Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ለኢትዮጵያ የሚበጀው ኮስተር ብሎ የባህር በር ጥያቄውን መግፋት ብቻ ነው›› ብሩክ ኃይሉ (ፕሮፌሰር)፣ አንጋፋ የዲፕሎማሲና የሚዲያ ባለሙያ

ለረጅም ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተምረዋል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፈረንሣይና በአሜሪካ ተመድበው በዲፕሎማትነት አገልግለዋል፡፡ ዳያስፖራው በ‹‹ኖ ሞር›› ንቅናቄ ሲያደርግ በማስተባበር ተሳትፈዋል፡፡ መንግሥትና ዳያስፖራው ለአንድ አገራዊ ግብ በጋራ መሠለፍ የሚችሉት እንዴት ነው በሚሉ ነጥቦች ዙሪያ በቅርበት ከሚያውቁት ተነስተው ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ ያደረጉትን ስምምነት ተከትሎ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር የገባችበትን ውጥረት በተመለከተ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡ በወቅታዊ የዲፕሎማሲና የጂኦ ፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ከዮናስ አማረ ጋር ያደረጉት ቆይታ ለንባብ በሚመጥን መንገድ እንደሚከተለው ተሰናድቷል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የዲፕሎማቶች ማኅበር መቋቋሙን ሰምተናል፡፡ ማኅበሩ እንዴት ተዋቀረ? ምን ዓይነት ሚና ይኖረዋል ተብሎ ነው የታሰበው?

ብሩክ (ፕሮፌሰር)፡- ጡረታ የወጡ እንዲሁም በሥራ ላይ ያሉ ዲፕሎማቶችን አንድ ላይ ያሰባሰበ ማኅበር ነው፣ ሙያዊ ማኅበር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ማኅበር ቢቋቋም አገሪቱ ትጠቀማለች የሚል እርሾ ውይይት ነበር፡፡ የዛሬ አራት ወር ግድም ግን ትልቅ ስብሰባ ተደርጎ ከአገር ቤትና ከውጭ ሁሉም ዲፕሎማቶች ተጋብዘው ምሥረታው ዕውን ሆነ፡፡ መተዳደሪያ ደንቡ በአደራጅ ኮሚቴው ቀድሞ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ውይይት ከተደረገ በኋላ ምርጫ በማድረግ የጠቅላላ ጉባዔ ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢ፣ ጸሐፊ፣ ምክትል ጸሐፊ፣ እንዲሁም ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ጸሐፊ ሆኖ በአጠቃላይ 11 አመራሮች ተመርጠው ወደ ሥራ እንዲገባ ተወስኗል፡፡ በሲቪክ ማኅበራት ድርጅት የማስመዝገቡ ሥራ እያለቀ ነው፡፡ በቅርቡም በዚሁ የማኅበሩ ምሥረታ ጉዳይ ላይ ይፋዊ መግለጫ ይሰጣል፡፡ በግሌ ያገኘኋቸው ዲፕሎማቶች በዚህ ጉዳይ ደስተኛ እንደሆኑ አይቻለሁ፡፡ የብዙ አገሮችን ተሞክሮ ስናይ በውጭ ግንኙነትና በዲፕሎማሲ መስክ ክፍተቶቻቸውን የሞሉት እንዲህ ባሉ መንገዶች ነው፡፡ ጥናት በማካሄድ፣ ከመንግሥት በኩል የሚቀርቡ አማራጭ ፖሊሲዎችን በማጥናት፣ በመተቸትና ግብዓት በመስጠት ገንቢ ሚና ሊኖረው ይችላል፡፡ በየአኅጉሩ ለብዙ ዓመታት እስከ አምባሳደርነት ያገለገሉ፣ የካበተ ዕውቀት ያላቸውና ሕይወታቸውን ለዚህ ሙያ የሰጡ ሰዎች በአንድ ጥላ መሰባሰባቸው ለአገሪቱ ዕምቅ አቅም የሚፈጥር ነው፡፡

ለምሳሌ እንደ አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ ያሉ ለ52 ዓመታት ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ጀምሮ በዲፕሎማትነት አገር ያገለገሉ ሰዎች አሉ፡፡ ውስብስብ የሆነውን የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ሆነ የአፍሪካ ኅብረት ጉዳይ ከሥር ጀምሮ የሚያውቁ ናቸው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጄኔቫ ተወካይ ሆነውም ሠርተዋል፡፡ በሌሎችም ቁልፍ አገሮች ሠርተዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎች መጽሐፍ ማለት ናቸው፡፡ እያንዳንዱ አገርን በዲፕሎማትነት ያገለገለ አምባሳደር በግሉ የሚናገረው ብዙ ታሪክ አለው፡፡ ይህንንም በመጻሕፍት መልክና በሌላ ለታሪክ ማስቀረት እንፈልጋለን፡፡ ሰው አላፊ ነው፣ ተንቀሳቃሽ ላይብረሪ የሆኑ ሰዎች ያላቸውን ሐሳብ ደግሞ መዝግቦ ለታሪክ ማቆየት አስፈላጊ ነው፡፡ ለምርምርና ጥናት ብቻ ሳይሆን ትውልዱ ይማርበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ወጣቱን ማነቃቃትም የማኅበሩ ዓላማ ነው፡፡ በዲፕሎማሲው ዓለም ያለው ትግል እየጨመረ ነው የሚሄደው፡፡ በባለብዙ ወገን ግንኙነትም ሆነ በሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮች አገር የሚወክሉ ወጣቶችን ማፍራት አስፈላጊ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አፅቀ ሥላሴ (አምባሳደር) ሹመትን እንዴት አገኙት?

ብሩክ (ፕሮፌሰር)፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 116 ዓመታት ያስቆጠረ ተቋም ነው፡፡ አፄ ምኒልክ ካቋቋሟቸው የመጀመሪያው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው፡፡ አሁን ደግሞ ይህን ተቋም ለመምራት አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ተሹመዋል፡፡ ጉምቱ ዲፕሎማት ለቦታው መሾሙ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ባልሳሳት ለረጅም ጊዜ ካየናቸው ካለፉት ሚኒስትሮች የአሁኑ የዲፕሎማሲ ባለሙያ ናቸው፡፡ ዲፕሎማሲ ልክ እንደ ጦር ሠራዊት ሁሉ ከሥር ተጀምሮ በደረጃ የሚታደግበት በጥብቅ ዲሲፕሊን የሚመራ ሙያ ነው፡፡ ከሥር ከጀማሪ ዲፕሎማትነት ጀምሮ አታሼ፣ ሦስተኛ ጸሐፊ፣ ሁለተኛ ጸሐፊ፣ አንደኛ ጸሐፊ እያለ በማደግ ወደ አምባሳደርነት የሚሸጋገር ዕድገትን ልክ እንደ ሠራዊቱ የሚከተል ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በፖለቲካ ሹመት፣ በፖለቲካ አሠላለፍና በፖለቲካ ማመጣጠን ነበር ሹመት የሚደረገው፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲሁም የፖለቲከኞች ጡረታ መውጫ ነበር አይደል?

ብሩክ (ፕሮፌሰር)፡- እውነቱን ለመናገር ወደ እዚያ ደረጃ ማውረዱ እንኳን ትንሽ ይከብዳል፣ ተገቢም አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም እዚያ ውስጥ ስለሠራሁ አውቀዋለሁ፡፡ ከውጭ ሊመስል ቢችልም ሀቁ እንደዚያ አይደለም፡፡ የእኔ ዋና ነጥብ ቀደም ባለው ጊዜ የካቢኔ ሚኒስትሮች ሹመት ሲደረግ እከሌ ከተባለው ፓርቲ እንዲህ ዓይነት ቦታ እየተባለ ለቦታው ይመጥናሉ የሚባሉ ሰዎችን የመመደብ ሁኔታ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥም ነበር፡፡ ሆኖም ይህንን አሠራር የዲፕሎማሲ ባለሙያዎችን ቦታው ላይ ከማስቀመጥ ጋር ስናነፃፅረው ሁለቱም የየራሱ አዎንታዊና አሉታዊ ጎን ያለው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የዲፕሎማሲ ባለሙያ ሆኖ ከታች ጀምሮ ጥርሱን ነቅሎ በዲፕሎማትነት ያደገ ነው ማለት ነው፡፡ ጉራንጉሩን ያውቀዋል፣ በየዴስኩ ቁልፍ በሆኑ ቦታዎች ሠርቷል፡፡ ከሪፖርት አጻጻፍ ጀምሮ እስከ መረጃ አሰባሰብ፣ እንዲሁም ስብሰባዎችን በመካፈል ብዙ ልምድ አካብቷል ማለት ነው፡፡ ለረጅም ዓመታት በዲፕሎማትነት ያገለገሉት አምባሳደር ታዬ እንደተሾሙት ሁሉ፣ በእነዚህ ደረጃዎች አልፎ የሚመጣ ሰው ለብዙ ጉዳዮች አዲስ አይሆንም፡፡ አምባሳደር ታዬ ይህን አልፈውና ንዑስ የሥራ ክፍሎችንና የሥራ ክፍሎችን ሁሉ መርተው ነው ወደ ሚኒስትርነት የመጡት፡፡ ይህም በመሆኑ የሚመሩት ዘርፍ በሁሉም አቅጣጫ ምን እንደሚገጥሙት በቀላሉ ይረዳሉ፣ በዚህም ሥራቸው የቀለለ ይሆናል ተብሎ ይታመናል፡፡

