Tuesday, April 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ፍጥነት ጋር ሊራመድ የሚችል የሕግ ሥርዓት እንደሚያስፈልግ ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት እያደገ የመጣውን አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ (ሰው ሠራሽ አስተውሎት) ሊገዛ የሚችል የሕግ ሥርዓት እንደሚያስፈልጋት ተገለጸ፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በጋራ የተሰናዳ የቢዝነስ ከባቢና ዲጂታል ኢትዮጵያ ኮንፈረንስ የካቲት 21 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት የኢንተርኔት ኢኮኖሚ አስተዳደር ቡድን መሪ ኢዮና አልባርስኮ ለሪፖርተር አንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ጅምር ሒደት ላይ በመሆኗ፣ ጠንካራ ሕግጋት ሊዘጋጁ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ ሥራው ቀላል ባይሆንም በሚደረጉ ድጋፎች በጠንካራ ማዕቀፍ ብዙ መሥራት ይቻላል ብለዋል፡፡

‹‹ዘመኑ በከፍተኛ ፍጥነት በዲጂታል እያደገ የመጣ በመሆኑ ከአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ፍጥነት ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል የሕግ ሥርዓት ሊበጅ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹የአቅምና ዕውቀት ችግር በየትኛውም አካባቢ እየፈተነን ነው፤›› ያሉት የቡድን መሪዋ፣ እያንዳንዱ የቴክኖሎጂ ዕድገትና ፍላጎት መጀመሪያ በዘርፉ የሠለጠነ ሰው ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡

በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ በዘርፉ ከአሥር ዓመት በላይ ያገለገሉ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ግለሰብ ስለአርተፊሻል ኢንተለጀንስ የቀን ተቀን አዳዲስ ክስተቶች ሲያብራሩ፣ ‹‹ኢንተርኔት ፈጣሪዎች ራሳቸውን እየተገዳደራቸው ያለው አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ኢትዮጵያን መደፍጠጥ የሚችል ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፤›› ይላሉ፡፡ ለዚህም እንዲረዳ ጠንካራና በቂ ምላሽ መስጠት የሚችሉ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የበቁ ባለሙያዎችና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ መኖር ጥያቄ የሌለው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

‹‹ይሁን እንጂ መንግሥት ፖሊሲ ያወጣል፣ ሕግ ያወጣል፣ ያቅዳል፣ ይናገራል፣ ወደ ውስጥ ሲገባ በአመዛኙ በዘርፉ የበቁ ሰዎች በጣም ውስን ይሆኑና ተግባራቸውም በሰዎቹ ቁጥር ከመወሰኑ በላይ፣ ኃላፊዎች በአመዛኙ በፖለቲካ ሥራ የተጠመዱ ስለሚሆኑ የታቀደው ሥራ አይከናወንም፤›› ሲሉ ያክላሉ፡፡

በመሆኑም ለዚህ ዘርፍ ከየትኛውም ጊዜ በተለየ ጥረትና ቁርጠኝነት አገሪቱ ያላትን ሕግጋት ማጠናከር፣ ሕግጋት ለሚያስፈልጋቸው ሕግ በማውጣት ቢያንስ እየፈጠነ ከሚሄደው የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ አዳዲስ ፈጠራ ጋር እየተቀራረቡ መሄድ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን 2025 ዕቅድን ለማሳካት የሚረዱ ሦስት ፕሮግራሞች በ500 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እየተከናወኑ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

‹‹አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም የሥጋትም የተስፋም ምንጭ ስለሆነ መንግሥት ጠንክሮ ይሠራል፤›› ያሉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ አብርሆት ባዩ (ዶ/ር)  ናቸው፡፡

የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በተመለከተ ከፍተኛ አማካሪው ሲያብራሩ፣ በኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ በፖሊሲ ላይ ተፅዕኖ የማሳደር አቅሙ ውስን ነው ብለዋል፡፡

‹‹በግሉ ዘርፍ ውስጥ በየትኛውም መድረክ የምንሰጠው ሐሳብ በመንግሥት ሰነድ ውስጥ ተካትቶ ይመጣል የሚል እምነት አለማደጉ፣ የግሉን ዘርፍ ሚና ያቀጭጨዋል፡፡ በመሆኑም ይህ መቀየር ያለበት ባህል ነው፤›› ያሉት አማካሪው፣ ‹‹በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሠማሩ የባለሙያዎች ስብስብና ማኅበራቶቻቸው የሚሰጡትን አስተያየት እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡

በውይይቱ በመንግሥት ይፋ ከተደረገ አራት ዓመታት ያስቆጠረውና አንድ ዓመት የቀረው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ዕቅድ መለካት ጥያቄ የተነሳበት ሲሆን፣ አማካሪው በሰጡት ምላሽ የዕቅዱ ስኬት መለካት ያለበት ከጅምሩ ይዟቸው በተነሳቸው ዓላማዎች ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ለዕቅዱ መሳካት የሚረዱ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በሕግና ደንብ ረገድ፣ በኢንተርኔት መሠረተ ልማቶች፣ በኤሌክትሮኒክ አስተዳደርና በመሳሰሉ ጉዳዮች ምን ተሠራ የሚለው በአግባቡ መፈተሽ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ የቴሌኮም ገበያው ነፃ መሆን አንደኛው የኢንተርኔት መሠረተ ልማት መስፋፋት መገለጫ መሆኑን ያስረዱት አማካሪው፣ በ2017 እና 2018 ዓ.ም. 17 ሚሊዮን ገደማ የነበረው የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር አሁን ወደ 37 ሚሊዮን መጠጋቱ አንዱ የዕቀዱ መሳካት ማሳያ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ የዲጂታል መሠረተ ልማት መስፋፋት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ አስቻይ ሥርዓቶች እንዳሉ ገልጸው፣ በተለይም የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለማንቀሳቀስ የሚረዳ ዲጂታል መታወቂያና ዲጂታል ክፍያ ለአንድ ኢኮኖሚ የደም ሥር በመሆናቸው አሁን ሁለቱም በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ለዲጂታል መታወቂያ መመዝገባቸውን የገለጹት አብዮት (ዶ/ር)፣ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ 70 ሚሊዮን ለማድረስ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች