Tuesday, April 23, 2024

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ማግሥት ጀምሮ እንደሆነ በርካታ የታሪክ መዛግብት አስፍረዋል፡፡ ለሺሕ ዓመታት የቆየውን ዘውዳዊ መንግሥት መነቅነቅ የጀመሩ የፖለቲካ ቡድኖች የተነሱት በፋሺስት ወረራ ማግሥት ነው ይባላል፡፡ በግለሰብ ደረጃ ዜጎች የፖለቲካ ለውጥ ሲጠይቁ መታየት የጀመሩት በዚሁ ወቅት መሆኑን ብዙዎች ይገልጻሉ፡፡ በተናጠል ከሚነሱ ጥያቄዎች እስከ ሥር ነቀል የፖለቲካ ለውጥ ጥያቄ በብዙ መንገዶች የሕዝብ ብሶቶች መስተጋባት የጀመሩት ከፋሺስት ወረራ በኋላ መሆኑ በስፋት ይወሳል፡፡

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ይህ ዑደት ደግሞ ወደ ተማሪዎች እንቅስቃሴ እስኪሸጋገር ድረስ በነበሩት ዓመታት፣ በግልም በቡድንም ሆነው ነፃነትን የጠየቁና መስዋዕትነት የከፈሉ የታዩበት እንደሆነ በብዙ ጸሐፍት ተከትቧል፡፡

ባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847-1983›› በሚለው መጽሐፋቸው በኢትዮጵያ ታሪክ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ላይ ተቃውሞ በማንሳት እንደ ብላታ ታከለ ወልደ ሐዋሪያት ዓይነት ሰዎች ቀዳሚ እንደሆኑ ያወሳሉ፡፡ ከአልጋ ወራሽነታቸው ጀምሮ የንጉሡ አገልጋይ የነበሩት ብላታ ታከለ በጣሊያን ወረራ ወቅት ንጉሡ ከአገር መሸሻቸው እንዳስከፋቸው ታሪክ ጸሐፊው ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህ ያቄሙት ብላታ ታከለ ከድል በኋላ የንጉሡን መመለስም ተቃውመዋል፡፡ በተለይ ሀቀኛ አርበኞች ወደ ጎን ተብለው ባንዳ የነበሩትን ንጉሡ መሰብሰባቸው እንዳስቆጣቸው ይነገራል፡፡ በህቡህ ተቃውሞ ሲያደራጁ እየተያዙ በተደጋጋሚ ታሰሩ፡፡ ከእስር ባለፈ መንግሥት ተቃውሞ እንዲተው በሹመትና በጥቅም ሊደልላቸው ሞከረ፡፡ ሆኖም ንጉሡን አምርረው የጠሉት ብላታ ታከለ በ1962 በንጉሡ ላይ ቦምብ በመወርወር የግድያ ሙከራ አደረጉ በማለት መጽሐፉ ይተርካል፡፡ በዚሁ ንጉሡን የማስወገድ ጥረታቸው በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን የሚገልጸው መጽሐፉ፣ ብላታ ታከለ ለ30 ዓመታት ንጉሡን በመቃወም እንደኖሩ ነው የሚተርከው፡፡

በግለሰብ ደረጃ በዘውዳዊው ሥርዓት ላይ ከተደረጉ ተቃውሞዎች መካከል በሁለቱ ወንድማማቾች ግርማሜ ነዋይና መንግሥቱ ነዋይ የተመራው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራም እንደ አብነት ይጠቀሳል፡፡ መንግሥት የመገርሰስ ሙከራው በቀጣይ ለመጡ የፖለቲካ ለውጦች አርዓያ በመሆን የሚያክለው እንደሌለ ይነገራል፡፡ የጦርም የቀለምም ትምህርት የቀሰሙት ወንድማማቾቹ ጥቂት ቁልፍ የሚባሉ ባለሥልጣናትን አሰባስበው፣ በታኅሳስ 1953 ዓ.ም. የንጉሡን ለጉብኝት ከአገር መውጣት ተገን አድርገው በመሩት የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ውጤቱ ባይሰምርም ሥርዓቱን በደንብ መነቅነቃቸው ይወሳል፡፡

ሁለቱ ወንድማማቾች የቆሰቆሱት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ሥርዓቱን መለወጥ አልቻለም፡፡ ይሁን እንጂ የመፈንቅለ መንግሥቱ አስተባባሪዎች ሙከራ የንጉሡ ሥርዓት አይነኬ ነው የሚለውን ጥላ መግፈፉና ቀጥለው ለመጡ የነፃነት ትግሎች አርዓያ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

