Tuesday, April 23, 2024

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አራት ካህናት በግፍ መገደላቸው ተሰማ፡፡ የገዳሙ መጋቢ አባ ተክለ ማርያም አሥራት፣ የገዳሙ ጸሐፊ አባ ኪዳነ ማርያም ጥላሁን፣ የገዳሙ የመጽሐፍ መምህርና ቀዳሽ አባ ገብረ ማርያም አበበ፣ እንዲሁም በአመክሮ የሚኖሩ ኃይለ ማርያም የተባሉ መናኝ በታጠቁ ኃይሎች በግፍ መገደላቸውን ያረጋገጠ ዜና ይፋ ተደረገ፡፡

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ሌሊት ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ መገደሉ ከተሰማ በኋላ በሻሸመኔ ከተማ በደረሰ ሁከት
ከተከሰቱ ቁሳዊ ውድመቶች በጥቂቱ
ፎቶ፡- ታምራት ጌታቸው

ዘገባውን በወቅቱ ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቪዥን፣ ግድያው ኦነግ ሸኔ ተብሎ በሚጠራው የታጠቀ ቡድን መፈጸሙን በወቅቱ ገልጾ ነበር፡፡ ለዚህ ውንጀላ የካቲት 17 ቀን 2016 ዓ.ም. የማስተባበያ መግለጫ ያወጣው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በግድያው እጁ እንደሌለበት አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቪዥን ጥቃቱን ኦነግ ሸኔ በሚባለው ቡድን እንደተፈጸመ መዘገቡን የተቃወመው የኦነግ መግለጫ፣ የኦሮሚያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ጥቃቱ በኦነግ ሸኔ የተፈጸመ ነው ማለቱንም አጥብቆ ተቃውሞታል፡፡

‹‹ኦነግ በንፁኃንና ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸም ግድያንና የሰብዓዊ መብት ረገጣን በሁሉም መልኩ መወገዝ እንዳለበት ያምናል፤›› ሲል የኦነግ መግለጫ ይገልጻል፡፡ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት መዋቅሮች የሁሉንም ዜጎች ሕይወትና ደኅንነት የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው ሲል የሚጠቁመው መግለጫው፣ በኢትዮጵያ ግን ይህ እንደሌለ አስታውቋል፡፡

ከዚህ ይልቅ ባለፉት አምስት ዓመታት ጥፋትን በሌላ አካል ማላከክና ማጭበርበር በመንግሥት እንደተለመደ ኦነግ ያወሳል፡፡ በዚህ የተነሳ በተደጋጋሚ እንዳደረገው ሁሉ ኦነግ በንፁኃን ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች በገለልተኛ አካል ተጣርተው ለፍትሕ እንዲቀርቡ እንደሚጠይቅ፣ በመግለጫ በማጠቃለያው ያሳስባል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል ብዙ ዓይነት ግጭቶችና ግድያዎች መከሰታቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ ሁሉ በርካታ ቁሳዊና ሰብዓዊ ውድመቶችን ያስከተሉ ቢሆኑም፣ ነገር ግን ተጣርቶ ለፍርድ የቀረቡ የወንጀል ጉዳዮች አለመኖራቸው እንደ ትልቅ ክፍተት ይነሳል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ለሚፈጸሙ ግድያዎች ኃላፊነት በይፋ የሚወስድ ወገን እስካሁን አልታየም፡፡ የኦሮሚያ ክልል፣ እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት ኦነግ ሸኔ የተባለው ኃይል ለግድያዎቹ ተጠያቂ ነው ሲሉ ሁሌም ይከሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከኦነግ ሸኔም ሆነ በኦሮሚያ እንንቀሳቀሳለን ከሚሉ ሌሎች የኦሮሞ ፖለቲካ ልሂቃን በኩል ግድያዎቹ በገለልተኛ አካል ይጣሩ የሚል ውትወታ ይደመጣል፡፡

ይህን በመሰለ ውዝግብ ለአምስት ዓመታት የቀጠለው የኦሮሚያ ክልል ግድያና የደም መፋሰስ አሁን ላይ ያለ ተጠያቂነት መታለፍ ከማይቻልበት ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስላል፡፡ የዝቋላ አቦው ግድያ ከተፈጸመ በኋላ በነበሩት ቀናት ሮይተርስ ይዞት የወጣው የምርመራ ሪፖርት በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችን በኦነግ ሸኔ ላይ ብቻ እያላከኩ ለማለፍ የማያስችሉ መረጃዎችን ነው ይፋ ያደረገው፡፡

ቆሬ ነጌኛ (የፀጥታ ኮሚቴ) በሚል ስለሚጠራ ሚስጥራዊ የመንግሥት ቡድን መመርመሩን የገለጸው ሮይተርስ ወደ 30 የፌዴራልና የኦሮሚያ ባለሥልጣናትን፣ ዳኞችን፣ ጠበቆችን እንዲሁም የጉዳት ሰለባዎችን ቃለመጠይቅ በማድረግ የተጠናቀረ ሪፖርት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን በወጡ በጥቂት ወራት ሥራ የጀመረው የፀጥታ ኮሚቴው መኖሩም ሆነ፣ ዝርዝር የሥራ እንቅስቃሴው በይፋ እንዳይታወቅ ተደርጎ መቆየቱን ይገልጻል፡፡ የገዥው ብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እስከ መሆን የደረሱ እንደ ሚልኬሳ ገመቹ ያሉ ከፍተኛ የቀድሞ አመራሮችን ጨምሮ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሌሎች የብልፅግና አመራሮች፣ ስለ“ቆሬ ነጌኛ” መረጃ በመስጠት መተባበራቸውን የሮይተርሱ የምርመራ ሪፖርት ያስረዳል፡፡

“ቆሬ ነጌኛ” በኦሮሚያ ክልል ከሚፈጸሙ በርካታ ግድያዎች፣ እስራትና አፈናዎች ጀርባ እጁ እንዳለበት ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡ “ቆሬ ነጌኛ” የሚፈጽመው (የሚያስፈጽመው) ግድያ ግን በአብዛኛው ኦነግ ሸኔ ነው የፈጸመው በሚል እንደሚታለፍ ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ ለአብነትም እ.ኤ.አ. በ2021 ወደ 14 የሚጠጉ ግለሰቦች በዚህ ቡድን ቢፈጸምም በኦነግ ሸኔ ተሳቦ መቅረቱን ያመለክታል፡፡

ሮይተርስ በምርመራ ዘገባው ያጠናቀረውን ሪፖርት የመንግሥት ተቋም ለሆነው ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ማቅረቡን ይገልጻል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡበት የተጠየቁት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) “ቆሬ ነጌኛ” የተባለው የፀጥታ ኮሚቴ በኦሮሚያ እንዳለ ኮሚሽናቸው እንደሚያውቅ አረጋግጠዋል ተብሏል፡፡ ኮሚሽነሩ ከዚህ በተጨማሪም ተቋማቸው ከሕግ ውጪ የተፈጸሙ በርካታ ግድያዎችን፣ ማሰቃየትን ጨምሮ እስራቶችን መመዝገቡን መግለጻቸው ተጠቁሟል፡፡

ይህ ኮሚቴ ከጥቂት የክልሉ አመራሮች ውጪ በይፋ ወይም በመዝገብ አይታወቅም ተብሏል፡፡ በኢሰመኮ እ.ኤ.አ. የ2021 አንድ ሪፖርት ላይ ‹‹የደኅንነት ኮሚቴ›› ተብሎ በስም ከመጠቀሱ ውጪ በዝርዝር ስለኮሚቴው የተጻፈ ነገር አለመኖሩን ያትታል፡፡ ሮይተርስ በ“ቆሬ ነጌኛ” ጉዳይ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነግ ሸኔ) የሚባለውን የትጥቅ ቡድን መሪ ጃል መሮን አስተያየት ጠይቆ እንደነበርም ይገልጻል፡፡ ጃል መሮ ስለ“ቆሬ ነጌኛ” አስቀድሞም እንደሚያውቅ መናገሩን በመጥቀስ፣ ቡድኑ በኦሮሚያ ለተፈጸሙ ግድያዎች ተጠያቂ ነው ማለቱንም ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡

ይህ የሮይተርስ የምርመራ ሪፖርት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ብዙ ሽፋን የተሰጠውና ከፍተኛ መነጋገሪያ ቢሆንም፣ ነገር ግን ሪፖርቱ ለጠቀሳቸው በርካታ መረጃዎችና ውንጀላዎች ከመንግሥት ወገን የተሰጠ ምላሽ አልተሰማም፡፡

ከሰሞኑ ከኦሮሚያ ክልል ሁሉም ዞኖች ከተውጣጡ የሕዝብ ወኪሎች ጋር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ውይይት አድርገው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ውይይት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያ ቀደም በተደረገው ከአማራ ክልል ከመጡ ተወካዮች ጋር በተካሄደው ውይይት ላይም የሰላም አስፍኑልን ጥያቄ ጎልቶ ተነስቶላቸው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ተደጋግሞ ለተነሳ ጥያቄ ኅብረተሰቡ የራሱን ሰላም ራሱ እንዲጠብቅ የሚመክር ምላሽ ነበር የሰጡት፡፡ በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በአማራ ክልልና በሌሎች አካባቢዎች ከታጠቁ ኃይሎች ጋር የሚደረጉ ግጭቶች እያስከፈሉ ያሉትን ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመቶችን ለማስቆም፣ መንግሥት መፍትሔ እንዲፈልግ የሕዝብ ተወካይ ከተባሉት ተሰብሳቢዎች ተደጋግሞ ተነስቶ ነበር፡፡

ይህን በተመለከተም መንግሥታቸው በሰላማዊ መንገድ በንግግር ችግሮችን ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን የተናገሩት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ኅብረተሰቡ ለሰላም ሲል የታጠቁ ኃይሎችን መክሮና ዘክሮ እንዲመልስ ነበር ሐሳብ የሰጡት፡፡ በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በሰላም ዕጦት የተነሳ በርካታ ሰብዓዊ ድቀቶች እየተከሰቱ ነው፡፡ በየአካባቢው በሚፈጠሩ ግጭቶች ሰላማዊና ከግጭቱ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ዜጎች ውድ ሕይወታቸውን እየከፈሉ መሆኑ ይነገራል፡፡ ለነዚህ ሁሉ ቀውሶች ኃላፊነት የሚወስድ መታጣቱ ብቻ ሳይሆን፣ ዘለቄታዊ መፍትሔ የሚሰጥ አካል አለመኖሩ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ እንዳደረገው ነው የፖለቲካ ልሂቃን የሚናገሩት፡፡

በቅርቡ ከሪፖርተር ዩቲዩብ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)፣ በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ምስቅልቅል ሊፈታ ያልቻለው መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ማስመሰል የበዛበትን መንገድ መንግሥት በመከተሉ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ወንጀል ሠርቷል ተብሎ የሚጠረጠር ወገን እንዴት የሽግግር ፍትሕ ይመራል?›› ሲሉ ጥያቄ ያነሱት መረራ (ፕሮፌሰር)፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ገለልተኝነት የጎደለውና በሀቀኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደማይመራ ገልጸዋል፡፡ አገሪቱ አጠቃላይ ቀውስ ውስጥ ናት ያሉት መረራ (ፕሮፌሰር)፣ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የመፍጠር ጉዳይ ሊታለፍ እንደማይገባ አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከመገዳደል ፖለቲካ እንዳልተላቀቀች፣ አንዳንዴ ቢለሰልስም ባለፉት 50 ዓመታት ከጠመንጃ አገዛዝ ተላቃ እንደማታውቅ አንጋፋው ፖለቲከኛ አስረድተዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ስለነገሠው የመገዳደል ፖለቲካ ሲናገሩም፣ ‹‹ራስን ፃድቅ ሌላውን ኃጢያተኛ የማድረግ የቡዳ ፖለቲካ፤›› ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የሚፈጸሙ ግድያ፣ ዕገታና እስራቶችን በሚመለከት ደግሞ ተጠያቂነቱ የተደባለቀ እንደሚመስላቸው ነው የተናገሩት፡፡ በመንግሥት የሚደገፉ ጫካ ያሉ የታጠቁ ቡድኖች መኖራቸውን፣ ሰዎችን አግተው ገንዘብ የሚቀበሉ መሆናቸውንም ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ፈረንጆቹን ጨምሮ ሦስተኛ ወገን ባለበት ለዚህች አገር ምን እናድርግ በሚለው ላይ ምንም ሲደረግ አናይም፤›› ብለዋል፡፡

በርካታ የፖለቲካ ልሂቃን በተለይ ለኦሮሞ ሕዝብ እንታገላለን የሚሉ ፖለቲከኞች በኦሮሚያ አላባራ ላለው ግጭትና ግድያ ኦነግ ሸኔ ብቻ ነው ተጠያቂው የሚለውን ሲቀበሉት አይደመጡም፡፡ መንግሥት በተለይ የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ከኦነግ ሸኔ እኩል ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት ብዙዎቹ ይናገራሉ፡፡

በቅርቡ ከአርትስ ቴሌቪዥን ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረገው ፖለቲከኛው ጃዋር መሐመድ እጅግ አነጋጋሪ የሆኑ ነጥቦችን ስለኦሮሚያ ክልል ቀውስ አንስቷል፡፡ ‹‹ሸገር በሚባለው ከተማ አስተዳደር ስር ቢያንስ 30 እስር ቤቶች አሉ፡፡ ዛሬ በኦሮሚያ ከመቶ ሺሕ በላይ የፖለቲካ እስረኞች አሉ፡፡ በክልሉ በየቀኑ በመቶዎች ያልቃሉ፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ተረኛ እየተባለ ቢወቀስም ዛሬ እያየ ያለውን መከራና ችግር መቼም ዓይቶት አያውቅም፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት የሞተው ኦሮሞ ቁጥር ከኃይለ ሥላሴ ጀምሮ የደርግና ኢሕአዴግን ብትደምረው አይስተካከልም፤›› በማለት ነው በኦሮሚያ ያለውን ሞት አስከፊነት ያስረዳው፡፡

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተደጋጋሚ ቀውስ እንደሚታይና አገሪቱም ሰላምና መረጋጋት እንዳጣች የተናገረው ጃዋር፣ ይህን ችግር ተነጋግሮ በድርድር መፍታት አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን አስረድቷል፡፡ ‹‹ሰሜን እየተቃጠለ ደቡብ አይለማም፣ ደቡብ እየተቃጠለ ሰሜን አይለማም፡፡ ጎንደር እየተበጠበጠና ወለጋ እየተበጠበጠ አራት ኪሎ እፀናለሁ ማለት ዘበት ነው፤›› በማለት የተናገረው ጃዋር፣ ይህ በተግባር ተሞክሮ እንደማይሠራ የተረጋገጠ እንጂ በንድፈ ሐሳብ ብቻ የሚነገር አለመሆኑን አስረድቷል፡፡

በቅርቡ ከሪፖርተር ጋር ሰፊ ቆይታ ያደረጉት የኦፌኮ ፓርቲ አባልና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ፣ በኦሮሚያ በሚከሰቱ ግድያዎችና ወንጀሎች የኦነግ እጅ ብቻ ነው ያለበት የሚባለውን ውንጀላ እንደሚጠራጠሩ ነበር የተናገሩት፡፡ ከኢሕአዴግ ሥልጣን መያዝ ጀምሮ በኦሮሚያ ከሐረርጌ እስከ አርባ ጉጉ፣ አሁን ደግሞ በወለጋና በሌሎች አካባቢዎች ለተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂው ኦነግ ነው መባሉ እንደማያሳምናቸው ተናግረው ነበር፡፡

‹‹ኦነግ በጭራቅነት እንደሚታይ ቢገባኝም፣ እንደሚባለው ጨካኝ ቡድን ቢሆን ኖሮ ከሥልጣን የሚያወርደው ኃይል ባልኖረ ነበር፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ ደስታ፣ በኦሮሚያ ብዙ የሕዝብ ድጋፍና ቅቡልነት እያለው ጭካኔና የፖለቲካ ሴራ የማይከተል በመሆኑ ብቻ ሥልጣን ማጣቱን ተናግረዋል፡፡

አሁን በአገሪቱ ያለውን ቀውስ በተመለከተ መንግሥትን ‹‹ደንታ ቢስና ምንም የማይመስለው›› ሲሉ የወቀሱት አቶ ደስታ፣ ሁሉንም ጥፋት ኦነግ ሸኔ ነው እያሉ ከመደፍደፍ ገለልተኛ አጣሪ ቡድን በማዋቀር ጉዳዩን አጣርቶ መፍትሔ መስጠት ተገቢነት አለው ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -