Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉዓድዋ የትውልዱ ቅርስና ትጥቅ እንዲሆን!

ዓድዋ የትውልዱ ቅርስና ትጥቅ እንዲሆን!

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

የበርካታ ትውልዶችና ዘመናት ታሪክ በወርቃማ ቀለም የተጻፈበት ታላቁ የዓድዋ ድል የአንድ ቀን ጦርነት ነበር፡፡ በሚገባ ከተሰናዱ፣ ከተደማመጡና ከተባበሩ እንደ አገር የገባንበትን ፈተና ቀይሮ አዲስ ታሪክ ለማስመዝገብ መስፈንጠሪያ መሆኑን ታላቅ ማሳያ ነው፡፡

በዓድዋ ተራሮች ላይ በመላው ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች አሸናፊነት የዓድዋ ጦርነት ሲደመደም፣ የጦርነቱን ውጤት በአኃዝ ካስቀመጡ ጸሐፍት አንዱ የሆነው ጰውሎስ ኞኞ፣ ‹‹አፄ ምኒልክ›› በሚባለው መጽሐፉ ያቀረበው መረጃ አንድነት፣ መደጋገፍ፣ ጀግንነትና ወኔ ምን ያህል ፋይዳ እንዳላቸው ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡

- Advertisement -

‹‹በዓድዋ ጦርነት 7,560 ኢጣሊያዊያንና 7,100 ጥቁር ወታደሮች ሲገደሉ፣ 954 ኢጣሊያዊያን ጠፍተዋል፡፡ 470 ኢጣሊያዊያንና 958 ጥቁር ወታደሮች ቆስለዋል፡፡ 1,100 መሣሪያዎችና የነበሯቸው 56 መድፎችም ምርኮ ሆነዋል፡፡ በኢትዮጵያ በኩልም ቢሆን 7,000 ሲሞቱ፣ 10,000 ቆስለዋል፤›› ሲል አትቷል፡፡

ይህ ድል በየትኛውም ዓለም በፍጥነቱና በማጥቃት ስፋቱ ከፍተኛ መባሉ ብቻ ሳይሆን፣ ይመጣጠናሉ ተብለው ባልተገመቱ ኃይሎች መካከል ለህልውናቸው የተሠለፉ ጀግኖች ቅኝ ገዥዎችን ያንበረከኩበት ፍትሐዊ ጦርነት በመሆኑም ትልቅነቱን ያሳያል፡፡

በ1888 ዓ.ም. በአገራችን ሰማይ ሥር ያውም በዓድዋ ተራራዎች ጫፍ ላይ ቅኝ ገዥዎችን የሰበረው የዓድዋ ድል ለትናንቱና ለአሁኑ ብቻ ሳይሆን፣ ለመጪውም ትውልድ የኩራት ምንጭ የተነሳሽነቱ መስፈንጠሪያ ማድረግ ግን ከአሁኑ ትውልድ ይጠበቃል፡፡ ይህ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁርና ጭቁን ሕዝቦች ዓይን ገላጭ የሆነ ድል ደካማ ትባል በነበረችው አገራችን ኢትዮጵያና በፋሽሽት ኢጣሊያ መካከል  የተካሄደ ቢሆንም፣ የአውሮፓውያንን የሀብት መቀራመትና የብዝበዛ ፖሊሲ ቆም ብለው እንዲያጤኑ ያደረገ፣ የአገራችንና የመንግሥቷን ክብርና ዝናም ከፍ ያደረገ ድል ነበር፡፡

በዘህ ጽሑፍ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ መሪነት ከ128 ዓመታት በፊት መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዓድዋ ጦርነት ያደረጉትን የነፃነት ተጋድሎና የተቀዳጁትን ድል መነሻ በማድረግ፣ ታሪኩ እንደምን የኩራትና የአብሮነት ምንጭ መሆን እንዳለበት መዳሰስና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ጉዳዩን አንድ አጀንዳ ማድረግ እንደሚያስፈልግ እንዳስሳለን፡፡

ነገሩ የሚጀምረው እንዲህ ነው፡፡ ከ19ኛው ክፈለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ የአውሮፓ ኢምፔርያሊስት መንግሥታት ርካሽ የሰው ጉልበት፣ የተትረፈረፈ ጥሬ ሀብትና ገበያ ፍለጋ የእስያ፣ የአፍሪካና የደቡብ አሜሪካ አገሮችን ተቀራምተዋል። በዚህ ቅርምት የተለያዩ ነፃነታቸውን ጠብቀው የኖሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖሪያ ምድር የሆነችው ኢትዮጵያ የጣሊያን ድርሻ እንድትሆን ተወስኖ ነበር።

አውሮፓውያኑ ዕጣ ተጣጥለው ጣሊያን ኢትዮጵያ እንድትገዛ ባለዕድል ብትሆንም፣ ይህን በዕጣ የተገኘ ዕድል ዕውን ማድረግ ግን የዋዛ አልነበረም። ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የመንግሥት ሥርዓት ያላትና በተደጋጋሚ በውጭ ኃይል የተቃጣባትን ወረራ ስትመክት የኖረች አገር መሆኗ (ከ1868 እስከ 1896 ዓ.ም. ድረስ ብቻ ከእንግሊዝ፣ ከግብፅ፣ ከድርቡሽና ከኢጣሊያ ጋር ከ12 ጊዜ በላይ ተዋግታ ድል ማድረጓን ልብ ይሏል) በቀላሉ ዘው ተብሎ የሚገባባት እንዳትሆን አድርጓል።

ስለዚህ የጣሊያን መንግሥት ሰበብ ፈልጎ እያለዘበ መግባትን ነበር የመረጠው፡፡ ከኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ጋር የኢትዮጵያን ነፃነት አክብሮ በአካባቢው ለመኖር ከኢትዮጵያ ጋር የውጫሌን ስምምነት የተፈራረመውም ለዚህ ነው። በተለይ የወቅቱ የኢጣሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍራንቺስኮ ክሪስፒ የላከው ኮንት አንቶኔሊ፣ ንጉሡን ለማግኘትና ውል ለመፈራረም ወደ መቀመጫ ከተማቸው አዲስ አበባ እስኪመለሱ እንኳን መታገስ አቅቶት ውጫሌ ድረስ ገስግሶ ለመፈራረም ነበር የሞከረው፡፡

በ20 አንቀጾች የተቀነበበው የውጫሌ ውል ሚያዝያ 25 ቀን 1881 ዓ.ም. ሲፈረም፣ ውሉ የሩቅ ግቡ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አክብሮ መኖር ሳይሆን ቅኝ ግዛቱ ለማድረግ ያለመ ስለነበረ ጣጣ ማስከተሉ ግን አልቀረም። በተለይ የውሉ 17ኛው አንቀጽ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ሥር የምትተዳደር አገር አስመስሎ መቅረቡ በትርጉም መገለጡ በሴራ የተተበተበ ነገር እንዳለ አጋለጠ (ይህም የወቅቱ አገር መሪዎችን ጥንቃቄና ድፍረት የሚያሳይ ነው)፡፡

በውሉ የጣሊያንኛ ትርጉም ላይ ኢትዮጵያ ከውጭ አገሮች ጋር የምታደርገው ግንኙነት ራሷዋን እንደቻለች ሉዓላዊ አገር ሳይሆን በጣሊያን በኩል የሆነ አስመስሎ ማስቀመጡ ነበር በኢትዮጵያዊያን መሪዎች በኩል ቁጣን የቀሰቀሰው። ይህ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥትና በጣሊያን መካከል እየከረረ ሄዶ ወደ ጦርነት የተሸጋገረ አለመግባባት እንዲፈጠር ያደረገ ምክንያት ነው። ይህን ጉዳይ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የራሱን ታሪክ ያህል ስለሚያውቀው ደግሜ ማሰልቸት አልፈልግም።

በኋላ ግቡን ለማሳካት በሁሉም መንገድ መሞከርን መርጧልና የጣሊያን መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር የገባውን ውል መሻሩን ተከትሎ በስተሰሜን የታጠቀ ሠራዊቱን አሠልፎ ቀይ ባህርን ተሻገሮ ወደ መሀል ኢትዮጵያ ለመዝለቅ መንቀሳቀስ ይጀመራል። እንቅስቃሴው ግን መረብን እንደተሻገረ በዓድዋ ላይ ተገደበ።