ሥዩመ እግዚአብሔር ተብሎ የሚጠራውንና አይነኬውን ሥርዓት ደፍሮ በመቃወም ቀዳሚ ከሆኑ ሌሎች ሰዎች መካከል የብርሃኑ ድንቄ (አምባሳደር) ታሪክ በብዙዎች ይነሳል፡፡ በንጉሡ መንግሥት በተለያዩ ኃላፊነቶች ተመድበው የሠሩት ብርሃኑ (አምባሳደር) በሳዑዲ ዓረቢያና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ሠርተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በሰኔ 1965 አድሏዊና የነቀዘ ያሉትን የንጉሡን መንግሥት በይፋ ከድተው በአሜሪካ ጥገኝነት መጠየቃቸው ይነገራል፡፡

የንጉሡን መንግሥት አላገለግልም ብለው ከአምባሳደርነታቸው መልቀቃቸው በጊዜው ታላቅ ድፍረት እንደነበር፣ ‹‹አይ ስታንድ አሎን›› ብለው በጻፉትና ‹‹ብቻዬን ቆሜያለሁ›› በሚል ርዕስ በተተረጎመው ግለ ታሪካቸው በሰፊው ከትበውታል፡፡ የዚያን ጊዜውን መንግሥት ተቃውሞ በአሜሪካም በመደበቅም ቢሆን ከባድ መስዋዕት ሳይከፍሉ ማምለጥ እንደማይቻል የሚገልጹት ብርሃኑ (አምባሳደር)፣ የመጣው ይምጣ ብለው ለንጉሡ በቀጥታ በጻፉት ደብዳቤ ተቃውሞአቸውን አስተጋብተዋል፡፡ አምባሳደሩ በዚህ ደብዳቤያቸው ከማስመሰልና ከመሸንገል ይልቅ፣ በሥርዓቱ ላይ እሳቸውም ሆኑ ብዙ ሕዝብ በሆዱ የቋጠረውን ያሉትን ብሶት በጠንካራ ቃላት አስተጋብተውታል፡፡

‹‹ሁሌም እንደምነግርዎት ለግርማዊነትዎ በቃላት የምንገልጽልዎና ህሊናችን ውስጥ የሚመላለሰው ሐሳብ እንደማይጣጣም ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች በአስመሳይነት ቢገፉበትም ውስጣቸው ላለው ግጭት እኔ አንድ ምስክር ነኝ፡፡ በነፃ ህሊናዬ አሁንም ለግርማዊነትዎ ማሳወቅ የምፈልገው ነገር ቢኖር አገራችን የምትድነው በከፍተኛ ሞራልና ነፃነት እንጂ እርስዎን በማሞገስና በማሞካሸት አለመሆኑን ነው፡፡ አገሪቱ ከሕገ መንግሥቱ ይልቅ በእርስዎ ትዕዛዝ በሚንቀሳቀሰው የጽሕፈት ሚኒስቴር እንደምትመራ የማያውቅ ሰው አለ ብለው ይገምታሉ? ሕዝቡም ነፃ ሆኖ እንዲናገር ከተፈቀደለት ሊነግርዎት ይችላል፡፡ የፍትሕ አስተዳደር ውስጥ ያለውን ብልሹ አሠራርና ግርማዊነትዎ በወንጀለኛና በፍትሐ ብሔር መቅጫ ሕግ ጠቅላይ ዳኛ ሆነው ፍትሕን እንዳሻዎ እንደሚነዱት የማያውቅ ያለ ይመስልዎታል? የፀጥታ ኃይሎችዎ በማናለብኝነት የሚፈጽሙት ተግባር የሌሎችን መብቶች እንደሚዳፈር የታወቀ ነው፡፡ በዚህ ደብዳቤዬ በግርማዊነትዎ አገዛዝ ዘመን የተፈጸሙትን በደሎችና ሥቃዮች ዘርዝሬ መጨረስ ያስቸግረኛል፡፡ ከሁሉ በላይ ግርማዊነትዎ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለው እንቅስቃሴ በተለይ የብሔሮች ጥያቄ አንድ ወቅት ፈንድቶ አደጋ እንደሚያመጣ እንዲገነዘቡት እፈልጋለሁ፡፡ ግርማዊነትዎ አቤቱታዬ እንደ ፊተኞቹ ደብዳቤዎቼ ያነጣጠረው የኢትዮጵያን ሕዝብ ለሥቃይና ለእንግልት የዳረጉትን ጭቆናዎችና ስህተቶች እንዲያስተካክሉና አሁንም ቢሆን ጊዜው እንዳልመሸ ለማሳሰብ ጭምር ነው፤›› በማለት ነበር አምባሳደሩ ለንጉሡ በጻፉት ደፋር ደብዳቤ ቀድመው ያስጠነቀቁት፡፡

