Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልኢትዮጵያ ከመቅደላ የተዘረፈው ጋሻዋን ለመሸጥ የወጣው ጨረታ እንዲሰረዝ  ጠየቀች

ኢትዮጵያ ከመቅደላ የተዘረፈው ጋሻዋን ለመሸጥ የወጣው ጨረታ እንዲሰረዝ  ጠየቀች

ቀን:

በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ዘመን በ1860 ዓ.ም. በመቅደላ ጦርነት የተዘረፈው የኢትዮጵያ ጋሻ ለመሸጥ የወጣው ጨረታ እንዲሰረዝ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን መጠየቁ ተገለጸ፡፡

ዘአርት ኒውስ ፔፐር እንደዘገበው ጨረታውን በእንግሊዝ ኒውካስል ታይን ለማከናወን ለሐሙስ የካቲት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ቀጠሮ ተይዟል።

 ጨረታው እንዳይከናወን በቅርስ ተሟጋቹ የኢትዮጵያ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) አማካይነት በኤክስ ማኅበራዊ ትስስር የተቃውሞ ድምፅ ተስተጋብቷል፡፡

- Advertisement -

ጋሻው ‹የሰብሳቢዎች ጨረታ› በሚል ለገበያ የቀረበው በአንደርሰን ኤንድ ጋርላንድ አማካይነት ነው፡፡ የ19ኛው ክፍለ ዘመን የተራራ ቅርፅ ያለው ጋሻው በብረት የተሠራ፣ በአበባ ቅርፅ የተጌጠ ሲሆን፣ በመሃሉ ‹‹Magdala 13th April 1868››  (መቅደላ ሚያዝያ 13 ቀን 1868) የሚል ጽሑፍ ተጽፎበታል፡፡ ይህም የእንግሊዝ ኃይሎች መቅደላን የወረሩበትንና ዳግማዊ ቴዎድሮስ እጄን አልሰጥም ብለው ራሳቸውን ያጠፉበት  የጦርነት ውሎ ያስታውሳል፡፡

የእንግሊዝ ጦር አዛዥ የነበረው ጄኔራል ሮበርት ናፒየር (በኋላ የመቅደላ ሎርድ ናፒየር) መቅደላን እንዲያቃጥሉ ትዕዛዝ መስጠቱን ወታደሮቹም ‹‹ወደ እንግሊዝ የወሰዱትን ብዙ ቅርሶችን ዘርፈዋል›› በማለት በካታሎጉ መጻፉም ተዘግቧል።

ስለጋሻው ይዞታ ከእንግሊዝ ወታደር የተገኘ ምናልባትም በቤተሰቡ ውስጥ ያለፈ ከማለት በቀር ዝርዝር መረጃ የለውም፡፡

ጋሻውን ለማጫረት የተገመተው መጠን አነስተኛና ከ800 እስከ 1,200 ፓውንድ እንደሆነ ዘገባው ጠቁሟል፡፡

የካቲት 15 ቀን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አበባው አያሌው ለአንደርሰን ኤንድ ጋርላንድ በጻፉት ደብዳቤ ጋሻውን ለመሸጥ ያወጡትን ጨረታ እንዲሰርዙ አጥብቀው ያሳሰቡ ሲሆን፣ ይህን የተዘረፈ ቅርስ ወደ ትውልድ አገሩ እንዲመለስ ሻጮቹን እንዲያነጋግሩ መጠየቃቸው ዘአርት ኒውስ ፔፐር ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል የሆኑት አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር)፣ ጋሻው እንዲመለስ እየጠየቁ ሲሆን፣ ከመቅደላ የተዘረፉ የቀንድ ዋንጫዎች እ.ኤ.አ. በ2021 በቡስቢ ጨረታ በብሪድፖርት ሊሸጡ ሲል የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጣልቃ ከገቡ በኋላ መሰረዙን ጠቁመዋል።

ጉዳዩን አስመልክቶ ለአንደርሰን ኤንድ ጋርላንድ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ አለማግኘቱን ጋዜጣው ዘግቧል።

የመቅደላው ዘረፋ

በኢትዮጵያ ውስጥ በጋዜጠኝነት ይሠሩ የነበሩት አንድሪው ሄቨንስ፣ እንግሊዛውያን በሚያዝያ 1860 ዓ.ም. በመቅደላ በፈጸሙት ወረራ ቅርሶቹን እንዴት እንደወሰዱት ፕሪንስ ኤንድ  ፕሉንደር  በተባለው መጽሐፋቸው ጽፈዋል፡፡ መጽሐፉ በዝርዝር የሚገልጽ ሆኖ፣ በዓይነት በዓይነት የተለዩ 538 ዕቃዎችን በለንደን ለይቷል፡፡

ስብስቦቹ ብራናዎች፣ ከቁርጭራጭ የእጅ ጽሑፍ እስከ የንጉሣዊው ቤተሰብ የእጅ አምባርና አልባሳት፣ ንዋያተ ቅዱሳትንና ዘውድን ያካተቱ ናቸው፡፡ ቅርሶቹ በተለያዩ ቦታዎች ከዓበይት ተቋማት እስከ ምክር ቤት ስብስቦች ድረስ በሁሉም ቦታ ይገኛሉ፡፡

‹‹ወታደሮቹ ከዘረፏቸው መካከል ብዙዎቹ በቦርሳዎቻቸውና በኪሶቻቸው የያዟቸው ሁሉም ዕቃዎች ማለት ይቻላል በማሳያ ቦታዎች በዕይታ ላይ አይደሉም። የዝርፊያ ታሪኩን ለመንገር እነዚህን ነገሮች ተከታትዬአለሁ። መጽሐፌ ቅርሶቹ እንዲመለሱ የሚጠይቅ የቅስቀሳ መጽሐፍ አይደለም። ያ የኢትዮጵያ ጉዳይ ነውና›› ሲሉ አንድሪው ሄቨንስ ጽፈዋል።

በብዙኃኑ ከሚታወቁት አንዳንድ ቅርሶች መካከል በዌስት ሚኒስተር አቢና በብሪቲሽ ሙዚየም ውስጥ የተቀመጡ ታቦቶች/ንዋየ ቅዱሳት፣ በቪክቶሪያና አልበርታ እጅ የሚገኙ ዘውድና ንጉሣዊ አልባሳት ይገኙበታል፡፡

ሌሎች ደግሞ በዌልኮም ስብስብ ውስጥ የእጅ ጽሑፎችን (ብራናዎች) የሚታወቁ ሲሆን፣ በሳውዝዋርክ ካውንስል እጅ የሚገኙት ከአንድ ሴንቲ ሜትር በታች የሚለኩ የክታብ ጥቅልሎች ከዚህ ቀደም ልብ ሳይባሉ ትኩረት ሳያገኙ ቆይተዋል።

ቪክቶሪያና አልበርታ ቅርሶችን ለኢትዮጵያ በረዥም ጊዜ ትውስት ለመመለስ ፍላጎቱን ሲያሳይና ሲነጋገር፣ ዌልኮም ኮሌክሽን ምንም ዓይነት ቅርሶችን ስለመመለስ ጥያቄዎች እንዳልደረሱት፣ ነገር ግን ‹‹እንደ ሁኔታው በጉዳዩ ላይ ውሳኔዎችን እንደሚወስድ፤›› ተናግሯል።

የኢትዮጵያን ታቦት አስፈላጊነትና ጠቀሜታን ጠንቅቆ እንደሚያውቅ የገለጸው ዌስት ሚኒስተር አቤይ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በጣም በተቀደሰ ቦታ ተጠብቆና ከዕይታ ተከልሎ የሚቀመጠውን ታቦት ለመመለስ ፍላጎቱ መሆኑን መናገሩ ይታወቃል፡፡

የብሪቲሽ ሙዚየም ‹‹የእኛ ቀጣይ ምኞት እነዚህን ንዋየ ቅድሳት/ታቦታት በእንግሊዝ ለምትገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመስጠት በትውፊታቸው መሠረት ቀሳውስት እንዲንከባከቧቸው ማድረግ ነው፤›› ማለቱም ይታወሳል።

ዘረፋው እንዴት ነበር?

‹‹የቴዎድሮስ አሟሟትና የመቅደላው ዘረፋ›› በሚል ርዕስ ጥናት ያከናወኑት ግርማ ኪዳኔ፣ አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም. ካጠፉ በኋላ የመቅደላ አምባን የወረሩት እንግሊዞች የፈጸሙትን ዝርፊያ በዝርዝር አቅርበውታል፡፡ እንዲህም አሉ፡-  

‹‹እንደ እንግሊዝ ጦር አዛዦች አባባል ተልዕኳቸውን የእንግሊዝ እስረኞችን ለማስፈታት ነበር፡፡ ከዚህ የተልዕኮ ሽፋን በስተጀርባ ግን ዓላማቸውን እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ታሪካዊና ባህላዊ ይዘት ያላቸውን ቅርሶች ለመዝረፍ ጭምር መሆኑ የሚያጠያይቅ አይሆንም፡፡ ሪቻርድ ሆምስ የተባለው የብሪትሽ ሙዚየም ተወካይ ከእንግሊዝ ጦር ጋር አብሮ እንዲመጣ መደረጉ ለዚህ የዘረፋ ተግባር መከሰት እንደነበረ ግልጽ ነው፡፡

‹‹የመጀመርያው ዘረፋ ቡድን ያተኮረው በሟቹ ንጉሥ ሬሳ ላይ ነበር፡፡ የአንገት መስቀልና የጣት ቀለበታቸውን፣ ሸሚዛቸውንና ሽጉጣቸውን ከመዝረፋቸውም ባሻገር ሹሩባቸውን ሳይቀር ሸልተው የወሰዱ ለመሆኑ በታሪክ መዛግብት መረዳት ይቻላል፡፡

‹‹ሁለተኛው የዘረፋ ቡድን ያተኮረው የቤተ መንግሥት ሕንፃ በመድፈር ነበር፡፡ ንጉሡ በሕይወታቸው ሳሉ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ለማቋቋም የሰበሰቧቸውን እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ መጻሕፍትን እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ የብሔራዊ ቤተ መዛግብት መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ አያሌ የመንግሥት ሰነዶችንና የተለያዩ መረጃዎችን ሳይቀሩ ዘርፈዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የአፄ ቴዎድሮስ ዘውዶችና ማኅተም፣ በተለይም ክብረ ነገሥት የተባለው ታላቁ መጽሐፍ ይገኙባቸዋል፡፡ ቀጥለውም ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ማዕድ ቤት ውስጥ በመግባት ሃያ እንሥራ የሚሆን የተጠመቀ ጠጅና የእህል አረቄ ዘርፈው ከመጠን በላይ ሰክረው ነበር፡፡ ከዘረፏቸው ቅርሶች ይልቅ ጥፋት ያደረሱባቸው አመዝነው ታይተዋል፡፡ ብዙ ቅርሶች ጥለዋል፣ ሰባብረዋል፣ መጻሕፍትንም ቀዳደዋል፣ አልባሳትንም ሸረካክተዋል፡፡

‹‹የሦስተኛው የዘረፋ ቡድን ከወሰዳቸው መካከል ከወርቅ የተሠራ የአቡነ ሰላማ አክሊል ወይም ዘውድ ጫማና ቀበቶ፣ ከወርቅ የተሠሩ ሁለት ጽዋዎች፣ ከወርቅ የተሠራ በአንገት ላይ የሚጠልቅ የአፄ ቴዎድሮስ የሰሎሞን ኒሻን እንዲሁም ንጉሡ ሲነግሡ ለብሰውት የነበረው የማዕረግ ልብስ ይገኙባቸዋል፡፡

‹‹አራተኛው ቡድን በዘረፋቸው መካከል የተለያዩ ጋሻዎች፣ ከእነዚህ ውስጥ የአፄ ቴዎድሮስ ጋሻ ሳይሆን አይቀርም ተብሎ የሚገመተውና የፊታውራሪ ገብርዬ ጋሻ፣ ልዩ ልዩ ጦሮችና ጎራዴዎች፣ ያሸበረቁ የፈረስ ዕቃዎች፣ በተጨማሪም የቴዎድሮስ እስረኞች የታሰሩበት የእግር ብረት ይገኙበታል፡፡

‹‹አምስተኛውና የመጨረሻው የዘረፋ ቡድን ያተኮረው አፄ ቴዎድሮስ በየአገሩ ሲዘዋወሩ ያርፉበት በነበረው ድንኳናቸውና ይጠጡበት በነበረው ዋንጫቸው፣ የማንነቱ  ባልታወቀ የፈረስ ልባብ ላይ ነበረ፡፡ ወታደሮቹ በዚህ ሳይገቱ የደረሱበትን በማሰስና እያንዳንዱ ቤት ውስጥ በመግባት ተመሳሳይ ዘረፋ ከማካሄዳቸውም ባሻገር ከተለያዩ ቤተ ክርስቲያኖች የተገኙትን መንፈሳዊ ሥዕሎችና እንዲሁም ቁጥራቸው አሥር የሚደርሱ ታቦቶችን ሳይቀሩ ወስደዋል፡፡ በአጠቃላይ ከንጉሠ ነገሥቱ ቤተ መንግሥት ጀምሮ በአነስተኛ ጎጆ ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ሳይቀሩ ተዘርፈዋል፡፡

