Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምኢኮዋስ የገጠመው ፖለቲካዊ ቀውስ

ኢኮዋስ የገጠመው ፖለቲካዊ ቀውስ

ቀን:

የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) በኒጀር ላይ የጣላቸውን በርካታ ማዕቀቦች መልሶ ለማንሳት ተገዷል፡፡

የኢኮዋስ አባል አገሮችን የናጠውን የፖለቲካ ቀውስ ለማረጋጋት በናይጄሪያ አቡጃ ጉባዔውን ያካሄደው ድርጅቱ፣ ዓምና በኒጀር የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ በአገሪቱ ላይ የጣለውን በርካታ ማዕቀብ ለማንሳት የወሰነውም፣ በማዕቀቡ ምክንያት ጎረቤት አገሮች ጭምር መረጋጋት በማጣታቸውና የፖለቲካ ቀውስ በመከተሉ ነው፡፡  

ከቅርብ ወራት ወዲህ በቀጣናው የተባባሰውን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት፣ አባል አገሮቹ ተከታታይ ውይይቶች ሲያደርጉ የሰነበቱ ሲሆን፣ በዚህም በኒጀር ላይ ጥለው የነበሩትን ድንበር የመዝጋትና ከአየር በረራ ማገድን ጨምሮ የተለያዩ ማዕቀቦችን አንስተዋል፡፡

- Advertisement -

የማዕቀቡ መነሳት ውሳኔው ከተላለፈበት ሰዓት አንስቶ ተግባራዊ መደረጉንም የኢኮዋስ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኦማር አሊዩ ቶሬይ መናገራቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

እንደ ቶሬይ፣ የማዕቀቡ መነሳት ዋና ዓላማ በማዕቀቡ ምክንያት የተከሰቱ ሰብዓዊ ቀውሶችን ለመፍታት ነው፡፡

በቀጣናው አባል አገሮች ውስጥ የሚደጋገመውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ለማስቆም ማዕቀብ መጣልን እንደ አማራጭ አድርጎ የወሰደው ኢኮዋስ፣ የሚጥላቸው ማዕቀቦች ለሕዝቡ ማኅበራዊ ቀውስ አስከተሉ እንጂ፣ በመፈንቅለ መንግሥት አድራጊው መከላከያው ላይ ያመጣው ይህ ነው የሚባል ተፅዕኖ የለም፡፡

ከአባል አገሮቹ በኒጀር፣ በማሊና በቡርኪናፋሶ የተደረጉ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቶች ሰብዓዊ ቀውስ ቢያስከትሉም፣ ሕዝባዊ ድጋፍ የተቸራቸው ነበሩ፡፡ ሆኖም የሕገ መንግሥትን መከበር አጥብቆ የሚደግፈው ኢኮዋስ፣ በአገሮቹ ማዕቀብ መጣል ብቻም ሳይሆን ከአባልነትም አግዷቸው ከርሟል፡፡

ኢኮዋስ አገሮቹን ከአባልነት ማገዱ ግን መፍትሔን ሳይሆን ለቀጣናው ፖለቲካዊ ቀውስ ይዞ መጥቷል፡፡ ኢኮዋስ ከአባልነት ማገዱን ተከትሎ፣ ሦስቱም አገሮች በዘላቂነት ከኢኮዋስ አባልነት ራሳቸውን እንደሚያገሉና የራሳቸውን ጥምረት እንደሚፈጥሩ ማሳወቃቸው ኢኮዋስ ራሱን እንዲያጤን በር ከፍቷል፡፡ በመሆኑም ሦስቱም አገሮች ወደ ኢኮዋስ ተመልሰው እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በናይጄሪያ አቡጃ የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. የተካሄደውን የኢኮዋስ ጉባዔ የከፈቱት የኢኮዋስ ሰብሳቢና የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ቦላ ቲኒቡ፣ ኢኮዋስ ካሉት 15 አባል አገሮች ውስጥ፣ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቶች በተካሄደባቸው ኒጀር፣ ማሊና ቡርኪናፋሶ እንዲሁም በወታደራዊ መንግሥት እየተመራች በምትገኘው ጊኒ የሚከተሉት አሠራር ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ከማክበር ጋር መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡  

ኒጀር፣ ማሊና ቡርኪናፋሶ ኢኮዋስ ያሳለፈውን ውሳኔ እንዲያጠኑ ቲኑቡ ጠይቀው፣ ኢኮዋስን እንደ ጠላት እንዳይቆጥሩትም አሳስበዋል፡፡

ኢኮዋስ በወታደራዊ መንግሥት በምትተዳደረው የጊኒ እንዲሁም የማሊ ግለሰቦች ላይ ጥሎት የነበረውን ማዕቀብም አንስቷል፡፡ ሆኖም አንዳንድ ፖለቲካዊ ገደቦች እንዳልተነሱ ፕሬዚዳንት ቲኑቡ ገልጸዋል፡፡

በኒጀር በየብስ፣ በባህር፣ በአየር እንዲሁም የኢኮኖሚና የፋይናንስ ተቋማት ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች ተነስተውላታል፡፡

ኢኮዋስ ማዕቀቡን ሲያነሳ፣ በመፈንቅለ መንግሥቱ ከእነ ቤተሰቦቻቸው የታሰሩት የኒጀር ፕሬዚዳንት መሐመድ ባዚም እንዲፈቱም ጠይቋል፡፡

የኒጀር ፕሬዚዳንት ባዚም ዓምና ሐምሌ ላይ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት እንደተካሄደባቸው ይታወሳል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በኒአሜይ በሚገኘው የፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት በቁም እስር ላይ ናቸው፡፡

ከሳምንት በፊት የኢኮዋስ ተባባሪ መሥራችና የቀድሞ የናይጄሪያ መከላከያ መሪ ጄኔራል ያኩቡ ጎውን፣ ኢኮዋስ በቡርኪናፋሶ፣ በጊኒ፣ በማሊና በኒጀር ላይ የጣለውን ሁሉንም ማዕቀብ እንዲያነሳ ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡

ማሊ፣ ኒጀርና ቡርኪናፋሶ ከኢኮዋስ አባልነታቸው በቋሚነት በመውጣት ራሳቸውን ‹‹አሊያንስ ኦፍ ሳህል ስቴት›› (የሳህል አገሮች ጥምረት) እንደሚፈጥሩ ማስታወቃቸው፣ ለኢኮዋስ የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ውድቀት ማሳያ ነው፡፡ የአልጄዚራ ተንታኝ እንደሚለውም፣ ኢኮዋስን የሚያንቀጠቅጥ ነው፡፡

ኢኮዋስ ቀስ በቀስ የነበረውን ጥንካሬና ተዓማኒነት እያጣ ነው፡፡ የመፈረካክስ ሁኔታም ተጋርጦበታል፡፡ ድርጅቱ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በማካሄዳቸው ምክንያት ከአባልነት ለጊዜው ያገዳቸውንም ሆነ በማዕቀብ ያሰራቸውን አገሮች መልሶ ወደ ራሱ መሳብ ካልቻለ፣ ለራሱ ህልውና ያሠጋዋል፡፡ በአባል አገሮቹ ውስጥ ተጨማሪ መፈንቅለ መንግሥቶች እንዲካሄዱም ዕድል ይፈጥራል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...