የወራሪው  ኃይል ዓድዋን ተጠግቶ ነበር የሰፈረው፣ የልዩ ልዩ ሕዝቦች መኖሪያ የሆነችውን ኢትዮጵያን ሲመሩ የነበሩት ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ ደግሞ ወራሪው ጣሊያንን ለመከላከል የጦርነት ክተት አዋጅ ለማወጅ ተገደዋል (በነገራችን ላይ እንደ ማንኛውም መሪ አፄ ምኒልክ በአገር ግንባታ ሒደታቸውና የአስተዳደር ወቅታቸው ጥፋት ሠርተዋል ቢባል እንኳን፣ በኋላቀር ዘመን ሕዝብን አንድ አድርገው ቅኝ አገዛዝን በመርታታቸው በትውልድ ቅብብሎሽ መወደስና በቅርቡ መታየት እንደ ጀመረው በዘላቂ ማስታወሻ መወሳት ያለባቸው መሪ ናቸው፡፡ ዓለምም የሚቀበለው ይኼንኑ ነው)፡፡

በመልክና በባህል የማይመስላቸው፣ ባህር ተሻግሮ የመጣው የጣሊያን ወራሪ ኃይል ርስታቸውን ሊቀማ፣ ማንነታቸውን (ባህላቸውን፣ ወጋቸውን፣ ቋንቋቸውን…) ሊያዋርድ፣ ፈጣሪ የሰጣቸውን በምድራቸው ላይ ያለውን መብትና ነፃነት ገፍፎ ለባርነት ሊዳርጋቸው ታጥቆ መመጣቱን የተገነዘቡት ኢትዮጵያዊያን በየመሪያቸው ሥር ተሠልፈው የምኒልክን ኃይል ለመቀላቀል አለማቅማማታቸው ነበር የድሉ ሚስጥርና አሁንም ቀና ብለን የመኖራችን ፋይዳ።

ከየአካባቢው በየመሪያቸው ከሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች እንደጅረት እየፈሰሱ የምኒልክን ኃይል የተቀላቀሉት ዘማቾች ግዙፍ ኃይል ፈጥረው፣ ተሳስበውና ተማምነው ያደረጉት ዘመቻ ለታላቁ ድል መገኘት ትልቁ እሴት ሲሆን፣ የአንድነትና አልበገር ባይነት መገለጫ ሆኖ ኖሯል። ይህ ግዙፍ ኃይል የጣሊያንን የሠለጠነ ወራሪ ለመግጠም ወደ ዓድዋ ሲተም የራሱን ስንቅ፣ የጦር መሣሪያና በእየ እምነቱ ፈጣሪውን ምርኩዝ አድርጎ ለአገሩና ለሰንደቁ ለመዋደቅ በማለምም ነበር፡፡ የአሁኑ ትውልድ ቢያድለው ሊማርበት የሚገባው አንዱ ቅርስም ይኼው ነው፡፡

እዚያው ትግራይ የነበሩትን ሳይጨምር ከሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የተሰባሰበው የኢትዮጵያ ኃይል ጥቅምት 1988 ዓ.ም. ላይ ወደ ዓድዋ ጉዞ ይጀምራል። በእግርና በአጋሰስ የራሱን ስንቅና የጦር መሣሪያ (ጥቂት ኋላቀር ጠመንጃዎች፣ ጦርና ሰይፍ፣ ዱላ…) ታጥቆ በወጉ የሠለጠነውንና የዘመኑ ቴክኖሎጂ ያፈራውን የጦር መሣሪያ የታጠቀውን የጣሊያን ኃይል ዓድዋ ላይ ለመግጠም ጉዞ ሲጀመር በከፍተኛ ሞራልና መደጋገፍ ሲሆን፣ የአገር ምሥረታ አዲሱን ጉዞ ለማጠናከር የረዳ መቀናጀትም ነበር የፈጠረው።

የኢትዮጵያውያን ኃይል ነፃነቴን አሳልፌ ከምሰጥ ብሞት እመርጣለሁ ብሎ የተሠለፈ ሲሆን፣ የጣሊያን ኃይል የመጣው ደግሞ በተቃራኒው ኢትዮጵያውያንን ነፃነታቸውን ነፍጎ፣ ፈጣሪ የሰጣቸውን የተፈጥሮ ሀብት ለመመዝበርና ለጣሊያኖች የተመቸች ምድር ለመፍጠር ነው። በርከት ባሉት በቅኝ ግዛት ተይዘው በቆዩ አገሮች እንደሚታየው በራሱ አምሳል እምነትና ታሪክ የለሽ ብሎም አጎብዳጅ ማኅበረሰብ ለማንበርም ያለመ ተልዕኮ ይዟል፡፡ አሁንም ድረስ በራሳችን የውስጥ ችግር መታመሳችን እንጂ፣ አኩሪ ታሪክ ያለን ሕዝቦች መሆናችንን የምንጠቅስበት አንዱ ቅርስ ዓድዋ ነው፡፡