‹‹ምንም እንኳ ጄኔራል ናፒየር ባዘዘው መሠረት በመቅደላ ተሰብስበው የነበሩት ሁሉ ቅርሶች ለጨረታ ቀርበው ነበር በማለት ለማስመሰል ተሞከረ እንጂ፣ አንዳንድ ባለ ሀብቶች በተለይም ሲቪሎችና ኦፊሰሮች ራሱ ጄኔራል ናፒየር ሳይቀር ቀደም ብለው ጨረታው በይፋ ከመጀመሩ በፊት ለየራሳቸው ያከማቿቸው ቅርሶች በብዛት እንደነበሩ ድርጊቱ ካለፈ በኋላ ሊታወቅ ችሏል፡፡ ለምሳሌ ለጨረታው ካልቀረቡት ቅርሶች መካከል የአፄ ቴዎድሮስ ዘውዶች፣ የክብርና የማዕረግ ልብሶቻቸው፣ በሺሕ የሚቆጠሩ የብራና መጽሐፎችና የቴዎድሮስ ማኅተም፣ የአቡነ ሰላማ የወርቅ አክሊል፣ በብር ያሸበረቀ ጋሻ፣ በክብረ በዓል ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውል የቴዎድሮስ ከበሮና የመሳሰሉት ከሌሎች ንብረቶች ጋር ከመቅደላ ቤተ ክርስቲያን አጥር ግቢ በነበሩት ጎጆዎች ወስጥ ታምቀው እንደነበር ይነገራል፡፡

‹‹በተለይም ከአቡነ ሰላማ መቃብር ላይ ተፈጽሞ የነበረውን የስርቆት ወንጀል አስመልክቶ ሲናገር ‹በጣም ከሚያስገርመውና ከሚያሳዝነው ነገር ሁሉ ከእስረኞቹ መካከል አንዱ ከስድስት ወር በፊት ተቀብረው የነበሩት ከአቡነ ሰላማ መቃብር ድረስ በመሄድ መቃብሩን አውጥቶና ሰብሮ ብዙ ሺሕ ዶላር ሊያወጣ የሚችል ከአልማዝ የተሠራ መስቀላቸውን ከአንገታቸው ላይ መንጭቆ መውሰዱ የቱን ያህል የተረገመ ሰይጣን እንደነበር ነው ሲል በዝርዝር አስቀምጦታል፡፡

‹‹የአቡነ ሰላማን ከወርቅ የተሠራ አክሊልና የቁርባን ጽዋ ከአንድ ጦር ሜዳ ላይ ከዋለ ወታደር የብሪትሽ ሙዚየም ተወካይ ሆልምስ በአራት የእንግሊዝ ፓውንድ ብቻ ገዝቶት እንደነበር ቀደም ሲል ተጠቅሷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ እንግሊዞች ድል አገኘን ብለው ወደ አገራቸው እንደተመለሱ የተጠቀሱትን ሁለት ቅርሶች ሪቻርድ ሆልምስ ከኮሎኔል ፍሬዘር፣ ከኮሎኔል ሚልወርድና ከኮሎኔል ካሜሩን ጋር ለብሪትሽ ሙዚየም በሁለት ሺሕ የእንግሊዝ ፓውንድ እንዲሸጥላቸው እ.ኤ.አ. ጁላይ 1 ቀን 1868 አቅርበውት እንደነበር የደብዳቤ ወረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

‹‹በሽያጭም ሆነ በስጦታ መተላለፋቸው ለጊዜው ባይታወቅም በአሁኑ ጊዜ ከመቅደላ የተወሰዱት  ቅርሶች በእንግሊዝ አገር ሙዚየሞች ውስጥ ባመጧቸው ሰዎች ስም ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ በጻፈው  ፕሬስተር ጆን ተብሎ በሚጠራው መጽሐፍ መጨረሻ ላይ ተርጓሚዎቹና አዘጋጆቹ ሀንቲንግፎርድና ቤክንግሃም እንደጠቀሱት በብሪትሽ ሙዚየም ውስጥ “ሆልምስ ኮሌክሽን” እየተባሉ የሚጠሩ አሥር ታቦቶች ከመኖራቸውም  በላይ ብዛታቸው ከአንድ ሺሕ በላይ የሚደርስ የኢትዮጵያ የእጅ ጽሑፍ መጽሐፎች በተጠቀሰው ሙዚየም ውስጥ ተደርድረው ይታያሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...