Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እስከ ግለሰቦች የሚደርሰው ወገን ፈንድ

ወገን ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ሕጋዊ ዕውቅና በማግኘት ከኢትዮጵያና ከተለያዩ አገሮች ልገሳን ለማሰባሰብ ‹‹ወገን ፈንድ›› የሚባል የበይነ መረብ (ኦንላይን) የድጋፍ ማሰባሰቢያ ድረ ገጽ ትግበራ ላይ አውሏል። ወገን ፈንድ የኦንላይን የድጋፍ ማሰባሰቢያ በበላቸው ጨከነ (ዶ/ር) እና በአቶ ሚሊዮን አጀበ በታኅሣሥ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡ ስለተቋሙ የሥራ እንቅስቃሴ በዋና ዳይሬክተርነት እየመሩ የሚገኙትን በላቸው ጨከነን (ዶ/ር)፣ ሰላማዊት መንገሻ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር:- ወገን ፈንድ ምንድነው?

በላቸው (ዶ/ር):- ወገን ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ከሚሠራቸው የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል አንዱ ወገን ፈንድ የተሰኘ የኦንላይን የድጋፍ ማሰባሰቢያ ድረ ገጽ ነው። የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ በሚፈቅደው መንገድ ምዝገባ በማካሄድ መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገ የቴክኖሎጂ ቢዝነስ ፕላትፎርም (መደላድል) ነው። ዋና ዓላማው የተለያዩ የግብረ ሰናይ ድርጅቶችና የሃይማኖት ተቋማትና አስቸኳይ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ግለሰቦች ዕርዳታ ሲያስፈልጋቸው በኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ውጪ ካለው ማኅበረሰብ ለማሰባሰብ እንዲረዳ የተዘጋጀ መተግበሪያ ነው። አዲስ የሥራ ፈጠራ ሐሳብ ያላቸው ግለሰቦች ሐሳባቸውን ዕውን ለማድረግ ይችሉ ዘንድ ድጋፍ ማሰባሰብ የሚችሉበት ገጽም ነው።

ሪፖርተር:- ይህ ድርጅት እንዴት ተቋቋመ? ዓላማውስ ምንድነው?

በላቸው (ዶ/ር):- እንደ ድርጅት ዓላማ አድርገን የተነሳነው የቴክኖሎጂ ሽግግር ማምጣት ነው፡፡ በቀጣይ ወጣቶችን የሚጠቅሙ ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅ ዕቅድ አለን፡፡ ወገን ፈንድ የተሰኘውን መተግበሪያ ዓላማው ማንኛቸውም አገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅቶች በየትኛውም ዓለም ከሚገኙ ደጋፊዎች ዕርዳታን እንዲያገኙ በቴክኖሎጂ ማገናኘት ነው። ኢትዮጵያውያን የምንታወቅበትን የመረዳዳት ባህል በቴክኖሎጂ ደግፎ የመጣ ነው፡፡

ሪፖርተር :- በዓለማችን በርካታ የድጋፍ ማሳሰቢያ ድረ ገጾች አሉ። ‹‹የወገን ፈንድ›› እንደ ጎ ፈንድ ሚ እና ጀስት ጊቪንግ እንዲሁም ሌሎች በአገር ውስጥ ዕርዳታ ከሚሰበሰብባቸው መንገዶች በምን ይለያል?

በላቸው (ዶ/ር):- በኢትዮጵያ ያሉ ግብረሰናይ ድርጅቶች በአብዛኛው በጥሬ ገንዘብ ወይም በአካውንት ድጋፍ የሚያገኙ ሲሆን፣ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ግለሰቦች ደግሞ በሶሻል ሚዲያና በጎፈንድሚ አማካይነት ነው። አብዛኛውን ጊዜ በገንዘብ የሚሰጡትን በትክክል ለተጎዱ ወገኖች ለማድረስ ጠንካራ አመራር ያስፈልጋል፡፡ ለአያያዝም አይመችም። በዚህም ምክንያት ድጋፍ ሰጪዎች ጋር አመኔታ አይኖርም። በሶሻል ሚዲያ የሚደረገው ድጋፍ በቀጥታ የግለሰቡ አካውንት የሚገባ ቢሆንም፣ አልፎ አልፎ የሚረዳውን ሰው ስምና አካውንት ቁጥር ኤዲት በማድረግ ለስርቆት ሊያጋልጥ ይችላል። በተጨማሪም ዕርዳታ ሚደረግበት ወቅት ከመቼ እስከ መቼ እንደሆነ ስለማይገለጽ የሞተ ግለሰብ በዩቲዩብ ወይም በሌሎች ሶሻል ሚዲያዎች ላይ ተለጥፈው ይቆያሉ። ዕርዳታ ሰጪዎች ቀኑን ወይም የግለሰቡን ማንነት ሳያረጋግጡ ገቢ በማድረግ ያለአግባብ ገንዘቦች ይወሰዳሉ። የጎ ፈንድ ሚ እና የሌሎች መተግበርያዎች ችግር ደግሞ ከኢትዮጵያ ሆኖ መመዝገብና ልገሳ ማሰባሰብ አለመቻሉ ነው። ለምሳሌ፣ በጎፈንድሚ ለመመዝገብ ከሚቀበላቸው ውሱን (19) አገሮች የመኖሪያ ፈቃድ ወይም ዜግነት ያላቸው መሆን አለበት። በውጪ በሚኖሩ ሰዎች የተሰበሰበ ገንዘብ በቀጥታ ወደ ተረጂው አካውንት ገቢ ለማድረግ አሰልቺ የሆነ የክፍያ ሒደት፣ የተሰበሰበውን ገንዘብ ወጪ ለማድረግ የውጭ አገር ዜግነት ያለው የባንክ አካውንት እንዲሁም መጨረሻ ላይ ገንዘቡን ከአካውንት ለማውጣት ብዙ ጥያቄዎች በመኖሩ ድጋፉን ሳያገኙ የሚቀሩበት አጋጣሚ አንደሚፈጠር ችግር ከገጠማቸው ሰዎች ተረድተናል። ወገን ፈንድ የተቋቋመው የድጋፍ አሰባሳቢዎችንም ሆነ፣ የድጋፍ ጠያቂዎችን ችግሮችን በሚፈታ መልኩ ነው። ማንኛውም ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት በሚጠየቀው መሥፈርት መሠረት የተመዘገበ ከሆነ፣ በወገን ፈንድ መጠቀምና ከኢትዮጵያና ከመላው ዓለም ልገሳን ማሰባሰብ ይችላል። ዕርዳታው የሚሰበሰብበትና የሚያበቃበት ቀንም ይገለጻል። እነዚህ ከሌሎች ድጋፉ ከሚደረግባቸው የገቢ ማሳሰቢያ መንገዶች ይለያሉ፡፡

ሪፖርተር:- የዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ብቻ ናቸው?

በላቸው (ዶ/ር):- በወገን ፈንድ ዋና ተጠቃሚ የሆኑት በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ፈቃድ ያላቸው ድርጅቶች ቢሆኑም፣ በአዋጅ ዕውቅና የተሰጣቸው የሃይማኖት ተቋማትና አስቸኳይ የሕክምና ዕርዳታ የሚፈልጉ ከሜዲካል ቦርድ ደብዳቤ የተጻፈላቸው ግለሰቦች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ የተለያየ የሥራ ፈጠራ ሐሳብ ያላቸው ሐሳባቸውን በማቅረብ ከኢትዮጵያውያን እገዛን ማግኘት ይችላሉ። በዚሁ ክፍል መጽሐፍ ለማሳተምና የተለያዩ የጥበብ ሥራዎችን ለማስፈጸም ገንዘብ ማሰባሰብ ይችላሉ።

ሪፖርተር:- በወገን ፈንድ ተጠቃሚ ለመሆን መሥፈርቶቹ ምንድናቸው?

በላቸው (ዶ/ር):- ተጠቃሚዎች የተለያየ መሥፈርት ማሟላት አለባቸው። የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ከሆኑ ከባለሥልጣኑ ያገኙት የምዝገባ ፈቃድና የመተዳደሪያ ደንብ ሰነድ ማያያዝ ይጠበቅባቸዋል። በሁለተኛ ደረጃ ያሉት ማንኛውም የሃይማኖት ተቋማት በእምነት ተቋሙ ኃላፊ ተጽፎ የተፈረመ ደብዳቤና የእምነት ተቋሙ መተዳደሪያ ደንብ እንዲሁም በሦስተኛ ደረጃ ያሉት አስቸኳይ ሕክምና የሚፈልጉ ግለሰቦች ደግሞ በሜዲካል ቦርድ የተወሰነ ውሳኔና የግለሰቦቹን ማንነት የሚገልጽ መታወቂያ ወይም ፓስፖርት ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል። ይህን ምዝገባ ካደረጉ በኋላ ድጋፉን የፈለጉበት ምክንያት ምን እንደሆነ በድረ ገጹ ላይ አጭር ማብራሪያ መጻፍ አለባቸው። እነዚህ መጠይቆች ተገምግመው በወገን ሶሉሽንና አብሮን የሚሠራው ባንክ ተገምግሞ ዕርዳታን ማሰባሰቡ ይጀመራል።

ሪፖርተር:- ወገን ፈንድ በሁለት ዓመት አገልግሎቱ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል? ምን ያህል ተቋማት ተመዘገቡ?

በላቸው (ዶ/ር)፦ በጣም ጥሩ ተቀባይነት አግኝቷል። በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ከ70 በላይ ድርጅቶች የተመዘገቡ ሲሆን፣ 140 ለሚደርሱ ምላሽ ለሚፈልጉ ክስተቶች ድጋፎች ማሰባሰብ ተችሏል። በወገንፈንድ መቄዶንያ፣ ሜሪጆይ፣ በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ፣ ማኅበረ ቅዱሳን ገዳማት ክፍል፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልና ሌሎች ትልልቅ ተቋማትን ጨምሮ 70 ተቋማት ተመዝግበዋል፡፡ ለድንገተኛ አደጋና ድርቅ ተጎጂዎች፣ ለትምህርት፣ ለአረጋውያንና ወላጅ ላጡ ሕፃናት፣ ስፖርትን ለማስፋፋትና ሴቶች ላይ ትኩረት ያደረጉ ልገሳዎች ተደርገዋል።

ሪፖርተር:- በቀጣይ በወገን ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የታሰቡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ምንድናቸው?

በላቸው (ዶ/ር):- የወገን ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የመክፈያ መንገዶችን አካቶ ወገን ፈንድ የኢትዮጵያ ጎፈንድሚ ሆኖ እንዲቀጥል ማስቻል ቀዳሚ ሥራችን ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ከመላው ዓለም ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ገንዘብ መላክ ሲፈልጉ የሚጠቀሙበት ወገን ሴንድ የተባለ መተግበሪያ ከሁለት ወር በፊት በሥራ ላይ አውሏል። በቀጣይ ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ይዞ በመምጣት ለኅብረተሰቡ የላቀ አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል።

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በአሁኑ ወቅት ከ21 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታ ይፈልጋል›› አቶ አበራ ሉሌሳ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ምክትል ጸሐፊ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ላለፉት 89 ዓመታት በመላ አገሪቱ የሰብዓዊነት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በድርቅ፣ በበሽታና በግጭት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የምግብ፣ የመጠለያ፣ የመድኃኒትና የ24 ሰዓት...

ከቢሻን ጋሪ እስከ ዶባ ቢሻን እንክብል

ዶባ ኢንዱስትሪያል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሦስት ዓመታት በላይ ጥናትና ምርምር ያደረገበትንና ለገበያ ያበቃውን ዶባ-ቢሻን እንክብል የውኃ ማከሚያ...

ለሴቶች ድምፅ ለመሆን የተዘጋጀው ንቅናቄ

ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በፆታ እኩልነት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሁም የሴቶችን ማኅበራዊ ችግር በማቃለል ዙሪያ በተለያዩ ክልሎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ...