ፣ በ1977 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ተከስቶ ለነበረው ድርቅ ዓለም ልቡን እንዲቸር በማድረጉ ረገድ ‹‹We are the world›› የተሰኘው ኦርጂናል የሙዚቃ ቅጂ የነበረውን ሚና በተለይም ለኢትዮጵያውያን የሚዘነጋ አልነበረም፡፡

ኪነ ጥበብ ኃያል መሣሪያ ነው፡፡ ኃያልነቱ ለበጎ የተጠቀምነው እንደሆን፣ ፈረንሣዊው አሰላሳይ ኤድዋርድ ዴ ቦኖ ‹‹ኪነ ጥበብ አዳዲስ በጎ እሴቶችን ለማንፀባረቅና ሰዎች ወደ በጎ አመለካከታቸው እንዲገቡ ለማድረግ ያገለግላል እንዳለው ዳና ጆያ (አሜሪካዊ ገጣሚ) ‹‹የኪነ ጥበብ  ዓላማ ብዙ አርቲስቶችን ማፍራት ብቻ ሳይሆን፣ ምንም እንኳን ያ ውጤት ቢሆንም፣ የኪነ ጥበብ ትክክለኛ ዓላማ በማኅበረሰብ ውስጥ ስኬታማና ውጤታማ ሕይወት መምራት የሚችል የተሟላ የሰው ልጅ መፍጠር ነው፤›› በሚል እንደመሰከረለት ይሆናል፡፡ ይህ የሚሆነው ግን ኃያል መሣሪያነቱን ለበጎ ካዋልነው ብቻ ነው፡፡ ሚናው ከተዛባ ግን አውዳሚ መሣሪያነቱን ለመቋቋም የሚቻለው ሌላ ኃይል ላይገኝ ይችላል፡፡

ትንባሆ ከክርስቶስ ልደት ከሦስት እስከ አምስት ሺሕ ዓመት በፊት ላቲን  አሜሪካ ፔሩ ውስጥ እንደተገኘች እየተወሳላት፣ ሚናዋም መንፈሳዊ አገልግሎት የምትሰጥ ‹‹ቅዱስ ዕቃ›› ተደርጋ ከመቆጠር ተሻግራ፣ ከ15ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛቶች ውስጥ የግብይት መሣሪያ ወደ መሆን ተላልፋ ‹‹ለብርታት›› በሚል ምክንያት በተለያየ መልኩ ተሰናድታ ግላጋሎት ላይ ስትውል የሰው ልጅ ሰውነት ውስጥ ገብታ በቀላሉ የምትወጣ ነገር አለመሆኗ ከተረጋገጠ በኋላ በ1716 በኒዎርክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹ፒ ሎሪላንድ›› በተባለ ኩባንያ አማካይነት በሲጋራ መልክ ተሰናድታ ለተጠቃሚ መቅረብ ጀመረች።

ከሲጋራ ሽያጭ የሚገኘው ትርፍ፣ በሲጋራ ምክንያት የሚከሰተውን ቀውስ ከመጤፍ ካለመቁጠር ያደርሳል። በ2019 888 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የነበረው ዓለም አቀፍ የሲጋራ ገቢ በያዝነው 2024 1.124 ትሪሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል። አምራች ኩባንያዎቹ ‹‹ይህንን ትርፍ በ0.5 ሳንቲም ሊቀንስብኝ ይችላል›› ብለው ያሰቡትን እንቅስቃሴ ተከታትለውና ሚሊዮኖችን አፍስሰው ያከሽፋሉ። ‹‹ለጤና ጎጂ ነው›› መባል በተጀመረበት ወቅት፣ ለዩኒቨርሲቲዎች ረብጣ ዶላር በማፍሰስ በዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች አፍ በታላላቅ መድረኮች ላይ ሲጋራ ምንም ዓይነት የጤና ጉዳት እንደሌለው ያስነግሩ ነበር።