በቀጥታ ሥርዓቱን ለመቃወም ከደፈሩ ሰዎች በተጨማሪ አገሪቱ ሊገጥማት የሚችለው አደጋ ቀድሞ የታያቸው ግለሰቦች በእነዚህ ጊዜያት ለንጉሡ መንግሥት ሲያሳስቡና ሲወተውቱ መቆየታቸው ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ የንጉሡ መንግሥት እነዚህን ማሳሰቢያዎችም ሆነ ማስጠንቀቂያዎች ተቀብሎ ማስተካከያ እንዳልወሰደ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡  

በተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩትና የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩት መላኩ ተገኝ (ዶ/ር) በዚህ ጉዳይ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ የንጉሡ መንግሥት የማይሰማ መንግሥት እንደነበር ገልጸዋል፡፡

‹‹አፄ ኃይለ ሥላሴ በፍጹም ማንንም የሚሰሙ መሪ አልነበሩም፡፡ አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ብቻ ሳይሆኑ ለሥርዓቱ በጣም የቀረቡ አራት ታዋቂ ሰዎችም ከእነ መንግሥቱ ነዋይ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ደብዳቤ ጽፈውላቸው ነበር፡፡ ጄኔራል ዓብይ አበበ፣ ሀዲስ ዓለማየሁና ተክለጻዲቅ መኩሪያ ያሉበት አራት ሰዎች ሆነው በአገሪቱ ሊደረግ የሚገባውን ለውጥ ጽፈው ለንጉሡ ሰጥተዋቸዋል፡፡ በአገሪቱ የፖለቲካ ማሻሻያ ተደርጎ ልክ እንደ እንግሊዞቹ ሕገ መንግሥታዊ ዘውዳዊ ሥርዓት ተፈጥሮ ሙሉ የመንግሥት ሥራው በጠቅላይ ሚኒስትር እንዲመራ ጠይቀዋቸው ነበር፡፡ እሳቸው ንግሥናቸው ሳይሻር መንግሥታዊ ሥራውን እንዲያስረክቡ ተጠይቀው ነበር፡፡ ንጉሡ ግን ይህን ሁሉ ውድቅ ነው ያደረጉት፤›› በማለት የንጉሡ መንግሥት ከአብዮቱ መፈንዳት ቀድሞ ያልተጠቀማቸው ብዙ ዕድሎች እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡

መላኩ (ዶ/ር) እንደሚሉት በኢትዮጵያ ወደ ተማሪዎች ትግል የተሸጋገረው የቀደመና ሲንከባለል የመጣ የሕዝብ የፖለቲካ ጥያቄ እንጂ፣ በተማሪዎች ንቅናቄ የተፈጠረ አዲስ ጥያቄ አልነበረም፡፡ የኤርትራ ፌዴሬሽን ሲፈርስ የትጥቅ ትግል ተጀምሮ እንደነበር ያነሱት ፖለቲከኛው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በርካታ ዓይነት የነፃነት ጥያቄዎችም አስቀድመው ማቆጥቆጣቸውን ያክላሉ፡፡ ከዚህ በመነሳትም በተማሪው ንቅናቄ ወቅት የተጠራቀሙ የሕዝብ ብሶቶች ጎልተው ከመስተጋባታቸው ውጪ፣ የተፈጠረ አዲስ ጥያቄ ወይም የብሔር ትግል እንዳልነበር ነው የሞገቱት፡፡ በኤርትራ፣ በትግራይ፣ በባሌና በሌሎች አካባቢዎች ቀድሞ ሕዝቡ ነፃነትን ሲጠይቅ እንደነበርም ያክላሉ፡፡ 

በርካታ የታሪክ መዛግብት ከትበው እንዳቆዩት የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ትግል የተጀመረው ከተማሪዎች የለውጥ እንቅስቃሴ ቀደም ብሎ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ግለሰቦች በተለያዩ መንገዶች በዘውዳዊ ሥርዓቱ ላይ ካነሷቸው የተናጠል ተቃውሞዎች በተጨማሪ በየጊዜው በየቦታው ብልጭ ድርግም ሲሉ የቆዩ በቡድን ወይም በማኅበረሰብ ደረጃ የተነሱ የነፃነት ጥያቄዎች መኖራቸው ይጠቀሳል፡፡  