ይሁን እንጂ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቀጥታ ወደ እዚህ ቦታ ቢመጣ ወይም ደግሞ አገር በሚመሩት ፓርቲዎች ውይይት ተወስኖ እከሌ ይመደብ ተብሎ ቢመጣ ራሱን የቻለ ፈተና ይኖረዋል፡፡ የግለሰቡ ጥረት ይወስናል፣ የራሱ ዝንባሌ ያስፈልጋል፣ የራሱ ብልህነት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን የሥራውን ሳይንሳዊ ባህሪ በመማር በኩል ጉድለት ይኖራል፡፡ ለምሳሌ አምባሳደር ታዬ በፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሩቅ ናቸው፡፡ የዲፕሎማሲ ሙያን የኖሩበት ናቸው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ የመሥሪያ ቤቱን ጣጣ፣ ከበጀት ጀምሮ እስከ ሠራተኛና ጉራንጉሩን ሁሉ የሚያውቅ ሰው መመደቡ ጥሩ ነው፡፡ ይህን ስል ግን ከውጭ ተመድቦ የሚመጣ ሰው የራሱ ጥሩ ጎኖች የሉትም ማለቴ አይደለም፡፡ አንዳንዴ የተበላሹ ነገሮችን ሥር ነቀል በሆነ መንገድ ለመቀየር ይረዳል፡፡ ደፈር ብሎ ነገሮችን በጥበጥ አድርጎ በበጎ ለመቀየር ያግዛል፡፡ በአብዛኛው ግን በውጭ ግንኙነቱ ረገድ የሚመደቡ ሰዎች ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ የፖለቲካ ምደባ ነው የሚል ነገር ቢኖርም ከእሱ በተጨማሪ ግን የሰዎቹ ለዘርፉ ያላቸው ዝንባሌ፣ የተግባቦት ሁኔታ፣ ሥነ ምግባር፣ የውጭ አገሮች ልምድና ሌላም ነገር ታይቶ እንደሚመደብ ይታወቃል፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ግንኙነቱ በፖለቲካ ምደባ መደረጉና ጡረታ መውጫ መሆኑ ካለው ከባድ ኃላፊነት አንፃር በአገሪቱ ላይ ችግር ፈጥሯል ይባላል፡፡ ይህንን መሰሉ የአሠራር ክፍተት ክምችት አገሪቱ ዛሬ ለገጠሟት ዲፕሎማሲያዊ ፈተናዎች መንስዔ ነውም ይባላል፡፡ በዚህ ይስማማሉ?

ብሩክ (ፕሮፌሰር)፡- ይህ ብዙ ክርክር ይነሳበታል፡፡ በዲፕሎማሲው ሰዎችን በሙያ መመደቡም ሆነ በፖለቲካ መመደቡ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን መላው ዓለም የሚሠራበት ነው፡፡ አሜሪካም ብትሆን 70 በመቶ በሙያ 30 በመቶ ደግሞ በፕሬዚዳንቱ ነው ሰዎች የሚመደቡት፡፡ ፕሬዚዳንቱ ወንድሙን መመደብም ይችላል፣ ሕገ መንግሥታዊ መብት አለው፡፡ ትራምፕ ለምሳሌ አማቹ ጀርድ ኩሽነርን መድቦ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የሴኔቱ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኮሚቴ እንዲህ ባሉ ውሳኔዎች ማመን አለበት፡፡ በአሜሪካ ፓርላማው ጥርስ ያለው ነው፡፡ የሚሾመው ሰው ለሥራው መዘጋጀቱ በደንብ ይገመገማል፡፡ በዚህ ጉዳይ ቀልድ የለም፡፡ ከጠዋት እስከ ማታ ሰውዬውን አስቀምጠው ለሥራው ብቃት ያለው መሆን አለመሆኑን አበጥረው ይመረምራሉ፡፡ ይህ ታልፎ ነው ሹመቱ ይሁንታ የሚያገኘው፡፡ ስለዚህ የበለፀጉ አገሮችም የፖለቲካ ምደባን ይከተሉታል፡፡ እንደ ፈረንሣይ ያሉ አገሮች ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ሙያዊ አሠራርን ሲከተሉ ይታያል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርብ ዓመታት በፐብሊክ ዲፕሎማሲው ዳያስፖራው ከፍተኛ ዕገዛ አድርጓል፡፡ ከ‹‹ኖ ሞር›› ንቅናቄ ጀምሮ ስኬታማ ሥራዎችን ሠርቷል ይባላል፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግሥትና በዳያስፖራው መካከል ሰፊ ልዩነት ተፈጥሯል፡፡ በፐብሊክ ዲፕሎማሲም ሆነ በሌላ መንገድ ገንቢ ሚና ከሚጫወተው ከዳያስፖራው ጋር መንግሥት በመጣላትና በመናቆር አትራፊ መሆን ይችላል? ይህን ልዩነት እንዴት ማጥበብና ለአንድ አገራዊ ጥቅም ተቀራርቦ መሥራት የሚቻለው?

ብሩክ (ፕሮፌሰር)፡- ይህ በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው ውስብስብና አሳሳቢ ጥያቄ ነው፡፡ ለብዙ ዓመታት ይህ ጉዳይ እንደ አንድ አባዜ ሲከተለን የቆየ ነው፡፡ እኔ ከመንግሥት አቅጣጫ ብቻ አላየውም፡፡ መንግሥት ከዳያስፖራው ጋር መልካም ግንኙነትና የፈለገውን ዓይነት መልካም ፍላጎት ቢኖረውም፣ ግንኙነቱን ማቃናቱ ግን ቀላል ሊሆን አይችልም፡፡ ከዳያስፖራው ወገንም ብዙ ዓይነት ፍላጎት አለ፡፡ እኔ እዚያ ውስጥ ስለነበርኩና ስለኖርኩበትም አውቀዋለሁ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ነው ዳያስፖራው ከአገሩ የወጣው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቢቀድምም ኢኮኖሚያዊ ምክንያትም ያስወጣው ብዙ ነው፡፡ በተለይ በአሜሪካ በሰፊው የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ከ50 ዓመታት በፊት ጀምሮ የወጣ ነው፡፡ አገር ውስጥ ብዙ ዓይነት የፖለቲካ ለውጦች ተፈራርቀዋል፡፡ መጀመሪያ ንጉሡ ወረዱ፣ ከዚያ ደርግ መጣ፣ ቀጥሎ ሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ ተፈጠረ፣ እንዲህ እያለ አሁን ድረስ የተፈራረቁ ለውጦች በዳያስፖራው ላይ የራሳቸው ተፅዕኖ አላቸው፡፡ ወይም ለእስር የተዳረገ፣ ካለው ሥርዓት ጋር ዓይንና አፍንጫ የሆነ፣ የሚወራወር ቀርቶ ሁሉም ዓይነት ሰው ነው ወደ ውጭ የሚሰደደው፡፡ በአሜሪካ የሚኖረውን ዳያስፖራ ባለፉት አምስት ዓመታት ከመንግሥት ጋር የነበረውን ግንኙነት ከዚያ ቀደም ከነበሩት 27 ዓመታት ጋር ልናነፃፅረው እንችላለን፡፡ ዳያስፖራው አንዳንድ ጊዜ ከመንግሥት ጋር የመቀራረብ ነገር ቢኖረው በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ግንኙነቱ በረድ ሲል ነው የሚታየው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ሲመጡ የነበረውን የዳያስፖራውን የሞቀ አቀባበል ታስታውሳለህ፡፡ አዲስ ምዕራፍ ውስጥ ገብተናል በሚል ብዙ ዓይነት የሞቀ ድጋፍ ለመንግሥት ሲያደርግ ነበር፡፡ እኔም በነበርኩበት ዋሽንግተን እስከ 50 ሺሕ ሰው ተሰብስቦ ነበር አቀባበል ያደረገው፡፡ መንግሥትና ዳያስፖራውን የሚያሰባስበው የአገር ጉዳይ ነው፡፡ ይህች የምንወዳትን ኢትዮጵያን በተመለከተ ነው፡፡ የምንወዳት ኢትዮጵያን የምናይበት መነጽር ግን የተለያየ ነው፡፡ ዳያስፖራው ደግሞ ወጥና አንድ የሆነ ሳይሆን የተለያየና ቅይጥ ነው፡፡ አገሩን ከመናፈቅ ጀምሮ ለአገሩ በጎ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚፈልግ አለ፡፡ አገሩን በዕውቀቱም በገንዘቡም መርዳት የሚፈልግ አለ፡፡ እዚህ አገር ቤት የተለያየ የፖለቲካ ፍላጎት እንዳለው ሁሉ፣ በውጭ በዳያስፖራው ውስጥም በተመሳሳይ የተለያየ የፖለቲካ አጀንዳ ያለው አለ፡፡ ‹‹አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል›› እንደሚባለው ሁሉ፣ በዚህ የሚፈጠር የፖለቲካ ሁኔታ በውጭም ይንፀባረቃል፡፡ ዳያስፖራው ከዚያ በተጨማሪም በመካከሉ በብሔርና በፖለቲካ አመለካከት የተለያየም ነው፡፡ መንግሥትን ለመቀበል ብዙ ችግር አለ፡፡ መንግሥትም እንደ አባት ሆደ ሰፊ ሆኖ ረባሽ ጨዋ ሳይል መቀበል ላይ ችግር አለበት፡፡ በመለስ ዜናዊ ጊዜ ለተወሰነ ጊዜ የመቅረብ ሙከራ ነበር ከዚያ ግን ፀረ ሰላም፣ ፀረ ልማት የሚባል ፍረጃ ሲመጣ ዳያስፖራውን አሸሸው፡፡ ስለዚህ ነገርዬው ከሁለቱም ማለትም ከዳያስፖራውም ከመንግሥትም አቅጣጫ መታየት ያለበት ነው፡፡

መንግሥት ምን አለመ? ምን ዕቅድ ይዟል? የሚለውን ብቻ ሳይሆን ዳያስፖራውስ ምን ፍላጎት አለው የሚለው መታየት አለበት፡፡ እኔ እዚያው ስለነበርኩ አንዳንድ ነገሮችን መታዘብ ችያለሁ፡፡ ከዚያ ከአሜሪካ ሆኖ በሪሞት ኮንትሮል ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካውን መለወጥ የሚፈልግ ዳያስፖራ አለ፡፡ ያልጣመውንና ያልፈለገውን መንግሥት እቀይራለሁ ብሎ ብዙ ነገር የሚያደርግ አለ፡፡ ችግራችን ውስብስብ ነው፡፡ በአገራችን ፖለቲካ አንድ ትልቅ ችግር ያለው ደግሞ መንግሥት ማንም ይሁን ማን፣ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ በአገሪቱ ሁለንተናዊ አስተዳደር ጉዳይ የሚመለከተው እሱ ነው ማለት ነው፡፡ አገሩን ከመምራት ጀምሮ ከወረዳ እስከ ቀበሌ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ፣ የድርቅ ጉዳይ፣ የውጭ ግንኙነት ጉዳይ፣ የጎረቤቶች ሥጋት፣ ውስጣዊ ችግርና ሌሎችም ሁለንተናዊ የአገር አስተዳደር ጉዳዮች መንግሥትን ይመለከቱታል፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች በየደቂቃውና በየሰከንዱ ምን እንደሚሆንም ያውቃል ተብሎ ይታመናል፡፡ ሕዝቡ ግን እነዚህን ነገሮች ላያውቅ ይችላል፡፡ ዳያስፖራው እነዚህን ነገሮች የሚመለከትበት መንገድ የተለየ ስለሚሆን ደግሞ በዚህ መሀል ልዩነቱ ይሰፋል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገው የባህር በር የመግባቢያ ስምምነት ዱብ ዕዳ ነገር አልሆነም? ስምምነቱ ከሶማሊያ ጋር ከባድ ውጥረት ውስጥ ከቷል፡፡ ከዚህ አንፃር ስምምነት ማድረጉ ያለው አስፈላጊነትስ ምንድነው?

ብሩክ (ፕሮፌሰር)፡- እንዲህ ያሉ ብዙ ነገሮችን የሚቀይሩ ነገሮች ሲፈጸሙ በቶሎ ወደ ሕዝብ አይሠራጩም፡፡ መጀመሪያ የውስጡን ሥራ ጨርሰህ ሁሉንም መልክ አስይዘህ ነው አንድ ደረጃ ስትደርስ ነው የምታወጣው፡፡ በቅርቡ ይፋ የሆነው የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ ስምምነት እኔ በግሌ በጣም ደስ ያሰኘኝ ነው፡፡ ለረጅም ዘመን ሕዝቡ አንዲት የባህር በር እንኳ ሳይኖረን እያለ ሲጠይቅ የነበረውን ጉዳይ መንግሥት ለመመለስ ያደረገው ጥረት በመሆኑ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ መንግሥትም በግልጽ እንዳስቀመጠው የባህር በር ሊኖረን ይገባል፡፡ 120 ሚሊዮን ሕዝብ እያለን ታንቀን መኖር አንችልም የሚለውን ሐሳብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚቀበለው ነው፡፡ ይህን ከዛሬ 30 ዓመታት በፊት ማሳካት የምንችልበት ዕድል ነበር፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ጭምር ማግኘት አለባችሁ የሚለውን ይገፋ ነበር፡፡ ሌላው ቢቀር አሰብን በድርድር አግኙ እያሉ ወትውቷል፡፡ ኤርትራ ሲባል ከላይ እስከ ታች ነፃ ነው በሚል ዕድላችንን ሳንጠቀም ቀርተናል፡፡ ሆኖም ፖለቲካ አንዴ ካመለጠ አመለጠ ነው አይመለስም፡፡ እያንዳንዱ መንግሥት ጥሩውንም መጥፎውንም ሥራ ተቀብሎ ነው የሚኖረው፡፡ ወደብ ያስፈልገናል የሚለውን በማመን መንግሥት ወደብ ካላቸው በዙሪያው ካሉ አገሮች ለማግኘት ጥረት ማድረጉ የሚደነቅ ነው፡፡ በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚና በሌሎችም መንገዶች አባብሎ ችግሩን ተረድተው ወደብ እንዲሰጡት መጠየቁ ጠቃሚ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ ነው ብሎ ከዚህ ዕድገት እንደሚጠቀሙ አሳምኖ የባህር በር ስጡኝ ማለት ኃጢያት አይደለም፡፡ ይህን ጥያቄ ለመመለስ ደግሞ ሶማሌላንዶች እሺ ብለዋል፡፡ ሶማሌላንዶች ይህን ጥያቄ ለምን ተቀበሉት የሚለው የራሱ መነሻ አለው፡፡ ገና ዕውቅና ያላገኙ አገር ናቸው፡፡ ዕውቅና ማግኘት ይፈልጋሉ፡፡ የመጀመሪያ አንድ አገር ዕውቅና ከሰጣቸው ደግሞ ሌላው ይከተላል ተብሎ ነው የሚታመነው፡፡ እንግሊዝ፣ ኢትዮጵያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ዴንማርክ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ ግብፅ፣ ቱርክና የመሳሰሉት አገሮች ሁሉ ሐርጌሳ ውስጥ ኤምባሲ አላቸው፡፡ ሶማሌላንዶች ዕውቅና ባይኖራቸውም ከብዙ መንግሥታት ጋር ግንኙነት አላቸው፡፡ ዕውቅና ካገኙ ደግሞ ይህን ዓለም አቀፍ ግንኙነታቸውን ለማስፋፋትና ለማጠናከር ጠቃሚ ይሆንላቸዋል፡፡ ሶማሌላንድ በታሪክም ካየን የእንግሊዝ ሞግዚት አስተዳደር ሥር የነበረች እንጂ ቅኝ አገር (ፕሮቴክቶሬት እንጂ ኮሎኒ) አልነበረችም፡፡ ‹‹ኮሎኒ›› ማለት በጉልበት መጥቶ ቅኝ ገዥ ኃይል አስገብሮ ሲኖር ነው፡፡ ‹‹ፕሮቴክቶሬት›› ደግሞ የበላይ ጠባቂ ሆኖ መተዳደር ማለት ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1884 እንግሊዞች በሶማሌላንድ በብዛት ከሚገኘው ከኢሳቅ ጎሳ ጋር በመስማማት የበላይ ጠባቂ ሆነው ማስተዳደር የጀመሩ ሲሆን፣ ሶማሌላንዶችም የራሳቸው የተወሰነ ነፃነት ይዘው ነው የቆዩት፡፡

ጣሊያኖች እ.ኤ.አ. በ1890 ባህረ ነጋሽ (ኤርትራን) ወረሩ፡፡ ከዚያም ወርደው ሶማሊያ የሚባለውን ደቡባዊ የሶማሊያ አካባቢን በቅኝ ግዛትነት ያዙ፡፡ በዕድሜ ራሱ ከታየ ሶማሌላንዶቹ ይቀድማሉ ማለት ነው፡፡ ሶማሌላንዶቹ ‹‹ፕሮቴክቶሬት›› እንጂ እንደ ሶማሊያ ቅኝ ተገዥም አልነበሩም፡፡ ነፃ በመውጣትም ቢሆን የቀደመችው ሶማሌላንድ ነበረች፡፡ ጣሊያን ከተሸነፈች ጊዜ ጀምሮ ቅኝ የምትገዛቸው አገሮች በሙሉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሥር ሲተዳደሩ ቆይተዋል፡፡ ሶማሊያም በተመድ ሥር ቆይታ ነው ነፃ የወጣችው፡፡ በጥቂት ቀናት ውስጥ ነበር ሶማሊያና ሶማሌላንድን የማዋሀድ ሥራ የተሠራው፡፡ ሶማሌላንዶቹ እንደጻፉትም በሞቅታና በሆይ ሆይታ ነበር የተዋሀዱት፣ ይህ መረሳት የለበትም፡፡ ሌላው ደግሞ ሶማሌላንዶች ከአንድነት መንግሥት ሥር ለመውጣትና ነፃ አገር ለመሆን ሲያምፁ ከውህደቱ በኋላ ሦስት ዓመት እንኳ አልፈጀባቸውም፡፡ በውህደቱ ተውጠው ነበር፡፡ በቁጥር ሁለት ሦስት እጅ ከሚበልጣቸው ከሶማሊያ ጋር መዋሀዳቸው በፖለቲካም፣ በቁጥርም፣ በሁሉም መንገድ እንዲዋጡ ነው ያደረጋቸው፡፡ ስለዚህ ወዲያው ነበር ነፃ ለመውጣት ትግል የጀመሩት፡፡ በዚያድ ባሬ ጊዜ ብዙ ጭፍጨፋ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ይህን ሁሉ አልፈው ተዋግተው ነው ነፃ የወጡት፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ከእነሱ ጋር በሰጥቶ መቀበል ስምምነት ነው የባህር በር ለማግኘት ጥረት የጀመረችው፡፡ ሳትጫን፣ በፍላጎትና በሰጥቶ መቀበል ነው፡፡ የባህር በር ሲሰጡን ከእኛ የሚጠብቁት ነገር አለ፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድና በኢትዮ ቴሌኮም ድርሻ እንዲኖራቸው ይደረጋል፡፡

አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እንደ ዋቢ ሸበሌ ያሉ የኢትዮጵያ ውድ የውኃ ሀብቶችን በካናል ጠልፎ ማጋራትንም የመሳሰሉ ዕቅዶች አሉ፡፡ ሶማሊያ 90 በመቶ በኢትዮጵያ የውኃ ሀብት ላይ ጥገኛ የሆነ ሕዝብ አላት፡፡ ዓባይን ለግብፅና ለሱዳን እንደምንሰጠው ሁሉ ገናሌና ዋቢ ሸበሌ የመሳሰሉ ሀብቶቻችንም ለሶማሊያ ይፈሳሉ፡፡ የሶማሊያ ግብርና በእነዚህ ሀብቶች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ተንኮል የምታስብ አገር አይደለችም፡፡ ሆኖም እነሱ ነገሮችን ባልተፈለገ አቅጣጫ የሚወስዱ ከሆነ እኛም ተፅዕኖ ማድረጊያ አማራጮች እንዳሉን በደንብ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ የሶማሊያ አፀፋ በጣም ፅንፍ የወጣ ነው የሆነው፡፡ ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነትና አንድነት እየተጋፋች ነው የሚል ስሞታ እያቀረቡ ነው፡፡ ይህን ደግሞ በዓለም መድረክ እያስተጋቡት ነው፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ በተደረገው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ላይም ከፕሮቶኮል ውጪ በሆነ ሁኔታ የታጠቁ ጠባቂዎቻቸውን ይዘው ወደ ስብሰባ አዳራሽ ለመግባት የሶማሊያ መሪዎች ጥረት በማድረግ አምባጓሮ መፍጠራቸው ይታወሳል፡፡ እስከ ግብፅና ሌሎች አገሮች ተሯሩጠው ድጋፍ ለማሰባሰብ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ እነሱ በኢትዮጵያ ላይ ችግር ለመፍጠር ላይ ታች በሚሉበት በዚህ ወቅት፣ ብዙ ሺሕ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሶማሊያን ለመጠበቅ በአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ሥር ተሠማርቶ ነው የሚገኘው፡፡ የእኛ ልጆች ናቸው ለሶማሊያ ሞተው ከመንግሥት አልባ አገርነት እንድትወጣ ሲታገሉ የቆዩት፡፡ እነ አልኢትሀድ፣ እስላማዊ ፍርድ ቤቶችና አልሸባብን በመዋጋት የኢትዮጵያ ሚና ትልቅ መሆኑ መረሳት አይኖርበትም፡፡

ሪፖርተር፡- ከሶማሊያ በኩል የገጠመው ፈተና ቀላል እንዳልሆነ እየታየ ነው፡፡ በተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ጉዳዩ እስከ መታየት ደርሷል፡፡ ሶማሊያውያን ቀላል የማይባል አንድነትና ትብብር በዚህ ጉዳይ ላይ ፈጥረዋል፡፡ በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ ያደረገችውን ስምምነት እንዴት ወደ ተግባር መለወጥ ትችላለች? ከስምምነቱ ማፈግፈግ ቀላሉ መፍትሔ አይደለም ወይ ስለሚባለው ምን ይላሉ?

ብሩክ (ፕሮፌሰር)፡- ያን ያህል አያስቸግረንም፡፡ አንደኛ አዲስ ነገር ስታመጣ የሚገጥምህ ተቀባይነት ቀስ በቀስ ነው የሚያድገው፡፡ መጀመሪያ ትርምስ ይፈጠራል፡፡ የሶማሊያን ሁኔታም ብታየው ቀስ በቀስ እየሰከነ ነው የመጣው፡፡ በሒደት ደግሞ ይረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በአካባቢው አገሮች ዘንድም ቢሆን ኢትዮጵያ እውነት አላት የሚለውን ለመረዳት ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ፖለቲካ ልክ እንደ ሽቶ ነው፣ አንዴ የረጨኸው ቀስ ብሎ ነው ሽታው የሚያውደው፡፡ የሶማሊያ ተቃውሞም ቢሆን ኢትዮጵያን የሚያስቆም አይደለም፡፡ የሶማሊያው መሪ ዝም ማለትም አይችሉም፡፡ ምክንያቱም አገር እየመሩ ዝም ካሉ የሚደርስባቸው የፖለቲካ ውርጅብኝ ቀላል አይሆንም፡፡ ስለዚህ ልቦናቸው እያወቀም ቢሆን የሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ኢትዮጵያን መቃወማቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ሆኖም እሳቸው ስለጮሁ የሚቆም ነገር አይደለም ጉዳዩ፡፡

ሪፖርተር፡- ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ በዙሪያው የሆኑ ነገሮችን ማየት አይገባም? በዚህ ጉዳይ ላይ ኢጋድና የአፍሪካ ኅብረት ጥንቃቄ የተሞላበት አቋም ነው ያንፀባረቁት፡፡ አጋር የሚባሉ የአውሮፓ ኅብረትም ሆነ አሜሪካ ቁጥብነትን ነው ያሳዩት፡፡ ቻይናማ ጭራሽ ተቃውማዋለች፡፡ ቱርክ ጉዳዩን ከመቃወም አልፋ ከሰሞኑ ከሶማሊያ ጋር የወታደራዊ ስምምነት እስከ ማድረግ ሄዳለች፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨባጩ ሁኔታ ሲታይ ኢትዮጵያ ብቻዋን የቆመች ይመስላል፡፡ መፍትሔው ምንድነው?

ብሩክ (ፕሮፌሰር)፡- መፍትሔው ማፈግፈግ አይደለም፣ ጉዳዩን ለሁሉም ማብራራት ነው፡፡ ቱርኮች ከሶማሊያ ጋር ወታደራዊ ስምምነት ቢፈራረሙም ከኢትዮጵያ ጋር በብዙ ቢሊዮን የሚነግዱ አገር ናቸው፡፡ ይህን በቀላሉ ማጣት የሚፈልጉ አይመስለኝም፡፡ የአፍሪካ ኅብረትና ኢጋድም ቢሆኑ በመርህ ደረጃ ከሶማሊያ ጋር መቆም አለባቸው፡፡ ይሁን እንጂ ለኢትዮጵያ የሚበጀው ኮስተር ብሎ የባህር በር ጥያቄውን መግፋት ብቻ ነው፡፡ አሁን የባህር በር ጉዳይን ለመመለስ ካልተነሳን ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን ብዙ መስዋዕትነት ሊከፍሉበት ይችላሉ፡፡ አሁን ጦር ሰብቀንና በወረራ አይደለም የባህር በር ስጡን ያልነው፡፡ በጂቡቲ ለምሳሌ ወታደራዊ የጦር ሠፈር ለመፍጠር ዘጠኝና አሥር አገሮች ይርመሰመሳሉ፡፡ ሩቅ ያሉ አገሮች መጥተው ላይ ታች ይላሉ፡፡ ጃፓኖች ጂቡቲ መጥተው ምንድነው የሚሠሩት? ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር በ50/60 ኪሎ ሜትር ርቀት ተቀምጣ ያለ ባህር በር አንገቷን የሚታነቀው በምን ምክንያት ነው? ዓለም አቀፍ ሕጉም ቢሆን የባህር በር የማግኘት ፍላጎታችንን ይደግፋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ሐሳብ ማቅረብ ባልተገባ መንገድ የሚያስበይን ከሆነ እንደ አገር በአጠቃላይ የሳትነው ነገር አለ ብዬ እገምታለሁ›› ደስታ ጥላሁን፣ የኢሕአፓና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና...

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ‹‹እርስዎ ንጉሥ ነዎት ወይስ ጠቅላይ ሚኒስትር?›› የሚል ጥያቄ እንዳቀረበች በሰፊው ሲወራ ሰንብቷል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያደረጉት የቅርቡ...

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...