የኩባንያዎቹን ድርጊት አስገራሚ ወይም ሲጋራ አጫሽ፣ የመጀመሪያውን ሲጋራ የለኮሰ ቀን እንጂ በቀጣይ ያለው ጊዜ የሲጋራ አምራቾች ንብረት ሆኖ፣ ነፍሱ በእጃቸው ተጥሎ ያሻቸውን ሊያደርጉት የሚችሉት ማሽን እንደሚሆን የሚያስገነዝብ በመሆኑ ጥቂት ነገሮችን እንመልከት።

በወቅቱ ‹‹ምሁራንን አዘጋጅቶ ሲጋራ የጤና ጉዳት የለውም›› የሚያስብሉበት ጊዜ አልፎ፣ የሲጋራ የጤና ጠንቅነት ግልጥልጥ ካለና የሰው ልጅን ከራስ ፀጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ የሚያበሰብስ ጠንቀኛ መርዝ መሆኑ በተጨባጭ ከታየ በኋላ፣ አዲስ ሲጋራ አጫሾችን ለማፍራት ተግዳሮት የገጠማቸው የሲጋራ አምራች ካምፖኒዎች አዲስ ሥልት ቀየሱ ይኼውም፣ ‹‹ነባር አጫሾችን በደንብ ማስጨስ›› የሚሉት ነው።

ሲጋራ አጫሽ ሳያውቀው ነብሱን ለእነዚህ ሰዎች አሳልፎ ሰጥቷልና ‹‹የትንባሆ ሽታ ያስጠላል›› ብሎ ለማፈግፈግ ቢሞክር በአፕል፣ በስትሮበሪና ሌሎች ፍሌቨሮችን የያዙ ሲጋራዎችን አምርተው ከበሩ ያደርሱታል። ‹‹ጉሮሮ ይከረክራል፣ ከንፈር ይጠብሳል›› ቢል እነሱ እቴ ሱሰኛ የሆነለትን የኒኮቲን ንጥረ ነገር የያዙና ባለመከርከር ከንፈር ባለመጥበስ በቀላሉ ሊያጨሳቸው የሚችላቸውን የኤሌክትሮኒክስ ሲጋራ ይዘው ከተፍ።

አጫሹ ሲጋራ ማጨሱ ሰቆቃ ውስጥ እንደከተተው ቢረዳም፣ በሱስ የጠመደውን ነገር መሸሽ ባለመቻሉ ወደ ማገገሚያ ማዕከል ይሸሸጋል። የሚገርመው ለሕክምና የሚውሉ በጊዜያዊነት ለግልጋሎት የሚውሉና አነስተኛ መጠን ያለው የኒኮቲን መጠን የተሸከሙ መድኃኒቶችን የሚያመርቱት፣ በሚያስደንቅ ሁኔታ እነዚህ ታላላቅ የትንባሆ አምራች ኩባንያዎች ናቸው። በአጫሹ ፈቃድ የምትጨሰው ሲጋራ የመጀመሪያዋ ብቻ እንጂ ቀሪው ጊዜ ነፍስ ለእነዚህ ኩባንያዎች ተላልፋ ተሰጥታለች።

‹‹ነባር አጫሹን በደንብ እናስጭሰው›› ከሚለው እቅዳቸው መሀል “እስቴካ” የተባለውን የአስተሻሸግ ዘዴ ማስተዋወቅ ነበር። ማለትም፣ 20 ሲጋራ የያዘ አንድ ፓኬት ተደርጎ ለገበያ ይቀርብ የነበረው ሲጋራ አሥር ፓኬቶችን የያዘ ‹‹ሴቴካ› የተባለ እሽግ አሰናድቶ ወደ ገበያ ማቅረብ የሚሉት ነው። ይኼውም ‹‹ሲጋራ አጫሹ ወደ ገበያ መመላለስ ሳያስፈልገው፣ እስቴካውን በመግዛት ከአንድ ፓኮ ወደ ሌላኛው በፍጥነት መሸጋገር ያስችለዋል፤›› የሚል ነው።

በቀጣይ ኪንግ ሳይዝ ምርትን ማስተዋወቅ ቀጠሉ። ይኼውም የመደበኛ ሲጋራ ርዝመት በአማካይ ሰባት ሳንቲ ሜትር ሲሆን፣ ኪንግ ሳይዝ የተባለው ወደ ዘጠኝ ሳንቲ ሜትር አድጎና በዋጋ ጨምሮ በማቅረብ፣ ነባር አጫሹ ከፍ ወዳለ አጫሽነት ተሸጋግሮ ትርፉን ያሳልጣል ማለት ነው።

‹‹ነባር አጫሹ እስከ ሕክምና መድኃኒት ድረስ አምርተው ተጠቃሚ በማድረግ ብቻ ትርፍ ማጋበሱ የልብ አያደርስም፤›› ያሉት እነዚህ የሲጋራ አምራቾች ሌላ መላ መዘየድ ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ኪነ ጥበብ ዓይነተኛ መንገድ ሆና ፍንትው ብላ ታየቻቸው።  ይህም እንደ አጠቃቀሙ ኪነ ጥበብ አውዳሚ መሣሪያ ሆና የቀረበችበት ገጠመኝ ነው፡፡

ታላላቅ ፊልሞች በእነዚህ ካምፓኒዎች የገንዘብ ድጋፍ ይዘጋጁ ጀመር። በየፊልሙ ተወዳጅ አርቲስቶች ሲጋራ ይዘው ተውኔቱን እንዲከውኑት ይደረጋል። በወጣቱ ዘንድ በፍቅር የሚተኮርባቸው ሙዚቀኞች መድረክ ላይ ሳይቀር ሲጋራ እያጨሱ ሙዚቃ መጫወት ጀመሩ። የሲጋራ አጫሽ ወጣቶች ቁጥር መቆጣጠር በማይቻል መልኩ አሻቅቦ ነፍሳቸው ለእነዚህ ሲጋራ አምራች ካምፓኒዎች ግብር ሆና መተላለፍ ብቻ ሳይሆን ሲጋራ ከጤና ጎጂነቱ ይልቅ አንድን ወጣት ፋሽን አዋቂ/አላዋቂነቱን የምትወስን ዓይነተኛ ሚና ተላበሰች። ካምፓኒዎቹ በኪነ ጥበብ ውስጥ ካከናወኑት ‹‹የአጭሱልን›› ጥሪ ውስጥ አንዱን አስገራሚ ጉዳይ ተመልክተን ወደሌላ ጉዳይ እንሻገራለን።

የሲጋራ ማስተዋወቅ ተግባር በሕግ መከልከሉ፣ የሲጋራ አምራች ኩባንያዎችን አስቆጥቶ ያጉረመርሙ የነበሩበት ወቅት ነበር። የካምፓኒዎቹ ማጉረምረም ወቅቱ ሴት የሲጋራ አጫሾች ያልነበሩበት ቢኖሩም ተሸሽገው የሚከውኑት እንጂ አደባባይ በኩራት ይዘው የማይታዩበት በመሆኑ፣ የሴት አጫሾችን ቁጥር የሚጨምሩበት ወይም ያልተነካውን ገበያ ሰብረው የሚገቡበትና በኪነ ጥበብ የተዋዙ የማስታወቂያ ሥልት በመቀየስ ላይ ሳሉ ሕጉ በመርቀቁ ነበር።

እነዚህ ካምፓኒዎች እንቅልፍ የላቸውምና ሌላ ዘዴ ቀየሱ። በኪነ ጥበብ የተዋዛ የሪል ስቴት ማስታወቂያ ላይ ልትተውን የተዘጋጀችውን ሱፐር ሞዴል አጠመዱ፡፡ በዚያ የሪል ስቴት ማስታወቂያ ሥራ ላይ እንስቷ ሲጋራ ይዛ እንድትታይ ተደረገ። ከዚህ ጊዜ በኋላ የበርካታ እንስት ሲጋራ አጫሾች ነፍስ እስከ ማገገሚያ ሆስፒታል ድረስ ላይለቋት ግብር ሆና ለእነዚህ ካሞፓኒዎች ተሰጠች። (ትምባሆና የጤና ጉዳቱ፣ ተካልኝ ለገሰ 2014 ዓ.ም. ይመለከተዋል፡፡)

በመጨረሻም ወደ አንቀጽ ዝግጅታችን አንኳር ሐሳብ የሚያሸጋግሩንንና ‹‹የኪነ ጥበብ ዓላማ ይህንን ይመስላል›› ያሉንን ግለሰቦች ሐሳብ እንመልከት፡፡ ‹‹የጥበብ ዓላማ ሰዎችን አስተሳስሮ ወደ ፊት ማምጣት ነው፤›› ጂም ኬሪ (የሆሊውድ ተዋናይ፣ ዘ ማስክ የሚለው ፊልሙን ያስታውሰዋል) ‹‹የጥበብ ዓላማ የሰውን መንፈስ ከፍ ማድረግ ነው፤›› Pope John Paul II፣ (1978-2005 የቫቲካን ጳጳስ) ‹‹የኪነ ጥበብ ዓላማ ጉጉትን መፍጠር ነው፤›› ፓብሎ ፒካሶ፣ (1881-1973 ከስፔን ተነስቶ ሥዕልና ቅርፃ ቅርፅ ሥራው ዓለምን የዋጀ) በዚህ አንቀጽ ልናወሳው በወደድነው ጉዳይ  ልክ ኪነ ጥበብ በአንድ አገር ያለን ማኅበረሰባዊ ትስስር ማስቀጠል፣ ትስስሩ እየላላ ከመጣ ማጥበቅ፣ ትስስር ያልነበራቸው ቢኖሩም ጅምሩን ማብሰር ሚናዋ ነው።

በአገራችን በሙዚቃው ዘርፍ፣ በቀደመ ጊዜ ‹‹በይ እንጓዝ በይ እንሂድ ሐረር፣ በል እንጓዝ በል እንግባ ሸገር›› በሚል በብዙነሽ በቀለና በጥላሁን ገሰሰ የተዜመ ሙዚቃ (ድምፃዊት ዘቢባ ግርማና ድምፃዊ ኢሳያስ ታምራት በቅርብ ጊዜ ግሩም አድርገው ድጋሚ ተጫውተውታል) የሚለውን ሙዚቃ ስንሰማ ያደግን ሰዎች፣ መላ ኢትዮጵያን ዞሮ፣ አዲስ አበባ ላይ ማረፊያ ማድረግ ስለፈለገ ፍቅር እንድናደምጥ ዕድል ይፈጥርልናል፡፡

ብዙዬ፡-

‹‹የወለጋን ወንዝ ባይን እናይና

ለጌጥ የሚሆን እንገዛና

ኢሉባቦርን ከፋንም አልፈን

በሸዋ በኩል ቤት እንሄዳለን›› ትላለች፡፡

ጥሌ፡-

ወሎን አልፈን ላሊበላን አይተን

በአዋሽ በኩል በገዋኔ ታጥፈን

አዋሽ ደርሰን በባቡር ተሳፍረን

አዳራችን ወደ ሐረር ገብተን›› ይለናል፡፡

ጂም ኬሪ፣ ‹‹የጥበብ ዓላማ ሰዎችን አስተሳስሮ ወደ ፊት ማምጣት ነው›› በሚል ያነሳውን ሐሳብ ፍንትው ብሎ ያሳየናል።

ኪነ ጥበብ ፖለቲከኛን ትዘልፍ ወይስ ፖለቲካን ትበልጥ? ፖለቲከኛን ስድብ አርቅቆ ለመሳደብ ምንስ መመሰጥ ያስፈልገዋል? ያልተሳደበውም የየብሔረሰቡ ሙዚቀኛ ቢሆን፣ ፖለቲከኞች የፈጠሩትን ውጥረት አርግቦ ከፖለቲካው በልጠው መገኘት ሲገባው  የብሔረሰቡ አባል በራሱ ኮርቶ ሲያበቃ ‹‹ከሌላው ጋር እንዴት በፍቅር ይኖራል፣ ይተሳሰራል›› የሚለውን ከማስገንዘብ ይልቅ፣ ልዩ እንደሆነ ከሌላው እንደሚበልጥ እንዲሰማውና ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን እያበሰረ ሲጓዝ፣ ‹‹ኪነ ጥበብ ሚናዋን በሳተ መልኩ የፖለቲካ ጡዘቱ ላይ ቤንዚል ማርከፍከፍ ጀመረች ማለት አይደል?›› እያልን ባለበት ሰዓት የሻምበል በላይነህ “የወሎ ልጅ” የሚል ሙዚቃ እንደገና በድምፃዊው ተሠርቶ ለአድማጭ ደረሰ።

