Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዝንቅየከተሞች ማማ ‹‹ድል ይብዛ››

የከተሞች ማማ ‹‹ድል ይብዛ››

ቀን:

ተራራ ላይ ስላለች ከተማ ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? ይህንን ግዙፍ የኢትዮጵያ ማማ ረግጠው መልሰው ቁልቁል ሲወረወሩ የሚያገኟት ቀደምት ከተማ ናት፡፡ ሰሜንኛ ነዋሪዎቿ ሕይወትን ከገብስ፣ ከእህልና ከእህሉ በሚዘጋጀው ጠላና ኮረፌ ይታገሉታል፡፡ የከተማዋ ስም ‹‹ድል-ይብዛ›› ይባላል፡፡ የበየዳ ወረዳ መዲና ናት፡፡

በአገራችን ከሚገኙ ከተሞች ከፍታ ላይ በመገኘት ወደር የሌላት ከተማ ‹‹ድል-ይብዛ›› ናት፡፡ በድል ይብዛ ግምብ ቤት የመንግሥት ቢሮዎች ብቻ ናቸው፡፡ ሊያውም የበየዳ ወረዳ ምክር ቤትና አስተዳደር፣ እንዲሁም የከተማዋ ጤና ጣቢያ፤ በነገራችን ላይ.. በየዳ የሚለው ስያሜ መነሾው ብዙ ነው፡፡ ከመላምቶቹ አንዱ ግን በቀድሞ ጊዜ ከጃናሞራ ጋር በጥምረት ግብር ይገብሩ የነበር መሆኑና በኋላም ‹‹በየ ዕዳችን እንክፈል!›› የሚለው መነሻ ነው፡፡

ተራራ ስለወጣን እንጂ ከጎንደር ከተማ ርቀን ብዙም ሩቅ አገር አልሄድንም፤ 242 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንገኛለን፡፡ ከአዲስ አበቤዎች ደግሞ ገና ሺ ደፍነን አልራቅንም፤ የበየዳ ምድር ውርጭ ከሀሩር የተቀላቀለበት ነው፡፡ ዳሽን ስር ያለችው የደጀኗ መዲና ድል-ይብዛ ግን ደጋ ናት፡፡ ጋቢ ያለበሰ ሰው የማይመለከቱባት ቤተስኪያን የምትመስል ከተማ፡፡

- Advertisement -

መሽቷል፤ መብራት የለባትም፡፡ አምስት የማይሞሉ ቤቶች የሚንዶቆዶቅ የነፍስ ወከፍ ኃይል ማመንጫ (ጄኔሬተር) አላቸው፡፡ ርቦናል…! መጀመሪያ ጥጋቤን አገኘነው፡፡ ስለ ጥጋቤ በመረጃ ነበር የሰማነው፤ ወጣት እንደሆነ ተነግሮናል፡፡ ጋቢ የተከናነቡ ሰውዬ ከጥጋቤ ደሳሳ ቤት ወጡ፤

‹‹ደህና አመሻችሁ

‹‹እግዚሃር ይመስገን ›› አፋቸውን ጋቢ ውስጥ እንዳፈኑ መልስ ሰጡ፤

‹‹ጥጋቤን ፈልገን ነበር›› ዘለዓለም ጠየቀ፤

‹‹እኔ ነኝ›› አሉ ሽማግሌው፤ ክው አልን…፡፡ ክንብንባቸውን አወለቁ…፡፡ ወጣት ነበር፤ ሊያውም ጥጋቤ…፤ ተገረምን…፤ በመገረም ውስጥ ሆነን ሰላምታ ተለዋወጥን፤ አመጣጣችን፣ ጉዳያችንን አወራነው፡፡ እግዜር ይስጠው ወደ ዘርፌ ቤት ወሰደን፡፡ ‹‹ዘርፌ ቤት እንሂድ›› ሲል ሚስቱ መስላኝ ነበር፡፡ ዘርፌ የበየዳ አድባር ናት፡፡ ባለ ምግብ ቤቷ ዘርፌ፤ ጥሩ በየዓይነቱና ሽሮ ፈሰስ ትሸጣለች፡፡ ሽሮ ፈሰሱን አዘን አስነካነው፡፡ አበላላችን እህል ከሌለበት አገር የሄድን አስመስሎናል፡፡ አምሮት አያልቅም አይደል? ቢራ አማረን፤ ጥጋቤን ጠየቅነው…፡፡

‹‹እዚህ ብዙም የለ… አንድ ሁለት ቤት ቢኖር ነው! እስቲ እንሞክር››

መንገድ ጀመርን፤ ቢራ ፍለጋ፡፡ ጨለማው በየዳ ገላ ላይ ወርዶ ተኝቷል፡፡ አሉ የተባሉት ሁለት ቤቶች ጠየቅን የለም፡፡ የተጠረጠሩት ቤቶች ሄድን የለም፡፡ ድል ይብዛ ከዳሽን ቢራ ይልቅ ሜታ ቢራ የሚጠጣባት የዳሽን ላይ ከተማ ናት፡፡ ቢራ ቢኖርም ‹‹እንትን ቢራ ይሁንልኝ››፣ ‹‹እንትን ቢራ አድርግልኝ›› ብሎ መምረጥ የለም፤ እርስዎ ቢራ ይጠይቃሉ፡፡ የተገኘው ይቀርብልዎታል፡፡

ተስፋ ቆረጥን…

‹‹ጠላስ! ጠላ አትጠጡም?›› አለ ጥጋቤ፤ ተስፋ ለቆረጠ ሰው ጥሩ ሐሳብ ነበር፡፡

‹‹በቃ ይሻላል›› አለው አሰግድ፤

እንግዲያውስ እኔ ቤት እንሂድና ሰው እናስልክ…››

ወደ ቤቱ ሄድን፡፡ ጠባብና ጭቃ ቤት፡፡ በጣም የምትበርድ፡፡ እሳት ተያያዘ…፡፡ ኩራዟ ምድር ላይ እንዲሞቀን በተያያዘው እሳት ወላፈን ብርሃኗ ተዋጠ፡፡ ጠላውን የተላከው ልጅ ይዞ መጣ፡፡ ግን ኮረፌ ነበር፤ ጠላና ኮረፌ ልዩነት የለውም፡፡ ኮረፌን ጠላ ይሉታል ሰሜኖች፡፡ በየፊናችን ትክክል ነበርን፡፡ የተላከው ልጅ የማንጠጣውን ኮረፌ ከጥጋቤ ጋር ተያያዘው፤ ወደ መኝታችን ሄድን፡፡

ሔኖክ ሥዩም ‹‹የመንገድ በረከት›› (2007)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...