Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበራሳቸው ወጪ ሕሙማንን የሚያክሙት ሐኪሞች

በራሳቸው ወጪ ሕሙማንን የሚያክሙት ሐኪሞች

ቀን:

የቅድመና ድኅረ ወሊድ ክትትል ለእናቶች ጤና በእጅጉ ወሳኝ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ ክትትል ተደራሽነት ሙሉ ለሙሉ ነው ባይባልም ከሞላ ጎደል መጠነኛ መሻሻል ይታይበታል፡፡ ይህም ሆኖ ግን አሁንም ቢሆን ብዙ እንደሚቀረው ዕሙን ነው፡፡

በአንፃሩ ደግሞ የከፋ የጤና እክል ያጋጠማቸው ሴቶች የሕክምናውን ወጪ መሸፈን አቅም በማጣታቸው የተነሳ ሲያዝኑና ሲጨነቁ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ይህንንም ችግር የተረዱት በጎ አድራጊ ሐኪሞች ከኪሳቸው እያዋጡ ወጪያቸውን ለመሸፈን ሲጥሩ ይስተዋላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ተነሳሽነት በአርዓያነት የሚታይ ቢሆንም ዘለቄታዊነቱ ግን ማጠያየቁ አይቀርም፡፡

ስለሆነም ዕገዛውና ዕርዳታው ቀጣይነትና ዘላቂነት እንዲኖረው በሕጋዊ ዕውቅና መንቀሳቀስ በማስፈለጉ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ የማህፀንና ጽንስ ትምህርት ክፍል የሕክምና ባለሙያዎች ‹‹ሔዋን የሴቶች ጤና ድጋፍ በጎ አድራጎት ድርጅት›› አቋቁመው ለከፍተኛ ሕክምና የተዳረጉ ሴቶችን ውጪ በመሸፈን ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ናቸው፡፡

- Advertisement -

በትምህርት ክፍሉ የማህፀንና ጽንስ ሰብ ስፔሻሊስቶች፣ ስፔሻሊስቶች፣ የስፔሻሊቲ ትምህርት በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎች፣ ሐኪሞች፣ አዋላጆችና ነርሶች ዕገዛና ተነሳሽነት የተቋቋመው ይኸው ድርጅት ጉዳዩ ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ሕጋዊ ዕውቅና ተችሮታል፡፡

የድርጅቱም ዓላማ፣ ለከፍተኛ ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ የመክፈል አቅም ለተሳናቸው ሴት ታካሚዎች ወጪያቸውን መሸፈን፣ ከክፍሉ/ከኮሌጁ ውጪ ማለትም በአረጋውያን ማዕከላትና ኑሮአቸውን በጎዳና ላይ ላደረጉና በተለያዩ ምክንያት ወደ ጤና ተቋም መሄድ አቅቷቸው በየቤታቸው ለሚገኙ ሴቶችና ልጃገረዶች ነፃ የቅድመ ካንሰር ምርመራ ማድረግ፣ በዚህም የከፋ ነገር ከታየ ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ ያመቻቻል፡፡

ከዚህም ሌላ በአገሪቱ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያዎች ለሚገኙ ሴቶችና ልጃገረዶችም ሕክምና እንዲያገኙ ማድረግ፣ ሥነ ተዋልዶና ጤናን አስመልክቶ የጉትጎታ (አድቮኬሲ) ሥራ ማከናወን የዓላማው አንዱ ክፍል ነው፡፡

ሐኪሞቹ ከሚሠሩበት ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በተጨማሪ በዳግማዊ ምኒልክና ራስ ደስታ ሆስፒታሎች በማህፀንና ፅንስ ክፍል ያሉ ታካሚዎችን ለመርዳት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ 

የድርጅቱ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የማህፀንና ጽንስ ሐኪም እንዲሁም የክፍሉ ኃላፊ የሆኑት ወንድሙ ጎዱ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ለድርጅቱ መቋቋም መነሻ የሆነው ወደ ክፍሉ ከሚመጡትና ከፍተኛ ሕክምና ከሚያስፈልጋቸው መካከል አብዛኞቹ የሚፈለግባቸውን ወጪ ለመሸፈን ሲቸገሩ ታይተዋል፡፡ ችግሩ በይበልጥ ጎልቶ የሚታየው ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል በሚገቡና በካንሰር ሕክምና ላይ ባሉ ሴቶች ዘንድ ነው፡፡

‹‹ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ሲባል ሁለት፣ ሦስት ሐኪሞች ሆነን በየወሩ ከኪሳችን ገንዘብ እያዋጣን ወጪያቸውን መሸፈኑን ተያያዝነው፡፡ ቀስ በቀስም ከኪሳቸው እያዋጡ ድጋፍ የሚያደርጉ ሐኪሞች ቁጥር እየጨመረ መጣ፣ ሲቀጥልም ይህ ዓይነቱን ድጋፍ ቅርጽ አስያዝነው፡፡ እናቋቁም የሚሉ በጎና ቅን ሐሳቦች መንፀባረቅ ጀመሩ፤›› ብለዋል፡፡

በዚህም የተነሳ ወዲያውኑ ‹‹ፔሸንት ፈንድ ኮሚቴ›› መቋቋሙንና የገንዘብ ድጋፍም በሦስት መንገዶች መቀጠሉን ገልጸው፣ አንደኛው መንገድ ሁሉም የክፍሉ ባለሙያዎች ደመወዛቸው ላይ የተወሰነ ገንዘብ በፈቃዳቸው እየተቀነሰ ለኮሚቴው ድጋፍ እንዲውል ማድረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ሁለተኛው መንገድ ደግሞ ከወር ደመወዛቸው ላይ ከሚቆረጠው ገንዘብ በተጨማሪ፣ በፍላጎታቸው ከኪሳቸው እያዋጡ የሚረዱ ባለሙያዎች መኖራቸው ሲሆን፣ የመጨረሻው አካሄድ ደግሞ በክፍሉ ዙሪያ ያሉ፣ ፈቃደኛ የሆኑና አቅም ያላቸውን በማስተባበር የሚገኝ የሀብት ምንጭ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

ለአንድ ዓመት ከመንፈቅ ባደረጉት ጥረት 150,000 ብር ሊሰበሰብ እንደተቻለ፣ በዚህም ገንዘብ የ70 ሴት ታካሚዎች ሕክምና ወጪ እንደተሸፈነ፣ በዓይነትም ድጋፍ እንደተደረገላቸው ከወንድሙ ጐዱ (ዶ/ር) ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሕክምና ኮሌጅ ፕሮቮስት ሲሳይ ሥርጉ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ባለው የጤና ሥርዓት ምክንያት በአንዳንድ መድኃኒቶች አቅርቦት ላይ የታየውን ክፍተት ባለሙያዎቹ ተረድተው ከግላቸው የተወሰነ ገንዘብ እያዋጡ ክፍተቱን ለመሸፈን ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

ይህም ሆኖ ግን ክፍተቱ ከግል በሚወጣውና በመንግሥት ብቻ ለመሸፈን የማይቻል ሆነው በማግኘታቸው፣ የተጠቀሰውን ድርጅት የማቋቋምና ሕጋዊ ዕውቅናም እንዲያገኙ በማድረግ ለሌሎች አርዓያ የሆነ ሥራ እንዳከናወኑና ለድርጅቱም እንቅስቃሴ የሕክምናው ኮሌጅ ተገቢውን ድጋፍና ዕገዛ እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡

የኮሌጁ ሜዲካል ሰርቪስ ፕሮቨስት ውለታው ጫኔ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹በመሠረቱ ነፃ ሕክምና ቀርቷል፡፡ ይኼም ሆኖ ግን መታከሚያ ያጡ ታካሚዎች ነፃ ሕክምና እንዲፈቀድላቸው ሲጠይቁና ሲያስጠይቁ ይስተዋላል፡፡ የትምህርት ክፍሉ ባለሙያዎች ያቋቋሙት የሴቶች ጤና ድጋፍ በጎ አድራጎት ድርጅት ክፍተቱን በተወሰነ መልኩ የመሸፈን ብቃት አለው፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...