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ የመላ አፍሪካ፣ እስያ፣ የደቡብ አሜሪካ ባለአገር ሕዝቦች ድል ተደርጎ ተወሰደ። በቅኝ ግዛትና በጭቆና ሥር ለነበሩ የዓለም ሕዝቦች በሙሉ የነፃነት ትግል ተነሳሽነትን ቀሰቀሰ። በዚህ ምክንያት የዓድዋ ድል የፀረ ቅኝ ግዛት ትግልና የድሎች ሁሉ አውራ ሆነ። የዓድዋን ድል ልዩና ታሪካዊ የሚያደርገውም ይህ ነው።

ሰሞኑን ተመርቆ ሥራ የጀመረውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ የጎበኙ የአፍሪካ መሪዎችና የኅብረቱ ስብሰባ ታዳሚዎች ኢትዮጵያን ከዓድዋ ድልና ከአፄ ምኒልክ ነጥሎ ማየት እንደማይቻል ሲገልጹ የነበሩትም ለዚሁ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የመታሰቢያውን ውበትና ታሪካዊ እሴትነት ሳደንቅ በታላቅ ኩራት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዚህ አኳኋን ነፃነታቸውን በነጭ ባዕድ ወራሪ ሳያስነጥቁ በእጃቸው አስቀሩ። ይሁን እንጂ መብትና ነፃነታቸው ምሉዕ መሆን አልቻለም ነበር። ዘውዳዊው ፊውዳላዊ መንግሥት የመሠረተው አሀዳዊ ሥርዓት በደማቸው ሉዓላዊነቷን ባስከበሩባት አገር፣ ለብሔራዊ መብትና ነፃነቶቻቸው ዕውቅና መንፈጉ አንድ ስብራት ነበር። ወታደራዊው መንግሥትም ቢሆን የሰው ልጆችን መብቶች በመጨፍለቅ፣ ሀብት ንብረትን በመውረስ፣ የእምነት ነፃነትንና ዋጋን በማሳነስ አገራችንን ወደ የማያባራ ጦርነት ከቷት አለፈ፡፡

በእነዚያ ደማቅ የዓድዋ ድሎችና ጀግኖች መስዋዕትነት የተጋመደው ኢትዮጵያዊነት ከደርግ ውድቀት በኋላ አንፃራዊ የዴሞክራሲ ጭላንጭል ቢታይበትም፣ አገራዊ አንድነቱን ከመዳከም አልታደገውም፡፡ በኢሕአዴግ ትውልድ የምጣኔ ሀብት ዕድገትና ፋታ የሰጠ ሰላም ቢገኝም፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት፣ ቀስበቀስ ወደ ቁርሾና ግጭት የሚወስዱ ትርክቶች፣ ድርጊቶችና ሕግጋት እየተደማመሩ ሄደው እነሆ ከዓድዋ በኋላ አራትና አምስት ትውልድ ተሻግረንም ከቀውስ፣ ከእርስ በርስ ግጭትና ትርምስ መውጣት አልቻልንም፡፡

አሁንም ድረስ ሰላምና መረጋጋት ተደነቃቅፎ፣ ዴሞክራሲያዊነት ጨንግፎ፣ የመንቀሳቀስ ነፃነት ተገድቦ፣ መደማመጥና መነጋገር ሳይቻል፣ በመገዳደል ለመቀጠል ሰይጣናዊ ምኞት ውስጥ አገር መግባቷ እንደ ቀጠለ ነው፡፡  ኢትዮጵያዊያንም አብረን ሆነን የተራራቅን መስለን አለን፡፡

ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በአገራችን የተጀመረውን ተስፋ ሰጭ የለውጥ መንፈስ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና መንግሥት በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላቸው ደም አፋሳሽ ጦርነቶች ተካሂደዋል፣ እየተካሄዱም ነው፡፡ ሚሊዮኖች ለሞት፣ ለአካል መጉደልና መፈናቀል ተዳርገዋል፡፡ የሚያሳዝነው ጉዳይ ከበርካታ አሥርት ዓመታት በኋላ እንኳን ኅብረ ብሔራዊና ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አንድነት የነገሠባት አገር በጋራ ለመገንባት እየተቸገርን መሆኑ ነው፡፡ ግን ለምን?

እሱ ብቻ አይደለም፡፡ አያድርገው እንጂ የከፋ የውጭ ጠላት ቢመጣ እንኳን እንደ ሕዝብ ተደማምጦ፣ አፍ ከልብ ሆኖ ለጋራ ጥቅሙ የሚዘመት ወይም ለሥር ነቀል አገራዊ ለውጥ የሚተጋና የተሰባሰበ ዜጋ እየታየ አለመሆኑም፣ ትውልዱ ከዓድዋ ቅርስና ትጥቅ ምን የወሰደው ትምህርት አለ የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ጭራሽ ከዚህም ብሶ በራሱ በዓድዋ ድልና በጀግኖቻችን ክብር አሰጣጥ ላይ እየተወዛገበ ያለ ትውልድና የፖለቲካ ኃይል መታየቱ መጪውን ጊዜ እንዳያከብደው አስግቷል፡፡

በመሠረቱ ዛሬም ሆነ ነገ በዓድዋ ድል አሻራዎች ላይ ተመሥርተን አገራችንን አስከብረንና ሉዓላዊነቷን ጠብቀን መኖር ከፈለግን ሰላም፣ አገራዊ ዕርቅና ድርድርን ማስቀደም አለብን፡፡ መሣሪያ በመወዝወዝና በእርስ በርስ ጦርነት የሚመጣ ለውጥ የለም ብለን የትናንቱ በቃን የሚል ጀግና መፍጠርም ግድ ይላል፡፡ በመሸናነፍና አንተ ትበልጥ አንተ በመባባል አገርን እናስቀድም፡፡ ከኖረው አዙሪት በመውጣት ጠባብነት፣ መለያየትና መገፋፋትን እናስወግድ፡፡ መታበይና ትምክህትም ይብቃ፡፡

ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳንሆን ሰዎች ሁሉ በማንነታቸው፣ በቆዳ ቀለም፣ በአካላዊ ቅርፅ፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ ወዘተ ተለይተው በሌሎች በበታችነት መታየትን፣ መናቅን፣ በገዛ አገራቸው ባይተዋርና የበይ ተመልካች መሆንን አይቀበሉም። እነዚህን ጫናዎች አለመቀበል የደመነፍስ ስሜት ነው። የመብትና ነፃነት መከበር ፍላጎት፣ ለመብትና ለነፃነት የመታገል ተነሳሽነት ምክንያቱ ይህ ደመነፍሳዊ ፍላጎት ነው። መንግሥትም ቢሆን ታዲያ ትናንት በውጭ ቅኝ ገዥዎች አልገዛም ያሉ ጀግኖች ልጆች መሆናችንን አስታውሶ ፍትሕ፣ እኩልነትና ዴሞክራሲን ለማስፈን መትጋት ነው ያለበት፡፡ ያለነፃነት አገር እንደሌለ መታወቅ አለበት፡፡

ከድህነት ለመላቀቅም ሆነ ይህች አገር ልታድግና ልትለማ የምትችለው ድህነትን ማጥፋት ስንችል ብቻ ነው። ዋናውና ቀዳሚው ጉዳይ ይህ ነው። አሁን በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር እየታየ ያለውን ድህነት፣ ኑሮ ውድነት፣ መፈናቀልና ሥራ አጥነት በቀውስና በጦርነት እሳት እያርገበገቡ ረጅም ርቀት መሄድ አይቻልም፡፡ ስለሆነም ፈጥኖ የፖለቲካ ድርድርና መፍትሔ መፈለግ የዓድዋን ድል በዓል ከማክበርም በላይ ዋጋ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡

በአጠቃላይ አያቶቹና አባቶቹ የውጭ ወራሪዎች የቃጡባቸውን ወረራ፣ እንዲሁም የራሳቸው ወገኖች የጫኑባቸውን ጭቆና የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለው ዳግም ላይመለስ አስወግደውታል። አሁን ትውልዱ በመነጋገር ሰላምና ደኅንነቱን ብቻ ሳይሆን የሰከነ ዴሞክራሲ ግንባታውን ዕውን ለማድረግ መነሳት አለበት፡፡ አንገት ከሚያስደፋው አዋራጅ ድህነት ጋር ተቆራኝቶ ላለመኖርም በትጋት የመነሳት ወኔ ከአያቶቹና ከአባቶቹ ወርሶ ድህነትን ለመሻር ሊነሳ ይገባል። ይህን የማድረግ ትውልዳዊና አገራዊ አደራ አለበት። ሰላምና ዴሞክራሲን አስፍኖ በሒደት ድህነትን ታግሎ ካልረታ እንደ አደራ በሊታ እንደሚቆጠር ማስታወስ አለበት።

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው nwodaj@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...