ስለሙዚቃው የመጀመሪያ ቅጂ በእርግጠኝነት መናገር ቢሳነን እንኳን፣ ሻምበል በላይነህ በተለያየ መድረኮች ላይ የወሎዋን ልጅ ይዞ ሐረር፣ ሐዋሳ፣ ጅማ፣ አርባ ምንጭ… ላይ ‹‹ያዝ አብሽር›› ማለት የፈለገ ኮበሌን ያስደምጠን ነበር። በአዲሱ ቅንብር ኮበሌው እዚያው ወሎ ውስጥ ባሉ ከተሞች ላይ ብቻ የወሎዋን ቆንጆ ማዝናናትን ሲመርጥ አደመጥን። ደነገጥን። ከአንድ ክፍለ አገር ወደ ሌላው ለመዘዋወር አዳጋች የሆነባት አንዲትን አገር ተመለከትን። አርቲስቱም ለካ ተስፋ ቆርጧል? ከያኒ ተስፋ የቆረጠበት ኪነ ጥበብ የትስ ይደርሳል? ስንል አጉተመተምን።

እንዲህ እያልን ወደቀድሞ የኦሮምኛ ሙዚቃዎችና ሙዚቀኞች የኋሊት ተመለከትን። ወቅቱ የኢትዮጵያ ሙዚቃ በባህላዊ መሣሪያዎቻችን ደምቆ፣ በአገራችን ቅኝት ተወስኖ ይጓዝ የነበረበት ወቅት ነበር። በምሥራቅ ኦሮሚያ በርካታ ወጣቶች ጊታራቸውን የልብ በሚያደርስ ቃና ሲጫወቱ ይደመጣሉ። ወጣቶቹ ከኢትዮጵያ አራቱ ቅኝቶች ተሻግረው ባለሰባቱ ዲያቶኒክ ቅኝት ጊታር ላይ ለመጫወት የተቸገሩ አልነበሩም።

ዲያቶኒክ የተሰኘውንና ብዙ ሰው የውጭ አገር የሚለውን ቅኝት ‹‹በዚያ ጊዜ ከየት አገኙት›› ይላል ውጭ ቆይቶ የመጣ። ሐረርጌዎች የአደርኛውን ሙዚቃ በዲያቶኒክ እስኬል የተዋቀረ በመሆኑ ይህንን ሲሰሙ አድገዋልና ወደ ኦሮምኛው አምጥተው ለመጫወት አቋራጭ ሆኗቸዋል። በዚህ መልኩ የተሰናዱ የኦሮምኛ ሙዚቃዎች ቋንቋውን በማይሰሙ የተቀሩት ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከአንጀት የሚወደዱ ሆነው ዘመን ተሻግረዋል። እንዲሁ ከምዕራብ ኦሮሚያ ውሉድ የሆነውን አንጋፋ የኦሮምኛ ድምፃዊ አብተው ከበደን ሰምቶ በሙዚቃው ለመተከዝ ኦሮሞ መሆንና ቋንቋውን መናገር አስፈላጊ አይደልም፡፡

ከዚህ የሐሳብ ማዕበል የሚያናጥፍ የዘመኑ አንዳንድ የኦሮምኛ ሙዚቀኞች ሥራ ተደመጠ። የፖለቲካ መጫወቻ ካርድ የሆኑ ነገሥታትና የከተማ ስሞች በረገዳ አጅለው ማቅረብ የታዋቂነትና የዝና ማግኛ ሆኖ ሲጠቀሙት በመላ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ልቦና በጥበብ የነገሠውን የኦሮምኛ ሙዚቃ የጥበብ ውቃቢ በራቀው አቀራረብ የጥቂቶች ለማድረግ ሲጋጋጡ ማድመጥ ሲለመድ፣ በክቡራን ካፒቴኖች ብዙኃኑን አሳፍራ ትጓዝ የነበረች የጥበብ መርከብ ክቡራኑ ሲያልፉ መዘውሩን ለመያዝ የተሰናዱት ወጣቶች ወዴት ሊዘውሯት ይሆን? ብለን አዲስ ሥጋት አጫረብን።

በዚህ ሥጋት ውስጥ ሳለን ግብ፣ ኪነ ጥበብ ፖለቲካን መስደብ ካለበትም እንዲህ ትስደበው የሚያሰኝ የሙዚቃ አቀራረብ ከምዕራብ አፍሪካዋ አገር ሴኔጋል፣ ቪቪያን ቺዲዲ በተሰኘች እንስት ድምፃዊት ሲቀነቀን ሰማን።

ቪቪያን  ሴኔጋላዊት የፖፕ ሙዚቀኛ ስትሆን፣ እ.ኤ.አ. ሴፕቴምበር 29 1973 በሴኔጋል አትላንቲክ ውቅያኖስ አቅራቢያ ካሉ የባህር ዳርቻ ከተሞች አንዷ በሆነችው ምቦር ተወለደች። አባቷ ከሊባኖስ፣ እናቷ ደግሞ ከሞሪታንያ ናቸው። ከእናቷ ወገን የሆኑት አያቷ ከማሊ የመጡ ናቸው። ይህ የዘር ቅይጥ በምትሠራቸው ሙዚቃዎች ውስጥ ትልቅ ሚና ሲጫወት ይስተዋላል። በሙዚቃዎቿ ‹‹ምባላክስ›› የተሰኘውን ባህላዊ የሴኔጋል ጨዋታ ከተቀረው ዓለም ሥልት ጋር አጣምራ መሥራት ይቀናታል፡፡

ኪነ ጥበብ ፖለቲካን በልጣ ከፍ ብሎ መታየት  ምሷ ቢሆንም፣ ‹‹መሳደብም ከፈለጉ እንዲህ ነው‹‹ ያስባለን የቪቪያን ሙዚቃ ‹‹ሴኔጋል›› ይሰኛል ርዕሱ። ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ፣ ‹‹የሚሠሩት ፊልም ጎንደር ላይ ያነጣጠረ ነው›› በሚል ጉዳዩን ከዘረኝነት የመነጨ እንደሆነ አድርጎ ለመጠየቅ በተሞከረበት ወቅት፣ ‹‹እኔ እኮ ስለማውቀው ነገር መሥራቴ ነው፣ የሚያውቁት መሥራት ሥራን የተዋጣ ያደርጋል፣ ጠንቅቄ ስለማላውቀው ሥፍራ እንዴት እሠራለሁ፤›› ሲሉ ተደምጠው ነበር። ቪቪያንም ስለትውልዷ አከባቢ መዝፈኗ አንድም ፕሮፌሰሩ ካነሱት ሎጂክ ጋር አቆራኝተን ማየቱ ተገቢነት አለው፣ ሲቀጥል ግን አንድ ሰው እትብቱ ስለተቀበረበት አፈር ፈጭቶ፣ ጭቃ አቡክቶ፣ በአዛውንት ተመርቆ ስላደገበት ቀዬ መዝፈኑ ፍፁም ጤናማነት ነው። በዚህም አግባብ ሴኔጋላዊቷ ‹‹ሴኔጋል›› ብላ መዝፈኗ ተገቢነት አለው። ሆኖም እንዴት እንደዘፈነችው መመልከት ግን ተገቢነት አለው።

የሙዚቃው ግጥም ፈረንሣይኛ ቢሆንም ምን እያለች መሆኑን ለማድመጥ የሚከብድ አይደለም። ስለሴኔጋል ጨርሳ ጎረቤት አገሮችን ‹‹ምርታኒያ፣ ማሊ፣ ጊኒ›› እያለች ስታነሳሳ እናደምጣታለን። ታልፍና ከድንበር ተሻግራ ‹‹ጋና፣ ካሜሩን፣ ናይጄሪያ፣ ቱኒዚያ ሁሉ ሳይቀራት፣ ሴኔጋል በተሰኘ ሙዚቃዋ ውስጥ ትጠቃቅሳቸዋለች። ይህንን አድምጠን አንድ አርቲስት ራሱን ዓለም አቀፍ ዜጋ አድርጎ ማቅረብ ግዴታው መሆኑን ከመገንዘብ በላይ ‹‹ቪቪያን የተዋረሰችው የተለያየ አገር ደም አስገድዷት ነው፤›› ልንልም እንችላለን። ግድ የለም እንበል። በመጨረሻም ግን ‹‹ሴኔጋል›› በሚል ጀምሮ፣ ጎረቤት አገሮችን ጠቃቅሶ፣ የማይዋሰኑትን አስታውሶ፣ በመጨረሻ ከፈረንሣይኛው ተለይቶ ጎላ ብሎ በሚሰማ የሲቃ ድምፅ፣ ‹‹Africa Unite, That is my Dream for Tomorrow›› ወይም ‹‹የነገ ሕልሜ አፍሪካ አንድ አገር ስትሆን ማየት ነው›› በሚል ይጠናቀቃል።

ልዩነት በፖለቲከኛ ያለ ልክ በሚዘራበት፣ የተዘራውም አሽቶ እያነኮትን ባለበት የት እንደሚደርስ ባይገባንም፣ ወንዝ ከመነሻው እስከ መድረሻው በተለያዩ ማኅበረሰቦች መሬት ላይ አቋርጦ በቅብብል የሚጓዝ ሆኖ ሳለ በወንዝ ልጅ ተደራጅቶ ለመለየት ጥድፊያው ባየለበት በአሁኑ ጊዜ የሰው ልጅ ዘሩ የተዘራበት ጋር ተተክሎ ዕድገቱ ግን እንደ ግራር ሰፍቶ የሚጓዝ መሆኑን ከመንገር በላይ፣ ‹‹እዚህ ጋ ብወለድም አገሬ እዛ ድረስ ነው›› ብሎ ከማስታወስ በላይ ‹‹በአንዲት ገበሬ ማኅበር ብወለድም፣ አገሬ ዓለም ናት ብሎ ማኅበረሰብን ከማንቃት በላይ ፖለቲካን መስደብ አለ? ከፖለቲካ በላይ መንሳፈፍ አለ? መርዛማ ፖለቲካን ማርከሻ ዘዬ አለ? ‹‹የጥበብ ዓላማ የሰውን መንፈስ ከፍ ማድረግ ነው›› በሚል በ Pope John Paul II፣ (1978-2005 የቫቲካን ጳጳስ)፣ ‹‹የኪነ ጥበብ ዓላማ ጉጉትን መፍጠር ነው።›› ፓብሎ ፒካሶ፣ (1881-1973 ከስፔን ተነስቶ ሥዕልና ቅርፃ ቅርፅ ሥራው ዓለምን የዋጀ) በሚል ለተገለጸው ሐሳብ ተጨባጭ ማመሳከሪያ ይህ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገራችን የአንዲት ቀበሌን ሕዝብ አገሩ እዛችው እንደሆነ እንጂ ሥነ ልቦናውን አስጉዘው የኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ ብሎም የዓለም አካል እንዲሆን የሚደረገው ጥረት የተዳከመበት ሁኔታ እየተመለከትን ወይም ፖለቲካን ከመብለጥ ይልቅ ፖለቲከኛን ከአሉባልታ ባልተናነሰ መልኩ የመስደብ ልማድ እየተበራከተ ባለበት ሁኔታ አስቻለው ፈጠነ ‹‹አስቻለ›› የሚል አልበም አደረሰን። በዚህ አልበም ላይ ሙያዊ ትንታኔ ለመስጠት ሳንዳፈር፣ ሆኖም ግን ከላይ ካየናት ሴኔጋላዊት ድምፃዊት ጋር ሥራውን ለማስተያየት ቃጥቶናል።

አስቻለው ከጎጃም ዳሞት መነሻውን ካደረገ አባት ቻግኒ ላይ ተወልዶ ያደገ በመሆኑና በተለያየ አጋጣሚ የተለያዩ የአገሩ ሥፍራዎችን ማየቱ ስሪቱ ላይ የተለያየ እጅ አርፎበታል። የከያኒ ከአንዲት ቦታ በቅሎ ዓለም አቀፋዊ ሆኖ የመገኘት ግዴታ ተላብሷል (ከያኒ ይህንን ለመላበስ ከሥፍራ ሥፍራ መጓዝ፣ ከተለያየ ደም መዋረስ ሳያስፈልገው በምዕናቡ ዓለም አቀፋዊነትን መላበስ ይቻለዋል)። ይህም እንደ ሴኔጋላይቷ ድምፃዊት ስለበቀለበት ሥፍራ፣ ስለቻግኒ ፍቅር ብቻ አንስቶ፣ መነሻውን ከድንበርተኞቹ ጋር ሳያስተሳስር ማለፍ ተስኖታል። ጎጃምና ጉሙዙን ድንበርተኛ ጎረቤቱን አነሳስቶ ባይዋሰነውም በታሪክ ንባቡ ልቡን ስለገዛው የጎንደር ሕዝብ ጆሮ ገብ በሆነ ልሳን አንስቶ ቀጥሎ ወሎ ይደርሳል፣ ሸዋ ይወርዳል። ይህንን ስናይ በወጣት ከያንያን ሥጋት ያጫረብን አንድን ቀበሌ ከዛው እንዳይሻገር የሚያደርግ አቀራረብ ተሻግሮ፣ ፖለቲካን መብለጥ እንጂ መሳደብ ኪነት አለመሆኑን አበክሮ፣ ሰው ሥሩ ከተተከለበት ተነስቶ እንደ ግራር ሥፍት ብሎ አድጎ፣ ዙሪያውን የሚያዳርስ መሆኑን ያስገነዝባል።

“ዓድዋ” አለ አስቻለው ማሰሪያ ሲያበጃጅ። የሰላሌውን ረገዳ አስደምጦን የጀመረው ሙዚቃ፣ ‹‹ተራራን የሚያገዝፈው ርዝመት ስፋቱ ሳይሆን የተጻፈበት  ታሪክ ነው›› ይላል በመሃከል ላይ በሚደመጠው በትግርኛ የተሰናዳው ግጥሙ። ኢትዮጵያውያን ይህ ቀረ በማይባል ተጋድሎ፣ በድል የገዘፈ ተራራ ላይ በደም ያበጃጁትን ኒሻን ከራሳቸው አልፈው ተርፈው ለጥቁር ሕዝብ ሲያበረክቱ እናደምጣለን። ሐሳቡ አፍሪካዊነትን ያቀነቅናል።

‹‹ሰውና ሰውና ሰው ወርዶ ገጥሞ በዋለበት፣

ጥቁር አሸንፎ ክንዱን አሳየበት፣

በነጩ ሰማይ ላይ ዓለም ተማረበት፣

ክብር በእየ እልፍኙ በየዋለበቱ፣

ግዳጅ ተቆንጥሮ ተሰጠው ማዕረጉ›› ይላል አስቻለው፡፡ ምክንያቱም ቪቪያን ቺዲዲ ሴኔጋል በሚለው ሙዚቃዋ፣ እናፍቀዋለሁ እንዳለችው እ.ኤ.አ. በ2063 አፍሪካን እንደ አንድ አገር የማዋቀር ፍፃሜ ለሚተልሙ ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ዓድዋ የቤዛነት ስጦታና ማዕረግ ሆኖ እንካችሁ ተብሏልና።

ወርኃ የካቲት ላይ ነን። እንዘክረዋለን። መልካም የዓድዋ በዓል!!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው habeshaw2022@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles