Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትለምን ፋይዳ ቢስ ‹ፓርቲ›ነትን ማለፍ አቃተን?

ለምን ፋይዳ ቢስ ‹ፓርቲ›ነትን ማለፍ አቃተን?

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ‹የብዙ ፓርቲ ሥርዓት› ተጀመረ የሚባለው በሕወሓት/ኢሕአዴግ ገዥነት ውስጥ ነው፡፡ ዕድሜውን ሰላሳ አድርገን እንውሰደውና በሰላሳ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከማይረቡ ያለፉ ፓርቲዎች ጎልበተው ለምን አልወጡም? ይህ እንቆቅልሽ ለብቻው ቦታ ሊሰጠው ይገባል፡፡

በሕወሓት/ኢሕአዴግ 27 ዓመት አገዛዝ ውስጥ ለኢትዮጵያ የምንታገልና ለብሔር የምንታገል የሚሉ ብዙ ፓርቲዎች መጥተው ሄደዋል፡፡ የተሞገሰውና መንበር የተቆጣጠረው ርዕዮተ ዓለም ብሔርኝነት እንደ መሆኑም የሚበዙት በየብሔር ሠፈር የተበጣጠሰ ዕይታ ዓላማ የነበራቸው ነበሩ፡፡ በየትኞቹም ዓይነት ፓርቲ ተብዬዎች በኩል ግን ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ትርጉም ያለው ጉልምስና ያሳዩ ቡድኖች አልተገኙም፡፡ የሆነ ቡድን ብቅ ሲል፣ ‹‹ሕወሓት/ኢሕአዴግ ጠፍጥፎ የሠራው/ተለጣፊ!›› አለዚያም ‹‹የዱሮ ሥርዓት ናፋቂ/ፀረ ሰላም!…›› የሚል ቅጥያ አብሮ ይወጣለታል፡፡ ዋል አደር ብሎ የውስጥ ሽኩቻ ይመጣል፡፡ አንጃ መፍጠርና መሰንጠቅ፣ ተነጥሎ መውጣት፣ ከሌላ ጋር መጣበቅ ወይም መቀላቀል፣ ምርጫ መዳረሻ ላይ ጠርቀም ያለ የሕዝብ ድምፅ ባገኝ ተብሎ ወይም ሕወሓት/ኢሕአዴግን በጠንካራ አቅም ለመገዳደር ተብሎ ትብብር ይፈጠራል፡፡ በትብብር ውስጥ ተናጭቶ መነጣጠል፣ በትብብር ጊዜ የተጀመረ መታመስ ወደ ተነጣጠሉት ቡድኖችም ማለፍ፣ እየተቦጨቁ ማነስ፣ ሌላ ስብሰብና ቅንብር ደግሞ መፍጠር… በብዙ ፓርቲዎች ኑሮ ውስጥ የታየው የዚህ ዓይነት እንዘጭ እምቦጭ ጉዞ ነው፡፡

- Advertisement -

በአመለካከት፣ በፖለቲካ ባህል፣ በድርጅት ዲሲፕሊንና ግዝፈት፣ በፖለቲካ ትንታኔ ልቀትና በሕዝብ ተሰሚነት ተከታታይ ዕድገት ለምን ቸገረ? የሚል ጥያቄ ሲነሳ ብዙ ሰዎች ላይ ቶሎ ድቅን የሚለው ማመካኛ የሕወሓት/ኢሕአዴግ አፈና፣ ሰርጎ ገብነት፣ ወንጀላና እስራት ነው፡፡ እውነት ነው፣ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ሰርጎ ገብቶ መበጥበጥንና ከውጭ ሆኖ በሕግ ስም ማሸትን አቀናጅቶ ሲገለገልበት ኖሯል፡፡ እውነት ነው፣ የኢሕአዴግ ሰርጎ ገብ ሻጥር ብዙ ድርጅቶችንና ኅብረቶችን ሲያፈርስ ዓይተናል፡፡ የአየለ ጫሚሶ ‹‹ቅንጅት›› መፈጠር፣ ኦብኮ ተፈንክቶ መጠሪያው ለተለጣፊው አንጃ መሰጠቱ፣ ቁልጭ ያሉ ጥቂት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ግን ሕወሓት/ኢሕአዴግ በቀጥታ የማይደርስባቸው በስደት ያሉ ቡድኖች አገር ቤት ካሉት የተሻለ ዕድገት አላሳዩም፡፡ እነሱም የኖሩት ሲሰባሰቡ፣ ሲተባበሩ፣ ሲባሉና ተመልሰው ሲበተኑና ሲሰነጣጠሩ ነው፡፡ እየሠረገ ተቀናቃኞቹን ሲያዳክም የኖረው ሕወሓት/ኢሕአዴግ ራሱ በአንጃ ከመታመስና ከመሰንጠቅ አላመለጠም፡፡ ንጠቱና ‹‹አንጃን የማጥራት›› ምንጣሮው በሕወሓትና አሕአዴግ ውስጥ ተካሂዶ የተገኘው ውጤትም ከበፊቱ ይበልጥ የአንድ ግለሰብ ተቆጣጣሪነት በግንባርም በመንግሥትም ውስጥ የተዘረጋበት ነበር፡፡

ከዓብይ አህመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ ሕወሓት ተቃዋሚዎቹን የማመስ እጁ ባያርፍም የደከመበት ጊዜ ነበር፣ ግን ሕወሓትን ተገላገልኩ ብለው እነ አረና ትግራይ፣ ኦፌኮ፣ መድረክና ሌሎቹ አገራዊ ነን የሚሉ ፓርቲዎች ሲፋፉ፣ ሲበስሉና ሲዳብሩ አልታዩም፡፡ እነ አረናና ኦፌኮ ከጋራ መድረካቸው ጭምር በኢትዮጵያ ፖለቲካና በሕዝብ ተቀባይነት ውስጥ የተረሱ ነገሮች እየሆኑ ነው የሄዱት፡፡ ሕወሓት በአዲስ የለውጥ አየር ራሱን ሊያንፅ አልቻለም፡፡ ኢሕአዴግ ወደ ወጥ ፓርቲነት አሳድጋለሁ ይል የነበረውን አጀንዳ ሸሽቶ ሲሄድ በብሔርተኛ/ጎጠኛነት ላይ ብቻ አልረጋም፡፡ ከዚያም ወርዶ ጥላቻና በቀል የተቆጣጠረው ጦረኛ ድርጅት ወደ መሆን ነው የዘቀጠው፡፡ እየተበጨቁና እየተሰነጠሩ ከኦነግ የተቀነሱት ቡድኖች በአያሌው ከነበሩበት የብሔርኝነት ግቢ ወጣ ያለ የአስተሳሰብ ዕርምጃ አላሳዩም፡፡ የኦነግን የመጨረሻ ገንታራ ቅሪት የለውጥ አየር አልገራውም፣ ንፁኃንን በጭፍን የሚገድል አራጅ ነው የሆነው፡፡

‹‹ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ!›› የሚል ‹‹ፖለቲካ›› ይዘው በሕጋዊ መድረኩ ውስጥ ደፋ ቀና ሲሉ፣ እየተሰባሰቡ የመበተን ኑሮ ኖረው የተራረፉትም፣ በለውጡ ጊዜ በአዲስ መንፈስ የመጎልመስ ሒደት ውስጥ አልገቡም፡፡ አንዳንዶቹ እዚያው ባሉበት (በቆሙበት) መሄዳቸውን ሲቀጥሉ፣ ቀሪዎቹ ከበረሃ ትግል ለተመለሰው ‹ግንቦት ሰባት› ዳጎስ ያለ ድርጅት የመገንባት እንቅስቃሴ ገበታና እርቦ ሆኖ ከማገልገል ያለፈ ፋይዳ አልነበራቸውም፡፡ ኢዜማ (የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ) በአዲስና በተነቃቃ ስሜት የተደራጀ ፓርቲ ቢሆንም ‹ቅንጅት›፣ ‹ኅብረት› እና ‹መድረክ› ማለፍ ያቃታቸውን መሰናክል አላለፈም፡፡ ፖለቲካው ከብሔርተኛነት ጋር የማይልኮሰኮስና የዜግነት ፖለቲካን የሚያራምድ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እውነታ ደግሞ ፖለቲካውም መላው የኅብረተሰቡ አስተሳሰብም 27 ዓመታት በብሔርተኛ ክፍልፋይነትና ስስት ሲላቆጥ የኖረ ነው፡፡ ፖለቲከኛ የሆነውም ያልሆነውም በብሔርተኛ ክፍልፋይነት የተሰረሰረ/የተመዘመዘ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ጉዳት ያለበት ኅብረተሰብ፣ ከመጣህ ወደ እኔ አቋም ና ከማለት ያለፈ ሥራን ይጠይቃል፡፡ ወዶም ሆነ ሳይታወቀው በብሔርተኛነት የተሟሸውን ሁሉ እንዴት ከዚያ ውስጥ ይዤ ልውጣ የሚል ድርጅታዊ የተግባር ኃላፊነትን በራስ ላይ መጫን ይፈልጋል፡፡ ይህንን ተግባር ለመሸከም አለመቻልም፣ ለኢትዮጵያ እንታገላለን በሚሉና ብሔርተኛነትን በሚፀየፉ የተለመዱ ፓርቲዎች ዓይን የመታየት ፈተና ውስጥ ይከታል፡፡ ለብሔረሰባቸው የሚቆረቆሩ ግን ብሔርተኛ ‹‹ያልሆኑ›› ሰዎችም በርቀትና በጥርጣሬ እንዲያዩት ያጋልጣል፡፡ ብሔርተኞችም በብሔረሰብ መብት ላይ የመጣ ሌላ ፓርቲ አድርገው የመቀስቀስ ቁማር እንዲጫወቱና ለማስገለል እንዲችሉ ይመቻቸዋል፡፡ ኢዜማ እዚህ ችግር ውስጥ ነው፡፡

እነ መድረክና ኅብረት የተሳናቸውን ኢዜማም ያልደፈረውን ትልቁን ፈተና የተጋፈጡት በዓብይ አህመድ መሪነት ወደ ወጥ (ውህድ) ፓርቲነት ‹‹የተሸጋገሩት›› ኢሕአዴግ›› እና ‹‹አጋር›› ሲባሉ የቆዩት ድርጅቶች ናቸው፡፡ ብዙ ዓመት በብሔርተኝነት ሙሽት ሲሠራ ከነበረ አዕምሮ በአንድ ጀምበር ወደ ውህድ አመላከከት መቀየር አይሟላም፡፡ ብልፅግና ፓርቲ በአሁኑ ደረጃ ውህድም ነው ውህድም አይደለም፡፡ ከሰርጎ ገቦች ውጪ ያሉት አባላቱ፣ በአመለካከታቸው በአንድ ጊዜ ኅብራዊነትም ብሔርተኛነትም ያለባቸው ናቸው፡፡ በፓርቲው ውስጥና በግለሰቦች ህሊና ውስጥ በኅብራዊና በብሔርተኛነት መሀል የሚኖረው ፍትጊያ ገና ይቀጥላል፡፡ ፍትጊው የፓርቲውን ተግባራዊ ፖለቲካ ሲያቀልምና ሲያንገላታ ቆይቷል፡፡ ወደፊትም እዚህም እዚያም ግርሻ እንደሚያስቸግረው ብዙ ተንጠባጣቢም እንደሚኖረው ግልጽ ነው፡፡ የፌዴራል አወቃቀሩ እከሌ ብሔር ወይም የእነ እከሌ ብሔር/ብሔረሰቦች ይዞታ ተብሎ የተሸነሸነ እንደመሆኑ ባለቤትና ባለቤት ያልሆኑ ብሔረሰቦች የሚል የአስተሳሰብ መሰናክልን፣ አልፎ ለመሄድ መዋቅሩ ራሱ ያደናቅፋል፡፡ በየ‹ክልል› ያለ የፓርቲ ስብስብን በብሔረሰብ አመጣጥ ክምችት ዥንጉርጉር ለማድረግና የአመከላከከት ውህዳዊ ልውጠትን በዥንጉርጉር የአባላት ጥንቅር ለማገዝ አያመችም፡፡ የሚያመች ሁኔታ ባለበትም ፈጥኖ ዥንጉርጉር አባልነትን ለማሟላት ሁለት ችግሮች ስለታቸውን ሞርደው ይተናነቃሉ፡፡ በአንድ በኩል ሜዳውን ተቀጣጥረው የኖሩት ብሔርተኞች፣ የክልል ‹‹ባለቤት›› የማይባሉ የማኅበረሰብ አባላት ውህድ ነኝ ባለው ብልፅግና ፓርቲ ውስጥ በጉልህ ሲገቡ እንኳን ታይተው ይቅርና ውህድ ፓርቲ ተፈጠረ በመባሉና ውስን የአባላት ዥንጉርጉርነት በመታየቱ ብቻ ‹‹አሀዳዊነት መጣ! ፌዴራላዊነት አከተመለት! የአንድ ፓርቲ አገዛዝ መጣ!…›› የሚል ውንጀላ ለመደርደር አልዘገዩም፡፡ በሌላ በኩል ኢብሔርተኛ ነን ከሚሉትና የብሔርተኛ ጥቃት ቁስለኞች ከነበሩ ባለቅሬታዎች ዘንድ የሚመጣው አላዋቂ ጉንተላና ትክተካ ብሔርተኛ ግርሻን ሊፈጠር የሚችል አደገኛ ችግር ነው፡፡ ዛሬም ድረስ ብሔርተኛነትን እንፀየፋለን የሚሉ ሰዎች የብሔርተኛነትን የመሰባበር ሒደት የሚያደናቅፉ የኢትዮጵያ ችግሮች ሆነው ይገኛሉ፡፡

ወጣም ወረደ ብልፅግና ፓርቲ ኅብረ ብሔራዊ አመለካከትን በማትባት የተወራረሰ የማኅበረሰቦች ትርክትን በማጉላት የፓርቲውን አባላትና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብን (በተለይ አዲሱን) ለማነፅ እየተጣጣረ ይገኛል፡፡ ጥረቱ አገሪቱ እንደገጠማት መጋጋጥ የበረከተበት ጉዞ፣ አበሰኛ ከመሆን ውጪ አይደለም፡፡ ብሔረተኞች ‹‹አሀዳዊ/ወደኋላ የተመለሰ የነፍጠኛ አገልጋይ!›› እንደሚሉት ሁሉ ለኢትዮጵያ እንታገላለን ባይ ቡድኖችም ‹‹መልኩን ቀይሮ የመጣ ብሔርተኛ! ሌላ ኢሕአዴግ/ብሔርተኛ አይደለሁም እያለ የብሔርተኞችን አጀንዳ የሚያስፈጽም…›› ይሉታል፡፡ ከሁለት በኩል ያለው ክስ ዛሬም ድረስ የቀጠለ ነው፡፡ በዚህ አኳኋን ብልፅግናን ከሁለት በኩል ዓይንህ ለፈር የሚሉ ቡድኖች፣ የኢትዮጵያንም የፖለቲካ ሰላም እያወኩ ነው፡፡

ያም እየሆነ ግን፣ ብልፅግና ፓርቲ ውህድ ፓርቲ ሆኖ መውጣት ይሳካለታል/ ኢትዮጵያንም ወደ ጥንካሬ ይወስዳል በሚል ተስፋ የሚደግፉትም (ብሔርተኛ የሆኑና ያልሆኑ) ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ቁጥራቸውና ጥንቅራቸው ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ ድረስ እየጨመረ ነው፡፡ የምሁሩ ንቁ ተሳትፎ በአገርም ውስጥ ከባህር ማዶም እየጨመረ መሆኑ ከኢትዮጵያ ተስፋ አኳያ ልዩ ትርጉም አለው፡፡ ብልፅግና ፓርቲ የቱንም ያህል ቢታማም፣ በውስጡ ገና የቀሩ የልውጠት ችግሮች ቢኖሩትም፣  ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ሁለገብ ግስጋሴ የቆመ አገር ወዳድ ፓርቲ መሆኑ እየጠራ የመጣ እውነት ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ብልፅግና ፓርቲ ለኢትዮጵያ በረከት የሆነበት ሌላው ጥንካሬ ኢትዮጵያን በኅብረ ብሔራዊ ጥንቅር የሚያንፀባርቅና አገርን አያይዞ ማቆየት የሚችል ትልቅ ፓርቲያዊ አውታር መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ፓርቲያዊ አውታርነት ያገኘውም በታሪክ አጋጣሚ፣ ሕወሓት ለበላይ ገዥነት ተግባር ካደራጀው የተቀጢላ ገዥነትን ሲቋደስ ከቆየ ‹‹የግንባር-አጋር›› መዋቅር ነው፡፡ ከዚህ የ‹‹ገዥነት›› አውታር ከፍተኛ መድረክ ውስጥ የለውጥ አስኳል መገኘቱና ከ‹ግንባር-አጋር› መዋቅር ወደ ውህድ ፓርቲነት መቀየር (ከሕወሓት በቀር) የሁሉም ቡድኖች ፍላጎት ሆኖ መከናወኑ፣ ለኢትዮጵያም ተያይዞ መቀጠል ሌላ በረከት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ከሠለጠነባቸው የብጥስጣሽነት ችግር አኳያ የሥልጣን ክፍተት ቀውስ ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ፣ እንዴት እንሆን ነበር ተብሎ ሲታሰብ፣ ብጥስጣሾቹና ንቁሪያ ወዳዶቹ ፖለቲከኞች ተያይዘው አገር ለማዳን ይበቁ ነበር የሚል ግምት ማስቀመጥ እጅግ እጅግ ያስቸግራል፡፡

በታሪክ አጋጣሚ ያገኘውን መነሻ ወደ ወጥ ፓርቲነት ቀይሮ ዛሬ ቁጥሩን እያሳደገ ያለው ብልፅግና ፓርቲ እየመራ ባለው መንግሥት አማካይነት የውስጥ ሰላምን አረጋግጦና የሕዝብ አመኔታን የሚጎዱ ጥፋቶችን ከመሥራት ተቆጥቦ፣ በፍትሐዊ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርና በልማት ግስጋሴ የሕዝብ ከበሬታውን እያበዛ፣ ‹‹የየክልል ዋና ሕዝብ›› በሚሉ ነገር ሳይታሰርና የብሔርተኞችን ዝልዘላ ሳይፈራ አባላቱን ከሁሉም ማኅበረሰቦች እያፈራና ሁሉም ማኅበረሰቦች የሁላችን ፓርቲ እንዲሉት የመሥራት ልምምድ ውስጥ እስካልገባ ድረስ ሥር የያዘ  የአመለካከት ልውጠት ሊያገኝ አይችልም፡፡ በፓርቲው ሁሉም ክልላዊ ቅርንጫፎች ውስጥ የማይጠወልግ/ የማይንሸራተት የአባላት ኅብራዊ አመለካከት የሚዋጣው የአባላቱ አስተሳሰብና ፓርቲያዊ ኑሮ የሁሉም ማኅበረሰቦች ትርታ ከመሆን ጋር ሲገናኝ ብቻ መሆኑ በቅጡ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

ኢትዮጵያዬ ሲሉ ካርታዋ ብቻ የሚታሰባቸውም ሆኑ ብሔርተኞቹ ብጥስጣሾች ያለባቸው የአስተሳሰብ እጥረት፣ ብልፅግና ፓርቲ ዛሬ ያለበት ኅብረ ብሔራዊ ትልቅ ፓርቲነት ላይ ለመድረስ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ስለኢትዮጵያ ሲያስቡ እጆቿን ወደ ፈጣሪ የዘረጋች/ፈጣሪ የሚጠብቃት ረቂቅ አገር የምትታሰባቸው ወይም የካርታዋ ሙሉነት ብቻ ድቅን የሚልባቸው ፖለቲከኞች ስለጥንቅር ሳይጨነቁ አምስት መቶም ሆነው አንድ ሺሕም ሆነው ፓርቲ ቢሆኑ ይህ ጎደለ የሚሉት ነገር የለም፣ ኢትዮጵያን ‹‹ለመወከል›› በቂ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ምድር ከዥንጉርጉር ሰዎቿ ጋር የሚያስተውሉና የኢትዮጵያ አንድነት የተንጠለጠለው ምድሯ ላይ ባሉ ዓይነተ-ብዙ ሰዎቿ ጥቅምና ፍላጎት መንፀባረቅና መስማማት ላይ መሆኑ የገባቸው ፖለቲከኞች፣ ኢትዮጵያን በድፍኗ ወይም በካርታዋ ‹‹ከሚረዷት›› በጣም የተለዩ ናቸው፡፡ አገር ወዳድነታቸው ሕዝቦችን አገሬ ብሎ የሚያይ ይዘት አለው፡፡ ለኢትዮጵያ መቀጠል መታገልም የሕዝቦቿን ጥቅሞች የማስማማት ትግል ሆኖ ይታሰባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያን በፓርቲ መወከልም፣ በጥንቅርም፣ በጥቅምም የሁሉ ሕዝብ ኅብራዊ መገለጫ መሆን ነው፡፡

ብሔርተኛ ቁርጥራጭ ቡድኖችም (ዛሬ ያሉትም ሆኑ ሌሎች ተጨምረው)፣ ቡድንነታቸው እንደተጠበቀ አንድ ላይ ተሰባሰበው ግንባር ቢሆኑ፣ ኢትዮጵያን በሠፈር እየተሻሙ ለመቦጥቦጥ ከመስማማት አያልፉም፡፡ ትልቅ ፓርቲ እንሁን ካሉ አንዱን ወይም ሌላውን ብሔር የእኔ ከሚል ጠባብ አመለካከት ለመውጣት ሳይቆርጡ አይሳካላቸውም፡፡ ብሔርተኞች ከነባራዊ እውነታዊ ታሪክና ከአሁናዊ ጉዞ ጋር ይጋጫሉ፡፡ እያንዳንዱ ብሔረሰብ የብቻ ታሪክ የብቻ ባህል የብቻ ጀግኖች፣ ወዘተ ያሉት አድርጎ የሚያስብ የየተናጠል ዓለም አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች/ማኅበረሰቦች በረዥም ዘመን ባለ ብዙ ፈርጅ የታሪክ መስተጋብር ውስጥ ያለፉና በዚያ ውስጥ ብዙ የተዘናነቁ እንደ መሆናቸው፣ የትኛውም ብሔረሰብ ዓይነተኛ ገጽታዎች እንዳሉት ሁሉ የተወራረሱ ገጽታዎችም አሉት፡፡ ዓይነተኛ መሆንና ዓይነተኛ አለመሆን ተስማምተው ተዳብለው ይገኛሉ፡፡ በሕዝቦች የኑሮ እውነታ ውስጥ የብሔረሰብን ሰው ወገኔ ማለትና ከብሔረሰብ ውጪ የሆነን ሰው ወገኔ ማለት አለ፡፡ በተመሳሳይ ማኅበረሰቦች ውስጥ ቅይጥነት አለ፡፡ በተሰባጠሩ/ውጥንቅጦች ውስጥም መወራረስ የሚገነባው ተመሳሳይነት አለ፡፡ በእያንዳንዷ ደቂቃ ውስጥ ብሔረሰብ ገብ ዝምድናዎች እንደሚፈጠሩ ሁሉ፣ ብሔረሰብ አለፍ ዝምድናዎች በግለሰቦች ኑሮዎች ውስጥ ይፈጠራሉ፡፡ የሥልጣኔ ዕድገትና መስፋት ደግሞ ከሁሉም ጥንቅር በላይ መሰበጣጠርን የሚያበራክት ነው፡፡ ብሔርተኛነት እየተቃረነ ያለውና ለመከተር የሚሞክረው ይህንን ሒደት ነው፡፡ የሕዝቦችን አውነተኛ ሕይወትና ጥቅም አይገልጽም መባሉ ልክ የሚሆነውም በዚህ ረገድ ነው፡፡

ሕዝቦች/ማኅበረሰቦች ኢትዮጵያን አገሬ የሚሉት ደረጃ አውጥተው (የበቀሉበትን ብሔረሰብ/አካባቢ ዋና አገር፣ ኢትዮጵያን ደግሞ በሁለተኛ ደረጃነት ዝቅ አድርገው) አይደለም፡፡ ሰዎች ከብሔረሰባቸው ውጪ ከሆነ ሰው ጋር ሲዛመዱ ሰውዬው ቅር እንዳይለው ብለው/ከአንገት በላይ የሆነ ገደብ ፈጥረው አይደለም፡፡ የቅርርባቸውን/የዝምዳቸውን ጥልቀት የሚወስነው የመጣጣማቸው/የመተሳሰባቸው ሥምረት ነው፡፡ የአንጀት መተሳሰብና መዋደድም ሆነ ከአንገት በላይ ጥርስ እያሳዩ መኗኗር በብሔር ብጤዎች መሀልም፣ ከተለያየ ብሔረሰብ በመጡ ሰዎች መሀልም፣ በሥጋ ዘመዳሞች መሀልም አለ፡፡ ብሔረተኞች መማር ያለባቸው ከዚህ እውነት ነው፡፡

ለኢትዮጵያና ለባንዲራዋ ያላቸው ፍቅር ዕንባ ድረስ የሚሄድ የኢትዮጵያን መፍረስ ቆሞ ከማየት ይልቅ ሞታቸውን የሚመርጡ ኢትዮጵያን ወዳድ ፖለቲከኞችም፣ ኢትዮጵያን አምልኮ ቀረሽ ስለወደዷት ይበጇታል ማለት እንዳልሆነ፣ ኢትዮጵያን እያወደሱ ባንዲራዋን ለብሰውና ጠምጠጥምው ኢትዮጵያን (ሳይታወቃቸው) ሊገዘግዟት እንደሚችሉ ገና በአግባቡ አልተረዱም፡፡ የሚወዷትን አገር ሳያውቁት ከማጥቃት ጥፋት የመራቅ ጉዳይ፣ ከሁሉ ነገር በፊት የዛሬዋ ኢትዮጵያ ብሔርተኞች የፈሉባትና ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ በብሔርተኛነት አስተሳሰብና አወቃቀር የኖረች የብዙ ማኅበረሰቦች አገር መሆኗን ፊት ለፊት ማስተዋል ተቀዳሚ ነው፡፡ ይህንን አስተውሎ ፖለቲካችን እንዳይሳጣ ወይም ብሔር/ብሔረሰቦች የሚባሉ ቅር እንዳይላቸው፣ ‹‹ኢትዮጵያ የብሔር/ብሔረሰቦች አገር መሆኗንና የቡድን መብት የሚባለውን እናውቃለን›› ብሎ ማለት አልሸሹም ዞር አሉ ነው፡፡ ጉዳዩ ለፖለቲካ ተሰሚነት ቢበጀን ትንሽ የአቋም ቀረጥ እንክፈል የማለት ጉዳይ አይደለም፡፡ ቀደም ብለን ስለብሔርተኞች ልውጠት እንደተናገርነው እዚህም የአመለካከት ልውጠት ውስጥ መግባት ግድ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መሬት ላይ ያለ ይዘት ተሰባጥረናል፣ ተጋብተናል፣ ተዋልደናል በማለት ብቻ የሚጠቀለል አይደለም፡፡ ከስብጥሩና ከፈርጀ ብዙው መወራረስ ጋር ወለል ብሎ የሚታየውንም ባለብዙ ባህልነት ባለብዙ ቋንቋነትና ባለብዙ ማኅበረሰብነት ማስተዋል ግድ ነው፡፡ አስተውሎም ይህንን የተወራረሰ ብዝኃነት ማንነቴ አገሬ ብሎ የመውደድ ጉዳይ ነው፡፡ እዚያ ፍቅር ውስጥ ከተገባ ለሁሉም ሕዝብ ባህልና ቋንቋ እኩልነት፣ ለፍትሐዊ ግስጋሴ መቆርቆርና መዋደቅ ይመጣል፡፡ የዚያ ዝቅተኛ መገለጫ ደግሞ በአንድ አገርነት ውስጥ ባለ የዥንጉርጉሮች መስተጋብር ውስጥ የብዙ ባህል ተጋሪ/የብዙ ቋንቋ ተናገሪ መሆንን ወዶ መረካበብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል አገራችንን በዥንጉርጉር ይዘቷ ማየትና መረዳት፣ ዥንጉርጉርነቷንም የራስ ማንነት ማድረግ ሲመጣ የሚገኘው የዜግነት ውጤት በኢትዮጵያ ድፍን ፍቅር ያበደ ዜግነት ወይም ካርድ ያዥ ዜግነት ሳይሆን፣ በዥንጉርጉርነት ኅብር የተገነባ (በብዙ እሴቶች የበለፀገና ብዙ ቋንቋዎች የሚናገር ኢትዮጵያዊነት ዜግነት) ይሆናል፡፡ በአጭሩ በሒደት የኢትዮጵያ ብዝኃነትና ኢትዮጵያዊነት ተወራርሰው ግለሰብነት ላይ በአያሌው ይታያሉ፡፡ የኢትዮጵያ የዥንጉርጉርነት (የብዙኃነት) ይዘት የኢትዮጵያ ዜጎች ገጽታ ይሆናል፡፡

ይህ ጉዳይ ለመኗኗር ስለሚጠቅመን በፕራግማቲዝም ዘይቤ እንፈጽመው የማለት ጉዳይ አይደለም፡፡ የማኅበራዊ ማንነታችንን እውነታዊ አካሄድን የመረዳት ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የረዥም ዘመን መወራረስና መፈላቀቅ ውጤት ነች፡፡ እየተለዋወሱ በብዙ ባህል ልማዶችና ሙዚቃዎች ውስጥ ማደግን፣ ብዙ ቋንቋ ተናጋሪ ሆኖ መቀረፅን የጀመረችው ገና ድሮ ታሪክ ነች፡፡ ይህንን ሁላችንን የሚበጅ የታሪክ ጉዞ ተረድተን ሆን ብለን እናሳልጠው ነው የዛሬያችን ጥያቄ፡፡ በዚህ ተግባር ረገድ የአገራችን ‹‹ልሂቅ›› አመለካከት አንድ ዓይና ሆኖ እየተደናበረ ነውና እናስተካክል ነው ጥያቄው፡፡ ምክንያቱም ተስተካክሎ ከኅብረ ብሔራዊ የማንነታችንን ጉዞ ጋር አለመስማማቱ እየተናጩ እስከ መጥፋት ሊያከስረን ስለሚችል፡፡

አንድ ሰው የምማረው ወይም በተወሰነ ሙያ የምሠለጥነው ለግል ኑሮዬ ብዬ ነው ሊል ይችላል፡፡ ላዩን ሲታይም እንደዚያ ይመስላል፡፡ ግለሰቡን የሚያሠለጥነው፣ በኋላ ‹‹ቀጥሮ›› የሚያሠራውና በግለሰብነቱ እንዲጠቀም የሚያበቃውም (የግል ኩባንያ ከፍቶ ቢሠራ እንኳ) ኅብረተሰቡ ነው፡፡ ግለሰቡ በግሉ መጠቀም የሚችለው ለኅብረተሰቡ አገልግሎ ነው፡፡ ሲማርም ኅብረተሰቡን እያገለገለ ለመጠቀም ነው፡፡ ግለሰብነቱና የግለሰቡ ጥቅም የኅብረተሰብነት መገለጫ ነው፡፡ የኅብረተሰባዊ ሥራም በግለሰቦች ሥምሪት የሚካሄድ ነው፡፡ መጀመሪያ ግለሰብ ነኝ፣ ቡድንነቴ ቀጥሎ የሚመጣ ነው ብሎ ነገር እጅግ የተሳሳተ ሸንካፋነት ነው፡፡ ልክ እንደዚያው ‹‹በተቀዳሚ የብሔር አባል ነኝ፣ ኢትዮጵያዊነት (የአገር አባልነት) አፍሪካዊነት ቀጥለው የሚመጡ ናቸው›› ብሎ ማሰብና ‹‹ባለሁበት የታሪክ እውነታ በአንድ ጊዜ የብሔር አባልነትም ኢትዮጵያዊነትም አፍሪካዊነትም የማንነቴ ገጽታዎች ናቸው›› ብሎ ማሰብ የሰማይና የመሬት ያህል ልዩነት አላቸው፡፡ መኗኗሪያ እውነታን የማወቅና ያለማወቅ ያህል የሚጣሉ ናቸው፡፡

ሰው የብሔርም የአገርም ማንነት ያላዳበረበት ጥንታዊ ዘመን በታሪክ እንደነበር ሁሉ፣ ወደፊት አገሮች ተቀላቅለው አኅጉር አገር የሚሆንበት፣ የብሔረሰቦች ሠፈር የለየ ክምችትም ከምንገምተው በላይ በመወራረስ የቀለመ የሆነበት ጊዜ ይመጣም ይሆናል፡፡ በዛሬ የዓለማችን የኑሮ እውነታ ግን፣ የትም ብንኖር በአንድ ጊዜ የማኅበረሰብ፣ የአገርና የአኅጉር አካል ከመሆን ውጪ አይደለንም፡፡ ከእውነታ የሚጣላ አስተሳሰብ ስንይዝ ማነታችንን ልንበጠብጥ እንችላለን፡፡ የሕወሓት/ኢሕአዴግ አስተሳሰብ ብሔርን ተቀዳሚ ማንነት ኢትዮጵያዊ መሆንን የቢሻኝ ማድረጉ፣ ‹‹የትም እየኖርክና እየሠራህ ለብሔርህ አስብ/ብሔርህን ጥቀም›› የሚል አስተሳሰብን ዘረጋ፡፡ ይህ አስተሳሰብ በተግባራዊ ፖለቲካነት ያስገኘው ውጤት የኢትዮጵያን አገረ መንግሥታዊ ቁመና ከማደርጀትና ከማደስ ፈንታ በህሊናም በተጨባጭ መዋቅርም ትጥቅ የማስፋት ያህል ጉዳት ነበር ያደረሰው፡፡ ብልፅግና ፓርቲን ከሕወሓት/ኢሕአዴግ የማይለይ አድርገው የሚቆጥሩ፣ ምናልባት ቢገለጥላቸው፣ ብልፅግና ዛሬ እየተጣጣረ ያለው ከፋም ለማም ሕወሓት/ኢሕአዴግ ትጥቅ ያስፈታትን ኢትዮጵያ በህሊና (በትርክት) እና በአካላዊ አውታራትም መልሶ በማስታጠቅ ተግባር ላይ ነው፡፡ መልሶ የማስታጠቁ ሥራ የሌለ ነገር የመፍጠር ነገር አይደለም፡፡ ወደ አሮጌ ነገር መመለስም አይደለም፣ ህዳሴ ነው፡፡ በድሪቶ አመለካከት ተሸፍኖ የቆየውን የኢትዮጵያን የተወራረሰ ጀርባ ያለው ኅብረ ብሔራዊ እውነታ አገረ መንግሥቷም በህሊናና በአካላዊ አውታር እንዲያንፀባርቅ አድርጎ የመገንባት ሥራ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብዝኃነትና መላለስ የተፋቀሩበትና ከጎረቤቶች ጋር የሚተጋገዙበት ጉዞ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የህልውናና የግስጋሴ ጉዳይ መሆኑ ቁልጭ ብሎ የወጣበት ግንባታ ነው፡፡ የህዳሴው ይዘት ይህ ነው፡፡

በተጨባጭ ኑሮ ውስጥ ያለው የማኅበረሰቦች መወራረስና ብዙ ቋንቋ ተናጋሪነት ሥርዓታዊ ኩትኮታና ልማት እንዲያገኝ ማድረግ ላይ ከተግባባን፣ ኅብረ ብሔራዊነትና ‹‹የዜግነት ፖለቲካ›› ፀበኞች አለመሆናቸውም ይገባናል፡፡ እዚህ ድረስ ዕይታን አርዝሞ ማስተዋልን የትኞቹም ቡድኖች ከቻሉ፣ ብሔርተኛና ኢብሔርተኛ ነን ብለው ተፈናግጠው የቆዩ ቡድኖች አንድ ላይ ተቀላቅለው የልውጠት ጉዞ ለመጀመር ዕድሉ አላቸው፡፡ ዛሬ ብልፅግና ፓርቲ የያዘው ጉዞ ከዜግነት ፖለቲካ ጋር የሚጣላ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ እውነታ የሚጠይቀውን የመላላስ (ኢንቴግሬሽን) ዕርምጃ በማሟላት በኩል ወደዚያ የሚያመራ መሆኑን መረዳት መከራ አይሆንም፡፡

ይህንን ስናወራ የማይጨበጥ ህልም የማውራት ያህል ብዥ ሊልብን ይችል ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የትኞቹም የኢትዮጵያ ቡድኖች ከዚህ ዓይነት የአመለካካት ለውጥና ርቆ የሚመጣ ውጤትን ከማስተዋል ያጠሩ ናቸው፡፡ ያለአመለካከት ለውጥ የኢትዮጵያን ኅብረተሰብ በጥንቅርና በተቀባይነት የሚወክል ትልቅ ፓርቲ መገንባት እንደማይችሉም ገና አልተረዱም፡፡ አለመረዳትም ብቻ አይደለም፣ ወደ እዚህ ለማምራት የሚሆን ጅምርም የላቸውም፡፡ በብዙዎቹ ቅንጥብጣቢ ቡድኖች ዘንድ ተሰዳድሮ በአንድ ፓርቲነት ረዘም ላለ ጊዜ ለመንቀሳቀስ መቻል እንኳ እየኮሰኮሰ እያሳከከ የሚያወራጭ ነገር ነው፡፡ ትንንሽ የፓርቲ ቡድን ይዞ ጌታ የመሆን ዛር ከሞላ ጎደል ሁሉንም ያነፍሳል ቢባል ውሸት አይሆንም፡፡ ራሳቸውን እያዳመጡ ከመለፍለፍና ሌላው ላይ ጣት ከመቀሰር በቀር ራሳቸውን በጥፋት መውቀስ፣ ራስን ማሳነስና በገዛ ተደማጭነት ላይ መዝመት ሆኖ ያቅራቸዋል፡፡ ራሳቸውን ቢተቹ፣ ቁንጥርጣሪ እንከኖች ነካክቶ ራስን ከመሸንገል ብዙም አይርቁም፡፡ ከሞላ ጎደል ምሁራዊ ጥልቀት ለሚባል ነገር ባይተዋር ናቸው፡፡ ምሁራዊ እንሁን ባሉ ጊዜ ከተግባራዊ ችግሮች ርቀው ፀጉር ስንጠቃ ውስጥ፣ አየር ላይ ያሉ ቲዎሪዎች ማፍተልተልና የቃላት አሳሳችነት ላይ የመራቀቅ ዝባዝንኬ ውስጥ የሚቀልጡ ናቸው፡፡ ይህን ችግር ለመረዳት ‹‹ሻይ ቡና›› የሚባል ዝግጅት ላይ የቀረቡ የፖለቲካ ሰዎች ምን ያህል ከኢትዮጵያ የተግባር ፖለቲካ በራቁ ስብርባሪ ጉዳዮች ላይ ሲወዛገቡ እንደሚቆዩ ዓይቶ መታዘብ ይቻላል፡፡ የተንሳፋፊነታቸው ደረጃ ከዚህም ይብሳል፡፡ ብሔርተኞችና አፄዎች ላይ የተንጠለጠሉ ፖለቲከኞች መድረክ ላይ ሲገናኙ፣ ከዛሬ አጀንዳ ይልቅ መከራከር የሚያምራቸው በእነ ቴዎድሮስና በእነ ምኒልክ ላይ ነው፡፡

የዚህን ሁሉ ችግር ሥረ መሠረት ከትምህርት ቤት አንስቶ የሰንካላነት (የዲፎርሚቲ) ጉዳት ከደረሰበት የኢትዮጵያ ልሂቃን ግንባታ ጋር ማያያዝ ይቻላል፡፡ ችግራችን ሥር ያለው ቢሆንም ግን፣ ከዚያ አምልጦ መሄድ ላለመቻል ማመካኛ አይሆንም፡፡ ‹‹ልሂቃዊ›› አገነባባችን መረጃዎችን ጎስሮ ከመያዝ አሳልፎ መረጃዎችን በመቆርጠም የሠለጠነ አዕምሮን ያላስታጠቀ ቢሆንም እንኳ፣ አዕምሮ ማትባትን ልማር ያለ ሰው አነሰም በዛ መማር ይችላል፡፡ የመማር ነፍስ ያለው ሰው፣ የፖለቲካ ስህተቶችና ጥፋቶች ኢትዮጵያ ላይ ካደረሷቸው ውድቀቶች ብዙ መማር ይችላል፡፡

ኢትዮጵያ ላይ የደረሱ ውድቅቶች በፖለቲከኞቹም ላይ የሚደርሱትን ቅጣቶችና ዝቅጠቶች ሁሉ ያካትታሉ፡፡ ልሂቃን ተገዳድለዋል፣ በነፃ ዕርምጃ ተረፍርፈዋል፣ በእስር ማቅቀዋል፡፡ ዛሬም መማር፣ መታረምና መለወጥ ተስኗቸውና አይዘቅጡ ዘቅጠው ንፁኃንን በጭፍን እያረዱ ‹‹ነፃ አውጪ›› ነን እስከ ማለት ምድርና ሰማይ የተምታታባቸው ሰዎችን እናገኛለን፡፡ ፋኖ ነኝ ያሉ የትጥቅ ትግል ታጋዮችም ፖለቲካንና ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ለማዛመድ እስከ መሞከር ሲቀወሱ ታይተዋል፡፡ ‹‹አሳምነው ፅጌ ብርጌድ›› ምንትስ የሚል ስያሜ ይዘው፣ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ጥብጣብ አሸብርቀው በአማራ አካባቢ ትርምስ ሲያባዙ ታይተዋል፡፡ ‹‹ምኒልክ ይሙት አዲስ አበባ በቅርቡ እንመጣለን!›› የሚል መልዕክትም ለጥፈውልናል፡፡ እነዚህን ከመሰሉ ‹አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም› የሚል መቃተት ውስጥ ከወደቁ ልምዶች በላይ ለመማርያ የሚሆን ምን ፍትፍት ‹‹ፖለከኞቹ›› ይምጣላቸው!! የውድቀት ልምዳቸው እኮ አፍ አውጥቶ ‹‹ዘመኑ ጠፍቶባችኋል! ከድሮ ዘመን ወጥታችሁ 21ኛ ክፍለ ዘመን ውስጥ ግቡ! ዓይናችሁን በልጥጣችሁ የዛሬዋን ኢትዮጵያ አጥኑ! የፍላጎቷንና የዕርምጃዋን ሀ፣ ሁ… ቁጠሩ!!›› እያላቸው ነው፡፡ የዛሬዋን ኢትዮጵያ በቀጣናዊ ዓውዷ ውስጥ አትኩሮ ያስተዋለና ዕይታውን ከዛሬ እውነታ ጋር ያገናዘበ ሰው፣ ልሂቅነቱ ሰንካላ ቢሆንም እንኳ ለመማር እስከ ቆረጠ ብዙ ይማራል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሳይገባቸው ፖለቲከኛ ነኝ ያሉ ሰዎች አንድ፣ አሥር ሆነው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ልምዶች በክፍት አዕምሮ ቢመርምሩ፣ በኢትዮጵያ ምሁራን ከተሠሩ ጥናቶች የተዋጡ የተባሉትን መርጠውና አሰባስበው ከዓለም ልምድ ጋር እያገናዘቡ ራሳቸውን ለማስተማር ቢተጉ፣ ራሳቸውን ፍሬ ወደሚሰጥ ልሂቃዊ አቅም ማሸጋገር ይችላሉ፡፡ ዛሬ ያሉት ቅንስናሽ ቡድኖችም ትንሽ ነገር ለቃቅመው እሷን እያመነዠጉ ከመቆነን ወጥተው ወደ እዚህ ዓይነት ለውጥ ውስጥ ቢገቡ ለኢትዮጵያ ስንት በጠቀሙ ነበር፡፡

‹‹ለኢትዮጵያ ስንት በጠቀሙ›› ለወግ ያህል የተባለ ቃል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ‹‹ፖለቲከኞች›› አሁን ካሉበት ሁኔታ አኳያ፣ ኢትዮጵያን እየመራ ያለው ብልፅግና ፓርቲ ቢጥምም ባይጥምም፣ በምርጫ ውድድር ላይ ቢሸፍጥም፣ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ተመርጦ በሥልጣን ላይ የመቆየት ዕድል ከእሱ ጋር መቀጠሉ አጠራጣሪ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያን መላ ሕዝቦች አስተባብሮ በመምራትና የኢትጵያን ዥንጉርጉርነት በአግባቡ በማንፀባረቅ ረገድ ከየትኛውም ፓርቲ የተሻለ አቅም ያለው እሱ ብቻ መሆኑ፣ የማይኮረፍና የማይሸሽ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡ በአሁኑ ደረጃ ብልፅግና ፓርቲን ለመግፋት የምንደፍረው የኢትዮጵያን (የሁላችንን አገራዊ ዕጣ) መድረሻው የማይታወቅ ሁኔታ ውስጥ ለመገፍተር ከጨከንን ብቻ ነው፡፡ የፖለቲከኞቻችን ድቀት ዕጣችንን ከአንድ ፓርቲ ጋር እንዲጣበቅ አድርጎታል፡፡

ጣብቂያው ከመፈረካከስ በማምለጥ ረገድ ብቻ የሚመዘን አይደለም፡፡ በአማራና በኦሮሚያ ውስጥ ካለው የሰላም ችግር ጋር እየተናነቀም የብልፅግና መንግሥት ከፍተኛ ተስፋ ያለው ልማት በብዙ አቅጣጫ በመምራት፣ ደጋፊዎቹንም ተቀናቃኞቹንም ምቀኞቹንም ለማስደመም የቻለ ነው፡፡ በሁለቱ አካባቢዎች ውስጥ ያለውን የሰላም ጉድለት ማቃለል ከቻለ ደግሞ የልማቱ ስፋትና ጥልቀት የበለጠ ማዳጉ፣ ከዚህም ጋር የሕዝብ ተቀባይነቱ የመንተርከኩ ነገር አሁን ካለው አያያዙ ሲገመት አጠራጣሪ አይሆንም፡፡ ይህ ደግሞ ደጉንም ክፉውንም እንድናስብ የሚያደርግ ነው፡፡ ሰላምን ተቆናጦ በኢኮኖሚ ግስጋሴ አማካይነት የሕዝብን ሰፊ ድጋፍ ይዞ የሚቆይ ብቸኛ ፓርቲ በምርጫ ጊዜ እበለጣሁ/ከሥልጣን ልወርድ እችላለሁ የሚል ሥጋት አይኖርበትም፡፡ ሥጋት የሌለበት ፓርቲ፣ ‹ሁሉ በጄ በደጄ› ብሎ ለመዘባነንና ለመንቀዝ አደጋ የበለጠ ይጋለጣል፡፡ በየወቅቱ እየተመረጠ በሥልጣን መቆየትን ለረዥም ጊዜ የለመደ ፓርቲ፣ አንድ ወቅት ላይ የመውረድ ዕድል አግጦ ቢመጣበት ሊያንዘረዝረውና ብዙ ጥፋት ሊሠራ ይችላል፡፡ ወይም የመውረድ አፋፍ ላይ ከመድረሱ በፊት የሥልጣን ጥፍጥና አይሎበት ሌላ አቅም ያለው ተፎካካሪ እንዳይጎለብት በማጫጫት ሴራ ሊጠመድ ይችላል፡፡ ይህም ዴሞክራሲን የመስለብ ተግባር ነው፡፡ እናም በአሁኑ የኢትዮጵያ እውነታ የመመረጥ ዕድል ከብልፅግና ፓርቲ ጋር መሆኑ ግልጽ ብሎ የሚታይ ቢሆንም፣ ይህ ፓርቲ መውረድም እንዳለ መላመዱ ለኢትዮጵያም ለዴሞክራሲም ጥቅም ነው፡፡ ይህ ጥቅም፣ ‹‹አገሬ በሰላም ትቆይ ይሆን? አብሮነታችን ይናጋ ይሆን?›› በሚል ሥጋት ሳንበጠቅ በመወዳደሪያ ዕቅዳቸው ልናማርጣቸው የምንችላቸው ጥቂት ትልልቅ ፓርቲዎች መገንባት ላይ እንድንሠራ ግድ ይለናል፡፡

እዚህ ላይ መሥራት የኢትዮጵያ ጥቅም ነው ስንል መላ ሕዝቦቿን እያሰብን ብቻ ሳይሆን ፓርቲዎችንም እያሰብን ነው፡፡ አንድ ፓርቲ በሥልጣን መቆየት ጣፈጠኝ ሲል የመንቀዝ አንድ ምልክት ነው፡፡ መንቀዝ የነቃዡን ነፃነት የሚነጥቅ ቅሌት ነው፡፡ ቅሌት የምርጫ ዘመን ሕግን በመቀየር ወይም ምርጫን በማጉደፍ የሥልጣን ዕድሜን ለማራዘም መትረክረክ ውስጥ ይከታል፡፡ ይህ ጥፋት በራሱ የበለጠ ነፃነትን ያሳንሳል፡፡ ያለ አግባብ በሥልጣን ለመቆየት የሚደረግ ትግል በበኩሉ ከሕዝብ ቅዋሜ ጋር ያጋጫል፡፡ ይህ ደግሞ ተገቢ ቅዋሜን በኃይል ለመምታት ወንጀል ያጋልጣል፡፡ በድቆሳ ወንጀል መጉደፍ ደግሞ ከበፊቱ ይበልጥ የጥፋት እስረኛ መሆን ነው፡፡ የጥፋት እስረኝነት እየተደራረበና እየከበደ መሄድ የሚያሰቃየው ደግሞ ሕዝብን ብቻ ሳይሆን እስረኛውን ፓርቲ ጭምር ነው፡፡ ሥቃዩና ቅሌቱ የበፊት ምሥጋናና ሞገስን አጥቶና ተዋርዶ ወህኒ እስከ መወረድ ሊያደርስ ይችላል፡፡ በዚህ ዓይነት ውርደት ሳይበልዙ የሕዝብ ድምፅ ሲጎድል ያለ ፍርኃት በመውረድና የሕዝብን አመኔታ እንደገና አግኝቶ ወደ ሥልጣን ለመመለስ ተፎካካሪ በመሆን ነፃነት ውስጥ መኖር፣ ከፊተኛው ጋር የቱ ይሻላል በሚል ሚዛን የማይለካካ ነው፡፡

ነፃነት ወዳድ ነፍስ አለኝ የሚል ፓርቲ እየገዛ ቢሆንም ባይሆንም፣ ለዚህ ዴሞክራሲያዊ አኗኗር የሚያስፈልጉ መደላድሎችን ለማሟላት መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ የፖለቲካ ሰላም የማይናጋበት የዴሞክራሲ ልምምድ መጎልበት የሚችለው እውነተኛ ተፎካካሪ ባለበት ሁኔታ ነው፡፡ የትኛውም ፓርቲ ከሕግ በታች መሆኑንና በሕዝብ ድምፅና ፍላጎት ውስጥ የሚያድር መሆኑን የሚያረጋግጠውና ዴሞክራሲን የሚንከባከበው (የዴሞክራሲ ነጣቂም አስነጣቂም የማይሆነው) በእውነተኛ ፉክክር ውስጥ የሚመላለስ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ዴሞክራሲን ጥቅሜና ህልውናዬ የሚል ፖለቲከኛና ፓርቲ ሁሉ እውነተኛ የአቅም ፉክክር ያለበት ዴሞክራሲ እንዲጎለብት መልፋት ይጠበቅበታል፡፡

‹‹መልፋት›› ያዘለው ትርጓሜ በምሁራዊ አቅም፣ በአመራር ጥበብ አቅምና በድርጅት አቅም መጎልበትን ሁሉ ያዘለ ነው፡፡ ለዚህ ዓይነት ጉልምስና የሚሆን ጅምር ስንቅ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የመኖሩ ነገር በሥጋት የተሞላ፣ እንዲያውም ገና ፍቺ ያልተገኘለት እንቆቅልሽ መሳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያን በአብሮነት መቀጠል ጥቅሜ/ ደኅንነቴ ብሎ በማሰብ ረገድ ሕዝብ ከልሂቃኑ በልጧል፡፡ በዛሬዎቹ ልሂቃን ውስጥ ‹‹የመጣው ይምጣ!›› የሚል ቁማርን በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ህልውና ላይ መጫወት ከጊዜ ጊዜ የሚታይ ችግር ነው፡፡ ይህ የዋዛ ጉድለት አይደለም፡፡ በብልፅግና መንግሥት ውስጥ መንግሥታዊ ኃላፊነት ተቀብለው የሚሠሩ የሌላ ፓርቲ ሰዎችን፣ የብልፅግና ፓርቲ አሽከሮች/‹‹የፓርቲያቸውን ዓላማ የካዱ›› አድርገው የሚመለከቱ፣ ካለው መንግሥት ጋር አብሮ መሥራትን የሚፈልጉ ብዙ ጉዳዮች አገሪቱ እንዳሏት የማይረዱ፣  እንዲያውም ያለውን መንግሥት ጠላት አድርገው የሚያዩ ፖለቲከኞች ጥቂት አይደሉም፡፡ በሥልጣን ላይ ባለው ፓርቲ ላይ የድጋፍ ጉድለትም ሆነ ጥፋት ባዩ ጊዜ፣ በጣም ጯሂ ተቃዋሚ በመሆንና የብሶት አጋጣሚዎችን ለሕዝብ ተቆርቋሪ መስሎ መታያቸው በማድረግ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ልብ የሚገዙ የሚመስላቸው፣ ግን የካሮት ዓይነት ጠባብ አበቃቀል ያላቸው የፖለቲካ ቡድኖች አሉ፡፡ በዛሬዋ ኢትዮጵያ መንግሥት ለመሆን ከሚያበቃ ብስለትና አቃጅነት ጋር እንደ ዋርካ በሁሉም አቅጣጫ በተዘረጋጋ ጠንካራ ሥር በሕዝቦች ውስጥ መንተርከክ መተኪያ የሌለው መሆኑ በአግባቡ ገና አልተጤነም፡፡

አልተጤነም ሲባል ሊያጤኑ የማይችሉትንና ሊያድጉ የማይችሉትንም ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ ሻል ያሉና መማር የቻሉ ፖለቲከኞችን/ቡድኖችን ወደ ጎን አድርገን እንቁጠር፡፡ አሳቢዎች የሌሏቸውና አሰር ባሰር የቀሩ ቡድኖች፣ እንደ ውኃ ሊሊ ተንሳፎ ከመዘዋወር የማያልፉ ቡድኖች፣ በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ ብሔራቸውን ማስቀደም ርዕዮተ ዓለማቸው የሆነ ቡድኖች፣ በአፄዎች አፍቃሪነት ርዕዮተ ዓለማቸውና መታወቂያቸው የሆነ የሠፈር ብሔርተኞች፣ ኢትዮጵያን ርዕዮተ ዓለማችን የሚሉ ግን ኢትዮጵያን ለቁማር አስይዘው የዓብይን መንግሥት ለመጣል የሚታገሉ፣ የትኛውንም የጥይት ተኩስ የማይቃወሙና በውጤቱ ከሚገኘው እናተርፋለን ብለው የሚጠባበቁ፣ ዘቅጠው ከፖለቲከኛነት ሠፈር ወደ ወንጀለኞች ያለፉ ቡድኖች፣ የኢትዮጵያ ፈተና ውስጥ መሆን ከሕግ ተጠያቂነት ቢያተርፋቸውም በሕዝብ ህሊና ውስጥ ወንጀለኞነታቸው የማይታወቅ/በምላስ ጥበብ ተደብቆ የሚኖር እየመሰላቸው ኒሻን ይገባናል የሚሉ የፖለቲካ ወመኔዎች፣ ከትናንት ወዲያም ትናንትናም ዛሬም የሚሉት የማይቀየር ክትሮች፣ ትናንትናም ዛሬም ሠፈርተኝነትንና ጥልቀት የለሽነትን ጥሰው ለመራመድ የሰነፉ አለዚያም ማሰብ ያቆሙ ቡድኖች፣ ማሽቃበጥን ወይም ተቃውሞን ነግዶ በማደሪያነት/በመወጣጫነት የሚጠቀሙበት እበላ-ባዮች፣ በፓርቲ ውስጥ ተሰድሮ መንቀሳቀስ የሚያሳክካቸው ቅብጥብጦችና ነገር ሠሪዎች፣ በሥልጣን ላይ ካለው ፓርቲ አካባቢም ሆነ ከተቃዋሚዎቹ ሠፈር ከጊዜ ጊዜ የወሬ ርዕስ ሆነው ብቅ የሚሉ ጀብደኞች (አደብ በማያውቅ ምላሳቸው ራሳቸውንም ቤተሰባቸውን ለችግር የሚዳርጉ፣  አገር/ሕዝብ ለመምራት ይቅርና ራሳቸውን ከእስር የመጠበቅ አስተዋይነት የሚቸግራቸው፣ ከእስር ገና ሲፈቱ ሌላ የሚያሳስር ጀብዱ አምጡ አምጡ የሚል ስሜት የሚጎተጉታቸው/በዚህ ዓይነት አባዜ እስር ቤት መመላለስ ‹‹ጀግንነት›› ሆኖ የሚያኩራራቸው)፡፡ …እነዚህን የመሳሰሉትን ለፖለቲካ ዕድገት የማይሆኑትን ሁሉ ቀንሰን፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሜዳ ላይ ምን ቀረን ስንል፣ ሜዳው ላይ እንደ ዓምድ ጎልቶ የሚታየው ትልቅ የጥያቄ ምልክት ሳይሆን አይቀርም፡፡

ከላይ በዘረዘርናቸው ረድፎች ውስጥ ለመሰደር የማይመቹ አስገራሚ ግለሰቦችን የኢትዮጵያ ፖለቲካ አሳይቶናል፤ እያሳየንም ነው፡፡ በሕግ ዶክትሮ፣ አሜሪካ ይሠራ የነበረ፣  በለውጡ አፍላ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶም ስለዴሞክራሲ ግንባታ ብዙ በመናገር ልብ የተባለ (የዓብይ መንግሥትም ይበጅ መስሎት በአሜሪካ የኢትዮጵያ ሚሲዮን ውስጥ ቦታ ሰጥቶት እንደነበር የሚወራለት) ሰው፣ በስተኋላ እንዳይሆን ሆኖ ሃጫሉ በተገደለበት የደቦ ነውጠኛ ቅጣትና የውድመት ጊዜ በ‹‹ኦኤምኤን›› ቴሌቪዥን ‹‹ነፍጠኛን ናደው! በለው!…›› የሚል ቀስቃሽ ሆኖ ስታገኙት ምን ማብራሪያ ይኖራችኋል!? እንዲህ ያሉትን ሰዎች የቱ ጋ ታስገቧቸዋላችሁ?

ልደቱ አያሌው ከመአሕድ ጀምሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያለፈ ወጣት ነው፡፡ በኢዴፓና በቅንጅት ፖለቲካ ውስጥ ኮኮብ ከነበሩት አንዱ ነበር፡፡ በቅንጅት ዝና ጊዜም ‹‹የኢትዮጵያ ማንዴላ›› ተብሎ ሲቆላመጥም ሰምተናል፡፡ በቅንጅት ውህደት መክሸፍና ድቆሳ ጊዜ ደግሞ ‹‹የሕወሓት/ኢሕአዴግ ሰርጎ ገብ›› ተብሎ አክ እንትፍ ሲባል ዓይተናል፡፡ ቅንጅት ተፈረካክሶ ኢዴፓ ለብቻው በተሰባሰበበት ጊዜ ለሥልጣን እንኳ ‹‹ዕንቢ›› ብሎ የነበረውና በዕንባ ንፅህናውን ‹‹የገለጸው››  ሰው ‹‹ከጠላታዊ ፖለቲካ የወጣ›› አስቂኝ ‹‹ሦስተኛ›› አቋም ሲይዝም ዓይተናል፡፡ ወህኒ የወረዱት የቅንጅት መሪዎች ለቀረበላቸው የይቅርታ ደብዳቤ ማጎንበስ የመፈታት ብቸኛ አማራጭ ሆኖባቸው፣ ፈርመው በወጡ ጊዜም እዚያ ‹‹የይቅርታ›› ደብዳቤ ላይ የተቀመጠውን ‹‹የጥፋተኛነት›› ቃል የእውነተኛ ወንጀለኝነት የእምነት ቃል አድርጎ በሚዲያ ሲሳለቅባቸው ታዝበናል፡፡ ይህ ሁሉ አልፎ ከሁለተኛ ደረጃ ብዙም ካልራቀ የትምህርት ደረጃ ጋር ብልጥ አዕምሮና ረዥም ምላስ የሰጠው ሰው አውሮፓ ለትምህርት ተሻግሮም ተመለሰ፡፡ ከዚያ በኋላ በነበረው ፖለቲካም የበሰለ መሰለ፡፡ ሕወሓት ከፌዴራላዊ የሥልጣን መንበር ዘወር ሲልም ከሰላይነትና ከሸፍጠኝነት ጋር የተያያዘ ታሪኩ ተላቆት የተሻለ የፖለቲካኛነት ታሪክ ይኖረዋል ተብሎ ተጠበቀ፡፡ መጀመሪያ ላይ የለውጡ ደጋፊ ሆኖ የተወሰነ ጊዜ ከቆየ በኋላ ተገልብጦ የለውጡ ተቃዋሚ ወደ መሆን ዞረ፡፡ የሚናገረው፣ የሚጽፈውና የሚሠራው ሁሉ በውስጠ ወይራ ተንኮልና የመከፋፈል ሻጥር የሚጠርጠርም ሆነ፡፡ ‹‹ልቤን! ልሞት ነው…›› ብሎ ከአገር ቢወጣም አገር የሚያቆስል እንጂ የሚጠግን ሥራ ሊወጣው አልቻለም፡፡ ይህንን ሰውና ብጤዎቹን የት ጋ እንፈርጃቸዋለን? ፍፁም እርጉምና ቅዱስ ሰው በልብ ወለድ እንጂ በገሃዱ ሕይወት ውስጥ የለም የሚል ማጠቃለያ እውነት እንደሆነ አልጠራጠርም፡፡ ልደቱን ፍፁም እርጉም ማለት ይቅርና እርጉም ለማለትም ይከብደኛል፡፡ ምላጭ የዋጠ ሞላጫ መሆኑን ግን አልጠራጠርም፡፡ በእሱና በእሱ ብጤዎች ኢትዮጵያ እየተከተከተች ነው፡፡ በየቀኑ የውዥንብር ባሩድና የጥይት ባሩድ ይለቀቅባታል፡፡

ከሞላጫነት ወደ ራቀ ሌላ ግለሰብ ልምጣ፡፡ ‹‹አማራ›› ኅብረተሰብ (እንደ አፋር ሁሉ) ከቅርብ ጊዜ በፊት ከጭፍን ጥቃቶች አንስቶ የታቀደ የመሠረተ ልማትና የተቋማት ዘረፋና ውድመት፣ እንዲሁም የግል ጥሪት ከጓዳ እስከ ኪስና መቀነት ድረስ የተሞለጨ እንደመሆኑ፣  ሺሕ ጥያቄዎችና ብሶቶች ቢኖሩም ሠርቶ ለመጉረስ ዕፎይታ እንዲያግኝ ከማገዝ በቀር፣ ሌላ የጠመንጃ ግርግር ፈጽሞ ሊታሰብለት የማይገባው ሕዝብ ነበር፡፡ ጎረምሶቹ ፋኖዎች ይህንን ባያጤኑት አይገርም ይሆናል፡፡ የሚያሳዝነው እንደ አንዳርጋቸው ጽጌ ያሉ የሽማግሌ ‹‹ፋኖዎች›› ይችን ያህል ሕዝባዊ አዛኝነት ቸግሯቸው፣ ጎረምሶች ለጀመሩት ትግል የአመራር ‹‹ዕገዛ ሊሰጡ›› ሰበር ሰካ ማለታቸው ነው፡፡ ስንት ልምድ ዓይቶ፣ ስንት ነገር ውስጥ ገብቶ ወጥቶ ቅንድቡ ድረስ ለሸበተ ሽማግሌ ሊከብደው የሚገባው ነገር፣ መስከንና መብሰል ሳይሆን ዛሬም ነገም አፍላ መሆን ነበረበት፡፡ አንዳንዶቻችን ጋ ግን፣ ምራቅ ሳይውጡ እንደ ማርጀት ያለ ከባድ ነገር ይቀለናል፡፡ አንዳርጋቸው ተፈሪ መኮንን ተማሪ በነበርንበት ጊዜ እንደ እኔው ፖለቲካ በዞረበት ያልዞረ ወጣት ነበር፡፡ ፖለቲካን የቀመሰው በኢሕአፓ ውስጥ ነው፡፡ በኢሕአፓ ውስጥ ስለነበረው የትግል ልምድ ከጊዜ በኋላ በጻፈው መጽሐፍ እንደ ተረከልን፣ ከእስር ለማምለጥ የፖለቲካ ተቃራኒዎቹ ዘንድ ተሸሽጎ በነበረ ጊዜም አዕምሮው ባንዳን በመቅጣት ፍላጎት ሲብከነከን እንደነበር አውስቶናል፡፡ ይህንን የነገረን የዚያን ጊዜ ምን ያህል ጭፍንነት እንደነበር ለመግለጽ ብሎ ነበር፡፡ ይህንን ገመናውን ሊደብቀን ያልሞከረውን ሰው ስለእናቱ የያኔ ድንቅነት ያወሳን ታሪክ ላይ አንጠራጠረውም፡፡ የእናቱ አርቆ አስተዋይነትና ሆደ ሰፊነት ለእናቶች ብርቅ አይደለም፡፡ የዚህ ባህርይ ሀብታም የነበሩት እናቱ በየትኛውም ረድፍ ያኔ ይመሩን ከነበሩ ፖለቲከኞች በአስተዋይነት ይልቁ ነበር፡፡ መጠማመድና መገዳደልን በልጠው ለሁሉም ስሱ ስለነበሩት እናቱ ሲተርክልንም በጊዜያት ውስጥ ከእናቱ ባህርይ ብዙ መማሩን ለመግለጽ መስሎን ነበር፡፡ መጽሐፉን የጻፈው ከብዙ ልምድ በኋላ በቅርቡ እንደ መሆኑም እንደዚያ ብንገምት ጥፋት አይሆንብንም፡፡ ከኢሕአፓ በኋላ ፈረንጅ አገር ገብቶ ቆይቶ፣ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ሥልጣን በኢትዮጵያ ከያዘ በኋላ ኢሕአዴግ ውስጥ ገብቶ ኢሕአዴግን ዓይቶ በቅዋሜ የወጣ ሰው ነው፡፡ ሲወጣም በሕወሓት ብሔርተኛ አስተሳሰብ በልዞ ነበርና ቅይጥ የብሔረሰብ አመጣጥ ላላቸው ኢትዮጵያውያን የአማራ ብሔርተኝነትን መፍትሔ ያለና የእነ ቴዎድሮስን ብሔርተኛ አለመሆን የተቸ መጽሐፍ ጻፈ፡፡ ከዚያ መልስ ደግሞ ብሔርኝነትን ጥሎ የቅንጅት ፖለቲካ ውስጥ ገባ፡፡ ቅንጅት ከተሰባበረ በኋላ ደግሞ በኤርትራ ይደገፍ የነበረውን ‹‹ግንቦት ሰባት›› የተባለ የትጥቅ እንቅስቃሴ ካዳራጁትና መሪ ከነበሩት አንዱ ሆነ፡፡ በዚያ ትግል ውስጥ እያለ በውጭ ለሥራ ሲንቀሳቀስ ተይዞ የኢሕአዴግ/ሕወሓት እስረኛ ሆኖ ቆየ፡፡ አንዳርጋቸው ከእስር የወጣውም ይመራው የነበረው የትጥቅ ትግል ነፃ መሬት እያሰፋ መጥቶ አልነበረም፡፡ ከእስር ለመፈታት የበቃው፣ በኢሕአዴግ ውስጥና ከኢሕአዴግ ውጪ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ሰላማዊ ትግል በዋናነት ባስገኘው የለውጥ ጅምር ነበር፡፡ የ‹አርበኞች ግንቦት ሰባት› ወደ አገር መግባትም በትግል ከተቆጣጠረው ነፃ መሬት ወደ አዲስ አበባ ከመምጣት ይልቅ ከስደት የመግባት ያህል ነበር ቢባል ውሸት አይሆንም፡፡ ይህ የቅርብ ልምድ በራሱ፣ ሕዝቦችን በጦርነት ነክ መከራ ለመማቀቅ ሳይዳርግ እንደ ሁኔታዎች አበሳሰል በብልኃት የሚራመድ ትግል፣ ሰላማዊ ትግል መሆኑን ለማንም የሚያስተምር ልምድ ነበር፡፡ ለአንዳርጋቸው ግን ይህ ሁሉ ልምድና የእናቱ ድንቅና ብልህ አስተዋይነት ትምህርት አልሆነውም፡፡ የጎለመሰ ብስለትን አላጎናፀፈውም፡፡ ሥራው ሁሉ ከትናንት እስከ ዛሬ የረባ ማሸቀብ የሌለበት ከአንዱ ወደ አንዱ በመፈናጠርና እየወደቁ በመነሳት የተሞላ ነው፡፡ ዛሬም ይኼውና የግፍ ጦርነት በመነጠረው አማራ ሕዝብ ላይ ሌላ መከራ ለሚጨምርና ኢትዮጵያ ላይ ለሚቆምር ትጥቅ ትግል አመራር ሊሰጥ ወደ ውጭ አመራ፡፡

ዕድሜያቸውን በመፈናጠር የሚጨርሱ እንዳሉ ሁሉ ከ1960ዎች ጊዜ አቋማቸው ንቅንቅ ያላሉ የአዛውንት ምንቸቶች ዛሬም አሉ፣ በአገር ውስጥና በፈረንጅ አገር፡፡ በፈረንጅ አገር ያሉቱ ደግሞ በደረቀ የፖለቲካ አቋማቸውና በገንዘባቸው የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚያቦኩት በአያሌው የውጭ ዜግነታቸውን መታወቂያ በደረት ኪሳቸው ይዘውና ጡረታቸውን አስከብረው ነው፡፡ በአዛውንትነት ወግ በኢትዮጵያ ጠመንጃ ተኳሽነት ቆሞ ሰላምና ልማት እንዲፀና ቡድኖች ወደ ንግግር ወደ መቀራረብ እንዲመጡ መሥራት/መማለድ ሲገባ፣ በረዥም ጊዜ የተካበተ ልምድን ረጋግጦና የአንድ ቡድን አጃቢ ሆኖ በስተርጅና ዘራፍ ማለት ከዕድሜም፣ ከልምድም፣ ለአገርና ለሕዝቦች ከማሰብም አንሶ መገኘት ነው፡፡

በ2016 ዓ.ም. መጋቢት 28 ቀን በአርትስ ቲቪ ‹‹በነገራችን ላይ›› የተሰኘ ዝግጅት ያነጋገረው ጃዋር መሐመድ ላይ ያየነው ትሁትነት ከዚህ ቀደም ከምናውቀው ጃዋር የተለየ ነበር፡፡ ትሁትነቱ ግን የፖለቲካ ግምገማ ስህተቶቹን ከማስተዋል ሊጋርደን አይገባም፡፡ እንደሰማነው ሕወሓት አውሬው እንዳይወጣ/ብዙ አባላቱ ወደ ለውጡ እንዲሳቡ የሚጠቅም ሚና ከመንግሥት ጎድሎ እንደነበር ጃዋር ሲጠቁም፣ በአጠቃላይ በፖለቲከኞቹ ዘንድ፣ በተለይም በራሱና በ‹ኦኤም› ሚዲያው በኩል የነበረውን ንቁ የጥፋት ድርሻ አለመጥቀሱ፣ የሕወሓቶችን የጦርነት ድግስ ከሥጋት የመጣ አድርጎ ማቅለሉ፣ የ‹‹ሁሉ በጄ›› ትዕቢት (ከውጊያ ልምድና ጥበብ አንስቶ በአገሪቱ የታጠቀ አውታር ውስጥ የነበራቸውን ሥውር እጅ ሁሉ ያስተዋለ ንቀት) ዋና ችግራቸው እንደበርም አለማንሳቱ ያስተዛዝባል፡፡ የሰሜን ዕዝን መትቶ ሕወሓት ጦርነቱን ከከፈተ በኋላ፣ ያንን ለመመከት የተደረገውን አገር የማዳን ግጥሚያ ከሕወሓት ነውር ጋር በአንድ ዓይን ከአየር ላይ ሆኖ መፍረዱም አጠያያቂ ነው፡፡ ‹‹ተረኝነት›› የሚባልን ነገር ከመንግሥታዊ ቢሮክራሲ ጋር በተያየዘ የዝርፊያ ተመሳጣሪነት በመተቸት ከመቆጠብ ፋንታ፣ የኢትዮጵያ የትኛውም ገበሬ በተረኝነት ገብቶ የሚያውቅ ይመስል የኦሮሞ ገበሬን ጉዳት ለትንታኔ መጠቀሙም አሳሳች ነው፡፡ ከእነዚህ ውጪ በክፍል ሁለት ቃለ ምልልሱ የተናገራቸው ነጥቦች ለሕዝቦች የሚቆረቆር አዕምሮ ያለው ሰው የሚስማማባቸው ናቸው፡፡ ዝርዝር ነገር ባይጠቃቅስልንም የጥፋት ፀፀቱም ተመስጌን የሚያሰኝ ነው፤ ድንጋይ ልቦች ሲቆነኑ እያየን ባለንበት ሁኔታም የምንሰጠው ዋጋ ቀላል አይደለም፡፡

እንዲህ ያለው ነገር ብዙም ሊያስገርመን አይገባም… የለውጥ ጊዜ በየትም አገር ፈተናዎች አያጣውም… ፈተናው በተወሳሰበበት ደረጃ ላይም ከለውጡ ጉዞ የሚንጠባጠብ መብዛታቸው፣ ቀዳሚዎች ኋለኞች ኋላኞች ፊተኞች መሆናቸው እንግዳ አይደለም ሊባል ይችላል፡፡ እንዲህ ያለ ንድፈ ሐሳብ ቀመስ ነገር ተንተርሶ ፈልሰስ ማለት ግን አይጠቅምም፡፡ የሕዝብ ሰላምና የኢትዮጵያ ፖለቲካ መጎልመስ የሚያሳስበው ሰው ወደ ውጊያ የሮጡትንም ‹‹ግፋ በለው!›› የሚሉትንም እባካችሁ የሕዝብ መከራ ከማርዘም ተመለሱ ብሎ እንደሚማፀን ሁሉ፣ ከወዲህም ከወዲያም ካሉ የአመራር ሰዎች ጋር ግንኙነት እንዳለው የነገረን ጃዋር ፀፀቱና ለሕዝብ አበሳ መቆርቆሩ ከአንጀት እስከሆነ ድረስ፣ ግንኙነቶቹን ሰላምን ለመማለድ እንዲጠቀምበት ይጠበቃል፡፡ በዚህም በዚያ ተብሎ በሚገኝ ሰላም ውስጥ የሚኖር ዕርምጃ ሲታሰብ፣ በዛሬ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያሉት የትናንትና ቅሪቶችና ርዝራዦች ዛሬና ነገን የማገኛነት ውስን ሚና ከመጫወታቸው በቀር፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ህዳሴ አዲሱ ትውልድ ላይ ፈጣንና ትጉህ ሥራ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ እንደ እዚያም ተሠርቶ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉልምስና ወዲያው ከች አይልም፡፡ የፖለቲካ ሜዳችን በአስተሳሰብ የተለወጡ፣ የሾሩና ርቀው የሚያዩ አዕምሮዎች የሚገማሸሩበት የመሆኑ ነገር ቢያንስ የ20 ዓመታት ሒደት የሚፈጅ ይመስለኛል፡፡ ይህ ሒደት በአሥር ዓመታት የመጀመሪያ ምዕራፉ ውስጥ የሚያስከትለው ለውጥ ራሱ ዛሬ ካለንበት ጋር የሚወዳደር አይሆንም፡፡ በአሥር ዓመት ውስጥ ዛሬ የምናውቀው ብልፅግና ፓርቲ ራሱ ብዙ ብዙ ይቀየራል፡፡ የሚያገኘውም የጥራት ለውጥ የአዲስ ፓርቲ መወለድ ያህል ሳይሆን አይቀርም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...