ባህሩ (ፕሮፌሰር) በመጽሐፋቸው ከፋሺስት ወረራ ማግሥት ጀምሮ በትግራይ የመጀመሪያው የወያኔ አመፅ (ቀዳማይ ወያነ) እንደተከሰተ ከትበዋል፡፡ በራስ አበበ አረጋይ ጦር አዝማችነትና በእንግሊዞች የጦር አውሮፕላን ድጋፍ በ1936 እስኪከስም ድረስ አመፁ ንጉሡን ሲፈትን መቆየቱንም ይገልጻሉ፡፡ ይህ ከተከሰተ ከ20 ዓመታት በኋላ በባሌ ኤልከሬ አካባቢ የኦሮሞና የሶማሌ ተወላጆችን በማስተባበር የተቀጣጠለው ትግል ለሰባት ዓመታት ሥርዓቱን እንዳስጨነቀ መጽሐፉ ያብራራል፡፡ ይህ እንቅስቃሴም በንጉሡ ጠንካራ ጦር ቢዳከምም በሌላ አቅጣጫ በተለይ በጎጃም የገበሬዎች አመፅ መቀጣጠሉም ተጽፏል፡፡ የጎጃም አመፅ እስከ 1965 ዓ.ም. ቢቀጥልም፣ ሥርዓቱ ልክ እንደቀደሙት ሁሉ በጦር ኃይል እንዳዳፈነው መጽሐፉ ይገልጻል፡፡ ከእነዚህ የለውጥ እንቅስቃሴዎች በተጨማሪም በወሎ የጁ፣ በሲዳሞና በጌዴኦ አካባቢዎችም የሕዝብ እንቅስቃሴ ወይም የቡድን ትግል እንደነበር በበርካታ የታሪክ መዛግብት ተዘርዝሯል፡፡

ከእነዚህ አመፆችና ትግሎች ጀርባ ደግሞ የረዥም ዘመን የአስተዳደር በደል ብሶትን ሕዝቡ ሲያነሳ ቆይቷል፡፡ የፖለቲካ ጭቆና ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ ጥያቄዎችንም እንቅስቃሴዎቹ ማስተጋባታቸው ይነገራል፡፡ ከጭሰኝነት የመላቀቅና አርሶ ከመጠቀም ነፃነት ጀምሮ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ሕዝቡ በተለያዩ መንገዶች ማስተጋባቱን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

ይህን የሚደግፍ አስተያየት የሚሰጡት መላኩ (ዶ/ር)፣ ‹‹ብዙዎች የተማሪዎች ንቅናቄን የብሔር ጥያቄን የቆሰቆሰና ዋነኛው ምንጭ አድርገው ያቀርቡታል፡፡ የተማሪዎች ትግል የመሬት ላራሹ ጥያቄን ጨምሮ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ጥያቄን ማንሳቱ አይካድም፡፡ ይሁን እንጂ የተማሪዎች ንቅናቄ ያስተጋባቸው ጥያቄዎች በሙሉ ቀድሞ የሕዝቡ ብሶት የነበሩ እንጂ አዲስ የፈጠራቸው አልነበሩም፡፡ አንዳንዶች ታሪክን ባለመረዳት ወይም ለማወቅ ባለመፈለግና ለማሳሳት በሚል የተማሪዎች ንቅናቄ ውልደትን ከተገንጣይ ብሔርተኝነት ጋር ሁሌም አያይዘው ያቀርቡታል፡፡ በወቅቱ የራሳቸውን የብሔር ቡድን ብቻ ቀስቅሰው ለመገንጠል የሚታገሉ አብዮተኞች እንደነበሩ አይካድም፡፡ የተማሪዎች ንቅናቄ መነሻውና ማጠንጠኛው የዋለልኝ መኮንን ጽሑፍ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ዋለልኝ ጽሑፉን ለማቅረብ የተሻለ ሰው ነው በሚል ተመርጦ አቀረበው እንጂ ጉዳዩ በተማሪዎች ንቅናቄ የተነሳ ነው፡፡ ብዙዎቹ የሚጋሯቸው ጥያቄዎች የንጉሡ ሥርዓት በፈጠረው አፈናና ጭቆና ሲያመረቅዙ የቆዩ የሕዝብ ብሶቶች ናቸው፡፡ የኤርትራን ፌዴሬሽን ያፈረሰው የንጉሡ መንግሥት ነው፡፡ ጭቆና በቃን የሚሉ፣ ከበደልና አድሎ ለመላቀቅ የሚታገሉ ሕዝቦች ብሶት ሲያሰሙ ነው የኖሩት፡፡ የተማሪዎች ንቅናቄ በወቅቱ እነዚህን ብሶቶች ጮክ አድርጎ አስተጋባ እንጂ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የፈጠረው አዲስ የፖለቲካ ጥያቄ አልነበረም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡  

‹‹የ20ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ›› በተባለ መጽሐፋቸው ጥላሁን ብርሃነ ሥላሴ በኢትዮጵያ በንጉሡ ዘመን ይነሱ የነበሩ የሕዝብ ብሶቶችን ይዘረዝራሉ፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የኑሮ ሸክም፣ የፍትሕ ዕጦት፣ የሙስና መንሰራፋት፣ የሃይማኖት ነፃነትና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እያሉ ይጠቃቅሳሉ፡፡ በንጉሡ ዘመን መታያ በሚል ሥልጣን ለማግኘት ሲባል ምልጃና ጉቦ መክፈል ተልምዶ ነበርም ይላሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል የወረዳ አስተዳደር ለመሆን ሦስት ሺሕ ብር፣ ለአውራጃ መሪነት አምስት ሺሕ ብር፣ እንዲሁም ለአገር ገዥነት አሥር ሺሕ ብር የመታያ ገንዘብ በሙስና መልክ ይከፈል እንደነበር ከትበዋል፡፡ እነዚህን መሠረታዊ ጥያቄዎች የሚፈታ መንግሥት መጥፋቱ ሕዝቡን ወደ መራር ትግል እንዲገባ አንዳደረገውም ጸሐፊው ይገልጻሉ፡፡   

ዘውዳዊው ሥርዓት በጊዜው የሕዝቡን ችግሮች የሚመልሱ ዕርምጃዎች ሲወስድ ነበር ብለው የሚሞግቱ በርካታ ሀያሲያን አሉ፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከፋሽስት ወረራ በኋላም ቀድመው ጀምረዋቸው የነበሩ ዘመናዊ ነገሮችን የማስፋፋት ሥራ በሰፊው ማጠናከራቸው በብዙ ጸሐፍት ይገለጻል፡፡

ለምሳሌ ሳሂድ አድጁሞቪ ‹‹ዘ ሂስትሪ ኦፍ ኢትዮጵያ›› መጽሐፉ ይህን ሐሳብ የሚደግፉ ነጥቦችን ያነሳል፡፡ አገር ሕገ መንግሥት ከማጻፍ ጀምሮ፣ ጠንካራ ብሔራዊ ጦር፣ አየር ኃይልና አየር መንገድን መመሥረት እንደቻሉ ይዘረዝራል፡፡ ፋብሪካዎችን ከመክፈት በተጨማሪ አዲስ አበባን ለማዘመን ጥረዋል፡፡ ይህ ሁሉ ግን ለሕዝብ ታስቦ የሚሠራ ሳይሆን ለሥርዓቱ ተጠቃሚነት ታስቦ የሚሠራ ነበር በማለት ጸሐፊው መልሶ ሐሳቡን ውድቅ ያደርገዋል፡፡ ንጉሡ በሒደት አገር ከማዘመን ይልቅ በፍጹማዊ በሆነ ፈላጭ ቆራጭ መዳፋቸው ሥር ሁሉንም ነገር መጠቅለላቸው ጎልቶ እንደወጣ ይኼው ጸሐፊ ይገልጻል፡፡

ራሳቸውም በተማሪዎች ንቅናቄ ማለፋቸውን የሚናገሩት የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ተቋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንጋፋው የሥነ ማኅበረሰብ ምሁር የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው በቅርቡ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የንጉሡ መንግሥት ላይ ተቃውሞ የበረታውና ወደ አብዮት ማፈንዳት ትውልዱ የገባው በስሜትና በውጭ ኃይሎች መሰሪ ቅስቀሳ እንደሆነ በሰፊው አስረድተው ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ደሃ አገር እንደሆነች መረሳት እንደሌለበት ያመለከቱት የራስወርቅ (ዶ/ር)፣ የዛሬ 50 እና 100 ዓመታት ደግሞ በባሰ ሁኔታ ላይ እንደነበረች በመጠቆም ነው ማብራሪያቸውን የሚቀጥሉት፡፡ 

‹‹ከየት ነው የተነሳነው የሚለውን ሁልጊዜ ማስታወስ አለብን፡፡ እኔ በተማሪዎች ንቅናቄ ወቅት ተሳታፊ ስለነበርኩ የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ይወቀስባቸው የነበሩ ነገሮችን አስታውሳለሁ፡፡ ወራሪው ፋሺስት ጣሊያን ከኢትዮጵያ የወጣው በ1933 ዓ.ም. ነው፡፡ ከ1933 ዓ.ም. ጀምሮ በእነ መንግሥቱ ንዋይ እስከተሞከረው የ1953 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት ወቅት ድረስ 20 ዓመታት ነው ያለፈው፡፡ በእነዚህ 20 ዓመታት ውስጥ ግን ስንት መንገድ እንደተሠራ አንመለከትም ነበር፡፡ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ብቻ የነበራት አገር ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ድረስ መድረሷን አናስተውልም ነበር፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንኳ ዕፍኝ የማይሞሉ የመሣፍንት ልጆች ግብፅ እስክንድሪያ እየተላኩ ነበር የሚማሩት እኮ፡፡ ከወረራው ማክተም እስከ 1953 ዓ.ም. በነበሩት ዓመታት በርካታ ሃይስኩሎች፣ ተግባረ ዕድ፣ ሚሊታሪ አካዴሚ፣ አየር ኃይል አካዴሚ፣ አውራ ጎዳና፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ ባንክና ሌላም ብዙ ነገሮች ተሠርተዋል፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ ልጅ ሳሉ እሳቸውና 13 የሚሆኑ ልጆች የቤተ መንግሥት ምንጣፍ ላይ ተቀምጠው ነበር ዘመናዊ ትምህርት መሰጠት የተጀመረው፡፡ እሳቸው ከሥልጣን ሲወገዱ ግን ሁለት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ልጆች በየተማሪ ቤቱ በመላ አገሪቱ ትምህርት ይከታተሉ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ለውጥ በአገሪቱ መጥቶም ግን ዕድገቱ በፍጥነት አልሄደም በሚል የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለውጥ እንጠይቅ ነበር፡፡ ያኔ በወጣትነት ልማት የለም! የንጉሡ መንግሥት ይውደም! ብንልም አሁን ላይ ሆኜ ተመልሼ ሳየው ግን ሁኔታው ሌላ ነገር ሆኖ ነው የሚታየኝ፡፡ ለዚህ ማነው ተጠያቂው ለሚለው እኛ አይደለንም፡፡ የቀደመው ትውልድ የተሠራውን ነገር አልነገረንም፡፡ የእኛ የመረጃ ምንጭ ታላላቆቻችን ሳይሆኑ ፈረንጅ ጸሐፊያን ነበሩ፡፡ ተቺ የሆኑ እንደ ሪቻርድ ግሪንፊልድ ያሉ የውጭ ጸሐፍት እንዲህ ነው ብለው የሚጽፉትን እያነበብን ነበር አብዮታዊ ለውጥ ካልመጣ ስንል የነበረው፡፡ በጊዜው የኢትዮጵያ መንግሥት ተጨባጩን መረጃ ከማቅረብ ይልቅ፣ አታንብቡ እያለ የውጭ ጽሑፎችን ያቃጥልና ይቆልፍባቸው ስለነበር ለእኛ የበለጠ ጉጉት የሚጨምር ሆነ፡፡ የውጭ ጸሐፊያንን ሂስ ከማንበብ በዘለለ ለትምህርት ወደ ውጭ አገሮች በመሄድ ሌሎች አገሮች የደረሱበትን ቦታ ስናይ፣ ኢትዮጵያ አብዮታዊ ለውጥ ያስፈልጋታል የሚል ስሜትን የሚያሳድር ነበር፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

በጊዜው በነበሩ አብዮተኞች ዘንድ ግን የነበረውን ማሻሻል ይቻላል ከሚለው ይልቅ፣ ያለውን አፍርሶ መገንባት ነው የሚሻለው የሚለው ስሜት ገዝፎ መስረጹን ያስረዱት የራስወርቅ በስሜት አብዮቱ እንደተፈጠረ ነበር የገለጹት፡፡ ጥቂት የማይባሉ ምሁራን ይህን ሐሳብ ቢደግፉትም በተቃራኒው ደግሞ የንጉሡን መንግሥት በአብዮት ወደ ማስወገድ የተገባው በራሱ በዘውዳዊ ሥርዓቱ ለውጥን አለመቀበል ባህሪ ገፋፊነት እንደሆነ ይሞግታሉ፡፡

በተማሪዎች እንቅስቃሴ ተሳታፊ የነበረችውና ‹‹ማማ በሰማይ›› በሚል ርዕስ የተተረጎመ ‹‹የታወር ኢን ዘ ስካይ›› ተነባቢ መጽሐፍ ደራሲዋ ሕይወት ተፈራ፣ የተማሪዎችን የፖለቲካ ለውጥ ጥያቄ ምንጭ በሰፊው ለማስቀመጥ ሞክራለች፡፡ ተማሪዎች በጊዜው እንቅስቃሴያቸው ጀብደኝነትና ስሜታዊነት የሚንፀባረቅበት ነው ቢባልም፣ መሠረታዊውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥያቄ ግን እንዳነሱ ጸሐፊዋ ትሞግታለች፡፡

‹‹መሬት ለአራሹ ሲሉ በአደባባይ የጮሁት ተማሪዎቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄን እንዳገኙት ይህ አንድ ማስረጃ ነው፡፡ ደረታቸውን ለሥርዓቱ ጥይት ለመስጠት ካልሳሱት ከእነዚህ አብዮተኛ ተማሪዎች መካከል ከራሱ ከዘውዳዊው ሥርዓት የተገኙ፣ ሀብታሞችና ምንም ያልጎደለባቸው ወጣቶችም ነበሩበት፡፡ ተማሪዎቹ ያን የለውጥ ጥያቄ ያነገቡት አንዳንዶች እንደሚሉት በርዕዮተ ዓለም ፋሽን ተጠምደው ወይም በጀብደኝነት ሳይሆን እውነተኛ በሆነ የአገር ፍቅርና ለወገን የመቆቀርቆር ስሜት ነው፤›› ትላለች፡፡

