Sunday, May 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በሰብዓዊ ቀውስና በውድመት የታጀቡ ግጭቶች በአስቸኳይ ይቁሙ!

በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ተጀምሮ አማራና አፋር ክልሎችን ያዳረሰው የሁለት ዓመቱ አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢገታም፣ ከነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል የተጀመረው ጦርነት ግን እንደ ቀጠለ ነው፡፡ ከአማራ ክልል በተጨማሪ ኦሮሚያ ውስጥም በተለያዩ አካባቢዎች ውጊያ እየተካሄደ ነው፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በመቶ ሺዎች አልቀው፣ ሚሊዮኖች ተፈናቅለው፣ ቁጥራቸው የበዛ ዜጎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞባቸው፣ ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አረጋውያንና አቅመ ደካሞች አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳቶች ደርሰውባቸውና በአገር ኢኮኖሚ ላይ መጠነ ሰፊ ውድመት ደርሶ በፕሪቶሪያ ስምምነት መገታቱ ትልቅ ዕፎይታ ፈጥሮ ነበር፡፡ ከአንዴም ሁለቴ በፌዴራል መንግሥትና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነግ ሸኔ) መካከል የሰላም ንግግር ቢጀመርም፣ በበርካቶች ዘንድ ተፈጥሮ የነበረው ተስፋ ንግግሩ በመቋረጡ እንደ ጉም ነበር የበነነው፡፡ በአማራ ክልል ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መልስ የክልሉን ልዩ ኃይልና ኢመደበኛ አደረጃጀት ትጥቅ ለማስፈታት የተደረገው ጥረት ተቃውሞ በመቀስቀሱ፣ የለየለት ጦርነት ውስጥ ከተገባ ሰባት ወራት ተቆጥረዋል፡፡

በቅርቡ አዲስ አበባን ጨምሮ በአማራና በኦሮሚያ ክልል ተካሂደው በነበሩ ሕዝባዊ ውይይቶች ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል፣ የአገር ሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ብዙዎችን ያሳሳበ ዋነኛ ጉዳይ ነበር፡፡ የአገር ሰላም ዕጦትን አስመልክቶ ጥያቄ ካቀረቡ የስብሰባዎቹ ተሳታፊዎች መገንዘብ እንደተቻለው፣ በየቦታው የሚካሄዱ ጦርነቶችንም ሆነ ግጭቶችን ማስቆም ለምን አቃተ የሚለው እንቆቅልሽ ለምን እንደማይፈታ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም አካባቢዎች በማኅበረሰቦችም ሆነ በግለሰቦች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት፣ እንደ ባህሉና እምነቱ መሠረት የሚከናወኑ የግጭት ማስወገድና የዕርቅ ዘዴዎች ከበቂ በላይ ይታወቃሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ነባር አገር በቀል የግጭት መፍቻ ዘዴዎች በስፋት በሚታወቁባት ኢትዮጵያ፣ በፖለቲከኞች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ለሕዝብ ዕልቂትና ለአገር ንብረት ውድመት ሲያስከትሉ ዜጎች ግራ ቢጋቡ አይፈረድም፡፡ በግጭቶቹ ምክንያት ሕዝብ ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለመራብና ለተለያዩ አስከፊ ጉዳቶች እየተጋለጠ ምን ዓይነት ዓላማ ግብ እንዲመታ እንደሚፈለግ ግራ ያጋባል፡፡ ለአገራቸው ልማትና ዕድገት በአንድነት መሠለፍ የሚገባቸው ዜጎች ጎራ ለይተው ሲጨፋጨፉ ማየት ይዘገንናል፡፡

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከአንድ አውዳሚ ጦርነት ወደ ሌላው እንደ ቀልድ ሰተት እያልን የምንገባበት ምክንያት ሲበዛበት፣ ነገና ተነገ ወዲያ በኢትዮጵያ ላይ የሞግዚት አስተዳደር ለመሾም ቢነሳ ምን ሊባል ነው? ‹ሰላማችሁን ማስጠበቅ አቅቷችሁ እርስ በርስ እየተፋጃችሁ እኛን ዕርዳታ አምጡ እያላችሁ ታስቸግራላችሁ፣ ታርቃችሁ ሰላም እንድታሰፍኑ መድረክ ስናመቻች እንቢ ትላላችሁ፣ ሕዝባችሁን በሮኬትና በድሮን ከመፍጀትና ከማስራብ በተጨማሪ ዘግናኝ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ትፈጽማላችሁ፣ በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስለማይቻል በሰላም ማስከበር ስም ገብተን በሞግዚት እናስተዳድራችኋለን፣ ወዘተ› ብለው በአንድነት ቢነሱ፣ እንደ ጥንቶቹ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ለቅኝ አገዛዝ የማንመች መሆናችንን ማሳየት የሚያስችል ቁመና አለን ወይ? ሰፊና ጥልቅ በሆነ ክፍፍል ውስጥ ሆነው በጭካኔ አንዱ ሌላውን ለማጥፋት የሚፋለሙ የፖለቲካ ልሂቃን በሙሉ፣ ለአፍታ ቆም ብለው ከውጭ ሊመጣ የሚችለውን አደገኛ ሁኔታ እያጤኑ ነው ወይ? አገር እያስተዳደረ ያለው መንግሥትስ ቢሆን ዙሪያውን ሰላም ጠፍቶ እንዴት አድርጎ ነው ባለው ሁኔታ መቀጠል የሚችለው?

አሁን ያለውን አስከፊ ሁኔታ በቅንነት ለሚታዘብ ማንኛውም ዜጋ እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶችም ይባሉ ጦርነቶች፣ አገርን ከማፍረስና ሕዝብን ለአደገኛው ስደት ከማመቻቸት የዘለለ ፋይዳ እንደሌላቸው ይረዳል፡፡ አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበት ጦርነት ሕዝብን ከማስፈጀት፣ ከማፈናቀል፣ ከማስራብ፣ ከማሰቃየትና የአገርና የሕዝብ አንጡራ ሀብት ከማውደም የዘለለ ምንም ጥቅም እንደሌለው ማንም የሚረዳው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ አሸናፊነት ለማለም ማሰብም ሆነ ያለ መታከት መድከም፣ አገርንና ሕዝብን ለመከራ ከመዳረግ ውጪ ትርፍ እንደማይገኝበት የታወቀ ነው፡፡ ይሁንና ‹የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም› እንደሚባልለት ወፈፌ በአጉል ጀብደኝነት የተገባበት የጥፋት ድግስ ግን፣ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሆነ በአፍሪካውያን ወንድሞችና እህቶች ዘንድ የሚያስንቅ ፀያፍ ድርጊት ነው፡፡ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አንጋፋና ወጣት ፖለቲከኞች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ወኪሎች፣ ምሁራንና ልሂቃን፣ እንዲሁም የአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው ዜጎች በሙሉ ተባብረው አሁን ያለውን ሁኔታ ካልቀየሩ የታሪክ ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡ ቀውሱና ውድመቱ ተባብሶ ዝምታ አያዋጣም፡፡

የዘመኑ ኢትዮጵያውን አንዴ ቆም ብለው ማሰብ የሚገባቸው ቁምነገር ችግሮች ሲያጋጥሙ፣ ሰከን ብሎ መፍትሔ ለማፈላለግ የሚያስችሉ አማራጮችን ማየት ነው፡፡ ብልህ ግለሰቦች በመካከላቸው አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በቀጥታ ግጭት ውስጥ ሲገቡ እስከ ሕይወት ማጣት የሚያደርሱ አደጋዎች ስለሚገጥሟቸው፣ ሰከን ብለው የተሻሉ አማራጮችን ይፈልጋሉ፡፡ ሞኞች ግን በደም ፍላት በሚወስዷቸው ዕርምጃዎች ምክንያት ሕይወታቸውን ያጣሉ፣ ወይም ደግሞ ዕድሜ ልካቸውን ችግር ውስጥ የሚከታቸው አደጋ ይገጥማቸዋል፡፡ በአገር ጉዳይ በፖለቲከኞች መካከል አለመግባባት ሲኖር የተለመደው ጦር መስበቅና ሰይፍ መምዘዝ፣ ሕዝብን ከዕልቂት በስተቀር ምንም አላተረፈለትም፡፡ ሕዝባችን በውስጡ ባደራጃቸው ዘመን ተሻጋሪ እሴቶቹ አማካይነት በባህላዊ ዘዴዎች ችግሮቹን መፍታት ከቻለ፣ አገር የሚመሩም ሆኑ አገር ለመምራት የሚፈልጉ ከዕልቂትና ከውድመት ለምን አይላቀቁም? በሰከነ መንገድ በጨዋነትና በመከባበር ስሜት ተሞልተው ከጀብደኝነት ጎዳና የሚወጡት መቼ ነው? በአራቱም ማዕዘናት የሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም ያለህ ብሎ ሲጮህ ለምን አዳማጭ ያጣል? አገርን በማመስና በማተራመስ የሚገኘው ጥቅም ምንድነው?

ኢትዮጵያን የተረጋጋች፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊት አገር ለማድረግ የሚያስፈልገው ቅንነትና በሀቅ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ነው፡፡ ይህ ግንኙነት በመከባበር፣ በመተሳሰብ፣ በጨዋነትና በማስተዋል ላይ የተመሠረተ ንግግርም ሆነ ድርድር ለማድረግ ያስችላል፡፡ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች፣ አንዱ የአገሩ ባለቤት ሌላው መጤ፣ አንዱ ዜግነት ሰጪ ሌላው ተቀባይ፣ አንዱ ቤተኛ ሌላው ባዕድ፣ ወዘተ ለመሆን በሚደረግ የቁልቁለት ጉዞ አገር ያተረፈችው የእርስ በርስ መጨፋጨፍና የሚዘገንን ድህነት ብቻ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ኢትዮጵያ ያለፈችባቸው የታሪክ ምዕራፎች የሚናገሩት ጦርነት፣ ዕልቂት፣ ስደት፣ መፈናቀል፣ ረሃብና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያሳፍሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ፣ ለመስማት የሚዘገንኑ ፆታዊ ጥቃቶችና የመሳሰሉት ውንጀላዎች በስፋት እየተስተጋቡ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ወንጀሎቹ የኢትዮጵያን አንገት እያስደፉ ነው፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ አረንቋ ውስጥ ሊያስወጡ የሚችሉ መፍትሔዎችን በጋራ መፈለግ የግድ መሆን አለበት፡፡ ለዚህም ሲባል በሰብዓዊ ቀውስና በውድመት የታጀቡ ግጭቶች በአስቸኳይ ይቁሙ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...