ሳራ ቮን እ.ኤ.አ. በ2003 ላይ ባቀረበችው ‹‹ኢትኒሲቲ ኤንድ ፓወር ኢን ኢትዮጵያ›› በተባለ የጥናት ሥራዋ፣ ንጉሡ የተማሪዎቹን እንቅስቃሴ ቀድመው እንዲቀጩ መመከራቸውን ታወሳለች፡፡ ‹‹እነዚህን የደሃ ልጆች ማስተማር ከቀጠሉ በኋላ አናትዎ ላይ ይወጣሉ በሚል በመኳንንቶቻቸው ተመከሩ፡፡ እሳቸው ግን በርካታ ኢትዮጵያውያንን ውጭ ሄደው እንዲማሩ አደረጉ፡፡ በአገር ቤትም ዩኒቨርሲቲዎችን ከፈቱ፡፡ ተማሪው እያደር ሲነቃና ዓለም የደረሰበትን ሁኔታ ሲገነዘብ ንጉሡን ለውጥ በሚል ጥያቄ ወጥሮ ያዛቸው፡፡ እ.አ.አ. ከ1970ዎቹ አንስቶ በኢትዮጵያ የተከሰቱ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ለውጦች በሙሉ የዚህ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውጤቶች ናቸው›› በማለት ነበር ጸሐፊዋ የተማሪዎቹ እንቅስቃሴ የፈጠረውን ተፅዕኖ ኃያልነት ያስቀመጠችው፡፡

ንጉሡ የተማሪዎችን ንቅናቄ በጊዜ ለማኮላሸት ብዙ መሞከራቸው ይነገራል፡፡ በርካታ የተማሪዎች እንቅስቃሴ መሪዎች መታሰርና መገደላቸው ይነገራል፡፡ ይህ ዕርምጃ የፈየደው ነገር ግን አልነበረም፡፡

‹‹መሬት ለአራሹ፣ ትምህርት ለሁሉም፣ ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም፣ የዴሞክራሲ መብቶች ይከበሩ፣ የሴቶች እኩልነት ይረጋገጥ፣ የሃይማኖት እኩልነት ይስፈን፣ የሠራተኞች ደመወዝ ይሻሻል…›› በሚሉና በሌሎችም በርካታ መፈክሮች የተስተጋቡት የለውጥ ጥያቄዎች ቀስ በቀስ ከተማሪዎች አልፈው የሁሉንም ኅብረተሰብ ክፍል ድጋፍ እያገኙ መምጣታቸውን ብዙዎች ይገልጻሉ፡፡  

እነዚህ የለውጥ ጥያቄዎች ከየካቲት ጀምሮ በተከታታይ በአደባባይ ትዕይንተ ሕዝቦች መስተጋባት በቀጠሉበት በዚያ ወቅት ደግሞ የሕዝቡን ቁጣ የሚያጋግሉ የተዳፈኑ የሥርዓቱ ችግሮች መጋለጥ መጀመራቸው፣ አብዮቱን የበለጠ እንዳጋመው ብዙዎች ጽፈዋል፡፡ የዘውዳዊው መንግሥት መወገዱ አስፈላጊ ነው የሚለው ተቃውሞ ሌላው ቀርቶ ወደ ራሱ ወደ ሥርዓቱ መዋቅር ውስጥ መዝለቁን በጊዜው የነበሩ ከትበውታል፡፡

ይህ በተማሪዎች የለውጥ ጥያቄ ትግል የተቀጣጠለው ተቃውሞ በዚህ መንገድ ግሎ አብዮቱን እንዳዋለደ የታሪክ ጸሐፍት ይገልጻሉ፡፡ የተናቁት ተማሪዎች ያነሱት ጥያቄ ወደ መላው ሕዝቡ ተሸጋግሮ በተፈጠረው አብዮት ለረዥም ዘመን ሲከበርና ሲታፍር የኖረውን ንጉሣዊ ሥርዓት ከሥር መንግሎ እንደ ጣለው ነው ብዙዎች የሚስማሙት፡፡

ከ1957 ዓ.ም. ጀምሮ ለአሥር ዓመታት ንጉሡን ሲፈታተን የቆየውን የተማሪዎች አመፅን በመስዋዕትነቱ አቻ የሌለው ጠንካራ ትግል ሲሉ ታሪክ ጸሐፊው ባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር) በመጽሐፋቸው አስቀምጠውታል፡፡ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ሕዝባዊ አመጽን አስከትሎ ንጉሣዊ ሥርዓቱን አዳከመው ይላሉ፡፡ በዚህ መካከል ግን ለሥልጣን ሲያደባ የቆየው ደርግ የተባለው ወታደራዊ ቡድን ሥልጣኑን እንደመነተፈ ይተርካሉ፡፡

አብዮቱ ለሁሉም ዱብ ዕዳ እንደነበር የሚጠቅሱት ባህሩ (ፕሮፌሰር) ‹‹የታገሉለትን ተማሪዎች ሳይቀር አብዮቱ እንደ ማዕበል መታቸው፡፡ የገዥው መደብ አባላት በአብዮት መመታታቸውን ለማጤን ፋታ ሳያገኙ ማዕበሉ ጠራርጎ ወሰዳቸው፡፡ ብዙዎች አብዮት መፈንዳቱን ያወቁት ዘግይተው ነው፡፡ የሒደቱን ማዕበል ለመግለጽ ፍንዳታ ከሚለው የተሻለ ቃል ማሰብ ይከብዳል፡፡ አብዮቱ መደናበርና መደናገር ባስከተለበት፣ እንዲሁም አሠላለፍን ከለውጡ ጋር ማስተካከል ፈተና በሆነበት በዚህ ወቅት አገሪቱን ፍጹማዊ ወታደራዊ አገዛዝ ጠቀለላት፤›› ሲሉ ነበር ያን የታሪክ ዑደት የገለጹት፡፡

ስለዚሁ የታሪክ አጋጣሚ የተጠየቁት የያኔው አብዮተኛ መላኩ (ዶ/ር)፣ አብዮቱ ወዲያው መሸነፉን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በእኔ ግምት የየካቲት አብዮት ተሸንፏል፡፡ ተሸነፈ ማለት ደግሞ የተነሳበትን ዓላማ አላሳካም ማለት ነው፡፡ ከተነሳባቸው ዓላማዎች መካከል ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም ከሚለው ጀምሮ እስከ መሬት ለአራሹና የሴቶች እኩልነት ብዙ ጥያቄዎችን አንስቷል፡፡ ከተነሳባቸው ዓላማዎች በእኔ ግምት 95 በመቶዎቹ አልተሳኩም፡፡ የመሬት ለአራሹን ጥያቄ ደርግ መለሰው ቢባልም ጉዳዩ ተድበስብሶ ነው ዛሬ ድረስ የቀረው፡፡ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄም ጽንፍ መንገድ ሄዶ ዛሬ አገር እያቃወሰ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኢሕአፓ የቀድሞ አባሉ እንደሚናገሩት ቢያንስ ሕዝባዊ መንግሥት ለማቋቋም ደርግ ፈቃደኛ ሆኖ ቢሆን ኖሮ፣ ብዙ ጥያቄዎች በሒደት ይመለሱ እንደነበር ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ በደርግ የተጀመረው የአብዮቱን መነሻ የሆኑ ጥያቄዎችን የማዳፈንና የማድበስበስ ጥረት በኢሕአዴግና ከዚያም ወዲህ መቀጠሉን ይገልጻሉ፡፡

‹‹በየካቲት አብዮት ደርግ እስኪመሠረት እስከ ሰኔ 20 ድረስ በየአደባባዩ በሚካሄዱ ተቃውሞዎች ይስተጋቡ የነበሩ የትግል ጥያቄዎችን አንድ በአንድ መዝግበናል፡፡ በዚህ ጊዜ ጭቁኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ ነፃ እንዲወጣ ከሚጠይቁ መፈክሮች ውጪ የብሔር መብት ይከበር የሚሉ የብሔር ጥያቄዎች አልተነሱም ነበር፡፡ በሒደት ደርግ በወሰዳቸው ዕርምጃዎች ግን ተገንጣይ ብሔርተኞች መፈልፈል ጀመሩ፡፡ ደርግ ከመጣ በኋላ በነበሩት ጥቂት ወራት ነበር እንደ ሕወሓት፣ ኦነግና የኦጋዴን ነፃ አውጪ ድርጅት የተመሠረቱት፤›› በማለት የአብዮቱ መሸነፍና የትግሉ መዘረፍ የብሔር ፖለቲካን የበለጠ እንዳጠናከረ ነው የተናገሩት፡፡

በአብዮቱ ወቅት የተነሱና የዚያን ጊዜው ትውልድ ሲያነሳቸው የቆዩ የነፃነትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በኢትዮጵያ የመመለስ ዕድል አላቸው ወይ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው መላኩ (ዶ/ር)፣ አሁን ከዚያ ይልቅ የአገሪቱ ህልውና ተጠብቆ መቆየቱ ጥያቄ ውስጥ ወድቋል በማለት ነበር ምላሽ የሰጡት፡፡ የአብዮቱ ጥያቄዎች ተመልሰዋል አልተመለሱም የሚለው ጥያቄ እስካሁንም ማከራከሩ እንደቀጠለ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -